የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በወቅታዊ ነባራዊ የቱሪዝም ዘርፉ እንቅስቃሴ ላይ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል ትናንት ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ ክፍል በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዋነኝነት ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት የምጣኔ ሀብቱ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ ስለመሆኑ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ዘርፉን ስላጋጠሙት ፈተናዎች እና ፈተናዎች አልፎ አሁን ያለበት ደረጃ ምን እንደሚመስል አይተናል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሌሎች ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር፣ በቱሪዝም ዲፕሎማሲው ከገጽታ ግንባታ ጋር የተሠሩ ሥራዎች፤ እየተከናወኑ ስላሉ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች… ወዘተ ያሉ ተጨባጭ እውነታዎችን ለማየት ሞክረናል። በዛሬው እትማችን የቃለ ምልልሱን የመጨረሻ ክፍል ይዘን ቀርበናል::
ጥያቄ- ዓለም አቀፍ ቅርሶች ሲመዘገቡ ይዘው የሚመጡት ትሩፋቶች ቅርሶች ላይ የሚደረጉ ጥበቃና እንክብካቤ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቀደም ሲል በተመዘገቡ ቅርሶቻችን ላይ የሚደረጉ ጥበቃዎች ተደጋግሞ ሲነሳ ቆይቷልና በዚህ ረገድ ምን እየተሠራ ነው ?
አምባሳደር ናሲሴ፡- የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ ዩኔስኮ እውቅና ሰጠም አልሰጠም እንደሀገር መሥራት አለብን፡፡ እነዚህን ቅርሶች ከአባቶቻችን ከአያቶቻችን የተረከብናቸው ናቸው፡፡ በታሪክ አጋጣሚ እኛ ላይ አርፈዋል፡፡ እኛም ጠብቀን ተንከባክበን ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ኃላፊነትም፤ ግዴታም አለብን፡፡ በዩኔስኮ ስለተመዘገቡ ሳይሆን እንደሀገር እንደ ሕዝብ ኃላፊነት ስላለብን እነዚህን ሥራዎች መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
ከቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ አንጻር ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው ከተባለ፤ እንደሚታወቀው እንደሀገር በጣም ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ ያ ማለት በጣም ብዙ ቅርሶች ይኖሩናል ማለት ነው፡፡ በየትኛውም መዳረሻ ስንሄድ በኢትዮጵያ ክፍል ቅርሶች አሉ። በጣም ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ፤ ለማኅበረሰብም ለዓለምም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው፤ ትምህርት ሊሰጡ የሚችሉ፣ መመዝገብም መጠበቅም ያለባቸው ብዙ ቅርሶች አሉ፡፡
ከዚህ አንጻር እንደተቋም ብቻ የሚሠራ ሥራ አይሆንም፡፡ ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ ኃላፊነት አለው፤ የራሱ ቅርስ ነው፡፡ ራሱ የተረከበውን ጠብቆ ማስተላለፍ አለበት፡፡ ማኅበረሰብ የራሱን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል፡፡ ሲቀጥል ደግሞ በየደረጃው ያሉ የተለያዩ አካላት ተቋማትን ጨምሮ የግልም የመንግሥትም ሊሆኑ ይችላሉ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ቅርሶችን ሊጠብቅ የሚችለው ሕዝብ ነው ፡፡ ብዙ ቅርሶቻችንን ተመልከቱ ዋና ጠባቂያቸው ሕዝብ ነው። ከሕዝብ ሲቀጥል ደግሞ ሌሎች ተቋማት ይመጣሉ። በፌደራል ደረጃ ያሉ ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ፣ ልክ እንደ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን፤ በክልል ያሉ ተቋማትም የራቸው የሆነ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
የተለያዩ ሲቪክ ማኅበራትም በቅርስ ጥበቃ ሥራ ላይ እንደ ሀገር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ፡፡ ቅርስ ማስመለስ ላይም ቅርስ እንዲጠበቅ የማድረግ ላይም የራሳቸው የሆነ አስተዋፅዖ ያላቸው ማኅበራት አሉ። የዚህ ሁሉ ቅንጅት ነው አንድን ቅርስ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚያደርገው፡፡ በዚህ ዘርፍ እንደሀገር ያለብን ክፍተት የመጀመሪያው ከሙያ አንጻር ነው፡፡
ቅርስ ጥበቃ በጣም የተለየ ሙያ ይጠይቃል። ለዚያ ሙያ የሚሆኑ ሰዎችን ማፍራት ያስፈልጋል፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ደግሞ በሀገር ውስጥ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የሚሰጥ ኮርስም የሚሰጥ ትምህርትም የለም፡፡ ስለዚህ ብዙ ጊዜ ቅርሶች ሲጠገኑ፣ እንክብካቤ ሲደረግላቸው ኦርጅናል ይዘታቸውን የመልቀቅ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡
እንደ ሀገር እነዚህን ሙያዎች የሚያሠለጥን ኮርስ የሚሰጥ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ክፍተት አለብን፡፡ ይሄን በተለያየ መልኩ ለመሙላት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ እሱም መቀረፍ አለበት፡፡ የእንጨት ሥራ ላይ ልምድ ያላቸው ፤ከድንጋይ ጋር ተያይዞ ልምድ ያላቸው፤ በተለያየ መልኩ ልምድ ያላቸው በጣም ብዙ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡
ከዛ በዘለለ እንደ ሀገር ያሉንን ትልልቅ የሚባሉ ቅርሶችን ከመጠበቅ አንፃር እንደ መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጣም ብዙ ርብርቦች ተደርገዋል። ከዓለም አቀፍ/ከኢንተርናሽናል አጋሮቻችን ጋር በመሆን የተለያዩ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በመሥራት ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡
እንደምታስታውሱት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከፈረንሳይ አቻቸው ጋር ተነጋግረው የላሊበላ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ ተጀምሯል፡፡ የዋናው ቅርስ ጥገና ሥራ ጥናቶች እየተጠናቀቁ ይገኛል፡፡ እንዲሁም ዋናው የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ እስኪጀምር ደግሞ አስቸኳይ የሆኑ የጥገናና የእንክብካቤ ሥራዎች በዘላቂነት /ሴስቴኔብል/ በላሊበላ እየተሠሩ ይገኛል፡፡
ይህ እንግዲህ ለቅርሱ የተለያዩ አስቸኳይ ጥገናዎችን የማድረግ ሥራ ብቻ ሳይሆን የቅርሱን ደረጃውን የማስጠበቅ፣ ተቀባይነት ወዳለው ደረጃ/ስታንዳርድ የመለወጥ እና አካባቢውን አብሮ የመጠበቅና የማልማት ሥራንም ያካተተ ነው፡፡
ለምሳሌ በላሊበላ ሰው ቀስ ብሎ የሚራመድበት መንገዶች /ዎክ ዌይ/ ተሠርተዋል፡፡ ከዚህ በፊት ገብቶ ለመውጣት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ የዲሽ ቁፋሮና ጠረጋ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ መብራት፤ ድልድይ የመሳሰሉ፤ የተለያዩ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
እነዚህ ሥራዎች ፋይዳቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ለምን ቅርሱ እንደተጠበቀ ከማቆየት አንፃር ብቻ ሳይሆን የበለጠ የቱሪስት ልምዱን ከማሳደግና መዳረሻ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ስላላቸው ነው፡፡
በተመሳሳይ በተለያየ መልኩ እየተጠገኑ ያሉ ቅርሶች አሉ፡፡ በተለያየ መልኩ በእቅድ የተያዙ ቅርሶችም አሉ። ነገር ግን ሁሉንም ከማዳረስ አንፃር እንደ ፌዴራል ተቋም ውሱንነቶች አሉብን፡፡ ምክንያቱም የቅርስ ጥገና ብዙ ሀብት የሚፈልግ ነው።
በዚሁ አጋጣሚ፤ ቅርስ ጥገና አንደኛው/ዋነኛው ተዋናይ ማኅበረሰቡ ነው፡፡ ሁለተኛ የክልል ተቋማትና የክልል መንግሥታት ናቸው፡፡ ቅርስ ጥገና ሲባል የሚመጣው ወደ ፌዴራል ከመሆኑ አንፃር እነዚህም ተቋማት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በዚሁ አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ሚኒስቴር መሥሪያ በቅርስ ጥበቃ ዙሪያ ከክልል የቱሪዝም ቢሮዎች ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚያደርጋቸው ጥረቶች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው ?
