የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች የመገናኛ ብዙኃን የዕለት ተዕለት ዜና መሆን ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። የችግሩ አሳሳቢነትም ዓለም አቀፍ አጀንዳ ከሆነ ውሎ አድሯል። መፍትሄ የማፈላለጉም ሥራ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ይገኛል።
ችግሩ በተለይም በድሆችና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ሕዝቦች ላይ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ” በመሆን፤ አጠቃላይ በሆነው የመልማት ፍላጎታቸው ላይ ትልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል። ምክንያት ላልሆኑባቸው ችግሮች ዋነኛ ገፈት ቀማሽ በመሆንም ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ተገደዋል።
በተለይም የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ ከሚከሰተው ድርቅ ጋር በተያያዘ ተጠቂ የሆኑ የአፍሪካ ሀገራት፤ ችግሩ ቀድሞውኑም በምግብ እህል ራሳቸውን የቻሉ ካለመሆናቸው ጋር ተዳምሮ ፤ሕዝቦቻቸውን ለከፋ አደጋ ተጋላጭ እያደረጋቸው ይገኛል።
የችግሩን አሳሳቢነት ቀድመው የተረዱ የአህጉሪቱ ሀገራት መንግሥታትም ቢሆኑ፤ ችግሩን ቀድመው ለመከላከል ለሚያደርጉት ዝግጅት በቂ የሆነ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ባለማግኘታቸው አደጋዎች ሲከሰቱ ባሰቡት ልክ ሕዝቦቻቸውን መታደግ የሚያስችል አቅም መገንባት ተስኗቸው፤ እጃቸውን ለርዳታ ለማንሳት መገደዳቸው የማይቀር ሆኗል።
ችግሩን እያስከተለ ካለው ዓለም አቀፍ ምስቅልቅል አንጻር ለማየት ፈቃደኛ ያልሆነው አንዳንድ አካላት በችግሩ ሰለባ በሆኑ ሀገራት ሕዝቦች ስቃይ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በየትኛውም ሰብአዊ መመዘኛ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።
ችግሩ በተደጋጋሚ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ሕዝቦች ላይ እየተከሰተና ዋጋም እያስከፈላቸው ነው። የቀጣናው ሕዝቦች በተደጋጋሚ የድርቅ እና የጎርፍ አደጋዎች እየተጠቁ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። በዚህም እየከፈሉት ያለው ዋጋ ነገዎቻቸውን እያደበዘዘባቸው ነው።
አሁን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የአየር ንብረት ለውጥ ተከትሎ በተከሰተ የድርቅ አደጋ ከፍተኛ ለሆነ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።ችግሩ ወደ ከፋ ረሀብ እንዳይቀየርም ስጋት ስለመፍጠሩ ከሁሉም በላይ ከችግሩ ዋነኛ ባለቤቶች እየተነገረ ነው።
ችግሩ በኛም ሀገር አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጋችን የአስቸኳይ ርዳታ ድጋፍ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፤ በቀጣይ ሦስት ወራትም የርዳታ ፈላጊዎቹ ቁጥር ወደ ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሊያድግ እንደሚችልም ይታመናል።
ከርዳታ ፈላጊዎቹ 80 በመቶ የሚሆኑት፤ በአማራ ክልል ስምንት ዞኖች፣ በትግራይ ክልል አራት ዞኖችና በአፋር ክልል ሦስት ዞኖች የሚገኙ ናቸው፤ ችግሩ ወደ ረሃብ እንዳይቀየር በመንግሥት በኩል ተከታታይ የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉ ነው።
መንግሥት ቀደም ባለው ጊዜ በምግብ እህል ራስን ለመቻል የጀመራቸው ጥረቶች እና ጥረቶቹ እያስገኙት ያለው ውጤት፤ችግሩ የከፋ አደጋ ከማስከተሉ በፊት መከላከል የሚያስችል ብሔራዊ አቅም መገንባት አስችለዋል። ከዚህ የተነሳም እስካሁን ባለው ሂደት ችግሩ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሳይሆን ቀርቷል ።
ችግሩን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ እስካሁን አብዛኛውን ድጋፍ እያቀረበ የሚገኘው መንግሥት ነው። ይህ መንግሥት ከፈጠረው የአደጋ መከላከል ዝግጁነት አንጻር ከፍ ያለ እውቅና ሊያሰጠው የሚገባና እንደ አንድ ስኬታማ ተሞክሮ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ከዚህም ባለፈ መንግሥት በተለያዩ ወቅቶች በመርህ ደረጃም “አንድም ኢትዮጵዊ በምግብ እጥረት ምክንያት መሞት የለበትም፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ያለንን ሀገራዊ አቅም በሙሉ በመጠቀም ዜጎችን ከአደጋ ለመታደግ ዝግጁ መሆኑን” ደጋግሞ ማሳወቁ ለዜጎች ሕይወት ያለውን ከበሬታ በተጨባጭ ያሳየ ነው።
እስካሁንም በመላ ሀገሪቷ ባሉት ከሶስት ሺህ በላይ የምግብ ማከማቻ ጣቢያዎች፤ ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር አንስቶ እስከ ታኅሣሥ መጀመሪያ ድረስ 11 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ቁሳቁሶችንና የምግብ ድጋፎችን በሶስት ዙሮች አቅርቧል። በዚህም የብዙ ዜጎችን ሕይወት መታደግ ችሏል።
ይህም ሆኖ ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ችግሩንና ከችግሩ በስተጀርባ ያለውን ተጨባጭ እውነታ ተሳቢ በማድረግ፤ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን የመደገፍ የሕግ ሆነ የሞራል ኃላፊነት አለበት።ለዚህም ከተለመዱ ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታዎች ወጥቶ ፈጥኖ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
የመንግሥት ጥረት ውጤታማ እንዲሆንም የችግሩን ግዝፈት እና አሳሳቢነት ከማውራት ወጥቶ፤አስፈላጊውን ድጋፍ ፈጥኖ በማቅረብ ኃላፊነቱን ሊወጣ፤ ከተጠያቂነት ራሱን ሊታደግ በሚያስችል ተጨባጭ ተግባር ውስጥ ሊገኝ ይገባል።
በተለይም ለአየር ለውጥ በዋነኛነት ተጠያቂ የሆኑ ሀገራት ፤እነሱ በፈጠሩት ችግር ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል እየተገደዱ ላሉ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ሕዝቦች አስፈላጊ የሆኑ ርዳታዎችን ከማቅረብ ጀምሮ የሀገራቱ መንግሥታት በምግብ እህል ራሳቸውን ለመቻል ለሚያደርጉት ጥረት ስኬት በቁርጠኝነት ከጎናቸው መሰለፍ ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን ጥር 4/2016