ጥምቀትን በበዓሉ እሴቶች!

መንፈሳዊ በዓላት ዘመናት ተሻግረው ዛሬ ላይ እሴቶቻቸውን ጠብቀው መገኘት የቻሉት የሃይማኖቱ ተቋማት እና በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ ስላደረጉላቸው እንደሆነ ይታመናል። የወደፊት ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸውም በዚሁ እውነታ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑም መገመት የሚከብድ አይደለም።

በተለይም እንደኛ ያሉ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ያላቸው ሀገራት በአንድም ይሁን በሌላ ለማንነታቸው ግንባታ አቅም የሆኑ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያከብሩባቸው በዓላት ባለቤት መሆናቸው የማይቀር ነው።

እነዚህን በዓላት ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ እሴቶቻቸውን ጠብቆ ለመጪዎቹ ትውልዶች ማስተላለፍ እና እንደ ሀገር ከፍ ያለ ኃላፊነት የሚጠይቅ ፣ የሁሉንም ዜጋ ንቁ ተሳትፎ የሚፈልግም ነው። እውነታው በዚህ ዘመን ካለው የእሴቶች መፋለስ ስጋት አንጻርም ማንነትን የመጠበቅ ያህል የሚታሰብ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እነዚህ ዘመን ተሻጋሪ በዓላት የአንድ ማኅበረሰብ የማንነት አሻራ ከመሆን በላይ የሰው ልጆች የጋራ እሴት መገለጫ ናቸው በሚል እውቅና እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው እያደረገ ነው። በዚህም ረጅም መንገድ እየተሄደ ነው።

በዚህ ሂደት ሀገራችን እስካሁን 16 /የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ/ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስመዝገብ ችላለች። ከነዚህም በየዓመቱ በመላ ሀገሪቱ በኦርቶዶክስና ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ በድምቀት በአደባባይ የሚከበረው የጥምቀት በዓል አንዱ ነው ።

በዓሉ ከሁሉም በላይ የሰላም በዓል መሆኑ ፤ ከዚህም ጋር አብረው የሚነሱት የበዓሉ ዋነኛ እሴቶች ከሆኑት ትህትና ፣አብሮነት ፤ወንድማማችነት እና ኅብረ ብራዊነት ላገኛው አለም አቀፋዊ እውቅና ዋነኞቹ መሰረት ናቸው።እውቅናውን አስቀጥሎ ለመሄድም ወሳኝ ናቸው።

እነዚህ እሴቶች ከዚህም ባለፈ በማኅበረሰባችን የማንነት ግንባታ ውስጥ የጎላ ስፍራ ያላቸው ናቸው። አሁን በብዙ እየተሸረሸረ ያለው ማኅበራዊ ማንነታችንም የነዚህ እሴቶች ህያው አሻራ መገለጫ አድርገው የሚወስዱ ብዙ ናቸው። አሁን ላለንበት ችግር የተዳረግነውም ለነዚህ እሴቶች በቂ ጥበቃ ባለማድረጋችን ነው።

እነዚህ እሴቶች እንደ ሀገር ለመጣንባቸው ረጅም ዘመናት ያበረከቱ እስተዋጽኦ ከፍያለ እንደሆነም፤ ዛሬም ላይ እንደሀገር እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎችን በጽናት ለመሻገር ለምናደርገው ጥረት ትልቅ አቅም በመሆን የጥንካሬያችን ምንጭ እንደሆኑም ይታመናል።

አሁን ያለው ትውልድ እንደ ሀገር እያጋጠመው ካለው የልዩነት ትርክትና ትርክቱ እያስከፈለን ካለው ያልተገባ ዋጋ አንጻር እነዚህን እሴቶች የመጠበቅ ኃላፊነቱ ከፍ ያለ ነው ።እያንዳንዱ የእለት የህይወት መስተጋብሩ ውስጥ ስፍራና ጊዜ ሰጥቶ ሊተገብረው የሚገባ ነው።

ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ በዓሉ የሰላም በዓል ከመሆኑ አኳያ፤ ለራሱ የውስጥ ሰላም ሆነ አጠቃላይ ለሆነው ለማኅበረሰቡ ሰላም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። ለሰላም ዘበ መቆም፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጂነት መፍጠር ይጠበቅበታል።

የበዓሉን መንፈሳዊ ይዘት በአግባቡ ተረድቶ ፤መረዳቱን አሁን ካለው ተጨባጭ ሀገራዊ እውነታ ጋር በማስታረቅ፤ ራስን የችግር ሳይሆን የመፍትሄ አካል ማድረግ ወደሚያስችል፤ የመንፈሳዊ ማንነት ልዕልና ሊያመራ/ሊጓዝ ይገባል።

ትውልዱ መንፈሳዊ በዓላት በአደባባይ ከመከበራቸው አንጻር የሚፈጥረው ድምቀት፤ በዓላቱ በዋናነት የያዟቸውን መንፈሳዊ እሴቶች እንዳይጋርዷቸው መጠንቀቅ ፤ ከሚፈጥሩት የአደባባይ ድምቀት በላይ ሊፈጥሩት ለሚገባው መንፈሳዊ መነቃቃት ትኩረት መስጠትም ይገባል።

ይህንን ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው መንፈሳዊ በዓላት ትርጉም ሊኖራቸውና ድምቀታቸውም የእውነት ሊሆን የሚችለው፤ ለዚህ ደግሞ የመንፈሳዊ በዓሉ ባለቤት ምእመናን በሁለንተናዊ መልኩ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።ጥምቀትም ጥምቀት የሚሆነው በዚህ መልኩ ብቻ ተዘጋጅተን ስናከብረው ነው!።

አዲስ ዘመን ጥር 10/2016

Recommended For You