ጠንካራ ማንነት እንዴት ይገነባል?

ጠንክራችሁ ሥሩ ስትባሉ ‹‹ደሞ ይሄ ለእኛ ሊነገረን ነው›› ልትሉ ትችላላችሁ። ሌሎቻችሁ ደግሞ ጠንክሮ ስለ መሥራት መንገር ለመኖር ምግብ መብላት አለባችሁ፤ ለመኖር ውሃ መጠጣት አለባችሁ እንደ ማለት ነው ብላችሁ ልታስቡ ትችላላችሁ፡፡ ልክ ናችሁ። ግን አንዳንዴ በሕይወታችን እንዘናጋለን። ሕይወት ተደጋጋሚና አሰልቺ ትሆንና ጠንክረን ከመሥራት እንሰንፋለን፡፡ በቃ! ሕይወት አሰልቺ ይሆንብናል፡፡ ስለዚህ የሚያባንነን፣ የሚያነቃንና ጠንክረን መሥራት እንዳለብን የሚያስታውሰን ነገር ያስፈልገናል፡፡

ጠንክረህ የምትሠራው ገንዘብ ለምታገኝበት ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ለትምህርትህም ጠንክረህ መሥራት አለብህ፡፡ ትዳርህን የተሳካና ጥሩ ለማድረግ ጠንክረህ መሥራት አለብህ፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወትህ ደስተኛ ለመሆን መጠንከር አለብህ፡፡ እንዴት መጠንከር እንዳለብህ ማወቅ ከፈለክ ደግሞ ይኸውልህ … በቃ! በሁሉም በኩል የተሳለ ሰይፍ መሆን አለብህ። ጠንካራ ማንነት ወይም ጠንክሮ መሥራት ከሰማይ ወርዶ እጅህ ላይ ዱብ የሚል ነገር አይደለም። እየገነባኸው፣ እየመሠረትከውና እያሳደከው የምትሄደው ነገር ነው። እንዴት ጠንካራ ማንነት ልገንባ፣ እንዴት ወጥሬ ልሥራ፣ እንዴት ጠንካራ ልሁን ካልክ ግን ይኸው ይህን ጽሑፍ አንብብ፡፡

ተሰጥዖ የለኝም አትበል፡፡ ስቴፈን ኪንግ የተባለ ደራሲ ‹‹ተሰጥዖ እንደገበታ ጨው ርካሽ ነው። ታላቁን ሰው ስኬታማ የሚያደርገው ጠንክሮ መሥራቱ ነው›› ይላል፡፡ ከተሰጥዖ በላይ ጉልበተኛ የስኬት ምስጢር አለ፤ ጠንክሮ መሥራት የሚባል። አንዳንዴ በዙሪያህ ያለውን ነገር ተመልከት እስኪ። ካንተ በእውቀት ያነሱ፣ ማንም የማይደግፋቸው፣ ገንዘብ ታበድራቸው የነበሩ፤ ብቻ ያልጠበካቸው ሰዎች አሁን ተቀይረውና ከፍ ብለው አንተን ከላይ ወደታች እያዩህ ነው፡፡ አንድ ደራሲ ‹‹ከታሪክ የምንማረው ሰዎች ከታሪካቸው አለመማራቸውን ነው›› ይላል። አሁንም በልፋቱ የበለጠህን ሰው ‹‹አይ እሱ እኮ ዘመድ አግኝቶ ነው፡፡ ሙስና ሠርቶ ነው›› ትላለህ። አሁን ጥያቄው ከኋላህ መጥቶ የተቀየረውን ሰው አይተህ ሰበብ ታበዛለህ፤ ወይስ ራስህን ትቀይራለህ? ነው፡፡ ጥያቄው ይሄ ብቻ ነው፡፡

አዳራሹ ከአፍ አስከ ገደፉ በሰዎች ተሞልቷል። ሁሉም ትኬት ገዝቶ ገብቷል፡፡ መሐል ላይ አንድ ፒያኖ ተጫዋች ቁጭ ብሏል፡፡ በጣም ታዋቂ ነው። የተከበረ ነው፡፡ ሰዎች በሙሉ እርሱን ለማየት ታድመዋል። በተመስጦ ተቀምጠዋል፡፡ ለሰዓታት ፕሮግራሙን አቀረበ፡፡ ፒያኖውን ተጫወተ፡፡ ሰዎች በተመስጦ ሆነው አደመጡት፡፡ ፕሮግራሙ አለቀ፡፡ በአዳራሹ የነበረው ሰው በሙሉ ተነስቶ አጨበጨበ። አደነቀው፡፡ መጨረሻ ላይ ይህ የፒያኖ ተጫዋች ዞር ሲል ከኋላው አንድ ወጣት ልጅ አጠገቡ ቆሞ አየው። ፒያኖ ተጫዋቹ እድሜው ወደ አርባዎቹ መጨረሻ ተጠግቷል፡፡ ወጣቱ ምን አለው? ‹‹እኔ እንዳንተ ፒያኖ መጫወት ብችል እድሜዬን፣ ጉልበቴን፣ ሁሉ ነገሬን አሳልፌ እስጥ ነበር›› አለ። ፒያኖ ተጫዋቹ መለሰ ‹‹እኔም ብሆን ያደረኩት እርሱን ነው›› አለው፡፡

በዚህ ዓለም ላይ በጣም የምትፈልጉት ስኬት ካለ በጣም ከባድ ላብ ሊያልባችሁ ይገባል። ደም መትፋት አለባችሁ፡፡ መልፋት አለባችሁ። መጣር አለባችሁ፡፡ ጠንክራችሁ መሥራት አለባችሁ። ጠንክሮ ያልሠራ ሰው ከፍታው ላይ መውጣት አይችልም፡፡ አየህ ወዳጄ! ያንተ ሕልም ሙሉ አቅምህን የሚጠይቅ ከሆነ ሙሉ አቅምህን ትሰጣለህ፡፡ ማልመጥና መቀለድ የለም፡፡ ጠንክረህ ትሠራልህ፡፡ ሁሉም ቢሆን ተራ ሕልም የለውም። ሁላችንም የምንፈልገው ነገር አለ። ጥልቅ መሻት አለ፡፡ የሆነ ማሳካት የምንፈልገው ነገር አለ፡፡ እሱን ለማድረግ ግን ጠንክሮ መሥራት ወሳኝ ነው፡፡

ሰዎች እንዲሁ ሊፈልጉህ አይችሉም፡፡ አንተን ለመፈለግ ወይም አንቺን ለመውደድ ምክንያት ይፈልጋሉ፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል? መጀመሪያ ራሳችንን መውደድ፡፡ ራስህን ስትወድ በብዙ ነገር ላይ ትጠነክራለህ፡፡ ልበ ሙሉ ትሆናለህ፡፡ ብዙ ነገሮችን ያለሰው እርዳታ ታሳካለህ፡፡ ያኔ በስንፍናህ ጊዜ ዞር ብለው ያላዩህ ሰዎች ምን እናግዝ፣ ከጎንህ ነን ይሉሃል፡፡ አየህ! ይህ የሰው ፀባይ ነው፡፡ ምንም ከሌለህ፣ ልፍስፍስ ከሆንክ ብትንፈራፈር እንኳን አያነሱህም፡፡ ዞር ብለው አያዩህም፡፡ ስለዚህ ከሰው መጠበቁን አቁመህ ወደ ራስህ አተኩር፡፡ ጠንካራ ጎንህ ላይ ጠንክረህ ሥራ፡፡ ሕልምህን አሳካ፡፡ ማንነትህን በሥራ ወይም በትምህርትህ አሳይ፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም ምርጫ የለህም፡፡

ልፋቱ ያለው መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ አየህ! ምንም ነገር እስክትለምደው ድረስ ከባድ ነበር። መራመድ እንኳን ከባድ ነበር፡፡ መፃፍ ከባድ ነበር። እጅህ እስኪጠነክር ትቸከችክ ነበር፡፡ ጠንክሮ መሥራትም ልምምድ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ውስጥህ እስኪለምደው ታገስ፡፡ ለራስህ ጊዜ ስጠው፡፡ ሮኬት ጉልበት የሚያወጣው መጀመሪያ ሲወነጨፍ ነው፡፡ አየህ! የመሬትን ስበት አሸንፎ አየሩን እስኪቀላቀል ነው የሚለፋው፡፡ አንተም ሕይወትህ መቀየርና መለወጥ እስኪጀምር ድረስ ጠንክረህ መሥራት አለብህ፡፡ ከዛማ ሥራውን ስታውቅበት ውሃ እንደመጠጣት ቀላል ይሆናል። ጠንክረው የሚሠሩ ሰዎች ‹‹ልፋቴ እኮ በጣም ቀላል ነው›› ቢሉህ እንዳትደነቅ፡፡ ስለለመዱት ነው። አንተም ጠንክሮ መሥራቱን ልመደው፡፡ ምንም አትሆንም፡፡

በቃ በርታበት፡፡ ጠንክረህ አጥና፡፡ ረጅም ሰዓት ቁጭ በልና አስብ፡፡ እንዴት ሕይወቴን ልቀይር በል፡፡ ጠንክረህ እንደምትሠራ ጠንክረህ አስብ፡፡ ያለበለዚያማ ዝምብም እኮ ትለፋለች። ልፋቷ ግን መና ነው፡፡ እንደ ንብ ልፋት፡፡ ማር ለሚሰጥ ነገር ማለት ነው፡፡ ሕይወትህን ለሚቀይር ነገር መልፋት አለብህ፡፡ ትርጉም ላለው ነገር ጠንክረህ ሥራ፡፡ እሱ ነው ከፍ የሚያደርግህ፡፡ እሱ ነው የሚቀይርህ። ከሰው በላይ የሚያደርግህ። ከናቁህ ሰዎች በላይ ከፍ የሚያደርግህ ጠንክረህ መሥራትህ ነው፡፡ ‹‹የውሃ ጠብታ እያደር ድንጋይ ይበሳል›› ይባላል። እንዴት ነው፣ ቆይ እጅ የማይሰብር ውሃ ድንጋይ የሚሰብረው? ግን አትርሳ ያ ጠብታ ተመሳሳይ ቦታ ላይ ዝምብሎ ከወረደ የሚያርፍበት ቦታ ብቻውን መዳከሙ አይቀርም። ድንጋዩ መፈርከሱ አይቀርም፡፡

ጠንክረህ ስትሠራ የመጀመሪያው ወር ደሞዝህ ሕይወትህን ላይቀይረው ይችላል። ኧረ! የአንድ ዓመት ደሞዜም ቢሆን ተጠራቅሞ ቢሰጠኝ እንዴት አድርጎ ነው ሕልሜን የሚያሳካልኝ እያልክም ይሆናል። ጠንክረህ ስትሠራ ግን የሆነ ሰዓት የአምስት ዓመት ደሞዝህ በአንዴ የወር ደሞዝህ የሚሆንበት ቀን ይመጣል፡፡ ከሚከፈለህ በላይ ስትሠራ ከምትሠራው በላይ ይከፈልሃል። አሁን የምታገኘውን ገቢ አይተህ ልፋትህን አትቀንስ፡፡ ነገ የምትደርስበት ነው ወሳኙ፡፡ ስለዚህ ለምን አቅምህን ትሰስታለህ፡፡ በሙሉ አቅምህ ሥራ፡፡ በሙሉ አቅምህ ተማር፡፡ ከዛ በሕይወትህ ላይ ተዓምሩን ታየዋለህ፡፡ ተዓምሩን ራስህ ትመሰክረዋለህ። ልፋትህን መውደድ አለብህ። ማፍቀር አለብህ፡፡ መቀየር አለብህ፡፡ ጠንክረህ ካልሠራህ ግን አትቀየርም፡፡ ካለፋህና ካልጣርክ ምንም ነገር በሕይወትህ ላይ አትጨምርም፡፡

አንድ ሰው ምን አለ መሰለህ፣ ‹‹በሕይወቴ በጣም እየለፋሁ፤ እየጣርኩ ምንም ለውጥ ማምጣት ሲያቅተኝ፣ ነገሮች በፈለኩት መንገድ አልቀየር ሲሉኝ ድንጋይ ፈላጮች ጋር እሄድና ቁጭ ብዬ አያቸዋለሁ፡፡ ድንጋይ ፈላጩ መዶሻ አንስቶ ድንጋዩን ይመታል፤ እኔ ደግሞ ቁጭ ብዬ እያየሁ እቆጥራለሁ፡፡ አንድ . . . ሁለት . . . ሦስት . . . እያልኩ፡፡ መቶ እደርሳለሁ፡፡ የሆነ ቁጥር ላይ መቶ ሃያ ስድስት ላይ ስደርስ ድንጋዩ ይሰበራል›› አለ፡፡ ታዲያ 126ኛው ኃይል ስላለው ይመስለሃል ድንጋዩ የተሰበረው? አይደለም! ፈላጩ ቀድሞ የመታቸው 125 ምቶች ድንጋዩን አድክመውት ነበር፡፡ 126ኛውን ፈላጩ ቀለል አድርጎ ቢልከውም ድንጋዩ መሰበሩ አይቀሬ ነበር።

አንተም በሕይወቴ እየለፋሁ ነው፣ ጠንክሬ እየሠራሁ ነው፤ ግን ደግሞ አልተለወጥኩም ካልክ 126ኛውን ቀን ጠብቀው፡፡ ሕይወትህ የሚቀየረው የሆነ ሰዓት ላይ ነው፡፡ ታገስ፡፡ ለውጡን ትፈልገዋለህ አይደል? ታገስ፤ ለምን ታቆመዋለህ፡፡ የመጨረሻውን ብርሃን ማየት ከፈለክ ጨለማውን መታገስ አለብህ፡፡ በቃ! ማስታመም አለብህ፡፡ ችግር የለም፤ እበረታለሁ፤ እጠነክራለሁ ማለት አለብህ፡፡ እኔ የምልህ ወዳጄ! እልህ ይዞህ ያውቃል? የሚንቁህና የበታችነት ስሜት እንዲሰማህ የሚያድርጉህ ሰዎች ሕይወትህን የቀን ጨለማ አድርገውት ያውቃሉ አይደል? እሳቱን ስትፈልግ ንብረት ለማውደም ትጠቀምበታለህ፡፡ ስትፈልግ ደግሞ ምግብ ታበስልበታለህ፡፡

ታዲያ ለናቁህ ሰዎች ማንነትህን ለማሳየት ጠንክረህ በስኬትህ የያዘህን እልህ ለምን አትወጣም። የምድራችን ጣፋጭ በቀል በናቁህ ፊት የሚያስከብር ስኬት መጎናፀፍ ነው፡፡ ታዲያ ለምን ጠንክረህ አትሠራም፡፡ ሕይወትህን የሚቀይረው፤ የሆነ ቀን ደስ ብሎህ ያስቀመጥከው ብር አይደለም። ወይ የሆነ ቀን በጥሩ ሙድ የሠራኸው ስፖርትም አይደለም። ወይ ያነበብከው መጽሐፍ አይደለም፡፡ ወዳጄ! ሕይወትህን የሚቀይረው በየቀኑ እየደጋገምክ የምታደርገው ልማድ ነው፡፡ ስኬት ማለት እኮ እየተዘጋጀህ እያለህ እድል ሲመጣልህ ነው፡፡ ስለዚህ በእውቀት፣ በልምድ፣ በገንዘብ ተዘጋጅ፡፡ እድሉ ሲመጣ እንዳንተ የሚጠቀምበት አይኖርም፡፡ ስኬቱ ይምጣና እዘጋጃለሁ ካልክ እየቀለድክ ነው ማለት ነው፡፡ ለጦርነት የምትዘጋጀው እኮ በሠላሙ ጊዜ ነው፡፡

አየህ! አሁን ከጠነከርክና ከበረታህ ከባድ ጊዜያት ባንተ ላይ አቅም አይኖራቸውም፡፡ ምርጥ ጊዜያት ደግሞ ወደ ከፍታው ይወስዱሃል፡፡ አሁን ከጠነከርክና ከበረታህ ከባድ ጊዜያት ባንተ ላይ አቅም አይኖራቸውም፡፡ ምርጥ ጊዜያት ደግሞ ወደ ከፍታው ያንደረድሩሃል፡፡ ጫፍ ያወጡሃል። ጠንክረህ የምትሠራ ከሆነ የትም ብትሄድ ይሳካልሃል። የትም ብትገባ ያልፍልሃል፡፡ በቃ! ጠንካራ ሠራተኛ ከሆንክ ምንም ውስጥ ብትገባ ከፍ ትላለህ። ዝቅ ብትል ትነሳለህ፡፡ ብታጎነብስ ቀና ትላለህ፡፡ ትጋት ያስፈልግሃል፡፡ ጠንክረህ መሥራት ያስፈልግሃል። ስለዚህ ጠንክረህ ሥራ፡፡ ልፋትህንም አታቁም፡፡ አስተውል! የተለወጡ ሰዎች ከጫፍ የወጡት፣ አንተ የምትፈልገውን ስኬት የተጎናፀፉት ሰዎች እድለኞች አይደሉም፡፡ ለፊዎች ናቸው፣ የሚጥሩ፣ የሚግሩ በጣም የሚታትሩ ሰዎች ናቸው፡፡

‹‹ትልቁ የስኬት ምስጢር የማይቆም ጥረት ነው። ወዳጄ እየለፋህ ከሆነ ዛሬ ከባድ ነው፡፡ ነገ በጣም ከባድ ነው፡፡ ከነገ ወዲያ ግን ምርጥ ነው፡፡ ዛሬን ተጨነቅና ቀሪ ዘመንህን በተስፋ ኑር እለዋለሁ ራሴን›› ይለናል ታላቁ ቦክሰኛ መሐመድ ዓሊ፡፡ አንተም አሁኑኑ ልደሰት አትበል፡፡ ለገንዘብ መሥራቱን አቁመህ ገንዘብ ላንተ መሥራት እስኪጀምር ድረስ ጠንክረህ ሥራ። የዚህ ዓለም ስኬት ትንፋሹን ለረጅም ጊዜ ተቆጣጥሮ ደስታውን ለሚያዘገይ ብቻ ነው፡፡ ዘላለም እንደሚኖር ሰው ወጥረህ ሥራ፡፡ ዛሬ እንደሚሞት ሰው ደግሞ ተደሰት፡፡ ወዳጄ አንተ ብትጠነክርም ባትጠነክርም ጊዜው እንደሆነ መሄዱ አይቀረም፡፡ ጠንክረህ ሥራ!! ለራስህ ስትል ነው፤ ለማንም አይደለም፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You