‹‹ለተጎጂዎች በሶስት ዙሮች በመንግሥት ድጋፍ ባይደረግ ሊፈጠር ይችል የነበረውን አደጋ መገመት አይከብድም››

አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር

የዛሬው የዘመን እንግዳችን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ናቸው፡፡ አምባሳደር ሽፈራው፣ ከዚህ ቀደም የፌዴራል ጉዳዮች እንዲሁም የትምህርት ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ አሁን ወዳለቡት የአመራርነት ቦታ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፤ በሌሴቶ እና ናሚቢያ የኢትዮጲያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ የዛሬው የዘመን እንግዳችን በኮሚሽኑ እየተከናወነ ስላለው እንቅስቃሴ በተለይም በአንዳንድ አካላት መንግሥት ድጋፉ የተቀዛቀዘ ነው በሚል በሚነገረው እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከሠብዓዊ ድጋፉ ጋር ተያይዞ አንዳንዶች ከረሃብ የተነሳ የሰው ሕይወት አልፏል በማለት ላይ ይገኛሉ፤ በእርግጥ በድጋፍ በእጦት የሞተ ሰው አለ?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- የአየር ንብረት ለውጡ በድርቅም በጎርፍም በመሬት መሸንራተትም ሆነ በተለያየ መንገድ በሚከሰትበት ጊዜ በአንድ በኩል የሰውን የኑሮ መሠረቱ የማናጋት ነገር ሊኖር ይችላል።፡ በሌላ በኩል ለሕይወትም አደጋ የሚሆኑ ነገሮችን ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በኑሮ መሠረትም በሰው ሕይወትም ላይ የሚያስከትላቸው ጫናዎች ይኖራሉ፡፡

ከድርቅና ከጎርፍ ጋር በተያያዘ መንግሥት በሁለት ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል፡፡ አንደኛው ድርቅ ወደረሃብ ተቀይሮ ሰው እንዳይጎዳ መከላከል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ይህንን አጋጣሚ ማለትም የድርቁን ሁኔታ ወደመልካም አጋጣሚ ፣መቀየር የሚያስችሉ ዘላቂ ልማት ሥራዎች መሥራት ነው፡፡

ይህ ሥራ የሚሠራው በሁሉም ደረጃ ነው። በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በኮሚሽን ይሠራል፤ በተመሳሳይ በክልሎችም ይሠራል፡፡ የክልሎች የተዋረድ መዋቅሮች አሉ፤ በእዛ ውስጥ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ይሳተፉበታል። ሌላውና ትልቁ ደግሞ በየደረጃው የሚሳተፈው ሕዝቡ ራሱ ነው፡፡ የተቸገረውን የኅብረተሰብ ክፍል የመደገፍ ሥራ ይሠራል፡፡

ይህንን ዘርዘር አድርገን ስናይ፤ ከታች እስከ ላይ ያለው የመንግሥት መዋቅር የሚያደርገው ርብርብ ሰዎች በድርቁ ምክንያት በግብርና ሆነ በእንስሳት ውጤትና በመሳሰሉት ላይ ጉዳት ስለሚደርስ ፤ በበቂ ደረጃ ተመጣጣኝ ምግብ የማግኘት ችግር ያጋጥማል። የውሃ እና የጤና አገልግሎት በሚስተጓጎልበት ጊዜም ሰዎች ተጓዳኝ ለሆኑ ችግሮች ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡

በእርግጥ ሞት ተፈጥሯዊ ጉዳይ እና ሁሌም ከማኅበረሰባችን ጋር አብሮ ያለ ነገር እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ “የሞተው በዚህ ጉዳይ ነው” በሚል ማረጋገጫ በመስጠት በእርግጠኝነት መናገር እጅግ በጣም አዳጋች ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ቀበሌ ወይም በአንድ ድርቁ ባለበት አካባቢ ሰው ቢሞት፤ ይህን ሰው የገደለው ድርቁ ወደረሃብ ተቀይሮ ነው የሚል አይነት መደምደሚያ መስጠት አግባብነት የለውም፡፡ የሞቱ ምክንያት ምን እንደሆነ ከመረዳት ጋር የሚያያዝ ነው። የሞቱ ምክንያት የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረ ሕመም አሊያም በሌላ ሌላ ምክንያት ሞት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ተፈጥሯዊ ምክንያች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዙሪያ ያሉ የጤና ችግሮች አጋጥመውትም ሊሆን ይችላል። ድርቁ ምንም ዋጋ የለውም ማለት ግን አይቻልም፡፡ በድርቁ ምክንያቱም የተመጣጠነ ምግብ በመደበኛነት ካለማግኘቱ የተነሳ የመከላከል አቅሙም ተዳክሞ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ በተለያየ መንገድ ተደራርበው የሚፈጥሩት ጫና ሊኖር ይችላል፡፡

በእኛ ስሌት እና አረዳድ ግን “ድርቁ ወደረሃብ ተቀይሮ ነው ዜጋውን ለሕልፈት ያበቃው” የሚለው መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የራሱ የሆነ ክትትል እና የራሱ የሆነ ማረጋገጫ መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ስናይ እስካሁን የፌዴራል መንግሥት በኮሚሽን ደረጃ ድርቁ ወደ ረሃብ ተቀይሮ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ ነው በሚል የሚያናፍሱ ዘገባዎች ትክክል ናቸው ብሎ አይወስድም፡፡

“ድርቅ ወደረሃብ እየተቀየረ ነው” በሚል የተነገረው ጉዳይ የተሳሳተ ድምዳሜ ነው፡፡ ሞትን የመሰለ ነገር “የገደለው ይህ ነገር ነው” ብሎ ለማለት እና ለመለየት የራሱ የሆነ ደረጃዎች አሉት፡፡ በዚያ መንገድ የሚቀርበው አቀራረብ የተሠሩ ነገሮችን በጣም አቅልሎ ለማሳየት የተደረገ ነው ባይ ነን፡፡ የተሠራውን ሥራ ተቧድነው አቅልሎ የማየት ሁኔታ ስለሆነ በእኛ በኩል በዚህ መንገድ የተደመደመ ነገር አለመኖሩን መግለጽ እወዳለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እስከተጠናቀቀው ታህሣሥ ወር ድረስ ያቀረበው ርዳታ ምን ያህል ነው?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- ባለፈው በ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር ጀምሮ እስካለፈው ታህሣሥ ወር ድረስ የመጣንበትን ሒደት ስናይ የአጋር ድርጅቶች በተለይም የአሜሪካ ልማት ድርጅት ድጋፍ የሚያደርጋቸው የዓለም ምግብ ፕሮግራምና ሌሎች ተቋማት ለስድስት ሰባት ወር ያህል ሠብዓዊ ድጋፋቸውን አቋርጠው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በዚያን ጊዜም ጭምር እነዛን ክፍተቶች ለመሙላት በመንግሥት በኩል ሰፊ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዚህም ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሣሥ ወር 2016 ዓ.ም ድረስ በሶስት ዙር ድጋፎች ተደርገዋል፡፡

ድጋፍ የሚደረግላቸው አካላት የሚለዩት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንጂ በግምት አሊያም ሰዎች ስለፈለጉ ወይም ስላልፈለጉ አይደለም፡፡ የመጀመሪያው የሚታወቀው የቤተሰብ ሕይወትን የመታደግ ምጣኔ ምንድን ነው የሚመስለው? የሚለውን የሚለይ ጥናት (House hold Economic Analysis) በሚባል ነው፡፡

በየአካባቢው ምን ያህል ተጎጂ ሊኖር ይችላል? ከዚያ ደግሞ ያንን መነሻ በማድረግ በየቀበሌው እያንዳንዱ ቤተሰብ ላይ ተጋላጭ የሆነ ቤተሰብ ማን ነው? የሚለው ጥናት ይደረጋል፡፡ ማን ነው ተጎጂ የሚለውም የሚለየው በዚያ አይነት መንገድ ነው፡፡ ሁለተኛው የተፈናቀሉ ማኅበረሰቦችን መለየት ነው። ይህ አሁን ላይ በአይ.ኦ.ኤም እና በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በጋራ የሚሠራው ነው።

ከእዚህ ውጭ በበርካታ ባለድርሻ አካላት እኛንም ክልሎችንም ጨምሮ ምን አይነት ሁኔታዎች አሉ? የሰብል ሁኔታ ምን ይመስላል? የእንስሳቱ ሁኔታ ምን ይመስላል? የጤና፣ የውሃ ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚል ግምገማ ይካሄድና ከዚያ ክልሎች ደግሞ እንደነባራዊ ሁኔታው የሚያመጡት ነገር ተጨምሮ ነው ይህ ውጤት የሚገኘው፡፡

የወቅቱ ተደጋፊ አካል ማን ነው? ምንስ ያህል ሊሆን ይችላል? እና የት ነው ያለው? እያጋጠመው ያለው ምን አይነት ጉዳት ነው? በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ ጥናቶች ሲደረግ በመጀመሪያዎቹ ዙር ላይ ሰባት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን፤ በሁለተኛ ዙር ላይ ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን እንዲሁም በመጨረሻ ላይ ያለው ሶስተኛው ዙር ላይ ደግሞ ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ድጋፍ ፈላጊዎች ተለይተው እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡

ሶስተኛው ዙር ድጋፍ ላይ አጋሮችም ተሳትፈውበት ስለነበር በጥቅሉ የነበረው ሲታይ የመንግሥት አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እንዳልኩት ሶስተኛው ዙር ላይ አጋሮችም ተቀላቅለው ስለነበር አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል እንዲደደርስ አድርጓል። በዚህ ውስጥ ደግሞ የሁለት ቢሊዮን ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ነበር፡፡ እነዚህ ተደማምረው ሲታዩ በዚያን ወቅት መንግሥት ለብቻው ያደረገው ድጋፍ 11 ቢሊዮን ብር ነበር። የአጋሮቹ ሲጨመር ደግሞ ወደ 15 ቢሊዮን ብር ይሆናል፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ከነበረው የጸጥታ ችግር የተነሳ በእኛ ዘንድ የርዳታ ክምችት ቢኖርም ለተረጂዎች ማድረስ አልተቻለም፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ በአማራ ከልል ሰሜን ጎንደር፣ ዋግ ኽምራ፤ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ምዕራብ ወለጋ ዞን አካባቢ ድጋፉን የተፈለገውን ያህል በማንቀሳቀስ ሒደት ላይ የተፈጠሩ ክፍተቶች አሉ፡፡

እነዚያ ክፍተቶች ቢኖሩም በተለይ ወደኋላ አካባቢ ከታህሣሥ አጋማሽ ጀምሮ አጋሮችም በተቻላቸው መጠን በኮሚሽኑም በኩል በተቻለ መጠን ለማዳረስ የሚሞከር አለ፡፡ እንዲያም ሆኖ በእነዚህ ምክንያት የሚንጠባጠቡ ቦታዎች እንዳሉ ለመግለጽ እወዳለሁ። ከዚህ ጋር አያይዘን በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ዙር ለመሥራት በዝግጅት ላይ ነን፡፡ ክምችቱም ያለው በእጃችን ነው፡፡ በዚያ መንገድ ወደ ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎቻችን ይታገዛሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በእስካሁኑ የሠብዓዊ ርዳታ ድጋፍ የቀረበው በየትኞቹ አካባቢ ነው?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- አስቀድሜ ባነሳኋቸው መስፈርቶች መሠረት ይህ ጥናት የሚካሄደው በሀገሪቱ በሙሉ ነው፡፡ አንዳንድ የማይደረስባቸው ቦታዎች ቢቀሩም በጥናቱ በተለየው መሠረት ለምሳሌ ከድርቅ ጋር በሚያያዝ በአማራ ክልል ወደ ስምንት ዞኖች ያህል፣ ትግራይ አራት ዞኖች እና አፋር ላይ ወደ ሶስት ዞኖች ከዚያ ኦሮሚያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ አንዳንድ ኪስ ቦታዎች አሉ።

እነዚህ በአንድ ላይ ተደምረው ወደ አራት ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ ተጎጂዎች ተለይተዋል፡፡ አስቀድሜ የጠቀስኳቸውን ቦታዎች ጨምረን ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ማኅብረሰብ በድርቅ አደጋ የተጎዱባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ይህ ማለት ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር እስከ አሁኑ ታህሣሥ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ያለው ነው፡፡

በፊትለፊታችን ባሉ ወራት ደግሞ ወደ ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የተለዩ ተረጂዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ ከድርቁ ጋር ተያይዞ ያሉትን ጨምሮ በሌሎችም የሀገራችን ክፍሎች በግጭትም ሆነ በጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍል አካቶ ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁጥራቸው ከፍ ያለ እንደመሆኑ መንግሥት በወቅቱ ድጋፉን ባያቀርብ ኖሮ ሊከሰት የሚችለው አደጋ ምን ይመስል ነበር ይላሉ?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- እንደሚታወቀው የድርቅ መጨረሻው ነገር በዙሪያው ካሉ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተቧድኖ ኅብረተሰቡን ለጉዳት ሊዳርግ ይችላል። እንዲህም ሲባል የኅብረተሰቡ የመከላከል አቅሙ እንዲዳከም፣ በዙሪያው ካለው ከንጹህ ውሃ ከማጣት የተነሳ ለበሽታ ሊጋለጥ ይችላል፡፡ ይህ ሲደራረብ ደግሞ ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ምንም ጥያቄ የለውም፡፡

ስለዚህም አስቀድሜ ባነሳሁት በሶስት ዙሮች ሲደረግ የነበረው ድጋፍ ድርቅ ወደረሃብ እንዳይቀየር ከፍተኛ የሆነ ድርሻ የነበረው ነው ማለት እንችላለን። ይህ ድጋፍ ሲደረግ የነበረው እነዚህ አጋር ተቋማት ድጋፋቸውን አቋርጠው በነበረበት ጊዜ ነው ። በዚህ ወቅት እኛ ወደ ሰባት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ቀጥሎም ሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሕዝብ ለመደገፍ እንቅስቃሴ አድርገናል ፡፡ ይህ ድጋፍ ባይደረግ ኖሮ ሊከሰት የሚችለውን ችግር መገመት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የአጋር ድርጅቶች ሚና እንዴት ይገለጻል? በቀጣይ ከእነርሱ ጋር ስላለው ግንኙነት የታሰበው ምንድን ነው?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- አጋር ድርጅቶች በአብዛኛው አሜሪካ የልማት ድርጅት የሚያግዛቸው ናቸው፡፡ አጋር ድርጅቶች መልሰው ወደዚህ ሥራ ሲገቡ ከዚህ በፊት ይሠራ በነበረው በ20 በመቶ ላይ የሚጨመር በመሆኑ አቅም የሚፈጥር ነው። ስለዚህ ባለፈው ዓመት ከነበረው ወደ 20 በመቶ አቅም ላይ መውረዳቸው ቀሪውን ክፍተት መንግሥት እንዲሸከመው መነሻ ሆኖ ቆይቷል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ከአጋሮች ጋር ያለን ግንኙነት እንደ የትኛውም ጊዜ መልካም ነው ብለን ብንልም ከሀብት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሲታይ ሒደቱ በየጊዜው እየቀነሰ ነው፡፡

ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ አካላት ጋር በጉዳዩ ከሚያገባቸው ጋር በጋራ በየሳምንቱ ጉዳዮቹን እየተከታተልን፤ እነሱም ድርሻቸውን እንዲያጎለብቱ እያደረግን የምንሠራው አለ፡፡ በዚህ በኩል የኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሠብዓዊ ድጋፍም ይሁን ከሌሎች ሠብዓዊ ድጋፍ ከሚያስተባብሩ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሠራን ነው፡፡

ባለፉት ወራትም በተለይም ከማዕከላዊ የድንገተኛ ድጋፍ ማዕከል (Central Emergency Response Fund) ከሚባለው ወደ 23 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተመድቦ በድርቅ ለተጎዱ፣ የበሽታ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው እና በጎርፍ ለተቸገሩ አካባቢዎች ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል፤ ከፊሉ ደግሞ በሀገር በቀል ተቋማት በኩል ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡

ነገር ግን የምግብ አቅርቦትን በሚመለከት የአጋር ድጋፍ በ20 በመቶ ላይ የተገታ ነው፡፡ ይህም የሆነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም (World Food Pro­gramme) ሆነ ሌላው ይሁን የሚሰጠው አገልግሎ የ20 በመቶው ፈንድን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል መንግሥት ድጋፉን በራሱ አቅም ለመሸፈን ዓላማ እንዳለው ሲነገር ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ያለው እቅድ ምን ይመስላል?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- ከዚህ አኳያ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ አንደኛው አሁንም ለሚቸገረው ማኅብረሰባችን ሠብዓዊ ድጋፍን በቅርበት ማዳረስ ነው፡፡ በዚህም ድርቁም ይሁን ሌሎች ነገሮች ዜጎቻችንን ወደሚጎዱበት ደረጃ እንዳይደርሱ መሥራት ነው፡፡ ይህንን በምንሠራበት ሒደት በፌዴራል ኮሚሽን ከአጋር ተቋማት፣ ከተባበሩት መንግሥታት የሚመለከታቸው ተቋማት በቅርበት እንሠራለን፡፡

ክልሎች እና ከክልል በታች ያሉ የመንግሥት መዋቅሮችም የራሳቸው የሆነ ተሳትፎ ይኖራቸዋል። ከሁሉም በላይ ሕዝባችን በተለመደው መንገድ ያለውን እና የመደጋገፍ እሴቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።

ሁለተኛው ሠብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም መቻል ነው፡፡ ይህ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ በሁሉም ደረጃ የሚፈለግ ነው፡፡ በአንድ በኩል የተረጂን ቁጥር ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን በስፋት መሥራትን ይፈልጋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ተጨማሪ ምርት በማምረት በተለይ ከገበያ ጋር መሻማት ሳያስፈልግ ለሠብዓዊ ድጋፍ የሚሆን ምርት ለሚያስፈልገው እንዲዳረስ መሥራት ነው፡፡

ይህንን በማድረግ ሒደት ላይ ሠብዓዊ ድጋፍ አስፈላጊ ሳይሆን ቀርቶ ምርቱ እጃችን ላይ በሚኖርበት ጊዜ ለገበያ ሊቀርብ ይችላል፤ ለውጭ ገበያ ሊቀርብ ይችላል፡፡ እናም ሁኔታዎች በዚህ መልኩ መሔድ ሲጀምሩ “የኢትዮጵያ ርዳታ” (Ethiopian Aid) በሚባል ደረጃም እስከዚያ ድረስ ላለው ድጋፍም ሊሆን የሚችል ነው፡፡

ስለዚህ በአንድ በኩል ሠብዓዊ ድጋፉ አቅርቦቱ ይቀጥላል፡፡ ይህንን በምናደርግበት ጊዜ ለሚገባው ብቻ እንዲሆን የማድረግ እና ሁሉም ባለድርሻ እንዲተባበር በማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛ ሠብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም መሥራት ነው፡፡ ሊለሙ የሚችሉ በጣም ሰፋፊ በመስኖ ልማት መሬት አለን። እንደሚታወቀው ወደሥራ ሊሰማራ የሚችል የወጣት ጉልበት አለ፡፡

በተለይም ትርፍ አምራች በሆኑ አካባቢዎች ላይ ውሃና ተስማሚ የሆነ የአየር ጸባይ አለ፡፡ የተወሰነ አካባቢ ድርቅ ያስቸግራል ብንልም በጣም በአመዛኙ ግን ሰፋፊ ቦታዎች ላይ ትርፍ ምርት ፤ ተስማሚ የሆነ የአየር ጸባይ ያላቸውን አካባቢዎች መሠረት በማድረግ ወደማምረቱ እንገባለን የሚል ነው፡፡

ከሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት አኳያ አሁን በሚቀጥሉት ጥር፣ የካቲት እና መጋቢት ላይ ወደስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተደጋፊ ዜጎች ይኖሩናል፡፡ ለዚህ የሚሆን ዝግጅትም በራሳችን በኩል አድርገናል። ስለዚህ አንድ ላይ ከመንግሥት በኩል ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ማኅበረሰብ ለመሸፈን የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ማለት ነው፡፡ ይህም ወደ 531 ሺ አካባቢ ኩንታል እህል የሚፈልግ ነው፡፡ የቀሩትን ደግሞ ከአጋር ድርጅቶች ሥራ ላይ የገቡ ስላሉ እነርሱ የራሳቸውን ድርሻ ወስደው ወደሥራ ይገባሉ ፡፡

በዚህ አይነት መንገድ ለሚቀጥሉት ጥር፣ የካቲት እና መጋቢት ድረስ ያለውን ድጋፍ ለማከናወን በመንግሥትም በኩል ዝግጅት አድርገናል፡፡ በሌላ በኩል አጋር ድርጅቶች የራሳቸው ድርሻ ይኖራቸዋል። ከዚህ በፊት የነበረውን ነገር በተጠናከረ መንገድ እንቀጥላለን፡፡

በጸጥታ እና በተለያዩ ምክንያት ለማዳረስ ችግር የሆነባቸው አካባቢዎችም በየአካባቢው ያለውን የጸጥታ መዋቅር እየተጠቀምን ድጋፉ የሚቀርብበትን ሁኔታ ላይ እየሠራን እንገኛለን፡፡ እሱም ላይ ውጤታማ የሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ሁኔታውን እየለየን እየሠራን እንቀጥላለን፡፡

በመጨረሻም ማስተላለፍ የምፈልገው በ70 ዓመት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የአየር ንብረት ለውጥ ማስተናገዳችን ይታወሳል፡፡ ባለፈው አምስት ተከታታይ ወቅቶች በሙሉ ዝናብ ጠብ ሳይል ቀርቶ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ችግር ውስጥ ገብቶብን ከርሟል፡፡

በተለይም ደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ እና ሰሜን ምስራቅ የነበሩ አካባቢዎች ላይ፤ አሁን ደግሞ በሰሜን አካባቢ በጣም በሰፋ መንገድ ፈተና ተጋርጦ ነበር። በጎርፍም በተባይም በአንበጣም የተደራረበ ችግር ተፈጥሯል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ የሁሉም አካላት ሰፊ ርበብር እና መተጋገዝ ብሎም መደጋገፍን የሚጠይቅ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በአጋር በኩል ያለውም 20 በመቶ ላይ የተንጠለጠለው ድጋፍ ከዚህ የተሻለ ቢሆን የሚመረጥ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ችግር አለ፤ ይህ የዓለም አቀፍ ችግር ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢም ችግር ነው፡፡ ድጋፉ ከዚህ አንጻር የተቃኘ ቢሆንና የተከሰቱ ችግሮችን ማየት የሚቻልባቸው እድሎች ቢኖሩ መልካም ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

በድጋፍ ላይ የሌሉ ወይም ለመደገፍ ያልታደሉ አካላት አሉ፡፡ እነዚህ አካላት መንግሥት፣ ሕዝብ እና ሌላው የሚያደርገውን ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኞች ያልሆኑ ናቸው፡፡ በየክልሉ በሚደረገው ድጋፍ ውስጥ የሌሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን የተደረገውን ድጋፍ ለማየት አይፈልጉም፣ የተደረገው ድጋፍ ያዳነውን የሰው ሕይወትም ለማየት ያልታደሉ ናቸው፡፡

እነዚህ አካላት ምናልባት ከዚህ አይነት አስተሳሰብ ተቆጥበው እነዚህን ዓለም አቀፍ እና አሕጉር አቀፍ ችግሮች በጋራ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ ደጋፊ ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ ለዜጎቻችን የኑሮ መሠረቶቻቸውን ለመታደግም ይሁን ሕይወታቸው ላይ አደጋ እንዳይደርስ በመሥራት በኩልም ተባባሪ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ ሁላችንንም የሚያስደስት እና የተሻለ ውጤት እናገኛለን ብዬ አስባለሁ፡፡

አስቀድሜ እንደጠቀስኩት እስካሁን በመንግሥት ደረጃ ወደ 11 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፤ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ተይዟል። ይህ ሁሉ ከመንግሥት ካዝና እየወጣ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ልክ እየተሠራ እያለ በአንዳንድ አካላት መንግሥት ለችግሩ ትኩረት እንዳልሰጠው ተደርጎ ሲነገር ይደመጣል፡፡ እንዲያውም መንግሥት ለዜጎቹ ችግር ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳለ ተደርጎ ለማቅረብ ይሞከራል። መንግሥት ችግሩ ግድ እንደማይለው አድርገው ለመሳል የሚፈልጉ አካላትም አሉ፡፡

በየትኛውም መስፈርት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት፤ በሕዝቡ እየተደረገ ያለን መደጋገፍ፤ ከዚያም ባለፈ በተባበሩት መንግሥታት አካላት የሚደረጉ ጥረቶችን፤ ላለማየትም ላለማዳመጥም መሞከር ለማንም አይጠቅምም፡፡ እነዚህ አካላት ካልተገባ መንገዳቸው ተመልሰው ችግሩን በጋራ ተረባርበን እና ተጋግዘን የምንሻገርበትን ሁኔታ መፍጠር የተሻለ ነው ለማለት እወዳለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሁልጊዜ ተባባሪያችን ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You