ኢትዮጵያ ሰሞኑን ራስ ገዝ ከሆነችው ሱማሌ ላንድ ጋር የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምት አድርጋለች:: ይህን ስምምነት ተከትሎ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ደስ የተሰኙ ሲሆን ጥቂቶች ግን በጥርጣሬ መንፈስ ሲያጤኑ ተስተውለዋል:: ከአገር ቤት ወጣ ሲባል ደግሞ ሶማሊያ ጉዳዩን ያወገዘችው ሲሆን፣ በተቃራኒው የሱማሌ ላንድ ሕዝብ ደስታውን በአደባባይ ሲገልጽ ለማየት ተችሏል:: እልፍ ሲል ደግሞ የተለያዩ አገራትና ተቋማት የየራሳቸውን መግለጫ በማውጣት ተጠምደው መሰንበታቸውም እሙን ነው:: ሁሉም የባህር በር ስምምነቱን አስመልክቶ እንደየጥቅሙና ስሜቱ የየራሱን ሐሳብ ይሰንዝር እንጂ ኢትዮጵያ የራሷን የከፍታ መንገድ መዳረሻ ይዛ እየተጓዘች ትገኛለች::
አዲስ ዘመን ከዚህ ከባህር በር ስምምነቱ ጋር ተያይዞ የየአገራቱ እና የየተቋማቱ መግለጫ የሚያመጣው ተጽዕኖ ምንድን ነው? ስምምነት ላይ መደረሱ ከኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አኳያስ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው? በሚሉትና በዲፕሎማሲው ዘንድ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ከቀድሞ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የቀድሞ ዲፕሎማት ከሆኑት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል:: መልካም ንባብ::
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ ያለውን የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ጉዞ እንዴት ያዩታል ?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ረገድ ውጤት ያስመዘገበችበት እና ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደረገችበት እንደ እኔ እምነት በ2015 ዓ.ም ላይ ነው:: በዚያን ዓመት ትልቅ ስኬት ያስመዘገበች ሲሆን፣ ይኸውም የብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን ያቀፈውን የብሪክስ አባል እንድትሆን የተረደረገበት ዓመት ነው:: ባሳለፈችው ዓመት በዲፕሎማሲው ረገድ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል::
ይህ ውጤት ለመገኘቱ ምክንያቱ ምንድን ነው? የተባለ እንደሆን በዋናነት መጥቀስ የምወደው ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን መቻሏ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ነው:: ብዙዎቻችን ስለብሪክስ ብዙ ግንዛቤ ላይኖረን ይችላል:: ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር ሆነች ሲባል ጠቀሜታው ምንድን ነው? እንዴትስ አባል መሆን ተቻለ? የሚለውን የሚያውቀውም ሆነ የማያውቀው አካል በብዙ ለማጥላላት እና ለማናናቅ ሲሞክር ይታያል:: ይህ ውጤት እንዴት መምጣት እንደተቻለ ለሚያውቅ አካል ግን ጉዳዩ ትልቅ ስኬት የተገኘበት መሆኑን ይገነዘባል:: መጤን ያለበትም ከዚህ አኳያ ነው::
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው ለማለቴ ምክንያቶች አሉኝ፡ አንደኛው ኢትዮጵያ ይህንን ብዙዎች የሚፈልጉትን እድል ማግኘት የቻለችው እውነቱን ለመናገር ከአገራችን በኢኮኖሚ በብዙ የሚበልጡ አገራት እያሉ መሆኑ የሚካድ አይደለም:: በኢኮኖሚያቸውም ከፍ ያሉና በፖለቲካው ዘርፍ የተሻሉ ናቸው የሚባሉ ከአፍሪካም ሆነ ከአህጉራችን ውጭ የሆኑ አገራት የብሪክስ አባል ለመሆን ጠይቀው እድሉን ያላገኙ አሉ::
ኢትዮጵያ ግን ይህንን እድል ለማግኘት ችላለች:: ይህ እድል የተገኘው ደግሞ ከበርካታ አገራት መካከል ለተመረጡ ጥቂት አገራት ብቻ እንደሆነ የሚታወቅ ነው:: ከአፍሪካ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ግብጽ እድሉን ያገኘች አገር ናት:: ከአፍሪካ እነ አልጄሪያና ሞሮኮም ጠይቀው ነበር፤ ኢትዮጵያን ከእነዚህ አገራት ጋር እንኳ ብናስተያየት በኢኮኖሚ ደረጃ እነርሱ ዘንድ ብልጫ መኖሩ ይታወቃል::
ይህን ስል ኢትዮጵያ በብዙ ፈተና ውስጥ ሆና ያገኘችው ስኬት መሆኑን ለመጥቀስ ነው:: በእርግጥ ኢትዮጵያ ጦርነቱ ባይደራረብባት ወደፊት መጓዝ የምትችል አገር ናት:: ፈተና እንዳያጣት የምዕራቡ ዓለም የራሱ የሆነ ጫና በየጊዜው የሚያሳድርባት እንደሆነም ግልጽ ነው:: ያን ተግዳሮት እየተሻገረች ይህን ድል ማስመዝገብ መቻሏ የማይታበል ሐቅ ነው:: ኢትዮጵያን ሲፈታተኗት የነበሩ ችግሮች እያሉ የብሪክስ አባል መሆን የሚያስችለንን ተቀባይነት አግኝተን አባል ሆነናል::
ሁለተኛው ምክንያት ብዬ የምጠቅሰው ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት የደረሰብን ፈተና ግልጽ ነው:: እንዲህ አይነቱ ችግር ደግሞ ተመልሶ ቢመጣ እንኳ የብሪክስ አባል አገር በመሆናችን ሊያግዘን የሚችል ወዳጅ አገኘን ማለት ነው:: ስለዚህ የሚያጋጥመን ተግዳሮት ካለ አብሮ የሚሆን አካል ከጎን መኖሩ ችግሩን አቅልሎ ለማየት ምቹ ከመሆኑም በላይ ለመጋፈጥ አቅም እንዲኖረን የሚያደርግ ነው::
ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ ይህ ስብስብ በአሁኑ ጊዜ ባለው ሁኔታ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ከ30 እስከ 40 በመቶ የያዘ ነው:: ይህን ቡድን መቀላቀል መቻል ትልቅ እድል ነው:: ከዚህ የተነሳም የቡድን ሰባት አባላት ከሚባሉ ስብስቦች ይልቅ ይህኛው የብሪክስ አባላት ስብስቦች ይበልጣል እየተባለም ይገኛል:: ይህንን የራሳቸው የመገናኛ ብዙሃን ጭምር እየተነተኑት ያለ ጉዳይ ነው::
እኛ ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚያችን በጣም ማደግ እንሻለን:: በጣም በከፍተኛ ደረጃ እየተነሳሳን ያለንበት ወቅትም ነው:: ስለሆነም የብሪክስ አባል መሆናችን ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ ለምናደርገው ሩጫ የሚጠቅመን ይሆናል ማለት ነው::
እንደሚታወቀው የብሪክስ አባል የሆኑ አፍሪካ አገሮች ከደቡብ አፍሪካ ውጭ ሁለት ነን:: አንዷ ግብጽ ናት:: ይህ የእኛ ለብሪክስ አባልነት መመረጥ አንድ የሚያሳየው መልካም ነገር አለ:: ይኸውም በሌሎች ዘንድ ያለን ግምት የተሻለ እና መልካም መሆኑን ነው:: ይህ የአገራቱ መልካም የሆነ አመለካከት ለወደፊቱም ቢሆን ከእኛ ጋር ተባብሮ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው:: ይህን ጉዳይ አቅልሎ ለማየት የሚዳዳቸው አካላት ባይጠፉም ለእኛ ግን በጣም ትልቅ ነገር ነው:: ከዚህ አቅጣጫ አንጻር የብሪክሱ አባል መሆን በጣም ትልቅ ነገር ነው:: ዲፐሎማሲውንም ከፍ ያደረገ ጉዳይ ነው::
ይህ በየመንደሩ የሚወራው እና የሚነገረው አካሄድ አላዋቂነት ነው:: ጉዳዩን ለማጥላላት መሞኮር በፍጹም ውሃ የሚቋጥር ሀሳብ አይደለም:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍ ብላ የታየችበት እና ውጤት ያስመዘገበችበት ወቅት ነበር ለማለት እወዳለሁ:: እንደዚያ ባይሆን ኖሮ በርካታ አገራት ቡድኑን መቀላቀል እየፈለጉ እድሉን አያጡም ነበር::
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ባሳለፏቸው የኢትዮጵያ መንግስታት ዲፕሎማሲ ዋጋ የተከፈለበት ጊዜ ነው የሚሉት የትኛውን ወቅት ነው? የነበረውንስ ተግዳሮት በመሻገር ምን የተገኘ ውጤት ነበር?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– አንድ አገር በዲፕሎማሲው ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅቶ ‹‹ይህንን እና ያንን ባገኝ የሚመጣብኝ ሁሉ እችላለሁ›› ብሎ የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ይኖራል:: ምናልባት በእኔ እድሜ ከዚህ ጋር ተያይዞ ያጋጠመኝ አሊያም ያስተዋልኩት ነገር አለ::
እኤአ በ1970 አካባቢ አሊያም በ1967 ዓ.ም አካባቢ ከምዕራቡ ጋር ያለንን ግንኙት በማቋረጥ ወደ ምስራቁ አገር ሔደን አገራችንን ከሱማሊያ ወረራ ያዳንበት ውጤት የማይረሳ ነው:: በወቅቱ የገንዘብም፤ የመሳሪያም እርዳታ እናገኝ የነበረው ከአሜሪካ ነበር:: ነገር ግን በአብዮቱ ምክንያቶች አሜሪካውያን ጣል ጣል ያደርጉን ጀምረው ነበር:: ስለዚህ በዚያን ጊዜ የነበሩት መሪ ‹‹ሶሻሊዝምን እቀበላለሁ፤ እኔ የሶሻሊስት አገሮች ደጋፊ ነኝ›› ብለው ወደእዛ በመግባት ያንን ያህል መሳሪያ ማግኘት የቻሉበት ጊዜ ነበር:: ከዚህ ጋር ተያይዞ እንዲያውም በወቅቱ ኒዮርክ ታይምስ ‹‹ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እንዲህ አይነት መሳሪያ በአውሮፕላን የተጓጓዘበት ጊዜ አልነበረም›› ሲል መዘገቡን አስታውሳለሁ::
በወቅቱ ሶቬዬት ኅብረት የሚባለው አገር ያንን ያህል መሳሪያ ልኮልን ጄኔራሎቻቸውም ጭምር መጥተው እንደነበር የማይዘነጋ ነው፤ እንዲሁም ወዳጃችን የሆኑት ኩባዎችም እንዲያግዙን አድርገው ከሱማሊያ ወረራ ባይታደጉን ኖሮ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር አሁን ባለችበት ሁኔታ ላትቆይ ትችላለች የሚል ጥርጣሬ አለኝ::
