በሀገሪቱ የማዕድን ዘርፍ ተስፋና ተግዳሮቶች ዙሪያ የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ከትናንት በስቲያ ከጋዜጠኞች ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ጥያቄ፡- እንደሚታወቀው መንግሥት በአስር ዓመቱ የልማት መሪ እቅድ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የማዕድን ዘርፍ አንደኛው እንደሆነ ይታወቃል። ዘርፉ አሁን ላይ ያለው አፈፃፀም ምን ይመስላል?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡– እንግዲህ ይህ ዘርፍ ብዙ ያልተጠቀምንበትና እንደ አዲስ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኖ የመጣ ስለሆነ ቀድሞ መሠራት የነበረባቸውን ብዙ ሥራዎች ጭምር አሁን ነው ገና እየሠራን ያለነው። ምናልባት ሰምታችሁ ከሆነ ከሕግ ማስተካከያ ጀምሮ ተቋማትን በዚህ መንገድ መገንባትን ጨምሮ በዚህ ዘርፍ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የትኩረት መስኮችን ባካተተ መልኩ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ዘርፉ ወዲያው ለማምረት ዝግጁ ያልነበረ ዘርፍ ነው። ለማምረት የሚመቹ ነገሮችንም አብረን እየሠራን ነው። ሀገሪቱ ካላት አቅም አኳያ አሁን ላይ ያለው አፈፃፀም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ያለውን ሀገራዊ አቅም እና በተጨባጭ ሊመረት የሚችለውን ታሳቢ አድርገን እየሠራን ነው።
የዘርፉ ዋና ዋና ትኩረቶች ሦስት ነገሮች ናቸው። አንደኛው የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ሲሆን፤ ሁለተኛ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ማስቀረት ነው። የማዕድን ዘርፍ ለሌላው የልማት አካል አምራች የሚባለው ዘርፍ ነው። ምናልባትም ብዙ ነገሩን ከሌላ ጋር ጥገኛ ሳያደርግ ሊያመርት የሚችል፤ ለሌሎች የግብር፣ የኢንዱስትሪ እና የኮንስትራክሽን ግብዓት መሆን የሚችል ዘርፍ ነው። በዚህ ዘርፍ ላይ የምንጠቀማቸውን ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት አንዱና ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው። ሦስተኛው የሥራ ዕድል መፍጠርና አካባቢንም ጠብቆ ማስኬድ ነው። እነዚህ በቀጣይ የሚከናወኑ ዋና ዋናዎቹ የትኩረት መስኮች ናቸው።
የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት አኳያ ለረጅም ዓመታት ዋና ትኩረት ተደርጎ እንደ ባሕል የሚታየው ወርቅ ነው። ነገር ግን ወርቅ ብቻ ሳይሆን እንደሀገር ሌሎች ብዙ ማዕድናት አሉን፡፡ ወርቅን ስናይ ወርቅ በሁለት መንገድ ነው የሚመረተው። አንደኛው በባሕላዊ መንገድ በየክልሉ በሚገኙ ማኅበራት የሚመረተው ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ በፋብሪካ ደረጃ የሚመረተው ነው ።
በፋብሪካ ደረጃ በአሁኑ ግዜ ሥራቸውን እየጨረሱ ያሉ፤ እንዲሁም ወደ ሥራ ገብተው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያሉ አንድ አምስት ተቋማት አሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በፋብሪካ ደረጃ ወርቅ ሲያመርት የነበረው ትልቁ ሜድሮክ ነው። ሜድሮክ ሕገ ደንብን ከመንግሥት ከወሰደ ጀምሮ በማምረት ላይ ይገኛል። ሌላው በቅርብ ጊዜ ወደ ዘርፉን የተቀላቀለው ኢዛና ነው እሱም ምርቱ ትንሽ ነው። ከዚህ ውጪ የሆኑ ሌሎች ትልልቅ ፋብሪካዎች ገበያውን ሊቀላቀሉ እየመጡ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ለማምረት ጫፍ ላይ የደረሱ ያሉ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ ገና ከዓመት በኋላ ወደ ሥራ የሚገቡ ናቸው።
የሀገራችን የወርቅ ምርት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ የምንችለው ከላይ በዘረዘርናቸው ሰፊና ተደራሽነት ባለው የገበያ አማራጮች ላይ ሲመሠረት ነው። ከዚህ በፊት በአብዛኛው ሊባል በሚችል ሁኔታ ምርቱ ይገኝ የነበረው በባሕላዊ መንገድ ስለነበረ ብዙ ችግሮችን ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ አሁንም ከጥቂት ክልሎች ከሚመጣው ውጪ በአብዛኛው ችግር ያለበት እንደሆነ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ይህም በኮንትሮባንድ እና በተለያዩ ሕገወጥ ንግዶች ሰለባ በመሆን ሀገር ማግኘት የነበረባትን እንዳታገኝ እክል ፈጥሯል፡፡ ከዛ ውጪ ግን በፋብሪካ ደረጃ ያለው ምርትና እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪና ዘርፉን የሚያነቃቃ እንደሆነ ማየት እንችላለን።
እንደ እውነቱ ከሆነ አፈፃፀማችን አሁንም ያሰብነውን ያህል አይደለም። ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት ነው፡፡ ሆኖም ግን ወደሥራ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ያሉ አዳዲስ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ኢትዮጵያ በዓመት የምታገኘውን ወርቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማምረት የሚችሉ ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የተቋማት ግንባታን ጨምሮ እንደ ሀገር ለዚህ ዘርፍ ትኩረት የተሰጠው የማዕድን ካውንስልን ጨምሮ ብሔራዊ የማዕድን ካውንሰልን ማቋቋም ነው።
ካውንስሉ ብዙ ተቋማትን የያዘ ነው። በዚህ ዘርፍ ላይ ያሉትን የሀገሪቱን ችግሮች ሊፈታ የሚችል በጣም በትልቅ ደረጃ የሚታይ ነው። ብዙ እርሾ ስላልነበረው ቶሎ ብለን ለማምረትና ከፍ ያለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ አልቻልንም። ዘርፉ በባሕሪውም ብዙ ዓመት ይወስዳል፤ ማዕድን የማፈላለጉ ሁኔታ ብቻውን አድካሚና አንዳንድ ቦታ ላይ እስከ አስር ዓመት የሚቆይ ጊዜ የሚወስድ ነው። ከዚህ ሂደት ጋር በተያያዘ የኦጋዴን ቤንዚን እንኳን ስንት ዓመት እንደፈጀ የምታውቁት ነው። ዓመታትን የሚፈለግ፣ በጣም ብዙ ካፒታል የሚያሻው የሀገርን ሠላም ጭምር የሚፈለግ ዘርፍ ስለሆነ በቶሎ ተጠቃሚ የምንሆንበት ዘርፍ አይደለም።
ጥያቄ ፡- ዘርፉን በማዘመንና ሕጋዊ ሥርዓትን ተከትሎ እንዲያመርት፤ በዚህም ሀገሪቱ የምታገኘውን ገቢ በማሳደግ በኩል ባለፉት ዓመታት የተሠራው ሥራ ምን ይመስላል?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡- ወርቅ በባሕላዊ መንገድ ነው ሲወጣ የነበረው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም የሚያደርጋት የፖታሽ ሀብት አላት፡፡ በሚፈለገው ደረጃ ማምረት ቢቻል ትልቅ የገቢ ምንጭ መሆን የሚችል ነው፡፡ ከፖታሽ ቀጥሎ ሊቲየም፤ ታንታለም የዘመኑ ግሪን ኢነርጂና ይህን ተከትሎ ያሉ ማዕድናት አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ማዕድናት ማየት ይገባል፡፡
የወርቅ ማውጣት ሥራ በባሕላዊ መንገድ የተመሠረተ ስለነበር አልፎ አልፎ ባሉ አለመረጋጋቶችና የኮንትሮባንድ ንግድን ተከትሎ ችግሮች አሉ፡፡ ችግሮችን ለመቅረፍ ብሔራዊ ካውንስል ተቋቁሞ እየተሠራ ነው፡፡ በጣም የከፋ የሚመስሉ ችግሮች መጥተው ነበር ብዙ የማይታወቁ የውጭ አገር ዜጎች ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ገብተው በባሕላዊ የወርቅ ማውጣት ሥራ ተሠማርተው ብዙ ችግር ፈጥረዋል፡፡
በተሠራው ሥራ እነዚህን ችግሮች ሥርዓት እንዲይዙ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በሀገር ውስጥ ተደራጅተው የሚያመርቱ ዜጎች አሁንም የሚፈለገውን ያህል የወርቅ ምርት ወደ ብሔራዊ ባንክና የሀገሪቱ ቋት እያመጡ አይደለም። ስለዚህ የወርቅ ምርትን በተገቢው መንገድ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ የውጭ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው የራሱ የሆነ የፀጥታ አካል እንደሚያስፈልገው ነው፡፡
ሥራው የሚጀምረው ትኩረት ከመስጠት ስለሆነ ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲመራ የተጀመረው ሥራ አበረታች ነው፡፡ ከገቢ አኳያ የተጀመሩ ተተኪ ምርት የማምረት ሂደት ጥሩ ነው፡፡ ከሰል፣ ሲሚንቶ በብዛት እየተመረተ ነው። ማዳበሪያም ለማምረት ትልቅ ኢንቨስትመንት ስለሚፈልግ ቅድመ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ግብዓት የሚሆኑ የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ከማምረት ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናየው የእስካሁኑ እርምጃችን ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡
ጥያቄ፡- በ2022 በአጠቃላይ ከአንድ ፐርሰንት በላይ ያልዘለለ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፤ ይህን ከማሳደግና በተለይም በዘርፉ ለሚከናወኑ ሥራዎች ማሽነሪዎችን ከማስገባት ጋር በተያያዘ ያለው ውጤት እንዴት ይገለጻል?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡– ቅድም እንዳልኩት ነው። በአንድ ዓመትና በሁለት ዓመት ጫፍ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት ለረጅም ዓመት የሚሠራ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ በአጭር ጊዜ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባውን ያህል ያልተሰጣቸው፣ እንደ ወርቅ ያሉ ፋብሪካ የሚያስፈልጋቸው ማሽነሪዎች ለረጅም ዓመታት በፍለጋ የቆዩ ናቸው፡፡
እነዚህ በፍለጋ ላይ ያሉ ተቋማት ሥራ ሲጀምሩ እንደ ሀገር የሚፈለገውን ምርት ያመርታሉ፡፡ የታወቀ ሊገመት የሚችል በዘላቂነት ሊገኝ የሚችል ምርት ማግኘት ትልቁ ችግር ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ወደ ሥራ ሲገቡ፤ የወርቅ ምርት እንደ ሀገር ስናገኝ የነበረውን ብቻቸውን ያመርታሉ፡፡
አሁን ትልቅ ችግር እየሆነ ያለው የታወቀ፣ ሊገመት የሚችል፣ በዘላቂነት የሚገኝ ምርት ማግኘት ነው። መንግሥት በብሔራዊ ባንክ በኩል የሆነ ማሻሻያ ሲያደርግ የሆነ ሰሞን ላይ በጣም ትልቅ ወርቅ ይመጣል። ጥቁር ገበያው ላይ ያለው ነገር ሲሰፋ ደግሞ መልሶ ይጠፋል።
ባሕላዊ ምርቱ እና የመሳሰሉት ላይ እንደዚህ አይነት ነገር አለ፡፡ አሁንም ጂዲፒው ላይ ያለው ድርሻ ብዙ ለውጥ የለውም፡፡ ነገር ግን ምናልባት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በጣም ከፍተኛ የሆነ ሼር (ድርሻ) ይኖረዋል። ቅድም ባልኩት መንገድ ሥራዎች እየተሠሩ ስላሉ ማለት ነው፡፡ አሁን ግን ምናልባት ባለፈው ዓመት ላይ የነበረውን ያህል ውጤት የለውም። ተከታታይ ጠንካራ ሥራዎች ግን እየተሠሩ ነው፡፡
አሁን ወርቁም ሌሎችም የከበሩ ማዕድናትም ተደማምረው የዓመት ኤክስፖርቱ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር ብዙም የዘለለ አይደለም። ነገር ግን የከበሩ ማዕድናት ብቻቸውን የኢትዮጵያ ፖቴንሻል በመሆናቸው፣ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ዩኤስ ዶላር ኤክስፖርት ማድረግ የሚችል አቅም ላይ ነን፡፡
የዚህ ሁሉ ዋና መነሻ ቅድም አንስቼዋለሁ፡፡ ለዘርፉ እንደ ሀገር ትኩረት መስጠት፣ የተለያዩ ድጋፎችን፣ ማበረታቻዎችን መስጠት፣ የእሴት ሰንሰለቱን በደንብ አድርጎ ማየት፤ የባለድርሻ አካላትን በተመለከተም ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ይህ ዘርፍ የራሱ የሆነ ተጠያቂነት ባለው፤ ለጋራ ሃብት ለሀገር በሚጠቅም መልኩ ሥራ ላይ ሊውል ይገባል፡፡ ለሁላችንም የሁላችንም ሀብት ነው የሚል እሳቤ ፈጥረን ካልተንቀሳቀስን፤ ሌሎች አፍሪካ ሀገራት ላይ ያጋጠመውን የሚመስል የራሱ የሆነ የፀጥታ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡
ከዛ የተነሳ ለከበሩ ማዕድናት ላይ የነበረው አፈጻጸም በጣም የከፋ (ዎረስት) ነበር፡፡ ምርቱ በብዛት አለ፡፡ አፈጻጸሙ ግን በጣም ዝቅተኛ ነበር። ይሄንን በአጭር ጊዜ ለማስተካከል ሞክረናል፡፡ የመሸጫ ከፍተኛና ዝቅተኛ ዋጋውን አስተካክለን ለማዘጋጀትና ለማየት እየሞከርን ነው፡፡
የብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ችግር በማዕድን ብቻ ሳይሆን፣ በግብርናውም ሆነ በሌሎችም ዘርፎች እሴት ጨምሮ ኤክስፖርት የማድረግ ችግር ነው። ከከበሩ ማዕድናት አኳያ ካየነው ያለው ችግር በጣም የባሰ ነው፡፡ እንዳለ ለሕንድ እና ለፓኪስታን፤ ለአሜሪካ ገበያ በጥሬው ነው የሚላከው፡፡ እና የተወሰነ እሴት ቢጨመርበት ብዙ ነገር ለሀገር ውስጥ መጠቀም እንችላለን፡፡
ባለፈውም ኤግዚቢሽን ላይ እንደታየው በጣም ብዙ ሃብት አለን፡፡ ማዕድናቱ ከወርቅ በላይ በጣም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡ እንደ ሀገር እነዚህን የመጠቀሙ ልምድ የለንም፡፡ ወርቅ እና ብር ነው የተለመደው፡፡ ግን ከዛ በላይ የከበሩ ነገሮች አሉን ፡፡
ገበያውን በደንብ አላስተዋወቅነውም፡፡ እሴትም አልጨመርንበት፡፡ ኢንቨስተሮችም በበቂ ሁኔታ አልመጡም፡፡ በርግጥ አሁን በማኅበርም የተደራጁ እና ማሠልጠን የጀመሩ ተቋማት አሉ፡፡ ከከበሩ ማዕድናት ፋውንዴሽን ጋር በመሆን የሚደረጉ ጥረቶች አሉ፡፡ ግን ብዙ ሥራ ይፈልጋል፡፡
ደላንታ፣ ወሎ አካባቢ ያለው ኦፓል ማዕድን ቢታይ በጣም የሚገርም ነው፡፡ በዓለም ገበያ ላይ ያለውን ዋጋ ሲነግሩን በጣም የሚያስገርም ነው፡፡ ነገር ግን በጣም በወረደ ሁኔታ ነው አመራረቱ፡፡ የእሴት ሰንሰለቱንም ፖሊሽ የሚያደርጉ ተቋማት ብዙም አይደሉም፡፡
በሂደት ቀስ በቀስ ይህንንም ዘርፍ ደግፈን፣ ዋጋ ሰጥተነው ልንጠቀምበት የሚገባ ነው፡፡ ለዚህም ማስተካከያዎችን እያደረግን ነው፡፡ ፍቃድ የሚሰጡ ክልሎች ናቸው፡፡ እኛ ኤክስፖርት እንዲያደርጉ ፈቃድ/የኮምፒውተንስ ላይሰንስ ነው የምንሰጠው። ነገር ግን በእኛ በኩል ያንን እሴት ጨምረው በትክክል ኤክስፖርት እንዲደርጉ ቼክ በማድረግ ላይ ነን። በተለይ ፍቃዶች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች፤ በመንግሥት መዋቅር፣ በክልልም፣ በፌደራልም ላይ ቢሰጡ ለሀገር በሚጠቅም መንገድ ቁጥጥር/ሬጉሌት እየተደረገ ቢመራ መልካም ነው፡፡
ጥያቄ፡- ዘርፉ የሥራ እድልን ከመፍጠር አኳያ ትልቅ አቅም እንዳለው ይታወቃል፣ አሁን ላይ የሥራ እድልን በመፍጠር ረገድ ያለው ሚና ምን ይመስላል?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡– ዘርፉ በጣም በርካታ ዜጎችን ያቀፈ ነው፡፡ በተለይ ቅድም እንዳልነው ብዙ ሥራው በባሕላዊ መንገድ የሚከናወን ነው፤ በመላው ሀገሪቱ በባሕላዊ ምርት ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተሰማርተዋል።
ዘርፉ ያለው አቅም ይህ ብቻ አይደለም። የከበሩ ማዕድናት ላይ ሥራዎችን ሠርተን፤ ወርቅ ላይም ሥራዎችን ሠርተን፤ እስካሁን ያልተጠቀምናቸው ማዕድናትም ሲወጡ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል ሊፈጠር ይችላል። ለሀገርም በዛኑ ያህል ገቢ ያስገኛል።
በሁሉም ዘርፍ በሀገሪቱ እየተመረተ ያለው ምርት ከአንድ ሚሊዮን የዘለለ አይደለም፡፡ ይሄ በጣም ትንሽ ነው፡፡ በሀገሪቱ ካለን አቅም አኳያ በእልህ ልንሠራ ይገባል። በእርግጥ ዘርፉ የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት ስለሆነ ሠላም ይፈልጋል፡፡
ኢንቨስተሮች አንድ ወርቅ ላይ የሚያመርት ኩባንያ መጥቶ አስር ዓመት ፈልጎ፣ ገንዘቡን በብዙ ዶላር ጠፍጥፎ፤ ከዛ እንደገና ለሃያና ለሠላሳ ዓመት ሊያመርት ነው የሚመጣው። በመሆኑም አስተማማኝ የሆነ ሠላም ይፈልጋል፡፡
ይሄ የዘርፉ የተለየ ባሕሪው ነው፡፡ እነዚህን እንደ ሀገር ማሰብ አለብን። ለተጨማሪ ኢኮኖሚ በሀገሪቱ ላይ እስከ አሁን ከምናውቃቸው ከግብርናና ከኢንዱስትሪ፤ ከተለመዱ ዘርፎች በተጨማሪ ተጠቃሚ መሆን ካለብን ይሄንን እንደ ሀገር ተስማምተን አውቀን፤ የሚቀጥለው ትውልድም እንዲጠቀም በሚያስችል መልኩ መጠቀም ያስፈልገናል፡፡
ጥያቄ፡- ከሠላምና መረጋጋት ጋር በተያያዘ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉ አካባቢዎች ካሉ?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡- ሁላችንም እንደምናውቀው ከሠላምና መረጋጋት ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ ያሉ አካባቢዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ፖታሽ ወደ አፋር አካባቢ ነው ያለው። ፖታሺየምን መጠቀም የጀመሩ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ፣ ትግራይ፤ እነዚህ አሁን ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ አካባቢ ያሉ በሙሉ የወርቅ አምራቾች ናቸው፡፡ ሊቲየም ታንታለም ያሉ ማዕድናት ያሉባቸው ናቸው። ሌሎች ገና ብዙ ተመራምረን ያላገኘናቸው ማዕድናት ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ ይህ አንድ ከፍተኛ የሆነ ችግር ነው። ቢሆንም እየታገለን እንሠራለን።
ሰው እድል ሲያገኝ፣ ወጣቶች ሲቀጠሩ ስለሆነ ሠላም የሚመጣው ባለው ሁኔታም ሥራዎች እየተሠሩ ነው። የፀጥታ መዋቅር ተመድቦ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ይህም ሆኖ ብዙ አካላት እንዲመጡ እንፈልጋለን። ብዙ ዓለምአቀፍ ትልልቅ በዚህ ዘርፍ ላይ ያሉ ተቋማት መጥተው ሀብታቸውን እንዲያፈሱ፤ ከሀገር በቀል ተቋማት እና ከግል ባለሀብቶች ጋር ሆነው በሽርክና እነዚህን ሀብቶች እንዲያለሙ እንፈልጋለን፡፡
በዚህ መልኩ አስበን፣ ይህን ሀብት ካላወጣን በስተቀር አሁን ካሉብን የኢኮኖሚ ችግሮች ለመውጣት በጣም እንቸገራለን። ይህንን እውነታ ሁሉም ዜጋ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ሀብታችንን በደንብ መጠቀም እንድንችል ሠላም ያስፈልጋል፡፡
ቅድም እንዳልኩት ባለሀብቶች ለሠላሳ ለአርባ ዓመት የሚቆይ ኢንቨስትመንት ውስጥ ለመግባት የሠላምን ጉዳይ ሳያረጋግጡ በቢሊዮን ዶላር ማፍሰስ ይቸገራሉ። ለዘርፉ ሠላም በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ዜጎች የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ የፀጥታ አካላት ተረባርበው ሰላምን እውን ለማድረግ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ፡፡
ጥያቄ፡- የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና አምራቾችን በዚህ ዘርፍ ላይ በበቂ ሁኔታ ለማሳተፍ ምን ድጋፍ እያደረጋችሁ ነው?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡- በመሠረቱ በአዲሱ ሕጋችን ላይ የሀገር ውስጥ አምራቾች ማምረት በሚችሉት ላይ የውጪዎቹ እንዳይገቡ ሕጉ ይከለክላል፡፡ በሕግ ደረጃ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ማምረት የሚችሉትን የውጭ ባለሀብቶች መጥተው ያምርቱት ቢባል ብዙም የሚጨምሩት ነገር የለም፡፡ እነሱ የራሳቸው ቅድሚያ ሊያሰጣቸው የሚችል ሥራ አላቸው፡፡ እሱ ብቻም ሳይሆን በሽርክና ነው የሚሠሩት፤ ብዙ ነገር ተጋግዘው ነው የሚሠሩት፤ የውጭ ባለሀብቱም በግልፅ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚፈልገው ብዙ ነገር አለው፡፡
ያንን እየሠሩ ያሉ ብዙ ተቋማት አሉ፡፡ በተጨባጭም አሁን ላይ ያሉ አሉ፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደገለፅኩት ዘርፉ ብዙ ቴክኖሎጂ ይፈልጋል፤ ትልቅ ቴክኖሎጂ፣ ትልቅ ኢንቨስትመንት ይፈልጋል፡፡ ከኛ ሀገር ምናልባት የስቶክ ገበያው ሲመጣ ሁላችንም ዜጎች ሼራችንን ገዝተን ትልቅ አቅም ሲኖረን እንደ ሀገር ለማምረት ብዙ ላንቸገር እንችላለን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይከብደናል። ለምሳሌ ኩርሙኩ የሚባለው ፋብሪካ ብቻውን መጀመሪያ ጊዜ 5 መቶ ሚሊዮን ዶላር ነው ኢንቨስት ያደረገው፡፡
ይሄንን ለብቻው ኢንቨስት ለማድረግ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ ይቸገራል፡፡ በሽርክና/በጆይንት ቬንቸር ግን ይሞከራል፡፡ በሁሉም አማራጮች አሉ፡፡ በራሳቸው ኢንቨስት ለማድረግ አቅም ካላቸው አሁንም ማንም የሚከለክላቸው የለም ነው የምንለው፡፡ ተባብሮ በጋራ እንደ ኮርፖሬት ኢንቨስት ማድረግም ይቻላል፡፡
ጥያቄ፡- የሀገር ውስጥ አምራቾች ዘርፍን ምን ያህል እየደገፉ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ውስንነት ከመቅረፍ አንጻር ምን ያህል አበርክቶ አላቸው፡፡
ኢንጂነር ሀብታሙ፡– ቴክኖሎጂ የሚመጣው አብሮ ምርቱ ሲመጣ ነው፡፡ ኢንቨስትመንቱ ሲመጣ እኛ እንደሀገር ስንደግፍ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በአብዛኛው ለግል ባለሀብቱ ክፍት ነው፡፡ ቴክኖሎጂ እኛ አምጥተን አይደለም የምናስተዋውቀው፡፡ ይሄ የቆየ ዘርፍ ነው፤ ብዙ እድሜ የሆነው ዘርፍ ነው፡፡ በጣም የበሰለ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ብዙ አዲስ የምንለው አይደለም። ከዚህ ዘርፍ ሌሎች ሀገሮች ብዙ ተጠቅመዋል። አንድ ቦታ ላይ መቶ ዓመት ጭምር የሚያመርቱ አውስትራሊያን፣ ካናዳን፣ ደቡብ አፍሪካን የመሰሉ ብዙ ትልልቅ ቴክኖሎጂው አላቸው፡፡
ቴክኖሎጂን በአብዛኛው የሚያመጡት ኢንቨስተሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን በትንንሽ እስኬል የሚያመርቱ ባሕላዊ አምራቾች አንዳንድ ጊዜ ለጤና አስጊ በሆነ መንገድ፤ አካባቢን ሊበክል በሚችል ደረጃ የሚመረትበት ሁኔታ ሲከሰት በነሱ ደረጃ ሊጠቀሟቸው የሚችሏቸውን ቴክኖሎጂዎች ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡
ኤክስፖ ስናዘጋጅም ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ መንግሥት ቴክኖሎጂዎችን ገዝቶ ለተደራጁ ማኅበራት በረጅም ጊዜ ብድር መስጠት ይቻል ይሆናል እንጂ ገዝቶ አይሰጥም፡፡
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴርም ከዚህ አኳያ አንዳንድ ነገሮችን እያመረተ ነው፡፡ አነስተኛ ማኅበራት ሊጠቀሙ የሚችሏቸውን ማለት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ተቋማቱ መጀመሪያውንም ቢዝነስን መሠረት አድርገው የሚያመርቱና የሚታወቁም ናቸው፡፡
አማራጮች አሉ፡፡ ይህንንም እድል ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ እድል ለሚመረጡ ተቋማት ለእነርሱ የገበያ እድል ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማድረግ ነው ኤግዚቢሽን የምናዘጋጀው፡፡ ገዝተን ለማቅረብ እየሞከርን ነው፡፡ ለመንግሥት ብዙም አመቺ ላይሆን ይችላል ሜጋ የሆኑ ተቋማት ግን ብቃትና ቴክኖሎጂው ያላቸው ናቸው፡፡
ጥያቄ፡- በሚኒስቴሩ ከሚሠሩ ሥራዎች አንዱ ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የኮንስትራክሽን ዘርፉ በምን መልኩ እየተደገፈ ነው?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡– ከኮንስትራክሽን አንጻር ሀገራችን ገና የምትገነባ ሀገር ነች፡፡ በሺዎች የሚቆጠር እድሜ ያላት ጥንታዊ የምትባል ሀገር ነች፤ ነገር ግን ገና የምትገነባ ሀገር ነች፡፡ ለግንባታ ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ሲሚንቶ ነው፤ ሌላው ብረት ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች በሀገር ውስጥ ማምረት መቻል በጣም ጠቀሜታ አለው፡፡
ባለፉት ዓመታት የሲሚንቶ እጥረት አጋጥሞ ነበረ። በነገራችን ላይ ከባለፈው ኤክስፖ ጎን ለጎን ሲቀርቡ የነበሩት ጥናቶች እንዳመላከቱት ኢትዮጵያ ያላት የሲሚንቶ ጥሬ ሃብት አቅም አፍሪካን ሙሉ መገንባት የሚያስችል ነው፡፡
25 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የቆዳ ሽፋን ለሲሚንቶ የሚሆን ግብዓት የሚገኝበት ነው፡፡ በሲሚንቶ ሀብት በጣም ሀብታም ነን፡፡ ግን አንዳንድ የፖሊሲ ጉዳዮችም ስለነበሩብን ያለው ይበቃል በሚል ፈቃዶች ቆመው ነበር፡፡
ለሀገር ካመረትን በኋላም ወደ ውጭ መላክ እንችላለን፡፡ የሲሚንቶ እጥረቱ ተፈጥሮ የነበረው፤ አንደኛ ሲያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም ባለማምረታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ መሶቦ በነበረው ግጭት ከምርት የወጣበት ሁኔታ ነበር፡፡ በምዕራብ አካባቢ የነበሩ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በነበረው ፀጥታ አሁንም ድረስ በብዙ መቆራረጥ ችግር ውስጥ ናቸው። ይህም ሌላው ያጋጠመ ችግር ነው፡፡ አልፎ አልፎ የውጭ ምንዛሪና የመለዋወጫ እጥረት ችግሮችም ነበሩ፡፡
ከዚህ ውጭ የፍላጎት መጨመር አለ፡፡ ጭማሪው በዓመት ከ 30 ሚሊዮን ቶን በላይ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ማምረት ያቆሙ ፋብሪካዎች በሙሉ ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል፡፡ ስለዚህ የተሻለ የሲሚንቶ ምርት ይኖራል።
ከዚህ በላይ አዳዲሶቹ በጣም እየመጡ ነው። ለሚን ሔዶ መመልከት ይቻላል፡፡ አሁን ባለው የመጀመሪያው ምዕራፍ ዳንጎቴና ደርባን አንድ ላይ የሚያሕል ነው። ደርባ የማስፋፊያ ሥራ ለመሥራት ተፈራርሞ ሥራ ጀምሯል። በረንታ የሚባሉ ሌሎች ሲሚንቶ ፋብሪካዎችም ሥራ እየጀመሩ ናቸው። ሲሚንቶ ላይ ተገማች በሆነ መንገድ ከችግሩ እንወጣለን፡፡ ለመገንባት ስጋት አይኖርብንም፡፡
ሌላው ትልቁ ችግራችን ብረት ነው፡፡ አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትም እየተቸግርን ያለው ብረት ላይ ነው፡፡ ከላይ ከጠቀስኩት አኳያ ብረትንም ልክ እንደ ወርቅና እንደሌሎች ትልቅ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ ነው፡፡ ሃብቱ አለን ፍለጋ ላይ ያሉ በቅርብ ጊዜ ሊያመርቱ የሚችሉ ተስፋ ያላቸው አሉ። እስካሁን ድረስ ግን ኢንቨስተሮችን እየጠራን ነው። ሀገር ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች ብረት አቅልጠው ምርት የሚያቀርቡ ፋብሪካዎችም፤ ብረትን ከሀብቱ አውጥቶ አቅልጦ መስጠት የሚል ነው። ጥሬ እቃውን በሀገር ውስጥ ማቀነባበር ነው ትልቁ ሥራ።
በከፊል ያለቀውን ምርት ከውጭ ማምጣትና እዚህ ያለውን ቁርጥራጭ ብረት ሰብስቦ አቅልጦ ማቅረብ ነው። ይህ ለሀገር በቂ አይደለም። አሁናዊ የብረት ፍጆታችን ከ1 ነጥብ 5 እስከ 2 ቢሊዮን ቶን ነው። ይህንን ከውጭ እያስገቡ መቀጠል አይቻልም።
ከዚህ የተነሳ ብረት ላይ ትልቅ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው። የተጀመሩ ሥራዎችም አሉ። ፍለጋ ላይ ያሉ ተቋማት አሉ፤ እነሱ እንዲሠሩ ሥራዎችን እየሠራን ነው። ነገር ግን በዚህ ዘርፍ ላይ አሁንም ኢንቨስተሮችን ወደ ዘርፉ እንዲገቡ እያበረታታን ነው።
ከነዚህ ውጭ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚሆኑ የዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ጋራናይት፣ ማርብል፣ ላይምስቶን፣ በጣም ትልቅ ሀብት ነው ያለን። በትናንሽ ችግሮች እክል ቢገጥማቸውም ሀብቱ አለን፣ ማምረትም እንችላለን።
በዋናነት ግን በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ቀጣይነት ያለው ልማት እንድንመጣ ትልቁ ትኩረት የሚፈልገው ብረት ነው። ለዚህም ሥራ እየሠራን ነው። ብዛት ያላቸው በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት እንዲመጡ እየጋበዝን ነው፤ ሀብቱንም እያስተዋወቅን ነው።
ጥያቄ ፦ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ዘርፉ ያለው ተስፋ ሰጭነት ምን ይመስላል?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡- ተስፋ ሰጭነቱ እዚህ ያለውን ሀብት ዝም ብላችሁ ዞራችሁ ስታዩት ሊታወቅ የሚችል ነው፡፡ እውነታው አንዳንዴ ቁጭትም ያሳድራል። ተስፋውም በዛ መጠን አለ ማለት ነው።
ለዘርፉ መንግሥት ይህን ያህል ትኩረት ከሰጠው፣ የሀገራችን የሰላም ሁኔታ ከተስተካከለ እና ሁሉንም አስበንበት ከተጠቀምንበት ተስፋችን ብሩህ ነው። በወርቅ ላይ ብሩህ ነገር አለ። ፖታሺየም ላይ እንደዚሁ ፍላጎት ያላቸው፣ የጀመሩም ተቋማት አሉ። ፖታሽ በጣም ትልቅ ነው። ብዙ ሰው ማዕድን ሲባል በአዕምሮው የሚመጣለት ወርቅ ነው። ሊቲየምና ታንታልየም የመሰሉ በቅርቡ ሥራ የሚጀምሩ አሉ።
ስለዚህ ኤክስፖርትም ለማድረግ ከውጭ የሚገባውን ለማስቀረት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሥራ እድል ለመፍጠር በጣም ተጫባጭ የሆነ ተስፋ ያለው ዘርፍ ነው፡፡ የተፈጥሮ ጋዙን ለመጠቀም ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በዚህ ብዙ ሀገሮች ብዙ ተጠቅመዋል፡፡ እኛ ገና ነን፡፡ ከእነሱ ምን የምንማረው ነገር አለ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። አገራችን እንድትሆን ወደሚፈለገው ለማምጣት ሁላችን ገና ብዙ መሥራት አለብን፡፡ ተስፋችን ግን ተጫባጭ ነው። ሥራዎች በሁሉም ዘርፍ ላይ እየተሠሩ ነው፡፡
ጥያቄ ፡- ባለፉት ስድስት ወራት በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፍ ምን ያህል ገቢ አግኝታለች?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡– በባለፈው ሦስት ወር ስንገመግም የነበሩ ቁጥሮች እንዳለፈው ወቅት በምናውቀው መንገድ ነው እየሄደ ያለው፡፡ መሻሻል እስኪመጣ ድረስ ያን ያህል ለውጥ የለውም፡፡ አሁንም ያለው ከእቅዳችን ወደ 60 በመቶ የሚጠጋ ነው። ሌሎችን አላመጣናቸውም ሲሚንቶ ላይ የተሻለ የሚመስል ነገር አለ፡፡
ጥቁር ገበያውና ኮንትሮባንዱ በአነስተኛ ደረጃ የሚመረቱ ምርቶችን በጣም እየተፈታተናቸው ነው፡፡ እሱ ከፍተኛ ፈተና እየሆነ ነው፡፡ ያንን አሁንም ተባብረን እስካላስቆምን ድረስ ችግር እንደሆነ ይቀጥላል። ምርቱ ግን አለ፣ እየተመረተም ነው፡፡ በጣም ከፍተኛ ምርት አለ።
በዚህ በኩል የውጭ ሕገወጥ አካላትን አስቁመናል ነገር ግን የሀገር ውስጡ ኃላፊነት ተስምቶት ሀገሬን ነው እየጎዳሁ ያለሁት፡ አገሬን ነው መርዳት ያለብኝ ብሎ አስቦበት ካልሠራ ለዘርፉ ፈተና ይሆናል፡፡ ያንን ሙሉ ለሙሉ እስካላስቆምነው ድረስ ችግሩ ይቀጥላል።
ችግሩን በዘላቂነት መቆጣጠር የምንችለው ሥራው በፋብሪካ ደረጃ ሲሠራ ነው፤ ያኔ የቁጥጥር ሥራው ይቀላል። አጠቃላይ የሆነውን መረጃ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ማየት ይቻላል፡፡ አሁን እቅዱ ላይ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉ ነው የሚታየው፡፡ የዝናብ ወቅትም ነው፡፡ የስድስት ወሩን ገምግመን ስንጨርስ መረጃውን ይፋ እናደርጋለን ፡፡
ጥያቄ፡ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረጋችሁን ተከትሎ በሀገር ምን ያህል ባለሀብቶችን መሳብ ቻላችሁ?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡- ብዙ አሉ፡፡ በሁሉም ዘርፍ ላይ ብዙ አሉ፡፡ ፍላጎቱ ብዙ ነው፡፡ ፍለጋ ላይም ያሉ በመቶዎች የሚቀጠሩ ናቸው፡፡ በፋብሪካ ደረጃም ሊያመርቱ የሚችሉም እንዲሁ አሉ፡፡ አምስት ስድስት የሚሆኑ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ነው የመጡት። ብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማት መጥተው መቀላቀል ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንዶቹም የፍለጋ ሥራቸውን የቀጠሉ ፍቃድ የምንሰጣቸው አሉ።
ነገር ግን ቅድም ባልነው መንገድ እኛ ለዚህ ዘርፍ እንዲመቻች አድርገን ብዙ ነገሮችን መሥራት አለብን። በፖሊሲ ደረጃ እና በተቋም ደረጃ የሠራናቸው ሥራዎች ለነሱ በጣም ጠቃሚ ናቸው። ለሀገር ውስጥም አምራች፣ ለውጭ አምራችም በጣም ጠቃሚ ናቸው። ፍለጋው ላይም የኛ ትልቁ ችግር ሀብታችንን በደንብ አናውቅም። የሀገሪቱን 30 በመቶ የቆዳ ስፋት ላይ ያለውን ሀብት ነው የምናውቀው። የቀረውን አናውቅም።
በመሆኑም ሀብቱን ማወቁ እራሱ አንዱ ትልቁ ነገር ነው። ምክንያቱም የምንሸጠው እሱን ነው። ይሄን ያህል የሚገመት ሀብት አለን ኢንቨስት አድርጉ ማለት ይፈልጋል። እዛ ላይም ሥራዎች እየሠራን ነው። አንዳንድ ተቋማት ጋርም ከተለመደው ውጪ ጠቋሚ የሆኑ ጠቅላላ የሀብት መረጃዎች ሊሰጡ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ከያዙ ሀገራት ጋርም እየተነጋገርን ነው።
ሥራዎችንም እየጀማመርን ነው። ትልቁ ሥራ እንዳውም እንደሀገር ቅድሚያ የሚሰጠው እሱ ነው። ሀብትን እስካላወቅን ድረስ የት ቦታ ምን አለ? በምን ያክል የሚገመት የሚል እስከሌለ ድረስ ባለሀብቶች ብዙ ሀብት በፍለጋው ላይ እንዲያወጡ ጊዜ እንዲያጠፉ ያደርጋል።
ስለዚህ እዛ ላይ ሥራዎችን እየሠራን ነው። በአጫጭር ወራት ውስጥ ጠቋሚ መረጃዎችን ሊሰጡ የሚችሉ ናቸው። እነዚህን ሥራዎች በቅርብ ጊዜ እንጀምራለን የሚል እምነት አለ። የመንግሥት ድጋፍም አለ። ዘርፉ በባሕሪው በሁሉም የመንግሥት መዋቅር የሚፈልግ ዘርፍ በመሆኑም የሁሉም የጋራ ትብብር ይፈልጋል።
ሀገራችን የሀብታም ደሃ መሆን የለባትም። ዜጋውና ትውልዱ ይሄንን ሀብት በአግባቡ መጠቀም አለበት የምንል ከሆነ ሀብቱ አለ። በመሆኑም ሀብቱን ማልማት ሁላችንም ይጠበቅብናል። በመንግሥት ያለውም ከዚህ በፊት ያልነበረ ነው። ይሄ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት እንኳን የተቋቋመው በቅርብ ነው። ተገቢ ትኩረት አለው፤ ለማምረት አንዳንድ ችግሮችን መፍታት እና ሀብታችንን ይበልጥ ማወቅ ጅምር ላይ ያሉ ተቋማትን በፍጥነት ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከቻልን በሚቀጥሉት አንድ እና ሁለት ዓመታት በጣም ጥሩ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ተስፋ አለ።
ጥያቄ፦ የወርቅ ኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ ነው ሥራው ምን ያህል ውጤት አስገኝቷል? ለችግሩ በዘላቂነት የተቀመጠ መፍትሔ አለ ወይ?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡– በወርቅ ዘርፍ ላይ ያልተፈቀደላቸው ብዙ አካላት ተሠማርተው ነበር። መረጃው አላቸው፡፡ እነዚህ አካላት በሕግ እንዲጠይቁና ከአካባቢው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ይሄ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ግብረ ኃይሉ ከሁሉም ፀጥታ አካላት ፣ ከክልሎች ጋር በጋራ እየሠራ ነው፡፡ በዚህም የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ አለ፡፡ ዘላቂነቱ በተመለከተ ማዕድናት ያሉባቸው አካባቢዎች የፀጥታ መዋቅር በቋሚነት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ድሮም ነበር፡፡
በቀደመው ጊዜም ቢሆን የማዕድን ፖሊስ በማቋቋም ትልልቅ ሜጋ የማዕድን ቦታዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ የተለመደ ነው። በግብረ ኃይሉም በኩል እየተሠራ ያለው ይኸው ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው የማጽዳት ሥራ ተሠርቷል። በወቅቱ ብዙ ሀብት ተወርሷል፤ ብዙዎችም ተጠያቂ ተደርገዋል። የብዙ አካላት ፈቃድ ተሰርዟል፡፡ ውጭ ሀገር ዜጎችም በዚህ ሕገወጥነት ውስጥ ተገኝተዋል፡፡
ክልሎች ብዙ በሕገወጥ መንገድ የተሰማሩ የሀገር ውስጥ ተቋማትን ሀብት ወርሰዋል ተጠያቂም አድርገዋል። ዘላቂነቱ እንግዲህ እንደ ሀገር ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ቅድም ባልኩት መልኩ ነው። ኮንትሮባንድን እንደሀገር የምናይበት መንገድ ለማዕድን ብቻ ሳይሆን በሁሉም ቦታ ላይ ነው። ኮንትሮባንድ ትልቁ ተግዳሮት እየሆነ ነው፡፡ እሱ እንደሀገር የሚሠራ ሥራ ነው፡፡
ጥያቄ ፦ በሀገሪቱ ‹‹ሊቲየም›› ለማልማት ወደ ሀገር ውስጥ የገባና ሥራ የጀመረ ኩባንያ አለ። እስካሁን ያለው አፈጻጸም ምን ይመስላል ?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡- ሊቲየም፣ ታንታለም እና ሌሎች ማዕድናት በአንድ አካባቢ ላይ ብቻ ሳይሆን ብዙ ቦታዎች ላይ ያሉ መሆኑን ጠቋሚ መረጃዎች አሉ። የነበረው ቦታ ላይ የምናወቀው ሊትየም ምርት ላይ እንዲያመርቱ ፈቃድ የተሰጣቸው አካላት አሉ፡፡
ዘርፉ ጥንቃቄ የሚፈልግ ዘርፍ ነው፡፡ ትክክለኛ አቅም ያላቸው አካላት፤ በዚህ ዘርፍ ላይ ልምድ ያላቸው እና የገንዘብ አቅምም ያላቸው ተቋማት በተለይ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ሥራው እንዲገቡ ሥራዎች መሥራት አለብን፡፡ ፈቃድ ለጠየቀ አካል ሁሉ መስጠት የለበትም፡፡ በጣም ጥብቅ የሆነ ሥራ መሥራት ይጠይቃል፡፡
ከዚህ በፊት የተወሰኑ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ ከዚህ የተነሳ አልሚዎች ችግር ሆነውብናል ብለው የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት በክልልም ሆነ በተቋማት ደረጃ እየተነጋገርን ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ይህንን ችግር እንፈታለን ብለን እናሳባለን። ወይ ችግሩ ተስተካክሎ ሥራ ይሠራሉ አለበለዚያ ሙሉ ለሙሉ የሥራ ውሏቸው ተቋርጦ ለሚያለማውና ብቃት ላለው አካል እንዲተላለፍ እናደርጋለን፡፡
ጥያቄ ፦ የፌዴራል መንግሥቱና የክልል የማዕድን ቢሮዎች መካከል የመናበብ ችግር እንዳለ በዘርፉ የተሠማሩ አካላት የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡ ምን ያህል ተናባችሁ እየሠራችሁ ነው ?
ኢንጂነር ሀብታሙ፡– የፌዴራል መንግሥቱና የክልል የማዕድን ቢሮዎች በተመለከተ ሁሉም በራሳቸው በአዋጅ የተቀመጠ ተግባርና ኃላፊነት አላቸው፡፡ የፊዴራል መንግሥቱ አዋጅ የማውጣትና ሜጋ ፕሮጀክቶችን እና የሀገር ቁልፍ የሆኑ ነገሮችን ነው በአብዛኛው በቀጥታ የሚያስተዳድረው፡፡ ክልሎች ራሳቸው የቻሉ አካላት ናቸው፡፡ ልክ እንደፌደራሉ ሕግ የሚያወጣ ሕጉንም የሚያስፈጸም የሚጠይቅ አካል አላቸው፡፡ በዚያ ደረጃ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው፡፡
ከዚያ ውጭ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ፣ ሀብት በማስተዋወቅ እና ሕግን በማውጣት የሚፈልጓቸውን ነገሮች ድጋፍ በመስጠት ረገድ ላይ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ ገና ብዙ የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ በሁሉም አካል የሚሰጡ የማዕድን ፕሮጀክቶች ተጠያቂነታቸው በሁሉም አካላት ነው፡፡ እነሱም እራሳቸው የቻሉ አካላት ናቸው፡፡
የፌዴራል መንግሥት ያለው ተግባርና ኃላፊነት አላቸው፡፡ ይሄ ተጠያቂነት እና ኃላፊነት አብሮ መኖር አለበት፡፡ በዚህ ሁኔታ ባለፉት ወራትም የተወሰዱ ማስተካካያዎች አሉ፡፡ አሁንም ብዙ መሥራት አለባቸው። ካውንስሉም በዚህ ላይ ያለውን ክፍተት ለመሸፈን ነው በዋናነት የተቋቋመው፡፡
አዲስ ዘመን እሁድ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም