በቴክኖሎጂ ፈጠራ ከተቀጣሪነት ወደ ኢንቨስተርነት

ከዛሬ 37 ዓመት በፊት ነው በኤሌክትሪክሲቲ ሙያ ከተግባረ-ዕድ ትምህርት ቤት በከፍተኛ ውጤት የተመረቁት፡፡ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ቤት የሚያሸጋግር ውጤት ቢኖራቸውም፣ ቤተሰቦቿቸውን በኢኮኖሚ ማገዝ እንዳለባቸው አምነው ሥራ ፍለጋ ማሰኑ። ይሁንና የተወለዱባትና ያደጉባት አዲስ አበባ ልክ እንደዛሬው በኢንዱስትሪ አልተከበበችምና እሳቸው በተመረቁበት ሙያ ልትቀጥራቸው አልቻለችም፡፡

እኚህ ሰው የዛሬው የስኬት እንግዳችን የኢ ሜክ ኢንጅነሪንግ እና አግሮ ኢንዱስትሪ ትሬዲንግ መሥራችና ጀነራል ማናጀር ኤፍሬም ኃይሉ ናቸው። ቀያቸውና ያሳደጋቸውን ማኅበረሰብ ለቀው ለመውጣት የተገደዱት እንግዳችን፤ በወቅቱ ግንባታ ላይ ወደ ነበረውና 575 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው ጣና በለስ ፕሮጀክት ነበር ሥራ ፍለጋ የተጓዙት፡፡

ለቴክኖሎጂ ልዩ ፍቅር የነበራቸው የያኔው ወጣቱ ኤፍሬም ሥራ ለመልመድ ብዙ አልተቸገሩም፤ በኤሌክትሪክና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉ እጃቸውን ከማፍታት አልፈው አዳዲስና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች የመፍጠር አቅም አጎለበቱ። ለ13 ዓመታት በሙያው ድንቅ ብቃታቸውን አሳዩ። በተለይም ከቅርብ አለቃቸው ጋር በመሆን ለፕሮጀክቱም ሆነ ከዚያ ውጪ በሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርቶችን በማምረትና በመጠገን ለሀገራዊ ልማቱ የበኩላቸውን ጥረት አደረጉ፡፡

አንዲት የሥራ አጋጣሚ ግን የሕይወት አቅጣጫቸውን እንደቀየረችላቸው አቶ ኤፍሬም ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ከአለቃዬ ጋር በመሆን አዲስ አበባ የድንጋይ መፍጫ ማሽን ለመትከል በመጣንበት ወቅት የሚያግዘን ባለሙያ ብንፈልግም ሙያውን የሚያውቅ አንድም ሠራተኛ ማግኘት አልቻልንም፤ በመሆኑም ለዚህ ችግር እኔው ራሴ የመፍትሔ አካል መሆን እንዳለብኝ አመንኩኝ፤ ያለውን ክፍተት በመጠቀም የራሴን ድርጅት ለመክፈት ወሰንኩኝ›› ይላሉ፡፡ ይህንን ውሳኔያቸውን የሰሙ አለቆቻቸውና ጓደኞቻቸው ሃሳባቸውን ደገፉላቸው፡፡

ከሦስት የቤተሰብ አባላት ጋር በመሆን በአምስት ሺ ብር ሥራውን መጀመራቸውን የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፣ ለስድስት ወራት ያህል ያለምንም ገቢ መሥራታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ይሁንና ትልቅ የመንፈስ ጥንካሬና ራዕይ በመሰነቅ በመነሳታቸው ለፈተናዎች ሳይበገሩ አዳዲስ የማኑፋክቸሪንግ ማሽኖችን ለመሥራት ተጉ፡፡ ‹‹ያን ጊዜ በዘርፉ ያለውን ክፍተት በማየት በድፍረት በመግባቴ እንደሃገር የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል የበኩሌን ተወጥቻለሁ፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ›› ይላሉ፡፡ ለዚህም አብነት አድርገው ‹‹ኢንዱስትሪው በሚፈልገው ደረጃ ባለሙያ ባለመኖሩ ብዙ ሥራዎች በእጅና ኋላቀር በሆነ መንገድ ነው የሚከናወነው ይከናወኑ የነበሩት። ሌላው ይቅርና እንደሥጋ መፍጫ ያሉ የማዕድ ቤት የኢንዱስትሪ እቃዎችን የሚጠግኑ ባለሙያዎች እጥረት ነበር፡፡ በዚህም እስከ ትላልቅ ሆቴሎች ድረስ የሚቸገሩበት ሁኔታ ነበር›› በማለት ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህ በመነሳትም የሰው ኃይሉን ከማሠልጠን ጀምሮ የጥገና እና የተለያዩ የውሃና ኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂዎች፤ እንዲሁም የመኖ ማቀነባበሪያ የመሳሰሉ የአግሮ ኢንዱስትሪ ማሽኖችን በማምረት ወደ ገበያው መግባታቸውን ያመለክታሉ፡፡ ‹‹ሰብ ኮንትራቶችን በመያዝ የውሃ ልማት፤ ኤሌክትሪክ፤ አግሮ ኢንዱስትሪ፤ የእንስሳት ማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በማምረት በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች አቅርበናል›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

በዋናነትም ኢትዮጵያ በቀንድ ሃብቷ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ መሪ ሆና ሳለ ከዘርፉ ተጠቃሚ አለመሆኗ የሁልጊዜ ቁጭታቸው ስለነበር ምርታማነታቸው የተረጋገጠ ቴክኖሎጂዎችን እንደሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ እሴት በመጨመር በድርጅታቸው በስፋት ወደማምረት መግባታቸውን ነው የሚያብራሩት፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በቀንድ ሃብቷ ተጠቃሚ ያልሆነችበት አንዱ ምክንያት የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን እጥረት በመኖሩ ነው፤ እኛም ሥራ በጀመርንበት ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበሩት ማሽኖች ከ20 አይበልጡም ነበር›› የሚሉት ጀነራል ማናጀሩ፤ ድርጅታቸው በዚህ ዘርፍ ላይ በቂ እውቀት ያለው በመሆኑ 30 በመቶ ማሽን የማምረት ሥራ፤ 70 በመቶ ደግሞ የማሽን ጥገና ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት መቀጠሉን ነው ያብራሩት፡፡ በተጓዳኝም ሌሎች ማሽኖችን የማምረት፤ የሠለጠነ የሰው ኃይሉንም የማበራከት፤ አዳዲስና ምርታማነታቸው የተረጋገጡ ማሽኖችን እየሠራ ለገበያው ማቅረብ መቀጠሉን ያነሳሉ፡፡

እንደ አቶ ኤፍሬም ማብራሪያ፤ ድርጅታቸው የሚያመርታቸው ማሽኖች በገበያው ተቀባይነት እያገኙ ሲመጡ በተለይም የመንግሥትና የተራድዖ ድርጅቶች በስፋት እንዲያመርቱ ግፊት ያድርጉባቸው ነበር፡፡ ከዚህም በመነሳት አዳዲስና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የዶሮና የከብት መኖ ማሽኖችን ለመሥራት ሰፊ ጥናት አድርገዋል፡፡ እስካሁንም ከ700 የሚልቁ ማሽኖችን በማምረት ለዘርፉ ያበረከቱ ሲሆን 11 የሚሆኑትን ለአዕምሯዊ ንብረት አስመዝግበው ለአራቱ እውቅና (ፓተንት) ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተጨማሪም 70 ዓይነት የተመጣጠነ የዶሮ መኖ ማዘጋጀት የሚችሉ ማሽኖችን ለተጠቃሚዎች አድርሰዋል፡፡

ድርጅታቸው በመላው ሃገሪቱ በሚከናወኑ ትላልቅ ልማቶች ላይ የመሳተፍ እድሉን ማግኘቱን ጠቁመውም ‹‹የአሜሪካ ኤምባሲ ግንባታ ሲከናወን ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን ኮንትራት ወስደን ሠርተናል፤ ካጅማ ደጀን ላይ ሲሠራ የሲሚንቶ ማደባለቂያ ማሽኑን የሠራነው እኛ ነን፡፡ ደብረማርቆስ ውሃ ልማት ሥራ ላይ ሰፊ ተሳትፎ ነበረን›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ አሁን ላይ ድርጅቱ ማሽኖችን ጥገና የማድረግ አቅሙ በከፍተኛ መጠን መጎልበቱን ጠቅሰው፣ ይህም በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እንዳስቻለ ይናገራሉ። በተጨማሪም ነፃ የማማከር አገልግሎት በመስጠት ለዘርፉ እድገት ሚናውን እየተወጣ ነው ይላሉ፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜም ድርጅታቸው የሚያመርታቸው ማሽኖች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን እንዲጠብቁ በማድረግም በርካታ ሥራ መሥራቱን አመልክተው፤ በተለይም ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ መለያ(ብራንድ) ይዛ እንድትቀርብ የተሠራው ሥራ ውጤታማ የሚባል እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለአፍሪካ ገበያም አቅርበናል፡፡ ይሁንና በገበያው ፍላጎት ቢኖርም የፋይንስ ውስንነት ስለነበረብን በስፋት አምርተን ማቅረብ አልቻልንም›› ይላሉ፡፡ በዚህ ተስፋ ሳይቆርጡ ሌሎች አጋዥ ድርጅቶችን እያፈላለጉ መሆኑንም አጫውተውናል፡፡

እንደ ጀነራል ማናጀሩ ማብራሪያ፤ ድርጅቱ እስካሁን ባለው ጊዜ ከ300 እስከ 400 የሚሆኑ ባለሙያዎችን አፍርቶ ለኢንዱስትሪው ያስረከበ ሲሆን ለ40 ዜጎች ደግሞ ቋሚ የሆነ የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡ ካፒታሉንም ከአምስት ሺ ተነስቶ ወደ 200 ሚሊዮን ብር አሳድጓል። በቅርቡም ድርጅታቸውን ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪነት ለማሳደግ የሚያስችለውንና ቦሌ ለሚ ላይ የሚገኝ 10 ሺ ካሬ መሬት ለመረከብ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

‹‹አሁንም ኢንዱስትሪ የሚፈልገውን ባለሙያ፣ የመለዋወጫ ዕቃና ቴክኖሎጂ በጥናት ላይ ተንተርሰን በስፋት ለማምረት እየሠራን ነው፤ ኢንዱስትሪው የሚጠይቀውን የትኛውንም ጥያቄ ሃገራችን ውስጥ ባለ ግብዓት መፍትሔ እየሰጠንም ነው›› ይላሉ። እስካሁንም ከአጠቃላይ አቅማችን 20 በመቶውን ብቻ ሠርተናል ብለው እንደሚያምኑ የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፤ ‹‹በቀጣይ የአቅማችንን 80 በመቶ ለማምረት በተለይ ቦታ፤ የፋይናንስ አቅርቦት የምናገኝ ከሆነ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ክልሎች ላይ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመት ውስጥ ከአንድ ሺ በላይ ሠራተኞችን ቀጥረን ለማሠራት ራዕይ አለን›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በቅርቡ ቦሌ ለሚ ላይ ሥራ ሲጀምር ደግሞ 20 በመቶውን ምርት ለወጭ ገበያ ለማቅረብ ድርጅቱ ማቀዱን ነው የጠቆሙት፡፡

በተጨማሪም ራሳቸው ያመረቷቸውን ቴክኖሎ ጂዎችን በመጠቀም በግብርና ሥራ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የተናገሩት ጀነራል ማናጀሩ፤ የተለያዩ አዝርዕቶችን በስፋት በማምረትና ከብትና የዶሮ እርባታ ላይ በመሰማራት የሃገሪቱን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ሥራ ላይ አወንታዊ ሚና ለመጫወት ተግተው እየሠሩ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

ድርጅታቸው መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ላይ በማተኮሩና ዘርፉ ሰፊ የእሴት ሰንሰለት በመኖሩ ተጨማሪ የሥራ እድል እንዲፈጠር ያደረገ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ‹‹እኛ የምናመርተው አንድ ማሽን ቢያንስ ከ15 እስከ 20 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራል›› ይላሉ፡፡ ከዚህ ባሻገርም መኖ ልክ እንደ ነዳጅ በየጊዜውና አካባቢው ዋጋው እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ በየአካባቢው የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ሲተከል የአካባቢውን ኅብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ሃገርንም ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ድርጅታቸው ነባርና በዘርፉ መሥራች ኩባንያ እንደመሆኑ በሀገር ደረጃ ያሉ የኢንዱስትሪ ነክ ችግሮችን ለመፍታት በኃላፊነት ይሠራል፡፡ ይህም መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እምነት በማሳደር ትልልቅ ሥራዎችን እንዲሰጧቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ድርጅቱ የሚያመርተው ምርት በየጊዜው የጥራት ደረጃ የሚለካ ሲሆን ይህንንም እንደመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ካሉ ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል። በተለይም ከምርምር ማዕከላት ጋር አብሮ የመሥራት ባሕሉን በማጠናከር በጤፍና በሌሎች ሃገር በቀል ምርቶችን ምርታማነት የሚያሳድግ ቴክሎጂዎችን ለማምረት እቅድ ይዟል፡፡

ቀደም ባሉት ግዜያት ኢትዮጵያ ያላትን የሰለጠነ የሰው ኃይል በአግባቡ የምትጠቀም ሃገር ያለመሆንዋ ትልቅ ቁጭት እንደሚያሳድርባቸው አቶ ኤፍሬም ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ከዛሬ 30 ዓመት በፊት በእርሻ መሣሪያዎች ላይ ብዙ የሚሠሩ ባለሙያዎች ነበሩ። ነገር ግን አዲስ አበባ ውስጥ የሚቀጥራቸው ድርጅት በማጣታቸው አብዛኛዎቹ ባለሙያዎች ወደ ሹፍርና ገብተዋል፡፡ በተለይም በኢንዱስትሪ ዘርፉ ብዙ ሃብት ፈሶበት የሠለጠነው ይህ ኃይል ሰው ሃብቱን የሚሰበስብ የለም›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያስችላት ልማት ላይ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የፋይናንስ እጥረትና ባንኮች ለዘርፉ ተዋናዮች ድጋፍ የማድረግ ፍላጎታቸው ዝቅተኛ መሆንም ኢንዱስትሪው እንዳያድግ ሌላው ማነቆ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹በየከተማው ቁጭ ብለው ‘አተረፍን’ የሚሉ ባንኮች የፈጠራና ምርምር ሥራ ለሚሠሩ አካላት ማበደር አይፈልጉም፡፡ በዚህ ምክንያት ዘርፉ ማደግ አልቻለም። ሰው ከከተማ ወጥቶ እርሻ መሥራት ካልቻለ፤ ገበሬው ቴክኖሎጂ መጠቀም ካልቻለ እድገታችን ወደ ኋላ የሚሆነው›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

ከአቢሲኒያ በኳሊቲ አዋርድ እንዲሁም ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እውቅና እና ሽልማት ያገኙት አቶ ኤፍሬም፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ዘርፉ እንዲያድግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ያሳስባሉ። በተለይም የፋይናንስ ተቋማቱ አዳዲስ የፈጠራ ውጤት ይዘው ያለሥራ የተቀመጡ ባለሙያዎችንና ኢንዱስትሪያቸውን የማስፋፋቱ ፍላጎቱ ኖሯቸው በፋይናንስ እየጥረት የተገደቡ ድርጅቶችን እንዲደግፉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You