አምባሳደር ናሲሴ፡- ከቅርሱ እንጀምርና ስለሌሎቹ ጉዳዮች እንሄዳለን፡፡ ከክልሎች ጋር ያለን የቅንጅት ሥራ በተመለከተ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በአብዛኛው ከሚባሉ ክልሎች ጋር በጋራ ይሠራል። የቅርስ ጥበቃውም እንክብካቤውም ሥራ ቅርሶች ክልል ላይ እንደመሆናቸው በከፍተኛ ቅንጅት ከእነዚህ ተቋማትና ከክልል መንግሥታት ጋር ይሠራል፡፡
ከላይ ያነሳሁት ጠቀሜታውና አስፈላጊነቱን ለማሳሰብ ነው እንጂ እነዚህ የቅንጅት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ አሁንም እየተጠገኑ ያሉ ቅርሶች በቅንጅት ነው። ጅማን፣ ፋሲለደስ የሚደረገውንም ጥገና መውሰድ ይቻላል፡፡
አሁን እያወራን ባለንበት ሰዓት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚደረጉ ጥገናዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ቤኒሻንጉል፣ አፋር፣ ሱማሌና በተለያዩ ክልሎች ብንወስድ የተለያዩ የቅርስ ጥገናዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ከክልሎች ጋር በመናበብና በትብብር እየሠራን ነው፡፡
ነገር ግን ብዙ ቅርሶች ያሉን ስለሆነ ትብብሩም ማጠናከርና በተሻለ ሁኔታ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ላይ ያለውን ነገር ከማሳደግ አንፃር ነው እንጂ የቅንጅት ሥራዎቹ አሉ፡፡ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ጥያቄ፡- ከቱሪስት ገቢ ጋር በተያያዘ በክልል የቱሪዝም ቢሮዎችና በቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል የሚወጡ መረጃዎች መጣረስ ይታይባቸዋል፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው ?
አምባሳደር ናሲሴ፡- የገቢ ስሌትን በተመለከተ ገቢ የሚሰላበት ዓለም አቀፍ አሠራር አለ፡፡ ይህን ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ከኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመን እንሠራበታለን፡፡ ለምሳሌ የቱሪስት ቁጥርን በተመለከተ ዋና የመረጃ ምንጭ የምናደርገው ኢሚግሬሽን ነው። ለምን? የኢሚግሬሽን የቁጥር መረጃ አይሳሳትም፡፡ መከፋፈያ መንገድ አለው፡፡
ማን ዘመድ ጥየቃ መጣ፣ ማን ለጉብኝት መጣ፣ ማን ወደ ሌላ ሀገር ሊሸጋገር መጣ የሚሉት እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች አሉት፡፡ ስለዚህ ዋና የመረጃ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለን የቱሪስት ቁጥር ስንናገር ኢሚግሬሽን ነው፡፡ የተለያዩ ተቋማትም ሲያወጡ እንደምታዩት እኛ የምናወጣው ቁጥር በብዛት ከዓለማቀፍ ተቋማት ከሚያገኙት የራቀ አይደለም፡፡
ኢንተርናሽናል ስታንዳርዱ እንደሚፈቅደው ከቱሪስት ገቢ ለመሥራት ይህ ቁጥር ሲባዛ በቀን ወጭ ሲባዛ በቆይታ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ የቆይታ ጊዜ ከዚህ በፊት በተደረገ ጥናት ይታወቃል። ማዕከላዊ/አቬሬጅ የቆይታ ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ፤ ስለዚህ ያንን የመጣ የቱሪስት ቁጥር ከቆይታ ጊዜ እንዲሁም በቀን ምን ያህል ያወጣል ተብሎ ከሚታሰበው ወጭው ጋር ይሰላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የራሱ የሆነ ሳይንቲፊክ ስሌት-ሜትድ አለው።
የሀገር ውስጥ ቱሪስትን ከወሰድን በአብዛኛው የመረጃ ምንጮች/የዳታ ሶርሳችን የክልል መረጃዎች /ዳታዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከክልሎች መረጃዎችን እንሰበስባለን/ፑል እናደርጋለን ማለት ነው። አንዳንዴ ቁጥርን አስመልክቶ የሚፈጠሩ ውዝግቦች ምንድ ናቸው የተባለ እንደሆነ እንደሀገር ብዙ የመረጃ ክፍተቶች/የዳታ ክፍተቶች ይኖሩብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ቱሪስት ምን ያህል ቆየ የሚለው ምናልባት ድጋሚ ሰርቬይ መሥራት የሚያስፈልገው ይሆናል፡፡
አሁን ባለው አሠራር አንድ ቱሪስት በአማካኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ10 እስከ 11 ቀን ይቆያል፡፡ ሲጓጓዝና የተለያዩ ነገሮችን ሲያደርግ ይቆያል፡፡ ስለዚህ ያንን በአማካኝ በየቀኑ የሚያወጣውን ነው የምናባዛው፡፡ ነገር ግን እነዚህን መረጃዎች/ዳታዎች የበለጠ ማጥራት የበለጠ መተርጎም ያስፈልጋል፡፡ በተለየ ደግሞ ከሀገር ውስጥ ቱሪዝም ጋር የሚያያዙ መረጃዎችን/ ዳታዎችን የበለጠ ማጥራት ያስፈልጋል፡፡
ይህን ችግር ለመፍታት አሁን ላይ ያዘጋጀነው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት አለ፡፡ በቀጣይ ወራት ወደ ሥራ የምናስገባው፤ ይህንን የቱሪዝም ሚኒስቴር ከልማትና ፕላን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሌሎችም የፌደራል ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ከግሉም ሴክተር፤ የአስጎብኚ ተቋማት ጋር አብሮ እየሠራ ነው፡፡
ያለው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት መረጃ/ዳታ በተለያየ መልኩ በኤክስፐርቶች ድጋፍ አየተደረገለት እየሠራ ይገኛል፡፡ የዚህ የቱሪዝም ሴክተር ሳተላይት አካውንት ዋና ፋይዳው፤ አንደኛ ምን ያህል ቱሪስት መጣ የሚለውን በሚገባ ያጣራል፡፡ ሁለተኛ ቱሪዝም ለጂዲፒ ያለውን አስተዋፅዖ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡
መረጃዎችን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች /ዳታ ሶርስ/ እናሰባስባለን/ፑል እናደርጋለን፡፡ ከአየር መንገድ፤ ከተለያዩ ባንኮች፤ ከኢሚግሬሽን እና ከተለያዩ ተቋማት፣ ከሥራና ክህሎት በጣም ብዙ ከሚባሉ ተቋማት ይሰበሰባል/ ፑል ይደረጋል፡፡ እንደ ሀገር ከምንሠራው ከብሔራዊ ቆጠራ የስታትስቲክስ ባለሥልጣን ከሚሠራቸው የተለያዩ ሰርቬዎች መረጃ ይሰበሰባል/ዳታ ፑል ያደርጋል፡፡
በዚህም ዘርፉ ለጂዲፒ ያለው አስተዋፅዖ ምን ያህል ነው የሚለውን ጥርት አድርጎ ማሳየት ያስችላል። መንግሥት ቱሪዝምን ከዋና ዘርፎች አንዱ ነው ብሎ ወስዷል፡፡ ኢንቨስትም እያደረግ ነው፡፡ እየወጣበት ያለውን ወጪ የሚመጥን አስተዋፅዖ አለው የሚለውን በሚገባ ያሳያል፡፡
ከዛ በተጨማሪ መንግሥትን ሆነ የግሉን ዘርፍ በዘርፉ ኢንቨስት የሚያደርገውን በሚገባ እና በግልጽ ያሳያል፡፡ በዘርፉ ስንት ሰው ተቀጠረ የሚለውን በግልጽ ያሳያል፡፡ በቀጥታ የተቀጠሩትንም ያሳያል፣ በተዘዋዋሪ የሥራ እድል የተፈጠረላቸውን በሚገባ ያሳያል፡፡ ስለዚህ ከጂዲፒ አስተዋፅዖ አንጻር ጥርት ያለ መረጃ/ ዳታ ይኖራል። ከሥራ ፈጠራ አንጻር፤ ከዚህ በፊት እንዳለው የሪፖርት መጋጨት እና የመሳሰሉት ችግር አይኖርብንም። ችግሮቹን በመቅረፍ ጥርት ያለ መረጃ/ዳታ ይኖረናል፡፡
ምክንያቱም ብሔራዊ ስታትስቲክስ በየጊዜው ከሚሠራቸው ሰርቬዎች በተለያየ መልኩ የሚሠሩ ስለሆኑ ጥርት ያለ መረጃ/ ዳታ ስለሚሰጡ እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥርት ያለ የቱሪዝሙ ስታትስቲክስ መረጃ/ዳታ እናገኛለን፡፡ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት አሁን ጨርሰን ወደ ሥራ እያስገባን ስለሆነ በዘርፉ ያለው መረጃ እየጠራ ይመጣል ፡፡
በዚህ ቀጥተኛም ሆን ቀጥተኛ ያልሆነውን አስተዋፅዖ እናያለን ማለት ነው፡፡ እስስካሁን ባለው ግን በተቻለ መጠን የቱሪዝም፤ የኢሚግሬሽን ዳታ ሰብስበን/ፑል አድርገን ዓለማቀፍ ስታንዳርዱ በሚያስቀምጠው መልኩ በቆይታ ጊዜ እናባዘዋለን፤ እንዲሁም በአቬሬጅ ዴይሊ ኤክስፔንዲቸር እናበዛዋለን፡፡
ጥያቄ፡- የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ከማስፋፋት አንጻር ምን እየተሠራ ነው ?
አምባሳደር ናሲሴ፡- የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ከማበረታታት አንጻር ያለፈው ዓመት የጀመርናቸው ትልቅ የሚባሉ ዋና ዋና ሥራዎች አሉ፡፡ በዚህ ዓመትም እነዛን ሥራዎች ማስቀጠል ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው፡፡
ያለፈው ዓመት ከጀመርናቸው ዋና ዋና ከሚባሉ ሥራዎች አንዱ የልወቅሽ ኢትዮጵያ ዘመቻ ነው። የልወቅሽ ኢትዮጵያ ዘመቻን በተለያየ መልኩ በዲጂታል ፎርሙ እንዲሁም በኮንቬንሽናል/በዋናው/ ሚዲያ መሥራት ጀምረናል፡፡ ያለፈው የእግር ኳስ ላይ ታስታውሳላችሁ፡፡ ያ ከፍተኛ መነሳሳትና የመጓዝ ፍላጎትን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡
ከዛ በተረፈ በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ጉብኝቶች እና መነሳሳቶች እንዲኖሩ እንደሀገር ከሠራናቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ የቱሪዝም ክበባትን መመሥረት ነው፡፡ የቱሪዝም ክበባትን በተቋማት በመንግሥት እና በግል ተቋማት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በተለያየ ቦታ ክበባት እንዲመሠረቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገናል፡፡
በጣም ብዙ የሚባሉ ተቋማት እስከታች ወርደው የጉዞ ክበባትን መሥርተዋል፡፡ ለምሳሌ ባንኮች እስከታች ቅርንጫፎች ወርደው፤ እንደገቢዎች ሚኒስቴር ያሉ ትልልቅ ተቋማት እስከታች ቅርንጫፎች ወርደው፤ የጉዞ ክበባትን መሥርተዋል፡፡ እንዲሁም ሌሎችም በግል ትምህርት ቤቶች ደረጃ የጉዞ ክበባትን መመሥረትና እንዲነቃቁ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡
ይሄ እንግዲህ እንደምታውቁት ድሮ የጉዞ ክበባት አሉ ሰዎች አዋጥተው አንድ ላይ አብረው ይጓዛሉ። ያንን ልምድ ማበረታታትና ድጋሚ ማምጣት ያስፈልጋል በሚል እሱ ተሠርቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከባንኮች ጋር የሠራነው ሥራ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከባንኮች ጋር የቁጠባ አካውንቶች፤ የተለያዩ ትርፍ ያላቸው የተለያየ ትርፎችን ማስገኘት የሚችል የቱሪስት የቁጠባ አካውንቶች እንዲከፈቱ ተደርጓል ለዚህም ከሌላው ቁጠባ አካውንት የተሻለ ጥቅም እንዲኖረው እንዲሁም የተለያየ ሽልማት እንዲኖሩት አድርገናል፡፡ እነዚህን በተለያዩ ባንኮች የመክፈት ሥራ ተሠርቷል፡፡
ከዛ በተጨማሪ ከቴክኖሎጂ አንጻር ያለፈው ዓመት ወደሥራ ያስገባነው የቪዚት ኢትዮጵያ አፕሊኬሽን እንደሀገር ስንጓዝ፣ ተጉዘን ስናበቃ የተለያየ ለማስታወቅ ይረዳ ዘንድ የተለያዩ አካላትም ልክ እንደማኅበራዊ ሚዲያ ጉዛቸውን ፖስት የሚያደርጉበት መዳረሻውን የሚያስተዋውቁበት ለመፍጠርም ልምዳቸውንም የሚያካፍሉበት ከማድረግ አንጻር ታስቦ መተግበሪያ ወደሥራ ገብቷል ፡፡
ስለዚህ በዚህ ዓመት የበለጠ እነዚህን በሚገባ የማጠናከር፣ የተለያዩ ዘመቻዎችን የማስተዋወቅ፤ የተመሠረቱት የጉዞ ማኅበራት ወደ ሥራ ገብተው ሰዎች መጓጓዝ እንዲችሉ ድጋፍ እየተሰጠ ይገኛል ነው፡፡ እነዚህንና ተጨማሪ የተለያዩ ጉዳዮችንም በመሥራት የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን የማነቃቃት ሥራ በሚገባ መሥራት አለብን ብለን እየሠራን ነው፡፡
ጥያቄ ፡- ከግል ዘርፉ ጋር በጋራ ለመሥራት ምን ታስቧል?
ክብርት አምባሳደር ናሲሴ፡- ያው እንግዲህ የቱሪዝም ዘርፉን ከማሳደግ አንጻር የግል ዘርፉን መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የተለያዩ ማበረታቻዎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ ተገብቷል። የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ ለምሳሌ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄዶ የሚያለማ ባለሃብት የታክስ እፎይታ ጊዜ ይሰጠዋል። ከግንባታ እቃዎች እስከ መገልገያ እቃዎች ደግሞ ከታክስ ነፃ እንዲያስገባ ሁኔታዎች ተመቻችተው ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከተሽከርካሪዎችም ጋር ተያይዞ በተለያየ መልኩ እስከ አሁን በጣም ብዙ የሚባሉ የጉዞ ወኪሎች/ ቱር ኦፕሬተሮች እንዲሁም የሆቴልና የሎጅ ባለቤቶችም በተለያየ ሁኔታ እንደሀገር ተደግፈዋል፡፡ እንደ ሀገር ያለን ማበረታቻ በጣም ብዙ ነው፤ ከማበረታታት አንጻር የበለጠ መጨመር ያለብን ቦታዎችም አሉ።
ለምሳሌ ከተለያዩ እቃዎች ጋር ተያይዞ በይበልጥም እዚህ ከማይገኙ እቃዎች ጋር ተያይዞ ከግምት ውስጥ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡ አዳዲስ ከሚከፈቱ መዳረሻዎች ጋር ተያይዞ፤ ለምሳሌ( የውሃ ስፖርት) እና የመሳሰሉት ጋር ተያይዞ አሠራሮችን ወደ ሥራ ማስገባት ይጠበቅብናል፡፡
ከኮንፍረንስ ቱሪዝም ጋር ተያይዞ አዳዲስ ማበረታቻዎችን አጥንቶ ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል። ያሉትም ማበረታቻዎች ወይም ድጋፎች በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ፤ የተለያየ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል። ድጋፎቹ ለትክክለኛ ሰው እየደረሱ ነው ወይ? ለትክክለኛው ባለ ሃብት ትክክለኛው ማበረታቻ እየደረሰ ነው ወይ? የሚለውንም ማጥራት ያስፈልጋል።
ከዚህ አንጻር የገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የምንሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ጥሩ በሚባል መልኩ ለግሉ ዘርፍ ድጋፎችን እየሰጠን እንገኛለን፡፡ አሁንም የሚቀሩ፣ የሚያድጉ፣ ብዙ ፍላጎቶች ቢኖሩም፤ እንደሀገር እያየን መጨመር ያለብንን በተለይም የቱሪዝም ሴክተሩን ከማሳደግ አንጻር አዳዲስ የሚባሉ ነገሮችን ማስለመድና ወደ ሀገር ማስገባት አለብን። ከዚህ አንጻር ማስተካከያዎችን እናደርጋለን፡፡
እንግዲህ የግል ዘርፉን/የፕራይቬት ሴክተሩን ከመደገፍ አንጻር ከሌሎች ተቋማት ጋር የሚሠሩ ሥራዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ የቱሪስት ፍሰት፣ የቱሪስት ልምድ፣ ለአንድ ሀገር ተወዳዳሪነት በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህ አንጻር ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጋር በመሆን በሠራናቸው ሥራዎች የተለያዩ ክለሳዎች ተደርገዋል፤ ከኦን ላይን ቪዛ አሁን ላይ ቪዛ ኦን አራይቫል 122 ለሚሆኑ ሀገራት ክፍት ሆኗል፡፡ ክብርት ሠላማዊት እዚህ በነበሩ ጊዜ ችግሩን በቅርበት ስለሚያውቁት፣ ችግሩን በፍጥነት ከመፍታት አንጻር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
ከጉምሩክ/ከከስተምስ ጋር ተያይዞም የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፤ በተለይም ከድህነታችን ጋር ተያይዞ በተከለከሉ የቱሪስት መገልገያ መሣሪያዎች ላይ የተለያዩ ቅሬታዎች ይቀርባሉ፡፡ እነዚህን ቅሬታዎች ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በቅርበት በመነጋገር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
አሁን ባለው አሠራር ችግሮች ሲያጋጥሙ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በቅርበት መነጋገር የሚያስችለው አሠራር ተፈጥሯል፡፡ ነገር ግን ይህ አሠራር ወደፊት እኛንም ሳያሳትፍ የሚሳለጥበትና ቱሪስቱ በቀላሉ ይዞ ገብቶ ይዞ የሚወጣበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ ነው፡፡
ለምሳሌ ካጋጠሙ ችግሮች አንዱ ከጎረቤት አገር በድንበር የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ጉዳይ ነው። በአብዛኛው በድንበር የሚገቡት ተሽከርካሪዎች አስጎብኝተው መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ጉምሩክ ኮሚሽን አንድ የገጠመው ችግር ግን እነዚህ ተሽከርካሪዎች በብዛት የማይወጡ መሆኑ ነው፡፡ ወይ ይሸጣሉ፤ ወይ ሀገር ውስጥ ተቀምጠው ለተለያየ ጉዳይ ይውላሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ አቁሞት ነበር፡፡
ነገር ግን አሁን አሠራር ተፈጥሮ ተጠያቂነት ባለው መልኩ የጉዞ ወኪሎች /ወኪሎች/ ቱር ኦፕሬተሮች ኃላፊነት እየወሰዱ ተሽከርካሪዎች በቀላሉ ገብተው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ልክ እንደዚህ አይነት አሠራሮችን እየፈጠርን ሀገርንም ለድህነትና ለአደጋ የሚያጋልጡ፤ ኢኮኖሚያችን በተለያየ መልኩ ማግኘት ያለበትን ጥቅም የሚጎዱ፣ ችግሮች ተቀርፈው የቱሪስቶች ፍሰቱና ልምዱ የተሳለጠ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ጥያቄ ፡- መጨመር የሚፈልጉት ሀሳብ ካለ?
