
- ከ5ሺህ በላይ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል
አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከአራት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ደረጃ እንዲሻሻል መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። ከአምስት ሺህ በላይ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውም ተገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ እቅድ ዝግጅት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ሀሰን እንድሪስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከ4ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች የደረጃ ማሻሻያ ተደርጓል።
በክልሉ ከደረጃ በታች የሆኑ ሦስት ሺህ 410 ትምህርት ቤቶችን ወደ ደረጃ ለማሳደግ ታቅዶ እንደነበር የገለጹት አቶ ሀሰን፤ እስካሁን አራት ሺህ 418 ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው እንዲሻሻል መደረጉን አመላክተዋል።
የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ከማከናወን በተጨማሪ ለመማር ማስተማር ሂደቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማዳረሱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል። እድሳት የሚያስፈልጋቸውን መማሪያ ክፍሎች ማደስ፣የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር፣ቤተ መጻሕፍት፣መጸዳጃ ቤቶች፣የውሃ አቅርቦት፣የአጥር ግንባታና ሌሎች አስፈላጊውን መሰረተ ልማቶች የማሟላት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቶች ደረጃ መመዘኛ መሰረት በደረጃ አንድና ሁለት የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ትምህርት ቤቶች ቢያንስ ደረጃ ሦስትና አራት መስፈርትን እንዲያሟሉ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ የትምህርት ቤቶች እድሳት በዘንድሮው ዓመት ትኩረት ተሰጥቶት በንቅናቄ መልክ እየተሰራበት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የትምህርት ቤቶች የደረጃ ማሻሻል ፣የመምህራን ቤቶችና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ቀጣይነት ባለው መልኩ በኅብረተሰብ ተሳትፎ እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በንቅናቄው በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ለመምህራን መኖሪያ ቤት ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ አራት ሺህ የመምህራን መኖሪያ ቤት ለመገንባት ታቅዶ አምስት ሺህ 369 የመምህራን መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን አስታውቀዋል።
በክልሉ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ለማስፋት ባለፉት ሁለት ዓመታት በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት አቶ ሀሰን፤ ባለፉት ወራት ሶስት ሺህ 764 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል ብለዋል።
የትምህርት ቤቶች እድሳት፣የመምህራን መኖሪያ ቤቶች፣የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመልክተው፤ በገንዘብ፣በጉልበትና በሙያውና በቁሳቁስ ድጋፍ 16 ቢሊዮን ብር ያህል ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ጥር 9/2016