ስለዚህ በዚያን ወቅት ከምዕራቡ ወደ ምስራቁ በመንጠልጠል አገራችንን አድነናልና ዲፕሎማሲው ምንም እንኳ ፈተና አጋጥሞት ቢሆንም ፈተናውን በድል መሻገር የቻልንበት ጊዜ ነበር ባይ ነኝ:: በወቅቱ ከፍተኛ ጫና የደረሰብን ቢሆንም አገራችንን ከመበታተን ማትረፍ የታቸለበት ወቅት እንደሆነ አስባለሁ:: የቱንም ያህል ኢትዮጵያ ዋጋ ብትከፍልም የደረሰችበት ውጤት አስደሳች ነበር::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ረገድ ስኬታማ መሆኗ ጥቅሙ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚተርፍ እንደሆነ ይነገራል፤ ከዚህ አኳያ ለቀጣናው ያበረከተችው ሚና የሚገለጸው እንዴት ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– ኢትዮጵያ በአህጉራችን አፍሪካ በዲፕሎማሲው መስክ የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ ነው:: በተለይ በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በሌሎችም አካባቢ አስተዋጽኦ አበርክታለች:: በተለይም ደግሞ የቀጣናውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ እና አገሮችን በማስተባበሩ በኩል ሆነ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ድምጻቸው እንዲሰማ በማድረግ ረገድ የተጫወተችው ሚና አለ:: ይህ ሚና ደግሞ እኛ ስለተናገርነው ሳይሆን በጉልህ የሚታይ ነው::
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት እኤአ በ1960ዎቹ አካባቢ የአፍሪካን አንድነት በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ውስጥ እንዲመሰረት ማድረግ ተችሏል:: ይህም አፍሪካውያን ለመጀመሪያ ጊዜ የራሳቸው አቋም እንዲኖራቸው በማድረጉ በኩል የራሱ ሚና ያለው ሲሆን፣ እንዲሁም በአንድ ድምጽ መናገር እንዲሞክሩም አድርጓል:: ከዚህ በተጨማሪም አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው ጥረት መፍታት እንዲችሉ ያደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመበት ጊዜ በመሆኑ ኢትዮጵያ የተጫወተችው ሚና እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑን በኢትዮጵያ እና ራስ ገዝ በሆነችው ሱማሌ ላንድ መካከል የባህር በርን አስመልክቶ የተደረሰበት ስምምነት አለ፤ ይህ የባህር በር ለማግኘት የተደረገ ስምምነት ከዲፕሎማሲ አኳያ እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- ከሱማሌላንድ ጋር የተደረሰው የባህር በር ስምምነት ጉዳይ ጥሩ ታስቦ በድፍረት የተደረገ ነገር ነው:: በነገራችን ላይ በደርግ ዘመነ መንግስት የሱማሌ ላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን አንድ ሆነን እንቀጥል የሚል ድምጽ ያሰማችበት ሁኔታ እና ኢትዮጵያ የጠየቀችበት ወቅት ነበር:: እኛ ግን በወቅቱ ድፍረቱ አልነበረንም:: የራሳችንን የውስጥ ችግር ሳንፈታ ሌላ ችግር አንጨምርም የሚል የፈሪ አመለካከት ነበር:: በኢህአዴግም ጊዜ አንዳንድ ሙከራዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ:: ይሁንና ተፈጻሚነት ላይ አልደረሱም:: እንደዚያ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ‹‹ከእከሌ ጋር ልጣላ እችላለሁ፤ እከሌ በዚህ በኩል ሊጎዳኝ ይችላል›› ከሚል ስጋት የመነጨ ሊሆን እንደሚችልም አስባለሁ:: በትክክልም እንዲዚያ የሚባል ነገር ነበር:: ነገር ግን ሁሌ በፍርሃት ውስጥ መሆን ዋጋ ስለሚያስከፍል ድፍረት አስፈላጊ ነው:: ሰሞኑን የተደረሰበት የባህር በር የማግኘት ስምምነት በትትክክለኛ ውሳኔ የታጀበ ድፍረት በመሆኑ መልካም ነው::
በተለይ አሁን እኛ ያለንበት አካባቢ የሚኖር መንግስት ወይም እንደ ኢትዮጵያ ያለ የሚገባኝን ከፍታ ይዣለሁ የሚል መንግስት በጠንቃቃ እና ልብ ባለው መንግስት የሚመራ ነው፤ መሆን ያለበትም አንደዚያ ነው:: ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከሱማሌ ላንድ ጋር ያደረገችው የባህር በር ስምምነት የሚገባትን ከፍታ ለመያዝ የሚያስችላት ነው:: ውሳኔዎችን በድፍረት መወሰን ማለት ደግሞ ዝም ብሎ የመጣ አካሄድ ሳይሆን ግራ ቀኝ ነገሮችን በማየት የተደረሰበት ነው:: ይህ ውሳኔ ሲደረግም ስለጉዳዩ አጥንቶ እና ከሌሎቹም ጋር ተመካክሮ መስራት የግድ አስፈላጊ ነው:: እንደዚያ ካልሆነ ግን ባለህበት እርግጥ ይሆናል::
ስለዚሀም በባህር በር ጉዳይ ላይ የተካሔደው ስምምነት በጣም አስፈላጊ ነው:: የባህር በር ሲባል ወደብ ብቻ ማለት አይደለም:: ወደብ የሚያስከትለው ችግር አለ፤ አንድ ወደብ ያለው አገር ወደብ ለሌለው አገር ‹‹ወደብ ባይኖርህም እኔ አንተን አላስተናግድህም›› ሊል ይችላል:: ነገር ግን ይህንን የዓለም አቀፉ ሕግ ይከለክላል:: የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ትልቁን ስብራት አስቀምጠን ዝም ብለን መኖር የለብንም:: ትልቁን ስብራት አላየሁም ብሎ መቀጠል የሚቻል አይደለም:: ይህ ጅማሬ በአንድ ጊዜ በአንድ ወቅት መቆም ያለበት ነው:: ይህም እየተከናወነ እንደሆነ አስባለሁ::
የባህር በር ሲባል ከወደብ የተለየ ነው:: ባህር በር ሲኖረን ተጭኖ ወደአገራችን የሚገባ የትኛውም ሸቀጥ በሌሎች ቁጥጥር ስር የሚወድቅ አይሆንም:: በተለይም በሌሎቹ አካላት እንዳይጠለፍም ሆነ እንዳይጎዳ ያስችላል:: ሸቀጣችንን እኛው ራሳችን አጅበን የምናመጣበት ሁኔታ ይፈጠርልናል:: ከዚህ በተጨማሪ የባህር ኃይላችንን በስፍራው መገንባት ስለሚያስችለን ህልውናችንን ያረጋግጥልናል:: ወደምንፈልገውም ከፍታ ለመዝለቅ ያስችለናል::
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ እና በራስ ገዟ ሱማሌ ላንድ የተሰደረሰውን የባህር በር ስምምነት ከምጣኔ ሀብቱ አኳያስ የሚገልጹት እንዴት ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– ከምጣኔ ሀብት አኳያ ብዙ የተጻፈ ነገር አለ:: በዚህ ጉዳይ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በርካታ ጥናት አውጥቷል:: በትልቁ የሚጠቅሱት የባህር በር ያለው አገር እና የባህር በር የሌለው አገር እኩል ማምረት ቢችሉ እና በሌላ ሌላ ነገራቸው ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ቢሆኑ አንደኛው አገር የባህር በር ብቻ በማጣቱ እስከ ሁለት ወይም ሶስት በመቶ እድገቱ ሊቀንስ ይችላል::
ስለዚህ የባህር በር የሌለው አገር እንደ ጉዳተኛ ታይቶ እና ተቆጥሮ መረዳት፤ መታገዝ አለበት:: የተለየ እርዳታ ሊደረግለት ይገባል:: ለእነዚህ የባህር በር የሌላቸው አገሮች የተለየ እርዳታ የሚሰጣቸው በባህር በር እጦት ከእጃቸው ሊገባ ያልቻለውን እድገት የሚሸፍን መሆን አለበት:: ይህ እኔ ያልኩት ሳይሆን ዓለም አቀፍ የተቀበለው እውነታ ነው::
ለምሳሌ ጂቡቲ በብዙ መንገድ ከእኛ ጋር የተጣመረች አገር ናት:: እኛ ከእርሷ እንደምንወስድ ሁሉ እርሷም ደግሞ ከእኛ ትወስዳለች:: ሁሉም እንደሚያውቀው የወደብ አገልግሎት ከጂቡቲ እናገኛለን:: በዚህ ሁኔታ በተፈጠረው ግንኙነት አንጻር ጉዳቱ ላይኖር ይችላል:: ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ያለምንም ችግር ከጂቡቲ ጋር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ሰላማዊ ነው፤ ችግር የለበትም፤ ጉዳቱ ዛሬ የለም ማለት ግን ነገ አይኖርም ማለት አይደለም:: አይበለውና ነገ እኛ ከአንዳቸው አገር ጋር ብንጣላ የተጣላነው አገር ጂቡቲን ‹‹እኛ ብሩን እንሰጥሻለን፤ በሩን ዝጊ›› ቢሏትስ? ጂቡቲም የተባለችውን ሰምታ ጉዳዩን ብትፈጽምስ? ምን ሊመጣ ይችላል? የምንበላውን ጭምር ሊያሳጣን የሚችል ስለሚሆን በዚህ በኩል ማሰብም ብልኅነት ነው::
ስለዚህ እንዲህ አይነት ሁኔታ ምናልባት ሊፈጸም ይችላል ብሎ ማሰብ ከአንድ መንግስት በእጅጉ የሚጠበቅ ነው:: ሰሞኑን የተደረገው አይነት የስምምነት ርምጃ መውሰዱ ከዚህ አንጻር ተገቢ ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድፍረት የወሰዱት እርምጃ በጣም አስደስቶኛል:: መንግስት ማድረግ የሚጠበቅበትን ያደረገ ስለመሆኑ ያስመሰከረበት ውሳኔ ነው እላለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያስ ለሱማሌ ላንድ የአገርነት እውቅና ለመስጠት የመጀመሪያ አገር መሆኗ የሚያመጣባት ጉዳት ይኖረው ይሆን?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– በመጀመሪያ አንድን አገር ማወቅ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድን ነው? የሚለው አንድን አገር ማወቅ የአንድ ሌላ ነጻ የሆነ አገር ሉዓላዊ መብቱ ነው:: ለምሳሌ ታይዋን የምትባለውን አገር ቻይና ‹‹የራሴ ናት›› ትላለች:: ነገር ግን ‹‹እኔ አውቄያታለሁ›› ብለው በርካታ አገራት ደግሞ ከታይዋን ጋር ግንኙነት ነበራቸው፤ አሁንም አላቸውም::
በእርግጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደ አገር አልተቀበላቸውም:: ይሁን እንጂ የተለያዩ አገራት ከታይዋን ጋር የሚያደርጉት ዲፕሎማቲክ ግንኙነቱ ቀጥሎ እናያለን:: ልክ ማንኛቸውም ሁለት ነጻ አገራት እንደሚያደርጉት ሁሉ ታይዋንም ያንን ሁሉ ታደርጋለች፤ እያደረገችም ትገኛለች::
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል መሆን አለመሆን ሌላ ጉዳይ ነው ማለት ነው:: እሱ የዚያ ድርጅት አባላት ውሳኔ የሚጠይቅ ነው:: ከዛ ባለፈ ግን ‹‹እኔ ይህችን አገር አውቄያታለሁ›› ለማለት የሚከለክል ሕግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የለም:: ስለዚህ ይህችን አገር እንደ አገር የሚያስጠራትን እውቅና ሰጥቻታለሁ ለማለት የሚያግድ ምንም አይነት ሕግ የለም ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ አገራት እንዲሁም ተቋማት ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ያደረገችውን የባህር በር ስምምነት ተከትሎ የተለያዩ መግለጫዎችን አውጥተዋል፤ ይህ አካሄዳቸው ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረው ጫና ይኖረው ይሆን?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- ሰዎቹ ወይም የተለያዩ ተቋማት ባወጡት መግለጫቸው እያሉ ያሉት ዳር ዳሩን ስንረዳ ‹‹እናንተ በምታደርጉት ሁኔታ እና ስምምነት የተነሳ የአካባቢው ሰላም እንዳይደፈርስ እና እንዳይናጋ ነው::›› የሚል ነው:: የአሜሪካ መንግስት መግለጫም ሆነ የተባበሩት መንግስታት ደርጅት መግለጫ እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በየመግለጫቸው ያሉት ነገር ቢኖር የአካባቢው ሰላም እንዳይደፈርስ ነው:: ኢጋድንም ያወጣውን መግለጫ ስንረዳ ከእነዚህ ጎራ ውስጥ ሊካተት የሚችል ነው:: ምንም የተለየ እና የሚከለክል ነገር የለውም::
ወደ አውሮፓውያኑ ስንመጣ ግን አንገታችንን ቀና እንድናደርግ የሚፈልጉ አይነት አይደሉም፤ ቀና እንዳንል እና አንገታችንን ወደመሬት እንድንደፋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳዩት ያለ ባህሪያቸው መሆኑን ልብ ማለት ይቻላል:: ለምን እንደሆነ እስከማይገባኝ ድረስ በኢትዮጵያ ላይ በፊት ያልነበረባቸውን ባህሪ በማሳየት ላይ ያሉ አውሮፓውያን ሆነዋል:: እኔ በስራ ምክንያት ቀደም ባሉ ዓመታት በአውሮፓውያኑ ዘንድ ቆይቻለሁ:: በወቅቱ አሁን የሚያሳዩት አይነት ባህሪ አልነበራቸውም:: ስለሆነም አሁን የእነርሱ ሁኔታ ትንሽ ጠንከር ያለ ነው::
ሌሎቹ ግን የቀጣናው አካባቢ ችግር እንዳይፈጠር ችግራችሁን እዛው ፍቱ ከሚል አመለካከት የተሰጠ መግለጫ ነው ብዬ አስባለሁ:: ስጋታቸውም ችግር እንዳይኖር ከሚል የሚመነጭ ነው:: ከዚህ የተነሳ ሁለቱ አገሮች ተስማምተው የሚያደርጉት ነገር ሰላም እንዳያናጋ ከሚል ፍራቻ እንጂ ‹‹ኢትዮጵያ እንዲህ እና እንደዚህ አድርጋለች ወይም ደግሞ ሱማሌላንድ እንዲህ እና እንዲያ አድርጋ የራሷን መሬት ለኢትዮጵያ አከራይታለች፤ ስለዚህ ይህን ማድረግ ወንጀል ነው፤ ከዚህ የተነሳ እናወግዛቸዋለን››› ብሎ የዘላበደ የለም::
በመሆኑም ኢትዮጵያ ይህን ስምምነት መፈጸሟ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን ላይ ሊያመጣ የሚችል አሉታዊ ተጽዕኖ የለም:: መንግስትም እያደረገ ያለው ብልኅነት የተሞላበት እንቅስቃሴ ነው:: ስለዚህ በኢትዮጵያ እና በራስ ገዟ ሱማሌ ላንድ የተደረሰው የባህር በር ስምምነት ስኬታማ ከሆነ እንደማንኛውም ነገር የራሱ የሆነ ጉዳትም ጥቅምም ሊኖረው ይችላል:: ጉዳት እና ጥቅሙ ምን ያህል ነው ብሎ የራስን ውሳኔ መወሰንና እርምጃ መውሰድ እና የተወሰደውን ርምጃ ደግሞ ማስፈጸም የአንድ መንግስት ትልቁ የቤት ስራ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::
አምባሳደር ጥሩነህ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥር 9/2016