ያልታየችው ጥበበኛ ትጣራለች

ልጅነት ደጉ …

የብርቱ ገበሬ ልጅ ነች፡፡ ቤተሰቦቿ ኮረሪማና ቡና ያመርታሉ፡፡ ለቤቱ ብቸኛ ልጅ ናት፡፡ ሁሉም አንደ ዓይኑ ብሌን ያያታል፡፡ ትንሽዋ እቴነሽ ፈጣንና ተጫዋች ነች፡፡ የታዘዘችውን ለመፈጸም አትዘገይም፡፡ በትምህርት ውሎዋ እሷ ከጓደኞቿ ትለያለች፡፡ ስትጫወት፣ ስታወራ ቀልጠፍ ማለቷ ከሁሉ ዓይን ጥሏታል፡፡

ይህን የሚያውቁት አባቷ ዘወትር ይጨነቃሉ፡፡ ቅልጥፍናዋ ከልጅነቷ ተዳምሮ ትኩረት እንዳትስብ ስጋታቸው ነው፡፡ ልጃቸውን የሚያዩ ብዙዎች በሌላ እንዳያስቧት፣ በድንገት ጠልፈው እንዳይወስዷት ይፈራሉ፡፡ ምን አልባት እንዲህ ከሆነ ስማቸው ይጠፋል፤ ክብራቸው ይዋረዳል፡፡

ከቀናት በአንዱ ግን አባት በድንገት ወሰኑ ፡፡ አሁን ልጃቸው እያደገች ኮረዳ እየሆነች ነው፡፡ ቆይታ ደግሞ ዕድሜ ታክላለች፡፡ ውበቷ ይታያል፣ ወጣትነቷ ይማርካል፡፡ ስለዚህ ማግባት፣ መዳር አለባት፡፡ ትዳር ከያዘች ለእሷም ለእሳቸውም ክብር ነው፡፡

ሙሽሪት ልመጂ

እቴነሽ ወንድሙ ስድስተኛ ክፍል እንደገባች ለትዳር ተጠየቀች። ይሄኔ አባት የልባቸው ሞላ፡፡ አብሯቸው ከኖረው ስጋት ድነው ‹‹እፎይ!›› አሉ፡፡ የዛኔ አስራ አራተኛ ዓመት ዕድሜዋን መጀመሯ ነበር፡፡ ትንሽዋ ልጅ ትዳር ስትይዝ ሁሉም ነገር ቀረ። የልጅነት ሩጫዋ፣ ሳቅ ጨዋታዋ ተገታ፡፡ ጅምር ትምህርቷ ተቋረጠ፡፡

ጎጆ ስትወጣ ለባሏ ጥሩ ሚስት ሆነች፡፡ ‹‹ሙሽሪት ልመጂ›› ያሏት ዘመዶቿ ከእሷ ቁም ነገርን ሽተው ብዙ ጠበቁ። 1977 ዓ∙ም የጫጉላ ጊዜዋ ሆነ፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ልጇን ታቀፈች፡፡

አሁን እቴነሽ ጥሩ ወይዘሮ ሆናለች፡፡ ስለ ትዳርና ጎጇዋ እንጂ ስለ ትምህርቷ፣ ሮጦ ስለመጫወት አታስብም። የመጀመሪያ ልጇ ትንሽ ከፍ እንዳለች ሁለተኛዋን አረገዘች። እሷን አይታ ሳትጠግብ ሶስተኛው ተደገመ፡፡ በአጭር ጊዜ አከታትላ የወለደችው እናት ኑሮን ከልጆች አስማምታ ማደሩ ይከብዳት ያዘ፡፡

የእቴነሽ ባለቤት ጉራጌ ሀገር ተወልዶ ያደገ ነው። ልጆች ሲበዙ፣ ቤተሰቡ ሲሰፋ ሕይወትን በተሻለ ሊኖር አሰበ፡፡ ሃሳቡን እውን ለማድረግ የመጀመሪያ ምርጫው ወደ ሀገሩ ጠቅልሎ መግባት ነበር፡፡

እቴነሽና ባለቤቷ ጅማን ለቀው ወደ ጉራጌ ምድር ‹‹አጨበር›› አቀኑ፡፡ ስፍራው ለምና አረንጓዴ ነው፡፡ እቴነሽ ቦታውን አልጠላችውም፡፡ በአካባቢው የባለቤቷ እህትና የመጀመሪያ ልጁ መኖራቸውን ታውቃለች፡፡ በስፍራው ከአንድ ዓመት በላይ እንደቆዩ እቴነሽ አራተኛዋን ልጅ ነፍሰጡር መሆኗን አወቀች፡፡ አልከፋትም፡፡ እርግዝናው እየገፋ አራት ወራትን አስቆጠረ፡፡

የቀን ክፉ ∙ ∙

አንድ ቀን በእነ እቴነሽ ቤት ከባድ ኀዘን ወደቀ፡፡ የትዳር አጋሯ፣ የልጆቿ አባት ‹‹አለኝ›› የምትለው መከታዋ በድንገት ሕይወቱን በሞት ተነጠቀ፡፡ እቴነሽ ትይዘው፣ ትጨብጠው ጠፋት፡፡ አሁን ከትውልድ ሀገሯ ርቃለች። እዚህ በቅርብ የምትጠራው ወዳጅ፣ ዘመድ የለም፡፡ ለሀገሩ ባዳ፣ ለሰው እንግዳ የሆነችው ነፍሰጡር ኀዘኗ ከፋ፡፡ ልጆቿን በትካዜ እያየች ስለነገው ተጨነቀች፡፡

ባለቤቷ ከተቀበረ ጥቂት ቀናት በኋላ የጎረቤት እግር ቀነሰ፡፡ ‹‹እንዴት ዋላችሁ፤ እንዴት ከረማችሁ?›› የሚል ጠፋ። ይሄኔ በወጉ አፋቸውን ያልፈቱ ልጆችን የየያዘችው እቴነሽ በባዶ ቤት ባዶነት ተሰማት፡፡ አባወራው የተወላት ሀብት ንብረት ከእጇ የለም፡፡ ወጣ ብላ ‹‹አበድሩኝ፣ አጉርሱኝ›› ለማለት የምትግባባበትን ቋንቋ አታውቅም፡፡ ችግር ሰተት ብሎ ቤቷ መግባቱን እያየች በጥልቅ ኀዘን ተዋጠች፡፡

እቴነሽ ሆዷ እየገፋ፣ ወሯ እየደረሰ ነው፡፡ ባለቤቷ በሌለበት በባዶ ቤት መውለዷን ስታስብ አስቀድሞ ሆድ ባሳት፡፡ የሚሆነው ከመሆን አላለፈም፡፡ በችግርና ኀዘን መሀል በሰላም ወልዳ ልጇን ታቀፈች፡፡ የአራስ ቤት ቆይታዋ መልካም አልሆነም፡፡ ‹‹እንኳን ማርያም ማረችሽ›› የሚላት የሚጎበኛት ጠፋ፡፡ በለቅሶ ብዛት ዓይኖቿ ደከሙ፡፡ አንጀቷ በጀርባዋ የተጣበቀ መስሎ ተሰማት፡፡

በአራስ ቤት ባዶነት፣ ብቸኝነት ይከብዳል፡፡ የዘመድ አዝማድ ጥየቃ፣ የወዳጅ ባልንጀራ እጅ ይናፍቃል፡፡ እቴነሽ ለቀናት ደጁን እያየች ሰው ጠበቀች፡፡ ‹‹ወድቀሽ ተነሺ›› የሚላት አልተገኘም፡፡ አሁን ከእሷና ከልጆቿ በቀር ቤቷ ባዶ ነው። እንደ ወጉ ገብቶ ያያት፣ የጠየቃት የለም፡፡ እቴነሸ ውስጧ በኀዘን ረመጥ ጋየ፡፡ ለቀናት በትኩስ ዕንባ ታጠበች፡፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር ደጋግሞ ሆድ ባሳት፡፡

መከራን በዘዴ

ውሎ ሲያድር እሷና ልጆቿ ረሃብ ጎበኛቸው፡፡ አሁን እቴነሽ ታጠባለች፡፡ ለህጻኗ ወተት፤ ለልጆቿና ለእሷ ምግብ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ምንም ተነስታ ወደ ጓሮ አቀናች፡፡ ገብስ ተቆልቶ የቀረው ገለባ በጆንያ ተሞልቷል፡፡ ገለባው ከብቶች ሲወልዱ ለመኖ እንዲያግዝ የተቀመጠ ነው፡፡ እቴነሽ ይህን አሳምራ ታውቃለች፡፡ ገለ ባውን በሰፌድ ማበጠር፣ ማንጓለል  ያዘች፡፡ ጥቂት የገብስ ፍሬዎችን አላጣችም፡፡

ያገኘችውን ገብስ አጠራቅማ እንደ ቅንጬ ቀቀለችው፡፡ ደጋግማ ገለባውን አነፈሰች፡፡ አሁንም ጥቂት ገብስ አላጣችም። እሱኑ ከልጆቿ ጋር ተቃምሳ ቀናትን አለፈች፡፡ ውሎ አድሮ ግን ገብሱ ነጥፎ ገለባው ብቻ ቀረ፡፡

እቴነሽ ዕብቁን ‹‹ይቅርብኝ›› ብላ አልተወችውም፡፡ ላይ ላዩን አንጓላ የሚቀረውን ድቃቂ ከሰው ጓሮ ለቅማ ባመጣችው ጎመን እየቀቀለች ለልጆቿ አጎረሰች፡፡ አንድ ቀን ግን ጡቷ ደረቀ። ትንሽዋ ልጅ ልትራብ ሆነ፡፡ ዕፍኝ የማትሞላ ገብስ ፈጭታ እንደ ወጉ አጥሚት ሠራች፡፡ ልጇ ከጡቷ በረከት እንድታገኝ የፈጠረችው ብልሀት ነበር፡፡

ሆድ ለባሰው

እቴነሽ በአካባቢው ‹‹ይሁን›› ብላ መቀመጥ አልፈለገችም። ሰውነቷ የበረታ ሲመስላት ብድግ ብላ መጥፋት ፈለገች፡፡ ትልቋ ልጅ ከአክስቷ ዘንድ ናት፡፡ የእሷን ተከታይ ደግሞ አዲስ አበባ ያሉት አክስት ወስደዋታል፡፡ አንድ ማለዳ እቴነሽ የልቧን ልትፈጽም ቆረጠች፡፡ በባዶ ሆዷ፣ ድንገት ጎጆዋን ዘግታ ከቤት ወጣች፡፡ አሁን ርቃ ልትሄድ፣ ልትጠፋ ወስናለች፡፡

ሁለቱን ልጆች ይዛ መንገድ እንደጀመረች አንድ ሰው አግኝቶ አስቆማት፡፡ የባለቤቷ የመጀመሪያ ልጅ ነበር፡፡ ገና እንዳያት ልቡ ጠረጠረ፡፡ ወዴት እንደምትሄድ ደጋግሞ ጠየቃት። እቴነሽ ውስጧ ተከፍቷል፡፡ መላ አላጣችም፡፡ አዲስ አበባ ያሉት የባሏ እህት ልብስ ሊገዙላት እንደ ቀጠሯት ነገረችው፡፡

የባለቤቷ ልጅ የህጻናቱን አብሮ መሄድ አልወደደም። ደርሳ እስክትመለስ አንደኛዋን ከእጇ ተቀበላት፡፡ እቴነሽ እንዷን ህጻን እንደ ያዘች አዲስ አበባ ዘለቀች፡፡ ስፍራው ስትደርስ ሁኔታዎች ግራ አጋቧት፡፡ የአዲስ አበባ ፀሀይ ጨለማ ሆነባት። ከገጠር ወጥታ መሀል ከተማ መግባቷ ለእሷ ፈተና ነበር፡፡ እንደ እንግድነቷ ለጥቂት ቀናት ከባሏ እህት ቤት አረፈች፡፡ ውሎ አድሮ ግን መቀጠል የማያስችሏት ምክንያቶች ተፈጠሩ፡፡ እቴነሽ አሁንም በድንገት ወሰነች፡፡ በጉልበቷ ሰርታ ለማደር ‹‹ጢያ›› ከተባለ ሀገር አመራች፡፡ ጢያ ከአዲስ አበባ በኪሎ ሜትሮች ይርቃል፡፡ ‹‹ለሀገሩ ባዳ ለሰው እንግዳ›› የሆነችው እቴነሽ አሁንም ሕይወትን እንደ አዲስ ል ትጀምረው ግድ አላት፡፡

አራት ልጆቿን በአንድ ቤት ማሳደግ ያልሆነላት ሴት ጉልበቷን ከፍላ፣ ላቧን ጠብ አድርጋ በምታድርበት ቤት ተቀጠረች፡፡ ሁሌም ልጆቿ በዓይኗ ውል ይላሉ፡፡ በሞት ያጣችው ባለቤቷ፣ ያለፈችበት ውጣ ውረድ በትዝታ ይፈትኗታል፡፡ አስር ዓመታት በቆየችበት የሠራተኝነት ሕይወት ብዙ መከራን አይታለች፡፡

ቀጥረው የወሰዷት የአዲስ አበባ ነዋሪ የሀገሩ ተወላጅ ናቸው። ሰውየው ጢያ ላይ የበዛ ሀብት አፍርተዋል። ንብረታቸው በታማኝ ሰው እንዲጠበቅ፣ ይሻሉ፡፡ ለዚህ የታጨችው እቴነሽ ከከተማው በሚርቅ አንድ የገጠር ወንዝ ዳርቻ ከነልጆቿ ተጓዘች። በርካታ ከብቶችና የጋማ እንስሳት የእሷ ሃላፊነት ሆኑ፡፡

ከአንድ ውሻ በቀር ማንም ጎኗ የሌለው ሴት ጉልበቷን እየገበረች ጥበቃዋን ቀጠለች፡፡ ጭው ባለው መንደር ታዛቢ በሌለበት ዓለም እቴነሽ ጉልበቷን አትሰስትም፡፡ ወፍ ሳይንጫጫ እበት ከበረት ትዝቃለች፣ አውድማ ትለቀልቃለች፣ እንሰት ቆርጣ ትፍቃለች፡፡ ለእሷ አሁንም በማታውቀው ሀገር ዝቅ ብሎ ማደር ብርቋ አልሆነም፡፡

ጉልበቷ እንጂ ቀለቧ ያልታሰበላት አገልጋይ ኑሮዋን ለማሸነፍ አትሆነው የለም፡፡ ስንደዶ እየቀጨች፣ ርቃ ሄዳ ጸጉር ትሠራለች። ባገኘችው ገቢ ልጆቿን እያጎረሰች አዲስ ቀን ትናፍቃለች፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ሰዎች ሊጎዷት፣ ሽፍቶች ሊዘርፏት ሞክረዋል። ጥንካሬዋ ብርታት ሆኗት ብዙ የፈተና ቀናትን በድል መሻገር ችላለች፡፡

የሰባቶች እናት…

ይህን ችግር ለማምለጥ የገባችበት፣ ሶስት ልጆችን ያፈራችበት ሁለተኛው ትዳር አልደላትም፡፡ እቴነሽ አጋር ይሆነኛል ብላ ያገባችው ሰው ሌላ ትዳር ነበረው፡፡ አሁን በአራቱ ላይ ሶስት ልጆችን አክላ የሰባቶች እናት ሆናለች። በቂ መተዳደሪያ ለሌላት ሴት እንዲህ መሆኑ ይከብዳል፡፡ ለእንጀራ ስትል የመጣችበት ኑሮ ያስገኘላት ቢኖር ሶስት ልጆቿን ብቻ ነበር፡፡ አንድ ቀን እቴነሽ ብዙ ካየችበት የጢያ ሕይወት ልትላቀቅ ወስና ጓዟን ሸከፈች፡፡ እግሮቿ ወደ አዲስ አበባ መለሷት፡፡

አዲስ አበባና እቴነሽ ዳግም ሲገናኙ ከጭንቅ ጋር ሆነ፡፡ አሁንም ለዚህች ሴት ይህች ከተማ ባህር ውስጥ እንደ መስመጥ ሆነባት፡፡ ዛሬም ትጠጋበት ዘመድ፤ ትጠራው ወዳጅ፣ ጓደኛ የላትም፡፡ አሁንም ያላት ምርጫ በጉልበቷ ማደር ብቻ ነው። ተመልሳ የቤት ሠራተኛ ሆነች፡፡ ጥቂት ጊዜ የቆየችበት ሥራ ብቻውን የሚያዋጣ አልሆነም፡፡ ልጆቿን አብልታ ለማሳደር ቤት ተከራይታ መኖር ግድ አላት፡፡

እቴነሽ አዲስ አበባ የገባች ሰሞን ያልሆነችው የለም። የዛኔ የአንድ ኪሎ በቆሎ ዋጋ አራት ብር ነበር፡፡ እሷ ይህን የመግዛት አቅም የላትም፡፡ ውሎ አድሮ ችግር ብዙ አስተማራት። የወፍጮ ቤት ጥራጊ በጥቂት ወጪ መግዛት ልምዷ ሆነ፡፡ ጥራጊውን፣ ከወረቀቱ፣ ከአሸዋውና ከአሰሩ ለይታ፣ ነፍታና አበጥራ እንጀራ ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ታልፎ ብጣሪው እንጀራ ከሆነ ግን ለዓይንና ጉሮሮ ይከብዳል፡፡ እሷና ልጆቿ ከዚህ ሌላ በልቶ ለማደር ምርጫ የላቸውም፡፡

ስለእንጀራ

ሶስት ልጆቿ ሁሌም የእሷን እጅ ይናፍቃሉ፡፡ አሻሮ እየቆላች፣ ከጉልበት ሥራ እየዋለች ከምታገኘው ጥቂት ገቢ ለዕለት ጉሮሯቸው ይዛ ትገባለች፡፡ ሲነጋ እነሱን ከቤት ትታ ከጉልበት ሥራዋ ትገኛለች፡፡ እቴነሽ የተጠየቀችውን ለመሥራት ሁሌም ታዛዥ ናት፡፡ ጉልበቷን አትሰስትም፡፡ ከአቅሟ በላይ ሲጭኑባት “ለምን?” ብላ አትጠይቅም፡፡

አንድ ቀን ለሥራ ከሄደችበት ቤት ሃምሳ ኪሎ በቆሎና ሃያ አምስት ኪሎ ገብስ እንድትቆላ ተሰጣት፡፡ እቴነሽ ወገግ ካለው እሳት ብረት ምጣዱን ጥዳ መቁላት ጀመረች። ብዛት ያለው እህል በእሷ አቅም ተቆልቶ እንዳለቀ ራሷን ስታ ወደቀች። ማግስቱን ግን ከውሎዋ አልቀረችም፡፡ ይህን ሁሉ ቆልታ የሚከፈላትን ሃምሳ ብር ለማግኘት ልቧን ደግፋ ከቦታው ተገኘች፡፡

እቴነሽ አውደ ዓመት በደረሰ ጊዜ ጉልበቷን የሚሹ ብዙ ናቸው፡፡ በቀን ሰባት ቤት ገብታ የዓመት በዓሉን እንጀራ በእንጨት ትጋግራለች፡፡ ለእሷ የዕለት ጉርሷ ነው፡፡ ከየቤቱ የሚሰጣት እንጀራ ለልጆቿ ይሆናል፡፡ የምታገኘው ጥቂት ክፍያ ተጠራቅሞ ለቤት ኪራይ ይውላል፡፡

እቴነሽ ሰባት ልጇቿን ለማሳደግ ከስታ ጠቁራለች፤ተርባ ተጠምታለች፡፡ ወድቃ ተነስታለች፡፡ ማንም የጎደጎደ ዓይኗን አይቶ፣ ማድያት የወረሰው ፊቷን ቃኝቶ ኑሮዋን መገመት አይሳነውም፡፡ ልጆቿ ከፍ ባሉ ጊዜ ጥቂት ነገሮች ይዛ ጉልት መሸጥ ጀመረች፡፡ እነሱም ከትምህርት መልስ የሚሸጠውን በአቅማቸው በየጉልቱ እያዞሩ ያግዟት ያዙ፡፡

እንዲያም ሆኖ ከቤት የሚላስ ፣ የሚቀመስ ሊጠፋ ይችላል። በእነቴነሽ ቤት ጦም ውሎ ጦም ማደር ብርቅ አይደለም። አንዳንዴ ለልጆቿ ባዶውን ጎመን ጨው ጨምራ፣ ቃሪያ ጣል አድርጋ ትሰጣቸዋለች፡፡ አያዝኑም፣ አይከፉም፡፡ በፍቅር ተቃምሰው በጨዋታ አዋዝተው ምሽቱን ያልፉታል፡፡

ከልጆቿ አንዷ የእናቷን ሸክም ለማቅለል ከአምስተኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ በቀን ሥራ ተሠማርታለች፡፡ ድንጋይ በባሬላ ተሸካሚዋ ልጅ እናቷ ትናንት የተበደረችውን ዛሬ እየከፈለች፣ ለኑሯቸው ታገለች፡፡ አሁንም የጎደለው አልሞላም። ቤተሰቡ በአቅም ማጣት በቤት ኪራይ ይንገላታል፡፡

ከቀናት በአንዱ አንዲት መልካም ሴት ወደ አርሷ ቀርበው የሚበጃትን አመላከቷት፡፡ እቴነሽ የቀበሌ መታወቂያ አወጣች። ይህን ተከትሎ ልጆቿን እያስተማረ የሚያሳድግ የውጭ ድርጅት አገኘች፡፡ ሁለቱ አዳሪ ትምህርት ቤት ገቡ፡፡ ሌሎች በየዘመዱ ቤት ኑሯቸውን ቀጠሉ፡፡ እቴነሽ ሸክሟ ቀለለ፡፡ ፈጣሪዋን አብዝታ አመሰገነች፡፡

ከድርጅቱ ጋር የተጀመረው ግንኙነት ፍሬው መልካም ሆነ። በልጆቿ መነሻ ሕይወቷ የተጎበኘው እናት የእጅ ሙያዎችን የመማር አጋጣሚ ተፈጠረላት፡፡ ይህ ጊዜ ለሥራ ወዳዷ፣ ለብርቱዋ እቴነሽ መልካም የሚባል ነበር፡፡ እሷን ከመሰሉ ሴቶች ጋር ተደራጅታ በጀመረችው ሥልጠና ከሌሎች በላቀ ውጤታማ ሆነች፡፡

እሷና አጋሮቿ በሚሰሯቸው የእጅ ሙያዎች የዕለት ገቢያቸውን አላጡም፡፡ በሥልጠና የቀሰሙት ዕውቀት ለእንጀራቸው ማግኛ ሆኖ ትኩረት አገኙ፡፡ በየጊዜው የእጆቻቸው ጥበቦች ይሸጡ፣ ይጎበኙ ያዙ፡፡ ሶስት ዓመታት በመልካም ሁኔታ አለፈ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ግን ድርጅቱ በድንገት መዘጋቱ ተሰማ፡፡ እንዲህ መሆኑ ለእንጀራ ፈላጊዋ እቴነሽ አስደንጋጭ ነበር፡፡

ዛሬን…

እቴነሽ ተመልሳ ወደ ጉልበት ሥራ መግባት ከበዳት፡፡ ይህን እያሰበች ባለበት ጊዜ አምሳለ የምትባል አንዲት ሴት ሥራውን የምትቀጥልበትን መንገድ ጠቆመቻት፡፡ እቴነሽ ምክሯን ተቀብላ ሞከረችው፡፡ የምትሠራቸው የአንገት፣ የእጅና የጆሮ ጌጦች ሞገስ አገኙላት፡፡ ያዩ፣ የጠየቁ ሁሉ ይገዟት ጀመር፡፡

ውሎ አድሮ ግን በእጇ ሙያዎቿ ብቻ ቀሩ፡፡ እንደቀድሞው የምትሸጥበት ዕድልና ቦታ አጣች፡፡ እቴነሽ ውብ ጌጦቿ ለዓይን ይማርካሉ፡፡ ዋጋዋ አነስተኛ ነው፡፡ እነሱን ሸጣ የምታገኘው ገቢ ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ እንዲያም ሆኖ ጥበበኛ እጆቿ ከሥራ አልታቀቡም፡፡ አሁን ከገበያ አገናኝቶ፣ ከእንጀራዋ የሚያውላትን ወገን ትሻለች፡፡

መልካም ዓይኖችን ፍለጋ ...

ዛሬ ልጆቿ በአቅማቸው ተምረዋል፡፡ አብዛኞቹ ግን ሥራ ላይ አይደሉም፡፡ ተአምረኞቹ፣ ጥበበኞቹ የእቴነሽ እጆች ሥራ ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም የቤት ኪራዩ ይከብዳታል፡፡ ጤፍ አስፈጭቶ እንጀራ መቁረስ ይቸግራታል፡፡ ጠንካራዋ ሴት እዩኝ፣ ጎብኙኝ እያለች ነው፡፡ በእሷ እጆች ያልተመነዘረ ጥሬ ገንዘብ፣ ያልታየ ድንቅ ውበት አለና፡፡

 መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You