ኢትዮጵያ የበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት ነች። የተፈጥሮ ሀብቶቿ ከኤርታኢሌ እስከ ዳሎል፤ ከራስ ዳሽን እስከ ታችኛው ኦሞ ሸለቆ ድረስ የተዘረጉ ናቸው። ከእነዚህም መካከል አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ እንዲሁም የሰው ዘር መገኛ ስፍራዎች ተካተውበታል። ሃይማኖታዊ በዓላትም የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ሆነው እና በዩኔስኮ ደረጃ ተመዝግበው ዛሬ የዓለም ቅርስ እስከ መሆን ደርሰዋል።
ለዚህ በዋነኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ደግሞ የጥምቀት በዓል ነው። በክርስትና ጥምቀት አንድ ሰው ከኃጢአቱ ንስሐ እንደገባና በማንኛውም ሁኔታ ሥር የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ እንደተስማማ በሰዎች ፊት ይፋ ለማድረግ የሚወሰደው ርምጃ ነው።
ኢትዮጵያ ዜና ጥምቀተ ክርስቶስን ከሰማችበት ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ በተለይም ከአጤ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት (6ኛው መ/ክ/ዘ) ወዲህ የጥምቀትን በዓል ዛሬ በሚታየው አኳኋን ስታከበር እንደ ቆየች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በክብረ በዓሉ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት የሚወርዱት ታቦታት በካህናቱ ሃሌታ፣ በምእመናኑ እልልታ እና በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ በተቋቋሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በመዝሙሮች ታጅበው በተመሳሳይ አኳኋን እንደሚመለሱ ይታወቃል።
የእምነቱ ተከታዮች አምረውና ደምቀው የሚታዩት በጥምቀት ነው። በጥምቀት የአርባ አራቱ ታቦት ፣ ሊቃውንት፣ ስመጥር የደብር አለቆችና ካህናት በሚያምረው ልብሰ ተክህኖ አምረውና ደምቀው ይታያሉ። በነጭ የባህል ልብሳቸው ላይ ጣል ከሚያደርጉት ጥቁር ካባቸውንና በራሳቸው ጥምጣም የሚታወቁት በጎንደር የቅኔ ፤ የመወድስና የአቋቋም ዝማሬ ሊቃውንት ባማረው አንደበታቸው የውዳሴ መዝሙር ጣዕመ ዜማ፣ ወረብና ሽብሸባውን በአደባባይ የሚያሰሙበት ልዩ አጋጣሚ ቢኖር ይህ የጥምቀት በዓል ነው። ሳይበረዝ፤ሳይከለስ የጥንቱ የጠዋቱ የጥምቀት በዓል የሚገኘውም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው።
የጥምቀት በዓል የአንድነትና የአብሮነት በዓል ነው።ሕፃን አዛውንቱ፤ሴት ወንዱ ብሔርና ቀለም ሳይለየው ታቦታቱን አጅቦ አደባባይ የሚገኝበት ነው። በዚህ የአደባባይ በዓል ላይ ኢትዮጵያውያን በባህላቸው ይደምቃሉ፤ በጭፈራቸው ይደሰታሉ፤ በአለባበሳቸው ይደምቃሉ፤ በሰላማቸው ይኮራሉ። ኢትዮጵያውያን በጥምቀት አንድነታቸው ይጸናል፤ አብሮነታቸው ይጎላል፤ ህብረብሔራዊነታቸው ያሸበርቃል።
ይህ ድምቀት ደግሞ ብዙዎችን ቀልብ ስቦ ከዓለም ዳርቻ ሁሉ ቀልብ እየሳበ ጥምቀትን ለመታደመ ኢትዮጵያ እንዲከትሙ ያደርጋል። ከዓለም ዳርቻ የተሰባሰቡት ቱሪስቶችም ያልተከለሰውንና ያልተበረዘውን የጥምቀት ትውፊት ተመልክተው ከልባቸው ረክተው ይመለሳሉ፤ ዳግም ለመምጣትም ቃል በመግባት ነገን በናፍቆት ይጠባበቃሉ።
ይህን ሁኔታ የታዘበውና ያጠናው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ጥናት ድርጅት (ዩኔስኮ) ጥምቀትን በዓለም ቅርስነት መዝግቦ የበለጠ እንዲያብብና ጥንታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲጓዝ አድርጓል።
ቦጎታ ኮሎምቢያ ውስጥ ድርጅቱ ስለ ቅርስ ጥበቃ በተነጋገረበት ስብሰባ ላይ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት በዓሉ በዩኔስኮ የተመዘገበ አራተኛው የማይዳሰስ ቅርስ ሆኗል። ጥምቀት በወርሃ ጥር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባዮች በድምቀት ተከብሮ የሚውል ሃይማኖታዊ በዓል ነው። የጥምቀት በዓል ከዋዜማው ጥር 10 ተጀምሮ እስከ ጥር 12 ቃና ዘገሊላም በድምቀት ይከበራል።
ጥምቀት የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ያስቻለው አንዱ ገጽታው ሰላማዊነቱና ሕብረ-ብሔራዊነቱ ነው። ሰላም የጥምቀት በዓል ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ዋናው መሰረቱ ነው። ያለሰላም ጥምቀትን ማሰብ አይቻልም። ሆኖም ከበዓሉ ትውፊት ውጪ የጥምቀት በዓልን የፖለቲካ ማስፈጸሚያና የግርግር ምንጭ እንዲሆን የሚሹ አካላት ስላሉ እያንዳንዱ ምዕመን ለእነዚህ አካላት ጆሮ ሳይሰጥ በዓሉ በሰላም እንዲከበር የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል።
በተለይም የበዓሉ ዋነኛ ፈርጥ የሆኑት ወጣቶች በመጪው ቀናት የሚከበሩትን የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ እንደተለመደው ለሰላም ዘብ መቆም ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን ጥር 9/2016