የወጣቶችን የወደፊት ተስፋ ያለመለመው የባህር በር ስምምነት

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ላይ ይዞታ የነበራትና ቀይ ባህርንም ስታዝበት የኖረች ሀገር ነች። 1ሺ800 ኪሎሜትር የሚረዝመውን የቀይ ባህር ይዞታ በቁጥጥሯ ስራ ያኖረችና ለወጭና ገቢ እቃዎች ሁለት ወደቦች የምታስተዳደር ሀገር ነበረች። ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ውጪ ቀይባህርንም ከኢትዮጵያ ውጭ ማሰብ አይቻልም ነበር።

ሆኖም የኢትዮጵያን ማደግ በማይፈልጉ ኃይላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትወገድ ተደርጓል። ላለፉት 30 አመታትም ያለወደብና ባህር በር ለመኖር ተገዳለች። በዚህም የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆንም ከስነልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ህዝቡ እንዲጋለጥ አድርጎታል። የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድም ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል።

ለበርካታ መሰረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ልማቶችን ይውል የነበረውን ከ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለኪራይና ለመጓጓዣ ከፍተኛ ዶላር ስለምታፈስ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል። በዲፕሎማሲ እና በተጽዕኖ ፈጣሪነትም ረገድ የኢትጵያ ሚና አሽቆልቁሏል።

በኢትዮጵያ አዲስ የመንግስት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በትኩረት ከሰራባቸውና ለውጥ ካመጣባቸው ጉዳዮች አንዱ የባህር በር ጥያቄ ነው። መንግሥት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባህር በር ጣያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። ለ27 አመታት ያህል ፈርሶ የቆየውን የባህር ኃይል እንደገና በማደራጀት ኢትዮጵያ እንደገና የባህር ኃይል እንዲኖራት አድርጓል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከ33 ዓመታት በኋላ የባህር በር የምታገኝበት አማራጭ ተገኝቷል። ሰላማዊ አማራጭን ሲከተል ቆየው የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን ከሶማሊ ላንድ ጋር የባህር በር የሚገኝበትን መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) ተፈራርሟል ።

ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው። ቀጠናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር የሚከፍት ነው።

ይህ ሁኔታ ዛሬ በኢትዮጵያውን ልብ ውስጥ ደስታን ጭሯል። የተስፋ ውጋጋንም ለኩሷል። ለዘመናት ያህል በቁጭት ውስጥ ለነበረው ህዝብም ስብራትን ጠግኖ የወደፊት ተስፋ አለምልሟል። በተለይ የነገ ሀገር ተረካቢ ለሆነው ወጣት ትልቅ ሞራል ሆኗል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ 126 ሚሊዮን እንደደረሰ ይታመናል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 70 በመቶ የሚሆነው ወጣት የህብረተሰብ ክፍል ነው። ይህ የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ አኪኖሚው ሲያድግ የስራ ዕድል ይከፈትለታል፤ጥራቱን የጠበቀ ትምህርትና የጤና አገልግሎት ያገኛል፤ ባለሀብት ሆኖ ሀገሩን ያገለግላል ከራሱ አልፎ ለቤተሰቡ ብሎም ለሀገር አለኝታ ይሆናል።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ሸብቦ የያዛትና አብዛኛውን ገቢዋን እየበላ ያለውን ለወደብ የሚወጣው በቢሊዮን ዶላል የሚቆጠር ወጪ ወደ ራሷ ካዝና ሲገባና የባህር በር ጥያቄዋም ሲመለሰ ነው። ይህንኑ የዘመናት ጥያቄም ለመመለስ መንግስት የተከተላቸው መንገዶች ተገቢና የወጣቱንም ወደፊት ህልም ያለመለመ መሆኑን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናግረዋል።

ቶሌራ ሙሉጌታ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቨርናንስና ዴቭሎፕመንት የ4ተኛ ዓመት ተማሪ ነው። ቶሌራ ሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የባህር በርን በተመለከተ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ሲሰማ ልቡ በሃሴት እንደተሞላ ይናገራል። ላለፉት ዘመናትም ኢትዮጵያ ወደብ እና ባህር በር አልባ ሆና በጎረቤት ሀገር ጥገኝነት ውስጥ መቆየቷ ሲያስቆጨው እንደቆየ ይናገራል።

‹‹ኢትዮጵያ ጥንታዊት ሀገርና እና ቀይባህርንም ለዘመናት ስትቆጣጠር የቆች ሀገር ብትሆንም የቅኝ ገዢዎች በሰሩባት ሴራ የባህር በሯን እድታጣ ተደርጋ ቆይታለች። በዚህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር ኢኮኖሚው እያደገ የሚሄደውን የስራ አጥ ቁጥር መሸከም ባለመቻሉ በርካታ ወጣቶች ተምረው ያለስራ ለመቀመጥ ተገደዋል።

ወጣቶች በሀገራቸው ላይም ተስፋ በማጣታቸው ሀገር ለቀው እንዲሸሹና እንዲሰደዱ ሆነዋል። ዛሬ ግን ወጣቱ የተስፋ ብርሃን አይቷል። ከዛሬ የተሻለ ነገ እንደሚመጣም ለመረዳት ችሏል። መንግስት ኢትዮጵያን ከ33 አመታት በኋላ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን ማድረጉም ሊያስመሰግነው የሚገባ ነው›› ብሏል።

ቶሌራ እንደሚለውም ኢትዮጵያ ከሶማሊ ላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስትፈርም በርካታ ኢትጵያውን የተደሰቱትን ያህል ጥቂት የሀገር ውስት ሰዎችና የኢትዮጵያን ማደግ የማይፈልጉ ሀገራት ጉዳዩን ለመጣጣል ሲሞክሩ ይታያሉ። ሆኖም ሁለቱ ሀገራት ያደረጉት ስምምነት ማንንም የሚጎዳ አይደለም። ይልቁንም አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው። ከሁሉም በላይ ግን የኢትዮጵያን ህዝብ የሞራል ስብራት የሚጠገን ነው።

ስለዚህም ወጣቱ መንግሥት ላከናወነው ተግባር ዕውቅና ሊሰጥ እንደሚገባ ወጣት ቶሌራ ጥሪ አቅርቧል። በተለይም ደግሞ ወጣቱ ሶሻል ሚዲያን በስፋት ስለሚጠቀም ኢትዮጵያን እና ሶማሊ ላንድ ያደረጉትን ስምምነት በአግባቡ ማስተጋባት አለበት። ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብት እንዳላትና ይህን መብቷን እንድትጠቀም ድጋፍ እንዲደርግ ወጣቱ ለመላው አለም ጥሪ ማድረገት አለበት ሲል ወጣቱ ሃሳቡን አሳርጓል።

ያስሚን አህመድ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ4ተኛ አመት የህግ ተማሪ ነች። ያስሚን እንደምትለው ኢትዮጵያ የባህር በር የሚያስገኝላትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊላንድ ጋር ማድረጓን ስትሰማ በጣም ተደስታለች። ከ33 አመታት በኋላ በእሷ ዕድሜ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የሚያደርጋትን እድል ማግኘቷ ልቧን በሃሴት ሞልቶታል።

እንደ ህግ ተማሪነቷ ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣቻችባቸው ምክንያቶች ተገቢ አለመሆናቸውን ትረዳለች። ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት እድትሆን የሚደግፉ በርካታ የህግ ማዕቀፎች ቢኖሩም እስካሁን ድረስ እንደሀገር በበቂ ትኩረት ስላልተሰራ ኢትዮጵያ ባህርና ወደብ አልባ ለመሆን ተገዳለች። አሁን ግን እንደሀገር ለባህርና ለወደብ ጉዳይ ትኩረት መስጠቱ የኢትዮጵያን የወደፊት ተስፋ እንደሚያለመልመው ትናገራለች።

ያስሚን ኢትዮጵያ ሰላማዊ አማራጮችን ብቻ በመጠቀም የባህር በር ባለቤት ለመሆን እያደረገች ያለው ጥረት ፍሬ እያፈራ መምጣቱን ተመልክታለች። ታህሳስ 22 ቀን 2016 ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት አማራጯን ያሳፋና በሰላማዊ መንገድ የኢትዮጵያ ጥያቄዎች ሊመለሱ እንደሚችሉ ተረድታለች።

ሆኖም ያስሚን እንደምትለው የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ያላስደሰታቸው ሀገራት አሉ። ከሶማሊ ሊፐብሊክ ጀምሮ ግብጽ እና የአረብ ሊግ ተጠቃሾች ናቸው። የሶማሊ ሪፐብሊክ የሚጠበቅ ቢሆንም ግብጽና አረብ ሊግ በማያገባቸው ጉዳይ ገብተው ነገሩን ለማባባስ የሚያደርጉት ጠረት ተቀባይነት ሌለው ነው። ላስለዚህም ወጣቱ ትውልድ ማህበራዊ ሚዲያን ለሀገሩ ጥቅም የሚያውልበት ጊዜው አሁን ነው።

‹‹በአሁኑ ወቅት ወጣቱ በከፍተኛ መጠን የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ላይ ይገኛል። ይህ የህብረተሰብ ክፍል ጊዜውን በማይረቡ ጉዳዮች ላይ ከማዋል ይልቅ የኢትጵያን ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ ይገባል። የኢትዮጵያን እድገት የማይሹና አሁን የጀመረችውም መንገድ የማይዋትላቸውን ሀገራት በማውገዝ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለቀሪው አለም ማሳየት የወጣቱ ሚና ሊሆን ይገባል። ›› ትላለች ሰሚራ።

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ አመት የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ተማሪ የሆነችው ተማሪ ማርያማዊት በጥሰት የሰሚራና ሃሳብ ትጋራለች። ኢትዮጵያ ለዘመናት ባለቤት ሆና ከቀየችበት የቀይ ባህር አካባቢ እንድትነጠል የተደረገበት መንገድ እንደዜጋ የሚያስቆጭ መሆኑን ታስዳለች።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ላይ የንግድ እንቅስቃሴ ስታደርግ የኖረችና በአካባቢውም ተሰሚነት የነበራት ሀገር ነበረች። ሆኖም ቅኝ ገዢዎች ከአንዳንድ የአካባቢው ሀገራት ጋር በመመሳጣር ኢትዮጵያን ባህር አልባ በማድረግ ከቀሪው አለም ጋር በአግባ እንዳትገናኝ አድርገዋት ኖረዋል። ይህ ደግሞ እንደዜጋ የሚያስቆጭ መሆኑን ትናገራለች።

ሆኖም መንግስት የዜጋውን ቁጭት በመንተራስ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን የምታረጋግጥበትን መንገድ መቀየሱ የሚያስመሰግነው ነው። በተለይም ለነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሀገር ጥቅም ማስጠበቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ታብራራለች።

ተማሪ ማራማዊት አክላም ወጣቱ ትውልድ ጊዜውን በአልባሌ ከሚያሳልፍና አልፎ ተርፎም በተሳሳተ ፖለቲካ ተጠልፎ እራሱንና ሀገሩን በሚጎዳ ተግባር ውስጥ ከመግባት ይልቅ ኢትዮጵያ የምትበለጽግበትን መንገድ አብዝቶ መሻት ይጠበቅበታል።

ማርያማዊት እንደምታምነው መንግስት ከሶማሊ ላንድ ጋር የፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በተመለከተ ወጣቱ ጥቅጠሙን በአግባቡ ሊረዳው ይገባል። የመግባቢ ሰነዱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማሳደግ ኢንዱስትርሪና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እንደሚረዳ እና በዚህም ምክንት እየተማረ ላለው ወጣት የስራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለወደብ ታወጣለች። ይህ ገንዘብ ለሥራ ፈጠራና ለወጣቱ ስብእና ቀረጻ ቢውል ያደገችና ብሎም የበለጸገች ኢትዮጵያን በቀላል መመልከት እንደሚቻል ተማሪ ማራማዊት ታስረዳለች።

በአጠቃላይ ወጣቶቹ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የያዘችው ጎዳና ለወጣቱ ተስፋ ሰጪ ነው። በተለይም የባህር በር የኢኮኖሚው ዋነኛ ዋልታ እንደመሆኑ መጠን ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት የወጣቶቹን የነገ ተስፋ አለምልሞታል።

ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው። ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ይከፍታል።

ሆኖም የተጀመሩት ጥረቶች ፍሬ እንዲያፈሩ ሰላም ያስፈልጋል። ወጣቱ ከሁሉም ነገር በላይ ለሰላም ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። ሀገር በጀመረችው ግስጋሴ መቀጠል የምትችለው ሰላም ሲኖር ነው። እዚህም እዚያም ያሉ ግጭቶች ሊቆሙ ይገባል። ወጣቱም በስሙ ከሚነግዱ ኃይሎች እራሱን ቆጥቦ ለሀገሩ ልማት ፊት አውራሪ ሆኖ ሊነሳ ይገባል የሚል መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ጥር 3/2016

Recommended For You