አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቀዳሚውና ፈር ቀዳጅ ዩኒቨርሲቲ ነው። ዩኒቨርሲቲው በረጅም ዘመን አገልግሎቱ በርካታ ምሑራንን አፍርቷል፤ ለሀገርና ሕዝብ የጠቀሙ የምርምር ሥራዎችን አካሂዷል። ዩኒቨርሲቲው እነዚህን ኃላፊነቶቹን በቀጣይም ለመወጣት እያካሄዳቸው ከሚገኙ ተግባሮች መካከል ለመማር ማስተማር፣ ምርምርና ለመሳሰሉት ተግባራት ወሳኝ የሆኑ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በተለያዩ ካምፓሶቹ እያካሄደ ይገኛል፡፡
ዩኒቨርስቲው በቅርቡ ደግሞ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ እየተካሄዱ የሚገኙትንም ሆነ በቀጣይ የሚያካሂዳቸውን የግንባታ ፕሮጀክቶችንም ሆነ ሌሎች ሥራዎቹን ይሄንን ራስ ገዝነቱን የሚመጥኑ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ለእዚህም የዲጂታላይዜሽን አቅም ማሳደግ፣ የመምህራን፣ የሠራተኞችንና የተማሪዎችን አቅም ማጎልበት ይጠበቅበታል። ዩኒቨርሲቲው ለተለያዩ ሥራዎች የሚጠቅሙትን የመሠረተ ልማት አቅሞች ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
በፋይናንስ አቅሙና በአገልግሎቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስቀመጠውን ራዕይ እውን ለማድረግ እየሠራ ነው። ተቋሙ ስድስት ኪሎ ያለውን ዋና ግቢን ጨምሮ በርካታ ካምፓሶች ያሉት ሲሆን በአብዛኞቹ ካምፓሳቹም በርካታ የግንባታ ፕሮጀክቶችን እያካሄደ ይካሄዳል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የተቋማዊ ለውጥ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ወንድወሰን ሙሉጌታ በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች አስመልክተው እንዳብራሩት፤ በዩኒቨርሲቲው የተቋቋመው የሪፎርም ቡድን ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በዩኒቨርስቲው 16 የሚደርሱ ከመሠረተ ልማት ጋር ተያያዥ የሆኑ ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን አብዛኞቹ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ ትላልቅ ሕንፃዎችን ጨምሮ እስከ ምድረ ጊቢ ማስዋብ፣ የአጥር እና የአካባቢ ውበት መጠበቅን የመሳሰሉ ስፋፊ ሥራ የሚካሄድባቸው ናቸው።
በጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እየተገነቡ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች መካከል የድንገተኛ ክፍል፣ የተመላላሽ ታካሚዎች፣ የተማሪዎች ማደሪያ ሕንጻ ግንባታዎች የሚገኙበት መሆኑን ዶክተር ወንድወሰን ይናገራሉ፡፡ በአቡነ ጴጥሮስ ካምፓስም እንዲሁ ለጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል እና ለሌሎች የሥራ ክፍሎች አገልግሎት የሚውሉ እንዲሁም ከፍተኛ ገቢ የማመንጨት አቅም ያላቸው የሕንጻ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ያስረዳሉ፡፡
በዋናው ጊቢም እንዲሁ የፎረም ሕንጻ ወይም አካዳሚክ ኮምፕሌክስ የሚባል በየካቲት 12 ሰማዕታት አደባባይ በኩል አየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚሁ ግቢ “ዎክ አፕ ዶርሚተሪ” የሚባል በርካታ ተማሪዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው የዶርሚተሪ ፕሮጀክት እንዲሁም የአጥርና አካባቢ ማስዋብ ሥራ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ነው ያብራሩት፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በአራት ኪሎ ካምፓስ እንዲሁ የጂኦፊዚክስ ወይንም ተዛማጅ ሥራዎች የሚሠራበት ሕንጻ፣ በአምስት ኪሎ ካምፓስም በተመሳሳይ የቢሮና የቤተ-ሙከራ የሕንፃ ፕሮጀክት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከእነዚህ ጋር በተዛማጅነት ሥራ ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ በያሬድ ትምህርት ቤት የኮንሰርት ወይም “የፐርፎርሚንግ ሆል”፣ በእንጦጦ ፓርክ የአርት ጋለሪም እንዲሁ የዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቶች አሉ፡፡
አብዛኛዎቹ የፕሮጀክቱ ሥራዎች ከረጅም ዓመት በፊት ተጀምረው በተለያየ ምክንያት እክል ገጥሟቸው የቆሙ መሆናቸውን ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ግንባታቸው የተጓተተባቸው መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በዋነኝነት በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን አንስተውም፤ ‹‹የገንዘብ አቅምን በማጠንከር፣ ከተቋራጮች እና ከአማካሪዎች ጋር በቅርበት በመሥራትና የፕሮጀክት ክትትል በማድረግ ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሠራ ነው›› ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በበርካታ ተቋራጮች የሚከናወኑ መሆናቸውን ዶክተር ወንድወሰን ጠቁመው፣ አንዳንድ ተቋራጮች ሁለት ፕሮጀክቶች የያዙበት አጋጣሚ መኖሩን ይገልፃሉ፡፡ አብዛኞቹ ተቋራጮች ከአማካሪዎች ጋር በተለያየ ጊዜ ኮንትራቶች መፈረማቸውን ዶክተር ወንድወሰን አመልክተው፤ በፕሮጀክቶች የፋይናንስ አፈጻጸሞች እና በግንባታዎቹ ላይ የአፈጻጸም ልዩነቶች እንዳሉባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
እንደምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ እስከ አምስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ርክክብ የሚደረግባቸው ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ በዋናው ግብ የሚገኘው ዎክአፕ ዶርሚተሪና የያሬድ ትምህርት ቤት ጊቢው የኮንሰርት አዳራሽ በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ። የሌሎቹም ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደት ከ75 እስከ 85 በመቶ በላይ የደረሱ ሲሆን ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም ያስፈልጋል።
ለማጠናቀቂያ ሥራዎች የሚያስፈልገው ወቅታዊ የገበያ ዋጋ ውድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም የሚጠይቁ፣ ይሁንና ለማጠናቀቅ ጥቂት ሥራዎች የቀሯቸው በአራት ኪሎ፣ በአምስት ኪሎ፣ በጥቁር አንበሳ እንዲሁም በአቡነ ጴጥሮስ ያሉ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ነው ያመለከቱት። አብዛኛዎቹ ለማጠናቀቂያ ሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ መሆናቸውን አንስተው፤ ‹‹በተለይም የአልሙኒየም፣ የኮርኒስ መሸፈኛዎች፣ አሳንሰሮች፣ ለሰፈረ ሰላም ካምፓስ የሚሠራው ጥቅም ላይ የዋለ ፍሳሽ ውሃን ለማከም እንዲያስችል እየተገነባ ላለው ፕሮጀክት የሚያስፈልጉት የማጠናቀቂያ እቃዎች ከውጭ የሚገቡ ናቸው›› ብለዋል።
በዚህ ወቅት ከሚታየው የወጭ ምንዛሪ እጥረት አኳያም ለፕሮጀክቶቹ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት በብሔራዊ ባንክና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ።
በበጀት ዓመቱ ለዩኒቨርስቲው በካፒታል በጀትነት የተመደበው ገንዘብ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዩኒቨርስቲው ራስገዝ ከመሆኑ እና መሠራት የሚገባቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ሰፋፊ ከመሆናቸው አንፃር የአቅም ማነስ እንዳያጋጥም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ የፋይናንስ ችግሮቹን ለመቅረፍ እየተሞከረ ነው ይላሉ። በተጨማሪም ሌሎች አጋዥ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን፣ ኤምባሲዎችን ለማስተባበርም ብዙ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።
በመሠረተ ልማት ፐሮጀክቶቹ ላይ ዋነኛ ተግዳሮት እየሆኑ ከመጡት ምክንያቶች አንዱ ፕሮጀክቶቹ ለረጅም ዓመታት መጓተት እንደሆነ አንስተው፤ ‹‹በኮንትራቱ የመግዣ ዋጋ እና አሁን ገበያ ላይ ባለው ዋጋ መካከል ልዩነት በመፍጠሩ በተቋራጮች በኩል ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይቀርባሉ›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡
በአማካሪዎች በኩል አልፎ አልፎ ፈተናዎች እንደሚገጥሙም ዶክተር ወንድወሰን ይናገራሉ፡፡ የኮንስትራክሽን ሥራዎች መዘግየትና ይህን ተከትሎ የሚታዩ የዋጋ ጭማሪዎች፣ የተገኘውን ገንዘብ ሥራ ላይ ለማዋል ያለው ፈተና በሚቀጥለው እቅድ ላይ ሳይቀር አሉታዊ አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ። በተቋራጮች በኩል ያለው መዘግየት እና ሥራዎችን በአግባቡ አሟልቶ ያለመላክ ችግሮች እንቅፋት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህንም በውይይት ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን ያብራራሉ።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት፤ እነዚህን የፋይናንስ አቅሞች በሚገባ ማንቀሳቀስ ከተቻለም ፕሮጀክቶቹ በቅርብ ጊዜ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ መግባት እንደሚችሉ ይታመናል። ሕንጻዎችን ወደ ሥራ ከማስገባት አኳያም አንድ ሕንጻ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ መጠበቁ ባለፈ የሕንጻውን የተወሰነ ክፍል ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየሠራ ነው፡፡ አንድ ትልቅ የሕንጻ ፕሮጀክት አራት ወይንም አምስት አገልግሎት የሚሰጡ ግንባታዎች ሁሉም እስኪጠናቀቁ ከመጠበቅ ይልቅ የተወሰነው የሕንፃው ክፍል አገልግሎት መስጠት እንዲችል ለማድረግ በከፊል ሕንጻዎችን የመረከብ ሥራ እየተሄደበት ይገኛል።
ለአብነትም በዋናው ግቢ የሚገኘውን የአካዳሚክ ኮምፕሌክስ ዘመናዊ ሕንጻን ጠቅሰው፤ ‹‹ሕንጻው የመምህራን ቢሮዎች፣ እስከ ሁለት ሺ ሰው የሚይዝ አዳራሽ፣ 18 መማሪያ ክፍሎች፣ 18 የኮምፒውተር ቤተ-ሙከራዎች እና ለቢዝነስና ለሬስቶራንት አገልግሎቶች የሚውሉ አምስት ሕንፃዎች እንዳሉት ይገልፃሉ።
የተወሰኑት ፕሮጀክቶች ገቢ እንዲያመነጩ የተገነቡ መሆናቸውን ዶክተር ወንድወሰን ጠቅሰው፣ ዩኒቨርስቲው ራስገዝ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ የዩኒቨርስቲውን የፋይናንስ አቅም ለማጎልበት ሕንጻዎቹ እድል እንደሚፈጥሩ ያመለክታሉ፡፡ ለእዚህም የሕንጻዎቹን ርክክብ በከፊል ለመፈጸም የሚያስችሉ ሥራዎችን እየተከናወኑ መሆናቸውን ያነሳሉ።
ለእዚህም ግንባታው ያለቀውንና ለመምህራን ቢሮ የሚሆነውን ለብቻው ራሱን ችሎ ያለውን የፕሮጀክቱን አካል፣ ቀጥሎም የትምህርት እና የኮምፒውተር ቤተ-ሙከራዎችን፤ ከዚያም የኮሜርሻል ክንፍ የሆነውንና ለንግድ ሊውል የሚችለውን የሕንጸ ክፍል ተራ በማውጣት በከፊል ኮሚሽኒንግ ሕንጻዎችን በመረከብ ወደ ሥራ ለማስገባት አቅጣጫ መያዙን ያስረዳሉ። እነዚህም ወደ ሥራ በሚገቡበት ጊዜ የመምህራን ሕንጻው ወደ አገልግሎት ይገባል፤ በቢሮዎች፣ በላቦራቶሪ እንዲሁም በመማሪያ ከፍል በኩል ያለው ችግርም ይቀርፋል በማለት ተናግረዋል።
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ እያሉ ከተለያዩ ወገኖች በመነጩ አዳዲስ ሀሳቦች እና የዲዛይን ማስተካከያዎች ለውጦች ተደርጎባቸዋል፡፡ ለውጦቹም ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ዩኒቨርሲቲው ተጠይቆ እንዲሁም በአማካሪው ተመርምሮና ፀድቆ ወደ ተቋራጩ ሄደው የተፈጸሙ ናቸው። በዚህ አይነት መልኩ በአንዳንድ የሕንፃ ፕሮጀክቶች ላይ ለውጥ ተደርጓል።
‹‹አሁን ባለበት ደረጃ በተቻለ መጠን ለውጦችን ላለመጨመር ጥረት እየተደረገ ነው፤ አንዳንድ ለሕንፃው አገልግሎት የግድ ያስፈልጋሉ የሚባሉ እና ያለእነዚህ ለውጦች ሕንጻው ወደ ሥራ የማይገባ ከሆነ በዩኒቨርሲቲው፣ በተቋራጩ እና በአማካሪ መሐንዲሱ በኩል ውይይት በማድረግ ሥራውን ለማስኬድ እየተሞከረ ነው›› ይላሉ፡፡ ይሁንና በተቻለ መጠን ባሉበት ሁኔታ ሕንጻዎቹን ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ ያስረዳሉ።
ጥቁር አንበሳ ላይ ያለው ፕሮጀክት ግን ከሌሎች በተለየ መልኩ እንደሚገነባ ዶክተር ወንደሰን ይናገራሉ። ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማሩ ሥራ በተጨማሪ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በኩል የሕክምና አገልግሎት በኩል መስጠት ግዴታው መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእዚህም የድንገተኛ እንዲሁም የተመላላሽ ሕክምና መስጫ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ በከተማ ያለውን የሕክምና አገልግሎት ችግር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚፈታ ያስረዳሉ።
በአቡነ ጴጥሮስ የዩኒቨርስቲው ካምፓስ ያሉትን የሕንፃ ፕሮጀክቶች በተመለከተም ሲያብራሩም ‹‹ለመማር ማስተማሩ ሥራ ከሚውሉ ግንባታዎች በዘለለ ዘመናዊ ስቱዲዮዎች፣ ለቀረፃ የሚሆኑና ለሬዲዮ ጣቢያነት የሚያገለግሉ አዳራሾች የተካተቱበት ነው። አብዛኛዎቹ ከትምህርት ጋር የተገናኙ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ናቸው›› ይላሉ፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ኮሜርሻል ሆነው የሚከራዩ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን ሊሰጡ የሚችሉ ሕንጻዎች መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ራስገዝ በመሆኑ ዩኒቨርስቲውን የሚመጥን ሰፋፊ እቅዶችን በማዘጋጀት ይሠራል። ከሌሎች ሀገሮች በተገኘው ልምድ መሠረት የራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ ከቢሮ፣ ከመማሪያ ክፍሎችና ከላቦራቶሪዎች በተጨማሪ፣ ስፔሻላይዝድ የሚባሉ ላቦራቶሪዎች ያስፈልጉታል። ይሄንንም በቀጣይነት እቅድ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ ነው። የፈጠራ ሀቦች፣ የስታርት አፕ ላቦራቶሪዎች ያስፈልጋሉ። ዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲ የመሆን ራዕይ ያለው በመሆኑ የውጭ ተማሪዎችን ማሳረፍ የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ ሆስቴልም ሊኖረው ይገባል። ገቢ ማመንጫ የሚሆኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎችም መሥራት አለባቸው።
አሁን እየተከናወኑ ያሉትን መሠረተ ልማቶች ማጠናቀቅ ብቻ በቂ ነው ማለት እንዳልሆነም ዶክተር ወንድወሰን ተናግረው፤ በሂደት የሚሟሉ በርካታ መሠረተ ልማቶች እንዳሉም ነው ያስታወቁት፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲው ስር ያለው ሆስፒታልም ደረጃውን የጠበቀ እና ሰፊ መሆንም ይኖርበታል፤ ሆስፒታሉንም ከመንግሥት ጥገኝነት በተወሰነ ደረጃ ማላቀቅ የሚቻለው የራሱን ገቢ ማመንጨት ሲችል ነው። የምርምር ተቋሞቹም በርካታ ፋሲሊቲዎች ያስፈልጓቸዋል›› ይላሉ። በኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ በኩል ሲታይም ከመደበኛው አገልግሎት እና ከተወሰኑ የዲጂታል ድጋፎች በዘለለ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ያሏቸውን ዓይነት የዲጂታላይዜሽን አቅም የሌለው በመሆኑ ቀጣዩ የዩኒቨርሲቲው የቤት ሥራ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም