የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ከመልክዓ-ምድራዊ ጉርብትና ባለፈ ከፍ ያለ ማኅበራዊ ትስስር ያላቸው ሕዝቦች ናቸው። የቅኝ ግዛት መስመሮች እንደ ሀገር ይከፋፍላቸው እንጂ፤ አሰፋፈራችው ከመስመሩ ያለፈ ስለመሆኑ አካባቢውን ለማየት ዕድል ላገኘ በቀላሉ ሊያስተውለው የሚችለው ተጨባጭ እውነታ ነው ።
በአንዱ ሀገር ያለ ሕዝብ በሁለንተናዊ ማንነቱ/ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ማንነቱ/ድንበር ተሻግሮ በሌላ ሀገር፣ በሌላ ዜግነት ሰፍሮ ማየት የተለመደ ነው። የሕዝቦቹ እንቅስቃሴም ቢሆን በድንበር መስመሮች የሚገታ አይደለም፤ ከዚያ አልፎ የሄደ ነውና።
በአብዛኛው የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች በባሕልና በሃይማኖት የተሳሰሩ፣ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው በመካከላቸው ጠንካራ ትስስርና ጉርብትና መፍጠር የሚችሉና የፈጠሩም ናቸው የዕለት ተዕለት ማኅበራዊ መስተጋብራቸውም ነገዎቻቸውን በጋራ እንዲሠሩ የሚያስገድዳቸው ነው።
ይህም የጋራ ሠላማቸውን በጋራ ማጽናት የሚያስችል፣ ከዚያም አልፈው ያላቸውን አቅም አቀናጅተው ነገዎቻቸውን ብሩህ ማድረግ የሚያስችል መልካም ዕድሎችን ብሎም ስለ ነገዎቻችው መክረው ለጋራ ተጠቃሚነት ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበትን የተሻለ አማራጭ ፈጥሮላቸዋል።
እስካሁን ባለው እውነታ ግን ይህ ሲሆን አልታየም። ከሁሉም በላይ አካባቢው ካለው የጂኦ-ፖለቲካል ስትራቴጂ አኳያ የብዙዎች ዓይን ማረፊያ፣ የብዙ ፍላጎቶች መሻኮቻ በመሆኑ የአካባቢው ሀገራት በተለያዩ ወቅቶች በሚከሰቱ ግጭቶች ሠላማቸውን በማጣት ብዙ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ተገደዋል፤ ዛሬም እንደተገደዱ ናቸው ።
ያለ ፍላጎታቸው በሚገቡበት ግጭት ለከፋ ድህነትና ኋላቀርነት፤ ግጭት ለሚያስከትለው ሞትና ስደት፣ የኢኮኖሚ ውድመት ተዳርገዋል፣ ሁሉ እያላቸው ቀናትን ለማሸነፍ ሁሌም እጃቸውን ለምፅዋት ማንሳት ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል። በዚህ ሁሉ ግን የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ፍላጎታቸው ሠላም እና ልማት ነው።
የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች እንደ ሀገር ካላቸው ሊለማ የሚችል የተፈጥሮ ሀብትና አምራች የሰው ኃይል አኳያ ከልማት ጋር የተያያዘው ፍላጎታቸው ሊያጋጥመው የሚችለው ተግዳሮት ሠላማቸውን መመለስ እስከቻሉ ድረስ ብዙም እንደማይሆን ይታመናል።
በተለይም የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ያላቸውን አቅም አቀናጅተው በጋራ መንቀሳቀስ የሚችሉበት ዕድል ከተፈጠረ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ሆነው ሊወጡ እንደሚችሉ ብዙም አጠያያቂ አይደለም። ለዚህ በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ተሞክሮ ማየት በቂ ነው ።
የሀገራቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ሆኖ የመውጣት አቅም፣ የሚያሳስባቸው፤ ለብሔራዊ ጥቅማችን ስጋት ነው ብለው የሚያምኑ ሀገራትና ቡድኖች አካባቢው የግጭት ማዕከል እንዲሆን እንቅልፍ አጥተው እየሠሩ ነው። በቀጣናው ላለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት የሆነውም ይሄው ነው።
ለዚህ ደግሞ በቀጥታ በሀገራቱ የውስጥ ጉዳይ ከመግባት ጀምሮ፤ በሀገራቱ መካከል ልዩነቶችን ለሚያቀነቅኑ ቡድኖች እና ሥልጣን ላይ ለሚገኙ መሪዎች ድጋፍ እያደረጉ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ዕጣ ፈንታቸውን በጋራ እንዳይሠሩ ግድግዳ ሆነውባቸዋል።
የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ቅኝ ገዥዎች ባሰመሯቸው የልዩነት መስመሮች ታግተው፣ ከገዛ ወንድሞቻቸው ጋር የጋራ ዕጣ ፋንታቸውን የሚወስኑበትን ነፃ ፈቃድ ተነጥቀው፣ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ሆነዋል። ይህም ችግሮቻቸውን ከማወሳሰብ ባለፈ ያመጣላቸው አንድም የተሻለ ነገር የለም፤ ሊኖርም አይችልም ።
አሁን ግን ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ፤ እንደ አንድ የቤተሰብ አባል የጋራ ዕጣ ፈንታቸውን በጋራ መወሰን የሚችሉበትን ተፈጥሯዊ መብታቸውን መጠቀም የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል። በአንድነት ተነስተው ለጋራ ብሩህ ነገዎቻቸው የሚነሱበትና በቁርጠኝነት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታም ተፈጥሯል ።
ይህ መብታቸው በየትኛውም የውጪ ኃይል የጥቅም መሻትም ሆነ፣ በመንግሥታት ፍላጎት እንዳይደናቀፍ፣ በየትኛውም ፈተና ተሰናክሎ እንዳይወድቅ ዘብ ሊቆሙ ይገባል፤ ትናንት በመከፋፈላቸው አቅም አጥተው የከፈሉትንና አሁንም እየከፈሉ ያለውን ያልተገባ ዋጋ በማጤን ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን የቀረበውን አብሮ የመልማት ጥሪ ሊቀበሉ ይገባል።
እንደ አንድ ቤተሰብ የጋራ ዕጣ ፈንታችንን በጋራ ለመሥራት፤ በዚህም ለራሳችን ሆነ ለመጪዎቹ ትውልዶች የተሻለች የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ለመፍጠር፤ በተባበረ አዕምሮና ክንድ አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ሆኖ ለመውጣት ጥሪውን በበጎ ሕሊና መቀበል ተገቢ ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም