ስምምነቱ ዘመኑን ከሚዋጅ ዓለም አቀፍ እሳቤ የተቀዳ ነው!

አሁን ላይ ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት ለማምጣት በፖለቲካ ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። የታሰበውን ያህል መጓዝ ባይቻልም አስተሳሰቡ ፣ እንደአስተሳሰብ ዘመኑን የሚዋጅ ስለመሆኑም ብዙ ተብሎለታል። የብዙዎችን ቀልብ በመሳብም ዓለም አቀፍ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ ዓመታት አልፈዋል።

በጉዳዩ ላይ ብዛት ያላቸው ጥናትና ምርምሮች ተካሂደዋል ፤ አስተሳሰቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ ብዙ መድረኮችም ተዘጋጅተዋል። መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ዋነኞቹ የሃሳቡ አራማጆች በመሆን ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። በጉዳዩ ዙሪያ ሰባኪና ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው ባላቸው አቅም ሁሉ ሲንቀሳቀሱም ተስተውለዋል።

ዓለም ከልዩነት ይልቅ በአንድነት ብዙ ልታተርፍ እንደምትችል ፤ ይህ አንድነት ዓለም አቀፍ ገጽታ እየተላበሰ ሲመጣ ፤ ምድራችን ለነዋሪዎቿ የተሻለች የመኖሪያ ሥፍራ እንደምትሆን ፤አሁን ላይ እያጋጠሟት ያሉትን መልከ ብዙና ውስብስብ ችግሮች በጋራ ለመፍታት እንደሚያስችልም እሳቤው ዙሪያ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች አረጋግጠዋል።

አሁን ላይ አስተሳሰቡ በብዙ ፈተናዎች ጫና ውስጥ ቢሆንም ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ፤ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎች በአንድም ይሁን በሌላ ይህንን አስተሳሰብ ታሳቢ ያደረጉ ፤ ለአስተሳሰቡ ተገዥ የሆኑ፤ ለአስተሳሰቡ ዓለም አቀፍ መሠረት መጣል የሚያስችሉ ናቸው።

ይህ ዓለምን ለነዋሪዎቿ የተሻለች ለማድረግ ፤ የተጀመረው ዓለም አቀፍ ንቅናቄ የጋራ ተጠቃሚነትን እና የጋራ ዕጣ ፈንታን በጋራ መሥራት ላይ መርህ ያደረገ ነው። በዚህም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በብዙ ጥያቄዎች ውስጥ ሆኖ አሳቤው ፤ ከዛሬ ፈተናዎቹ በስኬት አሻግሮ፤ የተሻሉ ነገዎች ይዞለት እንደሚመጣ ተስፋ እያደረገ ነው።

አስተሳሰቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ባለ ድምጽ ከመሰማቱ የተነሳም ፤ ሀገራት ለአሁናዊ ችግሮቻችው ሆነ ለነገ ስጋቶቻቸው፤ በፖለቲካ ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ዘርፎች መቀራረብን በመፍጠር ዘላቂ እና ስትራቴጂክ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሠሩ ነው።

ለዚህም በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል ሰሞኑን በወደብ አጠቃቀም ዙሪያ የተደረሰበት የመግባቢያ ስምምነት ተጠቃሽ ነው። ስምምነቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ፤ ከሁሉም በላይ በሕዝቦቻቸው መካከል የነበረውን ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሳድግ የሚችል ነው።

ቀደም ሲል በመካከላቸው የነበረውን የወንድማማችነት መንፈስ በብርቱ መሠረት ላይ ፤ በተሻለ መልኩ የሚገነባበትን መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ፤ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ በሰጥቶ መቀበል መርህ ፤ ግንኙነታቸውን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል ።

ስምምነቱ የአካባቢው ሀገሮች ካልተገባ ጥርጣሬና ማንንም ሊጠቅም ከማይችል የሴራ ፖለቲካ ወጥተው አካባቢው አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ሆኖ የሚፈጠርበትን ዕድል የሚያመቻች፤ የአካባቢው ሀገራት ዕጣ ፈንታቸው የተሳሰረ መሆኑን ነገ ላይ በተጨባጭ ማሳየት የሚያስችል ነው።

የቀጣናው ሀገራት በዓለም አቀፍም ሆነ በአካባቢያዊ መድረኮች የተሻለ ተደማጭነት እንዲኖራቸው ፤ በዚህም ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን በተሻለ መንገድ ማስጠበቅ የሚችሉበትን መልካም አጋጣሚ መፍጠር የሚያስችል ትልቅ ተጨባጭ ተሞክሮ ሊሆን የሚችል እንደሚሆንም ይታመናል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ከዚህም ባለፈ ዓለም ዘመኑን ይዋጃል ብሎ ዛሬ ላይ ብዙ ከመናገር አልፎ ስለተግባራዊነቱ ብዙ ርቀት እየተጓዘበት ካለው ዓለምን ወደ አንድ መንደር የመለወጥ አሳቤ የሚጣጣም ፤ በጋራ በመቆም የተሻለ ተጠቃሚነትን መፍጠር በመሆኑ ሊበረታታ የሚገባ ትልቅ ስኬት ነው!

አዲስ ዘመን ጥር 8/2016

Recommended For You