ሀገር ጸንታ የምትኖረው ዜጎችዋ ለብሄራዊ ጥቅማቸው በሁለንተናዊ መልኩ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ሲችሉ ነው ። ይህ ቁርጠንኝት በሰላም ወቅት የሀገርን ፖለቲካዊ ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማሳደግን ታሳቢ የሚያደርግ ፤ በችግር ወቅት ሕይወትን መስዋእት አድርጎ መስጠትን የሚጠይቅ ነው።
ብሄራዊ ጥቅም ከተወሰነ ቡድን ወይም በአንድ ወቅት በሥልጣን ላይ ካለ ፤ በሌላ ወቅት ከሚሰናበት መንግሥት ጋር የሚቆራኝ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አሁን ያለውንና ወደፊት የሚመጣውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ በመወሰን ሂደት ውስጥ ወሳኝ አቅም ነው። የትኛውም ማኅበረሰብ እንደ ማኅበረሰብ እስከ ድክመትና ጥንካሬው ፤ ልዩነቱና አንድነቱ ፤ በጋራ የሚቆምበት የጋራ አጀንዳው ነው።
ከመንግሥት ጋር ስለተኮራረፍን ፤ መንግሥት የሚያራምደው የፖለቲካ እሳቤ ስለማይስማማን ፤ ወይም አሁናዊ ሀገራዊ እውነታዎች ጥላ ያጠላበት ስለመሰለን ፤ እና ሌሎች መሰል ምክንያቶች አሳልፈን ለሌሎች የምንሰጠውም አይደለም ። ለአደጋዎች ሲጋለጥም አይተን እንዳላየን የምናልፈው አይደለም።
ብሄራዊ ጥቅም እንደ ቃሉ ብሔራዊ ጥቅም ነው ፤ የሕዝብ እና የሀገር ከዚያም ባለፈ የትውልዶች ጥቅም ነው። የራሳችን ፤ የወለድናቸው ልጆቻችን እና የልጅ ልጆቻቸው ጥቅም ነው። ይህ በትናንቱም ሆነ በአሁናዊው ዓለም የነበረና ያለ ፤ ዜጎች በየትኛውም መመዘኛ ለድርድር የማያስቀምጡት እውነታ ነው።
በተለይም ባለንበት ዘመን ዓለም አቀፋዊ እውነታው፤ በሁሉም አቅጣጫና እሳቤ ብሔራዊ ጥቅም የነገሮች ሁሉ መመዘኛ እየሆነ ባለበት ፤ ይህንን ጥቅም አሳልፎ መስጠት ፤ ብሩህ ስለሆኑ ነገዎች ተስፋ ማድረግ ቀርቶ ፤ ዛሬን እንደሀገር አሸንፎ ቆሞ መገኘት ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ይታመናል።
የትኛውም ሀገር እንደሀገር ብሔራዊ ጥቅሞቹ አደጋ ውስጥ ሲወድቁ ፤ ዜጎች የትኛውንም አሁናዊ ችግሮቻቸውን የይደር አጀንዳ አድርገው ለብሔራዊ ጥቅማቸው በሁለንተናዊ መልኩ ዘብ የመቆም ኃላፊነት አለባቸው። ይህ ኃላፊነት ሀገርን በተስፋዋ ላይ የማቆምና የማጽናት ኃላፊነትም ጭምር ነው።
ይህ እውነት በኛ ሀገር የረጀም ሀገረ መንግሥት ትርክት ውስጥ ትልቅ ስፍራን የያዘ ነው። ትውልዶች በብዙ ልዩነቶች ፤ ከዚያም ባለፈ ፤ የከፋ በሚባሉ ውስጣዊ ችግሮች በገዘፉባቸው ቀናቶች ውስጥ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን (እንደ ሀገር) የሚገዳደሩ ስጋቶችና አደጋዎች ሲያጋጥሟቸው ፤ የውስጥ ችግሮቻቸውን በይደር አስቀምጠው ለብሔራዊ ጥቅሞቻቸው ቅድሚያ በመስጠት አሁን ያለችውን ሀገር አ ስረክበውናል
በተጻራሪው ለብሔራዊ ጥቅሞቻችን ቅድሚያ በለመስጠታችን ፤ ጊዜ ፈጥሮ ለሚሽረው ፤ ዛሬ ለሚፈጠሩ ቅሬታዎችና መሻቶች ስንል ከሄድንባቸው ያልተገቡ መንገዶች የተነሳ የቀደሙት አባቶቻችን በውድ ዋጋ ያስረከቡንን የብሔራዊ ጥቅሞቻችን መሠረቶች አጥተን አሁን ላይ ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል እየሆንን ያለበት ሁኔታ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ይህ እውነታ ዛሬ ላይ ያለውን ትውልድ ብቻ ሳይሆን መጪዎቹን ትውልዶች ጭምር ሊፈታተን የሚችል ከፍ ያለ ተግዳሮት እንደሆነ ፤ በተለይም ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ውስጥ የሀገርን ሆነ የትውልዶችን ዕጣ ፈንታ የከፋ ስጋት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ፤ ሀገርን እንደ ሀገር ጸንታ እንዳትቆም የማድረግ አቅሙም ከፍያለ እንደሆነ ይታመናል ።
ይህ በአይነቱ በብሄራዊ ጥቅም ላይ የሚከሰት ስጋት በተለይም በድህነትና በኋላቀርነት ውስጥ ብዙ ዋጋ ለመክፈል ለተገደዱ ፤ ይህንን ችግራቸውን ተሻግረው ነገዎቻቸውን የተሻሉ ለማድረግ ተስፋ ለሚያደርጉ ሕዝቦች ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ፤ ከመጡበት የድህነትና የኋላቀርነት አዙሪት ለመውጣት የሚያደርጉትን ትግል ተስፋ ቢስ ሊያደርግ ይችላል።
ከዚህ አንጻር መንግሥት እንደመንግሥት ከትናንት ተንስቶ ፣ ዛሬን አይቶና ነገዎቻችን አሻግሮ ሀገርን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስትራቴከጂክ አቅሞችን በመገንባት ሂደት ላይ በስፋት እየሠራ ይገኛል። በዚህም ሀገር እንደ ሀገር አስተማማኝ እና ቀልጣፋ የወደብ አማራጭ አገልግሎት የምታገኝበትን መንገድ በማፈላለግ ላይ ነው፤ ይህንን ታሳቢ ባደረገ መንገድ በአካባቢው ለሚገኙ ወንድም ጎረቤት ሀገራት ጥሪ አቅርቧል።
ጥሪው ከሁሉም ባላይ የአካባቢው ሀገራት ያላቸውን አቅም ይዘው በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችላቸው ፤ ሀገራቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ሆነው የሚወጡበትን ዕድል የሚፈጥር ነው ።
ይህን ከኢትዮጵያ ሕዝብ የማንነት እሴቶች የሚመነጨውን አብሮ የመልማት ጥሪ ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተቀብለው ፤ ለተግባራዊነቱ ያሳዩት ቁርጠኝነት ፤ ከሁሉም በላይ ትውልዱ እንደቀደሙት አባቶች የቱንም ያህል ልነቶች ቢኖረው ፤ በብሔራዊ ጥቅሞቹ ላይ የማይደራደር መሆኑን በተጨባጭ ያሳየ ነውና ከፍያለ እውቅናና ክብር ሊሰጠው የሚገባ ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 7/2016