ልጆች እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? ትምህርት ጥሩ ነው? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ያሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የገና በዓል በመላው ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከብሯል፡፡ እናንተም በተለይ ክርስትና እምነት ተከታይ የሆናችሁ ልጆች በዓሉን በድምቀት እንዳከበራችሁ እገምታለሁ፡፡ ልጆች! ዛሬ ለየት ባለ ርዕስ መጥቻለሁ፡፡ ለመሆኑ ወላጆቻችሁ እናንተን በምን አይነት መንገድ ነው እያሳደጓችሁ ያሉት?
መቼም ሁሉም ወላጅ ልጆቹን ጠቃሚና ተስማሚ ነው ብሎ ባሰበው መንገድ እንደሚያሳድግ ጥርጥር የለውም። ሁሉም ወላጅ ግን ተመሳሳይ የልጆች አስተዳደግ ዘዴን ይከተላል ማለት አይቻልም፡፡ አንድ የሚያስማማ ጉዳይ ቢኖር ግን፣ አብዛኛው ወላጅ በየራሱ መንገድ ልጆቹን በተሻለ ሁኔታ አሳድጎ ጥሩ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጥረት ማድረጉ ነው፡ ፡ አያችሁ ልጆች! የእናንተም ወላጆቻችሁ ዋነኛ ፍላጎት እናንተን በጥሩ ሁኔታ ማሳደግና ለቁም ነገር ማብቃት ነው፡፡
ታዲያ ልጆች እናንተ በጥሩ ሥነ ምግባርና በመልካም ማንነት ተኮትኩታችሁ እንድታድጉ ወላጆቻችሁ ተጨማሪ የልጆች አስተዳደግ ዘዴዎችን ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ወይዘሮ ሳራ ዘመኑ የተባለችና በሙያዋ ነርስ የሆነች ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡ ለማሳደግ የሚያግዝ ‹‹ጤናማ የልጆች አስተዳደግ›› የተሰኘ መጽሐፍ አሳትማለች፡፡
ልጆች! ወይዘሮ ሳራ በሙያዋ ነርስ ናት፡፡ የነርሲንግ ሙያ ትምህርቷን የተከታተለችው በአሜሪካን ሀገር ነው፡፡ በዚህ የሙያ ዘርፍ ከሃያ ዓመት በላይ አገልግላለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሕክምና ተቋሙ ውስጥ እያገለገለች የምትገኝ ስትሆን ቨርጂኒያ በሚገኝ የኮሚዩኒቲ ኮሌጅ ውስጥም የነርሲንግ ትምህርት ታስተምራለች፡፡ በተጨማሪም ወላጆችን በማሠልጠን ሙያ ሰርተፍኬት አግኝታ ወላጆችን ስለልጆች አስተዳደግ ታስተምራለች፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ ‹‹እናት ለእናት›› የተሰኘ የዩቲዩብ ቻናልና ፌስቡክ ገፅ ከፍታና ግሩፕ መሥርታ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በኢትዮጵያና በውጪ ሀገራት ለሚገኙ ወላጆችና ሴቶች ስለልጆች አስተዳደግና ቤተሰብ በማስተማር ማኅበረሰቡን እያገለገለች ትገኛለች፡፡
አሁን ደግሞ ለንባብ ባበቃችውና ‹‹ጤናማ የልጆች አስተዳደግ›› በተሰኘው መጽሐፏ የልጆች አስተዳደግ ዘዴን በሁለት ምዕራፍ ለወላጆች ለማቅረብ ሞክራለች፡፡ አንደኛው ምዕራፍ እድሜን ያማካለ የልጆች እድገትን በሚመለከት የሚያትት ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የልጆችን የማሳደግ ተግባራዊ እንክብካቤን ይዳስሳል፡፡
ወይዘሮ ሳራ ይህን መጽሐፍ ያዘጋጀችው በተለይ በልጆችና በወላጆች መካከል ያለውን ክፍተት በማየትና ልጆችን እንደየ እድሜያቸው ደረጃ ማሳደግ ተገቢ መሆኑን በመረዳት ነው። ይህንኑ መሠረት በማድረግ ልጆችን ተንከባክቦ ማሳደግ የሚቻል ከሆነ ወደ ፊት ልጆች ትክክለኛውን መስመር ተከትለው በመሄድ የሚፈለገው አቅጣጫ ላይ ይደርሳሉ ከሚል እሳቤም ጭምር ነው መጽሐፉን አዘጋጅታ ለወላጆች ማቅረብ የፈለገችው። በተለይ ደግሞ አሜሪካን ሀገር ሳለች በነርስ ሙያ መምህርነት ስታገለግል በቆየችባቸው ጊዚያት ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን እናቶች በልጆቻቸው አስተዳደግ ዙሪያ ሲቸገሩና እንዴት ማሳደግ እንችላለን? የሚሉ ጥያቄዎች ይቀርቡላት እንደነበርና ይህም በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ቁጭትና ተነሳሽነት አሳድሮባታል፡፡
ብዙ ጊዜ ልጆች ፈሪዎች ናቸው፣ ራሳቸውን አይችሉም፤ ተነሳሽነት የላቸውም የሚባሉት ከልጅነታቸው ጀምሮ ተገርተው ባለማደጋቸው፣ በራሳቸው እንዲተማመኑ ሆነው ባለማደጋቸው፣ ከውስጥ ወደ ውጪ እንዲያብቡ ባለመደረጋቸው ነው የምትለው ወይዘሮ ሳራ፣ ጊዜው ካለፈ በኋላ ልጆችን ወደ መስመር ለመመለስ አስቸጋሪ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ከልጅነታቸው ጀምረው የሚያዩበትን መነፅር በማስተካከል ልጆች ለራሳቸው፣ ለማኅበረሰባቸው ብሎም ለሀገራቸው እንዲበቁ የሚያስችል መጽሐፍ ስለመሆኑ ትናገራለች፡፡
ወይዘሮ ሳራ እንደምትለው እናቶች ልጆቻቸውን በአግባቡ ለማሳደግ በጣም ይተጋሉ፤ ይለፋሉ። እንዲያም ሆኖ በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ አሁንም የእውቀት ክፍተት ይታያል፡፡ ይህንን ክፍተት በማየት ትንሽ መደገፍ ይቻላል በሚል በዩቲዩብ ቻናሏ አማካኝነት በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ ፕሮግራም ጀመረች፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከውጪው ሰው ባላነሰ ኢትዮጵያውያን እናቶችም በልጆቻቸው ባሕርይ ላይ ለውጥ እያዩ በመምጣታቸው በዩቲዩብ የምታቀርበውን ፕሮግራም ወደ መጽሐፍ በመቀየር ‹‹ጤናማ የልጆች አስተዳደግ›› በሚል አሳትማዋለች፡፡
ልጆች! የወይዘሮ ሳራ ምኞት መጽሐፉን ብዙ ወላጆች ወስደውት እንዲጠቀሙበትና ልጆቻቸውን ነቅተው እንዲያሳድጉበት ማድረግ ነው፡፡ በተለይ ጊዜው የመረጃና የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ ወላጆች ጊዜውን በዋጀ ሁኔታና ዘመኑ የሚፈልገውን ነገር መሠረት ባደረገ መልኩ ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉም ፍላጎት አላት፡፡ ለዚህ ታዲያ “መጽሐፌ በቂ መልስ አለው ትላለች፡፡ በወላጆችና በልጆች መካከል ያለውን ክፍተት መሙላት የሚቻለው ከልጆች ጋር ትስስር በመፍጠር መሆኑን ትገልፃለች፡፡ ጥሩ ትስስር ካለ ደግሞ መልካም መግባባት እንደሚኖር ትጠቅሳለች፡፡
መጽሐፉ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች አንብበው ተግባራዊ ቢያደርጉት በልጆቻቸው አስተዳደር ዙሪያ ተጨባጭ ለውጥ የሚያዩበት እንደሆነም ወይዘሮ ሳራ ተናግራ፤ አንደኛው የመጽሐፍ ምዕራፍ በእድሜ የተከፈለ ሲሆን እድሜን ያማከለና ሳይንሳዊ መንገድን የተከተለ የልጆች አስተዳደግ ዘዴ ሲሆን፣ ወላጆች ልጆቻቸው በየእድሜ ደረጃቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመወሰን እንደሚረዳቸው ትገልፃለች፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ልጆችን የማሳደግ ተግባራዊ እንክብካቤ ምን እንደሚመስል ወላጆች እንዲረዱ የሚያስላቸው መሆኑን ትናገራለች፡፡
ልጆች፣ እናንተም ነገ አድጋችሁ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የምትሰማሩና ሀገር ተረካቢ ዜጎች ናችሁና በመልካም ሥነ- ምግባርና በእውቀት ታንፃችሁ እንድታድጉ ከመምህራን በተጨማሪ ወላጆቻችሁም ለእናንተ አስተዳደግ ትልቅ አስተዋፅዖ አላቸውና ወይዘሮ ሳራ የፃፈቸው ‹‹ጤናማ የልጆች አስተዳደግ›› የተሰኘውን መጽሐፍ እንዲያነቡ ጋብዟቸው፡፡ መልካም የትምህርት ጊዜ ይሁንላችሁ!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 5/2016