አምባሳደር ናሲሴ፡- በእርግጥ ሁሉንም ጉዳይ ነካክተናል፤ ያልነካካነው ነገር የለም፡፡ ምናልባት ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ ማስተላለፍ የምፈልገው መልእክት፤ አንደኛ ለግሉ ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ዋናው ተዋናይ የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ ስለዚህ የግሉ ዘርፍ ጋር ቀርበን በሚያስፈልጋቸው መልኩ ለመደገፍ ጥረት እናደርጋለን። በማበረታቻ ፣ በሕግ ማዕቀፍ ወዘተ… ፡፡
የግሉም ዘርፍ ደግሞ አሁን ባሉ እንቅስቃሴዎች ተነቃቅቶ ሊሠራ ይገባል፡፡ አሁን እንደሚታወቀው ቱሪዝም ቱሪዝም የሚል መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ የግሉ ዘርፍ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ኢንቨስት ማድረግ እና የሀገራችንን ውበት ማውጣት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ከአደራ ጭምር ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡ ይህ እንግዲህ ወኪሎች/ቱር ኦፕሬተሮች ሌሎችንም ይጨምራል፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ ዘርፉ ለሕገ- ወጥ ተዋናዮች የተጋለጠ ነው፡፡ የተለያዩ ሕገ-ወጥ ኦፕሬተሮችን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ የተሠማሩ ባለሃብቶች እነዚህን ሕገ-ወጥ ተዋናይን በማጋለጥ እና ወደ መሥመር እንዲገቡ በማድረግ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የማስተላልፈው፤ ቱሪዝም ሚኒስቴር እንደተቋም ሀገርን የማስተዋወቅ ኃላፊነት፣ የሀገርን ውበት የማሳየት፤ የሀገርን ገጽታ የመገንባት ኃላፊነት ይኑርበት እንጂ፤ የሀገራችንን ውበት ማሳየት፣ የሀገራችንን ቱባ ባሕል እና ብዝኃነታችንን የማሳየት፤ ረጅም ታሪኳን የማሳየት እና በሁሉም ዘርፍ የሀገራችንን ውበት አሳይቶ ቱሪስቶች ወደ ሀገር እንዲገቡ ማድረግ፤ በሀገር ውስጥም ያለ በውጭም ያለ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡
ስለዚህ በሀገራችን በጎ በጎ ነገሮች ላይ እና የበለጠ የሀገራችንን ገጽታ በመገንባት ላይ ብናተኩር፣ ከስልካችን ጨምሮ የያዝናቸውን ዲጂታል አፕሊኬሽኖች ለመልካም ነገሮች ብንጠቀም፤ በተለይ የሀገራችንን ገጽታ የሚገነቡ፤ በኢኮኖሚ የበለጠ ሀገራችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ወደ ሀገራችን ቱሪስቶችን መሳብ የሚችሉ ነገሮች ላይ ትኩረት እንድናደርግ ከአደራ ጭምር ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፡፡
አምባሳደር ናሲሴ፡- እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም