“የገበታ ፕሮጀክቶች የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት በርካቶች ወደ ቱሪዝም ኢንቨስትመንት እንዲገቡ እያስቻሉ ነው” – የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ

 የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በወቅታዊ ነባራዊ የቱሪዝም ዘርፉ እንቅስቃሴ ላይ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሙሉቃል

ጥያቄ፡- በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዋነኝነት ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት የምጣኔ ሀብቱ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ ነው ። በአስር ዓመቱ መሪ የልማት እቅድም ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ነው። እቅዱ ለመተግበር ወደ ሥራ ከተገባበት በ2013 ዓ.ም ጀምሮ ኮቪድ 19 ጨምሮ በሰሜኑ የሀገሪቱ አካበቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች ለዘርፉ ፈተና ሆነዋል ። ዘርፉ እነዚህን ፈተናዎች አልፎ አሁን ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?

አምባሳደር ናሲሴ ፡– እንደሚታወቀው በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ልማታችንን እና እድገታችንን ያፋጥናሉ ተብለው ታሳቢ ከተደረጉ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ነው። ይህንንም ስናደርግ በምክንያት ነው። አንዱ ምክንያት ያለንን ሃብት ታሳቢ በማድረግ ነው፣ ያለንን የተፈጥሮ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ሀብት ለቱሪዝም በጣም የተመቻቸ በመሆኑ ነው።

ሁለተኛው ታሳቢ የተደረገው ያለንበት ጂኦግራፊካል አቀማመጥ / ሎኬሽን ነው። እንደሚታወቀው ያለነው በጣም ስትራቴጂክ ቦታ ላይ ነው። ለብዙ ሀገራት ቅርብ ነን፤ ይህ ብቻ አይደለም፤ ለምሳሌ አውሮፓን ብንወሰድ ዋና ገበያችን ነው፤ ለአውሮፓ ቅርብ ነን። መካከለኛው ምሥራቅንም ብንወስድ ትልቅ ገበያ እየሆነ ያለ ስፍራ ነው። የአፍሪካ ሀገሮችን ጨምሮ ለሌሎች ሀገሮችም ቅርብ ነን፤ ከዚህ በተጨማሪ ለቱሪዝም ከሚያስፈልጉ አንዱ ዓለም አቀፍ በረራ የመኖሩ ጉዳይ ነው ። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ120 ሀገራት በላይ ይበራል። ይህም ለእኛ በጣም ጥሩ ሁኔታን ይፈጥራል። ስለዚህ ታሳቢ የተደረጉ ብዙ ጉዳዮች አሉ ማለት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ አፍሪካ የሚመጣው የቱሪዝም ፍሰት እያደገ ይሄዳል የሚል እሳቤ አለ። የሚቀጥሉትን ዓመታት ካየን እስከ 2050 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ቱሪስቶች ወደ አፍሪካ የሚያደርጉት ፍሰት ከሌሎች በበለጠ እያደገ ይሄዳል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ታሳቢ ተደርገው ነው እቅዱ የወጣው።

እቅዱ በጣም ሰፊና ትልቅ እንደመሆኑ ያንን ለማሳካት ደግሞ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በጣም ብዙ ሥራ ያስፈልጋል። እንደተባለው ደግሞ አስቀድሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር፤ ከዚያም ደግሞ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ፤የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ ለዘርፍ ተግዳሮት ነበር። ያንን ተከትሎ የተለያዩ የጉዞ ክልከላዎችና የመሳሰሉት ሁኔታ ተፈጥረው ስለነበር የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በጣም ብዙ ፈተናዎች የነበሩባቸው ነበሩ።

ነገር ግን ለእነዚህ ፈተናዎች አልተንበረከክንም። በጣም ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል። ምንም እንኳን ብዙ ተግዳሮቶች የነበረበት ጊዜ ቢሆንም፤ችግሮቹ ዓለምአቀፍ የቱሪስት ፍሰቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳረፉ ቢሆኑም ፤ በጣም ብዙ የቤት ስራዎች ስለነበሩን እነሱ ላይ ትኩረት ለማድረግ ተሞክፘል። እንደ ሀገር ካሉን የቤት ስራዎች መካከል የመዳረሻ ልማት ስራዎች ይጠቀሳሉ።

በጣም ብዙ መስህቦች አሉን። ታሪካዊ ሀብታችን ብዙ ነው። የብዝሀ ባህል መገለጫዎች ነን። በተለያዩ ኮርነሮች የተለያዩ ትልልቅ ፌስቲቫሎች ሊሆኑ የሚችሉ ሃይማኖታዊ ሆኑ ባህላዊ ኩነቶች አሉን። ከዛም ባለፈ የተፈጥሮ፣ የመልክአ ምድር፣ የአየር ፀባይ ውበት አለን፤ ለቱሪዝም ዘርፍ የአየር ፀባይ በጣም አስፈላጊ ነው።

በዱር እንስሳትም በተለያየ መልኩ በተፈጥሮ የታደልናቸው ሀብቶች ብዙ ናቸው። ነገር ግን እነዚህ ብዙ ጉድለቶች አሉባቸው። ብዙዎቹ መስህብ ናቸው እንጂ መዳረሻ አልሆኑም።በመስህብና በመዳረሻ መካከል ልዩነቱ ምንድነው ከተባለ መስህቡ አለ ነገር ግን መደረሻ ለማድረግ ግን የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ማሟላት ይጠበቃል።

መሰረተ ልማቶች ብቻ ሳይሆኑ ደግሞ ከመሰረተ ልማትም ባለፈ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማሟላትን ግድ ይላል። የተወሰኑ ምሳሌዎችን ለማንሳት እሞክራለሁ፤ በቅርቡ የተከፈተውን የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅን ብናይ የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ እዛው ነበረ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን መጥተው ስሙን እስክንሰማ ድረስ ብዙዎቻችን ስለፓርኩ አናውቅም፤ ብዙዎቻችን ስለፓርኩም አልሰማንም።

የመጀመሪያውን ጉዞ ያደረጉት ሰዎች እንደሚገልፁት፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጨምሮ መሄጃ መንገድ እንኳ ስላልነበረ በጣም ዳገት ቧጦ በእግር በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ነበር ማየት የተቻለው። በአጠቃላይ ተደራሽ አልነበረም ማለት ነው። ስለዚህ መስህቡ አለ ነገር ግን መዳረሻ መሆን አይችልም።

ቱሪስቶች ሄደው እዛ ለመድረስ መሄጃ መንገድ የላቸውም፤ ከደረሱም በኋላ ደግሞ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ፣ የሚያርፉበት፤ ቡና የሚጠጡበት የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ አካል የለም። ስለዚህ አንዱ የነበረን ትልቅ ክፍተት የቱሪስት መሰረተ ልማትና የቱሪስት መዳረሻ አለመኖር ነበር። በእነዚህ ዓመታት በተለያየ መልኩ የመዳረሻ ልማት ስራዎች በሰፊው ተሰርተዋል።

ለእዚህም የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች መጥቀስ ይቻላል። ከዛም ቀጥሎ ገበታ ለሀገርን ማንሳት ይቻላል። አሁን ደግሞ ወደ ገበታ ለትውልድ እየገባን ነው። በገበታ ፕሮጀክቶች የተለያዩ የመዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል ፤ ይህም ደግሞ የግሉን ዘርፍ አነቃቅቶ በርካቶች ወደ ቱሪዝም ኢንቨስትመንት የገቡበት ሁኔታ ታይቷል። አንዱ የቤት ስራችን እሱ ስለነበረ እሱን ስንሰራ ቆይተናል።

ሁለተኛው የቤት ስራችን ዓለም አቀፍ ቱሪዝምን ለማሳደግ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እድገት በጣም ያስፈልጋል። ምክንያቱም የሀገር ውስጥ ቱሪዝም አንደኛ ለመሰረተ ልማትና ለቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መስፋፋት በር ይከፍታል። ሁለተኛ የማስተዋወቅ እድልንም ይጨምራል። ምክንያቱም እየመጣ የሚጠቀም ሁሉ በሶሻል ሚዲያ ፖስት ሲያደርግና በተለያየ መልኩ ስያስተዋውቅ መዳረሻዎች የበለጠ እየተዋወቁ ይሄዳሉ።

ሶስተኛ ደግሞ የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ገበያ ሲቀዛቀዝ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማቶቻችን እንዳይጠፉ እንዳይከስሙ፣ የተፈጠሩ የሥራ እድሎች እንዲቀጥሉ ያስችላልና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሰራነው የቤት ሥራ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ንቅናቄን ማስጀመር እና እሱ እንዲቀጥል ማድረግ ነው።

አራተኛው የቤት ስራችን የማስተዋወቅና የኢትዮጵያን ገፅታ የመገንባት ሥራ ነው። ከዚህ አንፃር ምንም እንኳ ያው ጦርነት ውስጥ የነበርንም ቢሆንም፣ ምንም እንኳን ተግዳሮቶች የነበሩበት ወቅት ቢሆንም፣ በተለያየ መልኩ ወደ ሀገራችን የሚመጣ የቱሪስት ፍሰት እንዳይቀዛቀዝ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ከተደረጉ ጥረቶች መካከል በተለያየ ዙር በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ለትውልደ ኢትዮጵያን የተደረጉ ጥሪዎች ናቸው ።

በዚህም በጣም ብዙ ጎብኚዎችን ወደ ሀገር ውስጥ የመሳብ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም አቀፍ መድረኮች በመገኘት ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ እና ስለኢትዮጵያ እውነታውን የማስጨበጥ ስራዎችም ተስርተዋል። ባለፉት ጊዜያት እነዚህን የቤት ስራዎች ስንሰራ ቆይተናል። ከጥራት ጋር የተያያዙም ብዙም ባይባል የሞከርናቸው ስራዎች አሉ፤ እነሱን እናስቀጥላለን።

እነዚህን በመጀመሪያው ዓመት በስፋት መሰራት የነበረባቸውና የተጠራቀሙ የቤት ስራዎች ተሰርተዋል። ነገር ግን የተለያዩ ፈተናዎች የሉም ማለት አይደለም ። ሀገር በጦርነት ውስጥ ስትሆን ፣ ጦርነት ለልማት የሚሆንን ሀብት መጠየቁ አይቀርም፤ ያም ሆኖ የመስራት አቅማችን ያን ያህል የተገደበ አልነበረም። ፈጠራ የተሞላባቸው መፍትሔዎችን ፈልገን ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል።

ጥያቄ ፡- ገቢ ከማሳደግ እና የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ ?

አምባሳደር ናሲሴ ፡– ቅድም እንዳነሳሁት ትላልቅ ግቦችን አስቀምጠናል። ከቱሪስት ፍሰት አንጻር በጣም ትልቅ ግብ አስቀምጠናል። የስራ ዕድል ከመፍጠር አንጻርም ትልቅ ቁጥር አስቀምጣናል። ከመዳረሻ ልማት አንጻር እንዲሁ ትልቅ ቁጥር አስቀምጠናል /ይህን አሁን የከለስንበት ሁኔታም አለ/ ከመዳረሻ ልማት አንጻር መድረስ የየምንፈልግበት ቦታ አለ።

እነዚህን ግቦች ተሳቢ በማድረግ የተለያዩ የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል ላይ ነን ። ይህንንም በማድረጋችን በጣም ብዙ ጥቅሞችን እያየንብት ነው ። ለምሳሌ ያለፈውን የ2015 በጀት አመት የመጨረሻ ወራት / ከጥር እስከ ሰኔ አካባቢ ያሉትን ወራት/ ብንወስድ የአለም ቱሪዝም ድርጅት /WTO/ ባወጣው ሪፖርት መሰረት የቱሪዝም ስራዎቻችን ዳግም ማሰራራት ችለዋል፤ ማንሰራራት ብቻም ሳይሆን ብዙ የቱሪስት ቁጥር ካዩ የአፍሪካ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ እንዷ መሆን ችላለች።

ይህ የሆነው ለምንድን ነው ? እነዚህ ሁኔታዎች ተደማምረው ነው። አዳዲስ መዳረሻዎች ወደ ስራ መግባታቸው፣ በሃገር ገጽታ ግንባታ ላይ በቂ ስራ ባይሰራም ጥሩ ጅምር መኖሩ፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም መነቃቃት መቻሉ.፣ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ የግሉ ዘርፍ በዘርፉ በስፋት ማሳተፍ በመቻሉ ነው።

የቅንጅት ስራዎቻችንም ሌሎች አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው። ከተለያዩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ጋር ስራዎችን አብረን ማከናወናችን ፤በተለይ በማስተዋወቅ ረገድ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድና ቱር ኦፕሬተሮች ከመሳሰሉት ጋር የተከናወኑ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። እነዚህ የቅንጅት ስራዎች የቱሪስት ፍሰቱ እየጨመረ እንዲመጣ እና ከፍተኛ መነቃቃት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አድርገዋል። ያለፈውንም ሩብ ዓመት ስንመለከትም ከዚህ የተለየ አይደለም ። የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ጨምሮ የቱሪስት ፍሰቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ።

ልንደርስብት ከምንፈልገው ቁጥር አንጻር ሲታይ ግን አሁንም ብዙ የቀሩን የቤት ስራዎች እንዳሉን ታሳቢ እናደርጋለን። ከእቅዳችን አንጻር ጥሩ መጥናል ፤ነገር ግን ደግሞ በስፋት ሰርተን ያስቀመጥነውን ቁጥር ቢቻል ማሳካት ካልተቻለ ቀረብ ማለት ያስፈልጋል።

ጥያቄ ፡- በአቅዱ መነሻ ላይ በ2012 ዓ.ም ወደ 850 ሺ ቱሪስቶች ሀገሪቱን ይጎበኙ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፤ በእቅዱ ማብቂያ ላይ ደግሞ ይህን አሀዝ ወደ ሰባት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ለማድረስ ነው እየተሰራ ያለው። በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የመዳረሻ ልማት ስራዎች ለእዚህ አጋዥ ይሆናሉና የመዳረሻ ፕሮጀክቶቹ /የገበታ ፕሮጀክቶቹ/ ተጽእኖ ምን ይመስላል?

አምባሳደር ናሲሴ ፡ እንደሚታወቀው መንግሥት በዋናነት አስቻይ ፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ ማውጣት ፣የግሉን ዘርፍ የማበረታታት ሚና ነው ያለው ። አሁን የምናያቸው የልማት ስራዎች የግሉ ዘርፍ ደፍሮ እንዲገባባቸው የሚያደርጉ ናቸው ። ምክንያቱም የግሉ ሴክተር በብዛት በከተሞች አካባቢ የመወሰን ሁኔታዎች ይታይበታል ። ደፍሮ በርቀት ያሉ ቦታዎችን ማልማት ላይ ውስንነት አለ።

እነዚህን ውስንነቶች አንድም ለመቅረፍ ሁለትም “ኢንስፓየር” አድርጎ ሌሎችም እንዲገቡ ለማስቻል ነው ። ሶስተኛው ደግሞ አስፈላጊ የመሰረተ ልማቶች ወደእነዚህ ቦታዎች እንዲደርሱ ለማድረግ ነው። እነዚህ መሰረተ ልማቶች ወደ ሩቅ በቦታ ሲዘረጉ የፕርይቬት ሴክተሩ በተሻለ ሁኔታ ተነቃቅቶ ወደ ሥራ ይገባል የሚል ሃሳብ ነው ።

ከዚህ አንጻር ምንድን ነው የመጣው ለውጥ ? ከተባለ ከዚህ አንጻር ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። አንደኛ የሀገሪቱ ሙሉ ገጽታ እንዲታይ ማድረግ አስችሏል። አሁን እየተገነቡ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ከወሰድን እንደ ሀገር የነበረው የቱሪስት እንቅስቃሴ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ ነበር። ልማቱ በጣም ውስን ቦታዎች ላይ ይህን የቱሪስት እንቅስቃሴ ማስፋት አስችሏል።

ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ ውብ ናት። ሁሉም አቅጣጫዋ ታሪክ ጠገብ ነው። ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በጣም ያማረ ውብ የሆኑ ባህሎች አሉት፤ ተፈጥሮውም እንደዚያው ያማረ ነው። ስለዚህ እንደ ሀገር እዚህን ሁሉ ሀብቶቻችን መጠቀም ስንችል ነው እድገት የሚታሰበው ። ሀገርን በሙሉ ገጽታ ከማስተዋወቅ ረገድ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እንዳሉ ይታወቃል። ቀጣይ ደግሞ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ቦታዎች በተለይም ከዚህ ቀደም ባልተለመዱ ቦታዎች ላይ የሚሰሩ ይሆናል። ይህ ደግሞ መዳረሻዎቻችን ቁጥራቸው እንዲጨምር እና የቱሪስት እንቅስቃሴው ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል እንዲሆን አስተዋጽኦ አለው። ያ የመጀመሪያው የገበታ ፕሮጀክቶች ዋና አላማ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ የእነዚህ የገበታ ፕሮጀክቶች ዋና አላማ መሰረተ ልማቱን ወደተለያዩ የሀገራችን ክፍል ማድረስ ነው ። ብዙ ሰው የገበታ ፕሮጀክቶች የሎጅ ግንባታ ስራዎች ብቻ ይመስሉታል። ነገር ግን ዋና አላማቸው የቱሪስት መሰረተ ልማት ናቸው ። መብራቱ፣ ውሃው ፣ ቴሌኮሙ የመሳሰሉት አገልግሎቶችን ጭምር ነው ይዞ የሚሄደው ።

ይህ ደግሞ አንደኛ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ። ሁለተኛ ደግሞ የግሉ ዘርፍ ደፍሮ ወደእነዚህ ቦታዎች ሄዶ እንዲያለማ መንገድ ይከፍታል። ይህንን ለምሳሌ በጨረራ አካባቢ ማየት ይቻላል። በወንጪ አካባቢም እየተጀመረ ነው ። በሌሎች አካባቢዎች በግሉ ዘርፍ ላይ መነቃቃት ፈጥሯል።

በሶስተኛ ደረጃ የቱሪስት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር እንዲሁም የሀገር ገጽታን እንዲገነባ አስችሏል። የሀገር ጎብኚዎች ፍላጎት እንዲጨምር እያደረገም ነው። ከቤት ወጥቶ የመሄድ የማየት ፍላጎቱ እንዲጨምር አድርጓል፤ የውጪውም ቱሪስት አዳዲስ ያልታዩ ቦታዎችን ወጣ ብሎ ማየት እንዲችል አስችሎታል።

በአጠቃላይ ስናየው እነዚህ ስራዎች በቱሪስት ፍሰቱ ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ አጠቃላይ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ላይ እንዲሁም እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጾኦ አበርክቷል።

ጥያቄ ፡- የቱሪዝም ሚኒስቴር ከሌሎች ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ፣እንዲሁም በቱሪዝም ዲፕሎማሲው ገጽታ ከመገንባት ጋር በተያያዘ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች ውጤታማነት ምን ይመስላል?

አምባሳደር ናሲሴ፡ እንግዲህ፣ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቱሪዝም ከሁሉም ዘርፎች ጋር የተሳሰረ ነው። መልቲ ሴክተራል ዘርፍ ነው። ከሁሉም ዘርፍ የሚፈልጋቸው ግብዓቶች አሉ። ለሁሉም ዘርፍ የሚሰጣቸው ፀጋዎችም አሉ። ስለዚህ የቅንጅት ሥራ በጣም አስፈላጊ ነው። የቅንጅት ሥራውን በተለያየ መልኩ ከፋፍለን ማየት እንችላለን።

አንደኛ ከመንግሥት ተቋማት ጋር ያለ ትስስርና ቅንጅት ነው። ከዚህ አንፃር በአጋርነት የምናያቸውና በጣም በቅርበትና በጋራ የምንሰራቸው ተቋማት ብዙ ናቸው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከማስተዋወቅ አንጻር፣ ውጭ የሚደረጉ ሥራዎች፣ እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ጋብዘን ከሌላ ሀገር ጋር የምናደርጋቸው የትውውቅ ጉዞዎች ጋር በጣም በቅንጅትና በመተሳሰር አብረን እንሰራለን።

እንዲሁም፣ የኢትዮጵያን ገጽታ ከማስተዋወቅ አንፃር የተሰሩ ቪዲዮዎች ላይ አብረን በቅርበት እንሰራለን፤ በተመሳሳይ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም እንደዚሁ ከማስተዋወቅና የሀገርን ገጽታ ከመገንባት አንፃር በጣም በቅርበት አብረን የምንሰራው ተቋም ነው። ምክንያቱም እንደ ሌሎች ሀገራት ውጭ ሀገር ላይ ራሱን የቻለ የቱሪዝም ቢሮ የለንም።

እኛ ያ ባይኖረንም ኤምባሲዎቻችንን በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር ከውጭ ጉዳይ ጋር በተቻለ መጠን እየሰራን እንገኛለን። የፈለግነው ደረጃ ላይ ደርሰናል ወይ? ከተባለ ገና ብዙ መንገድ ይቀረናል፤ የምናሻሽላቸውና ቅንጅቱን የምናጠብቅባቸው ቦታዎች ይኖራሉ። በዚያ መንገድ አብረን እንሰራለን ማለት ነው።

ዲያስፖራውንም እንደ አምባሳደር በመጠቀም ከማስተዋወቅ አንፃርም ከዚሁ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር አብረን የምንሰራ ይሆናል ማለት ነው። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተለያዩ ጉዞዎችን እያዘጋጀን እዚህ ያሉ ዲፕሎማቶች፣ እዚህ ያሉ አምባሳደሮች ቱሪዝም ስንል ምን ማለት ነው? የሰው ሕይወት ከቱሪዝም ጋር እንዴት የተሳሰረ ነው? የሚሉትን በደንብ እንዲረዱ እያዘጋጀን እንገኛለን።

ይህ ለምን ያስፈልጋል ካልክ፤ እዚህ አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ የጉዞ ክልከላዎችን ማድረግ ቀላል ነው። በእርግጥ ስጋት ኖሮባቸው የጉዞ ክልከላ የሚደረግባቸው ቦታዎች ይኖራሉ። አካባቢዎችን እየወሰዱ የማሳየት ጥቅምን በሚገባ እንዲረዱ፣ የሕዝቡን ትስስር፣ ከቱሪዝም ጋር ያለውን ትስስር በሚገባ እንዲረዱ ለማድረግ ያስችላል።

ለዚህ ምሳሌ ላሊበላን ብንወስድ፣ ላሊበላ ኑሮው የተሳሰረው ከቱሪዝም ጋር ነው። ኢኮኖሚያዊ ገቢውም የሚያገኘው በአብዛኛው ከቱሪዝም ነው። ስለዚህ በዚህ ላይ ክልከላ ስታደርግ በዚህ ሕይወት ላይ ችግር እንደሚያስከትል (አፌክት እንደሚያደርግ) ቦታው ላይ ሄዶ በማሳየት ነው።

ለዚህም የግንዛቤ ሥራ ለመሥራት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ ኢንተርናሽናል ተቋማት፣ እንደ ዩኔስኮ ካሉት ጋር በመሆን ለዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲው መድረኮችን እናዘጋጃለን ማለት ነው።በቀጣይ ተመሳሳይ ብዙ መድረኮች ይኖሩናል።

ከዚያ በተረፈ ሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አሉ፤ በቅርበት የምንሰራቸው የሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር ሥራን ከመፍጠር አንፃር፤ በተለይ እንደ ዘርፍ ቱሪዝም ሥራ ፈጣሪ ነው። እንደሚታወቀው፣ በዓለም ላይ ካሉ አሥር የሥራ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ቱሪዝም ነው። ያ ማለት በጣም ትልቅ አቅም ያለው ነው ማለት ነው። ከዚህ አንፃርም ከእነርሱ ጋር በቅርበት የምንሰራባቸው ቦታዎች አሉ።

ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ባህል አንዱ የቱሪዝም ግብአት እንደመሆኑ ከእነርሱ ጋርም የምንሰራቸው ሥራዎች አሉ። እንዲሁም ደግሞ ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ እንደ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ኢንሳ ከመሳሰሉ ተቋሞች ጋር በቅርበት እንሠራለን። ለምሳሌ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር ቢሮን ከማደራጀት አንጻር፤ ሎካል ሰርቨሮች፣ ዴታ ቤዞች የተለያዩ ሥራዎችን ሊያሳልጡ የሚችሉ አፕሊኬሽኖችን ከመሥራት አንጻር አብረን እንሠራለን።

ከኢንሳ ጋርም እንደዚሁ፣ ለምሳሌ በቅርቡ የምናስመርቀው የማርኬቲንግና ፕሮሞሽን የሆነ ሀገራዊ ፕላት ፎርም እየሠራን እንገኛለን። ዘርፉ ወደ ቴክኖሎጂ መምጣት ስላለበት ከእነዚህ ተቋማት ጋር አብረን እንሠራለን። ከባንኮች ጋር በተለያየ መልኩ አብረን እንሠራለን። ለምሳሌ ከንግድ ባንክ ጋር እንደምታውቁት የቱሪስት ስማርት ካርድ ወደ ሥራ እንዲገባ አድርገናል።

ከሌሎች ባንኮች ጋርም የተለያዩ ትብብሮች አሉን። ከዚያ በተረፈ እንደ ኢምግሬሽን፤ ከሰተምና ከመሳሰሉት የግድ ሥራዎችን ጋር ስለሚያስተሳስረን፤ ቱሪስቱም ጥሩ ልምድ ኖሮት እንዲመለስ፤ ከእነዚህ ተቋማት ጋር አብረን በቅርበት እንሠራለን። ፌደራል ፖሊስ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን ከጸጥታ ጋር ተያይዞ ብዙ ጉዳዮች ስላሉ።

በቅርቡ እንዲያውም የምንፈራረመው ይኖራል ማለት ነው። እዚህ ጋ የረሳኋቸው ሊኖሩ ይችላሉ፤ ልረሳ እችላለሁ፤ ያልጠቀስኳቸው ተቋማት ሊኖሩ ይችላሉ። እንደ ናሽናል ባንክ፤ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ከመሳሰሉት ጋር የቱሪስት ሳታላይት አካውንት እየሠራን ስለሆን፤ ግብአት ከእነዚህም ስለ ምንወስድ ከተለያዩ፣ ከጠቀስኳቸውም ካልጠቀስኳቸውም ተቋመት ጋር በቅንጅት እንሠራለን።

ይህ ደግሞ አንደኛ ዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ መሠረት እንዲይዝ ያስችላል። ሁለተኛ ደግሞ የቱሪስት አገልግሎቱ እየተሳለጠ እንዲሄድ ያደርጋል። ስለዚህ ከሞላ ጎደል ከመንግሥት ጋር እነዚህን ሥራዎች እንሠራለን። ሌላኛው አስፈላጊ ነገር ከግሉ ዘርፍ ጋር የምንሰራው የቅንጅት ሥራ ነው።

እንደሚታወቀው የግሉ ዘርፍ የቱሪዝም ሴክተሩ ዋንኛ ተዋናይ ነው። ስለዚህ ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት መሥራት በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህ አንጻር እንግዲህ ከኦፕሬተሮቻችን፣ ከቱር ጋይዶች፣ ከሆቴል ማህበራትና ከመሳሰሉት ጋር በጣም በቅርበት እንሠራለን። ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ፣ መስከረምና ጥቅምት ላይ በሳይንስ ሙዚየም ያደረግነው ኤግዚቢሽን ነው።

ሙሉ የቱሪዝም ቤተሰብን አንድ ቦታ ሰብስቦ ጥሩ የሆነ ነገር ለማሳየት ችለናል ማለት ነው። ከዚያ በተጨማሪ ግን በዋናነት የኢትዮጵያን ገጽታ ከመገንባት አንጻር፤ ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅ አንጻር ከእነዚሁ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ጋር ሥራዎችም እንሠራለን። ለምሳሌ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ትሬድ ፌሮችን ስንሳተፍ ይዘን የምንሄደው የግሉን ዘር ተዋናዮች ነው። ቱር ኦፕሬተሮች ወደ 40 በመቶ የሚሆነውን እንዲያስተዋውቁ እናደርጋለን። ከእነርሱ ጋር በቅርበት እንሠራለን ማለት ነው። በተለያየ ዘርፍ ከግሉም ጋር፤ ከመንግሥት አካላትም ጋር በቅርበት እየሠራን እንገኛለን።

ጥያቄ፡- በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው

አምባሳደር ናሲሴ፡ ከሰው ሀብት ጋር ተያይዞ ሁለት ክፍተቶች አሉ። አንደኛው ክፍተት በዘርፉ በቂ ሰለጠነ የሰው ኃይል አለ ወይ? ብትለኝ፤ በቂ የሆነ፣ በምንፈልገው ደረጃ በስልጠና አልፎ የመጣው የሰው ኃይል በጣም ጥቂቱ ነው።

,በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አቅርቦት ብቻ ሳይሆን የክህሎት ጉዳይ ነው፤ ክህሎት ስል ሠልጥኖ ፤ የሚፈለገውን ክህሎት በሚፈለገው ደረጃ አዳብሮ ወደ ሥራ የገባ የሚለውን ነው። የመጀመሪያው ጋር ስንሄድ በጣም ብዙ ተቋማት፣ በጣም ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች በቱሪዝም ዘርፉ ሥልጠና ይሰጣሉ። ከዛም ተጨማሪ በቲቪቲ ደረጃ ሲቲቲአይን ጨምሮ፤ ሌሎችም ተቋማት እንደዚሁ ሥልጠናዎችን ይሠጣሉ።

እነዚህ እንግዲህ ቶሎ ወደ ሥራው ይወሰዳሉ። አሁን የግሉ ዘርፍም እየተነቃቃ ብዙ ኢንቨስት እያደረገም ነው። አሁን እነዚህ ወደ ተቋማት ይገባሉ። ነገር ግን አሁንም በምንፈልገው ደረጃ፤ ሙሉ በሚባል ደረጃ በሆቴሎቻችን ላይ፣ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የምናያቸው ሙሉ በሙሉ የሠለጠኑ ናቸው ማለት አይቻልም።

ምናልባት ባለ ኮከብ ሆቴሎች ላይ ብዙ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን እናይ ይሆናል። ነገር ግን ደግሞ ወደ ታች ወረድ እያልን ስንሄድ የማናይበት ሁኔታ በጣም ሰፊ ነው። ስለዚህ ከዚህ አንጻር የሚሰሩ ብዙ ሥራዎች ይኖራሉ። የካሪኩለም ማሻሻያዎች ላይ የበለጠ ልምምድ በሚሰጥበት ሁኔታ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ስርአተ ትምህርቱን ከመከለስ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን እንሰራለን።

ነገር ግን ይሄ በቂ አይደለም፤ ቅድም እንዳነሳሁት ክህሎቱን ማዳበር፤ ሰልጠን አንድ ነገር ነው። የበለጠ ክህሎትን ማዳበር ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ስለዚህ ክህሎትን ከማዳበር አንጻር እንደ ሀገር አንድ ያለብን ክፍተት የኤክሰለንስ ሴንተር (የልህቀት ተቋም) የለንም። የኤክሰለንስ ሴንተር ስለሌለን ብዙ ባለሙያዎች ትልልቅ ሆቴሎች፣ ለምሳሌ ኢንተርናሽናል ሆቴሎችን ወደ ኢትዮጵያ ስናስገባ እነዚህን ሙያዎች ይፈልጋሉ።

የሰለጠነና ልምድ ያለው ሼፍ፣ የጣሊያን ሼፍ ሊሆን ይችላል፤ የቻይና ምግብ የሚሰራ ሼፍ ሊሆን ይችላል። እንዲሁም የተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያሉ ባለሙያዎችን በዛ ጥራትና ደረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል። እነሱም ይህንን ይፈልጋሉ። ስለዚህ ሌላው እንግዲህ በትኩረት ወደ ፊት መስራት ያለብን ክፍተቶቻችንና የቤት ሥራዎቻችን ናቸው ብለን የምንወስደው ያሉንን ተቋማት ወደ ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ (የልህቀት ማእከል) ማሳደግ ነው።

አሁን ባሉበት ደረጃ በጣም ብዙ ሥራ ይቀረናል። ስለዚህ ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ መገንባታችን የግድ ይሆናል። ስለዚህ በሱ ላይ ብዙ ሥራ የሚጠይቀን ይሆናል ማለት ነው። እነዚህን ክህሎት አዳብረው፤ ያንን ክህሎት ይዘው ሊወጡና ወዲያው ወደ ሥራ መግባት የሚችሉ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ አሁንም ብዙ ሥራ ይቀረናል።

ጥያቄ፡- እናንተ የምትሰጡት የብቃት ማረጋገጫ ሆነ የቁጥጥር ስራዎች ለዘርፉ እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል ?

አምባሳደር ናሲሴ፡ ያው እንግዲህ እንደሚታወቀው የተለያየ የብቃት ማረጋገጥ ሥራዎችን እንሠራለን። የደረጃ ምደባ ሥራዎችን እንሠራለን። የደረጃ ምደባና የብቃት ማረጋገጥ ሥራ በመሰረቱ ጥሩ ሆኖ ሁሌም ብቃት ማረጋገጥ፤ ሁሌም ደረጃ መመደብ ጥሩ ሆኖ በራሱ ብቻውን በቂ አይደለም።

የሀገራችንን የሰርቪስ ኳሊቲ (የአገልግሎት ጥራት) ወደ ተፈለገው ደረጃ ለመውሰድ ብዙ መስራት ያሉብን ጉዳዮች ይኖራሉ። ነገር ግን እነዚህ የብቃት ማረጋገጥና የደረጃ ምደባ ሥራዎች የራሳቸው የሆነ፣ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አላቸው፤ ለምሳሌ የቱር ኦፕሬተሮችን መውሰድ ይቻላል። የብቃት ማረጋገጥ ሥራዎችን እንሰራለን። እነዚህ የብቃት ማረጋገጥ ሥራዎች የቱር ኦፕሬተሮች በየጊዜው ራሳቸውን እንዲያበቁ፤ የሚቀጥሯቸው ሠራተኞችም በሚገባ የሰለጠኑ፤ ሙያው ያላቸው እንዲሆኑ ያስችላል።

እንደዛ ሲሆን ደግሞ ያው ለሌላው የሚሰጠው አገልግሎት (ሰርቪስ) ያንኑ ያህል ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የራሱ አስተዋጽኦ አለው። የሆቴል ደረጃ ምደባንም ካነሳን በተመሳሳይ መንገድ የምናያቸው፣ የተለያዩ መመዘኛና መስፈርቶች አሉ።የሰው ኃይል እናያለን፣ ፋሲሊቲውን እናያለን፤ የተለያዩ ጉዳዮችን እናያለን። ይህም ስራ ምን ሊሆን ያስችላል፣ ቢያንስ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡና ተቋማት ወደዛ መንገድ እንዲሄዱ ያስችላል። ሙሉ በሙሉ እዛ ደርሰዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

እንደምታወቀው የኮከብ ደረጃ ማለት ዓለም አቀፍ መግባቢያ ቋንቋ ነው። ኢትዮጵያ ያለ አንድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ዱባይ ካለ ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ሆቴል በታች መሆን የለበትም። ምክንያቱም ባለ አምስት ኮከብ ማለት ዓለም አቀፍ መግባቢያ ቋንቋ ስለሆነ። ስለዚህ ሆቴሎቻችንን ወደዚያ ደረጃ ማድረስ ስለሚያስፈልግ ያንን እየተከታተሉ በቁጥጥር ሱፐርቪዥን፣ በድጋፍ ሱፐርቪዥን ወደዛ ደረጃ እንዲበቁ ማድረግ ያስፈልጋል።

ኮከቡን መስጠት ብቻም ሳይሆን። ስለዚህ ከዚህ አንጻር የጀመርናቸው ጥሩ ጥሩ ስራዎች አሉ፤ ሁለቱ ስራዎች ጥሩ ሆነው፣ ነገር ግን እንደአጠቃላይ እንደ ሀገር ደግሞ የቱሪስት አገልግሎት አሰጣጣችን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ብዙ መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ። ስለዚህ ለመጀመር የምናስበው ፕሮግራም አለ። “ናሽናል ሰርቪስ ኳሊቲ አሹራንስን” ወደ ሥራ ለማስገባት ጥናቱም ዲዛይኑም አልቋል።

ይህንን ማድረግ ለምን ያስችላል፣ አንደኛ አቅርቦት ላይ ከማተኮር ይበልጥ ደግሞ የአገልግሎት ጥራት ላይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲያተኩሩ እድሉን ይፈጥራል። ሁለተኛው በይበልጥ የአገልግሎት አሰጣጥ መስፈርት ምንድነው የሚል ማህበረሰብንና የወረደ አገልግሎትን የሚጠየፍ ማህበረሰብን መፍጠር ነው። ምክንያቱም በተለያዩ ሀገራት እንደሚታወቀው ሰዎች ደረጃ የሚሰጧቸውን ነው ሌላውም እያየ የሚሄደው።

ሬስቶራንት ስትፈልግ “የትኛው ነው ጥሩ?” የሚለውን ጉግል አድርገህ በደንብ ታውቃለህ። በኢትዮጵያም ስታንዳርድ ወደዚያው መሄድ ስላለብን የወረደ አገልግሎት የሚጸየፍ ህብረተሰብን መፍጠርና በተለያየ ቴክኖሎጂ ተደግፎ፣ የምዘና ሲስተም ተዘጋጅቶ ሁሉም እየተመዘነ፣ ደረጃው እየታወቀ መሄድ ይኖርበታል ማለት ነው። ስለዚህ ወደ ፊት ጉግል አድርገህ የትኛው ሬስቶራንት ወይም ሆቴል ጥሩ ነው የሚለውን እንደ ሀገር መድረስ ይኖርብናል ብለን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሰራን ነው።

ጥያቄ ፡- ወደ ቱሪዝም ዲፕሎማሲው እንመለስና በቅርቡ የጨበራው ዳና ሎጅ ሲመረቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያቀረቡት ጥሪ ነበር። በተለይም የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበው ነበር። በዚህም እርስዎም በመጀመሪያዎቹ ቀናት አቀባበል ሲያደርጉ ነበር፤ አሁን ያለበት ደረጃ እንዴት ነው?

አምባሳደር ናሲሴ፡ ቅድም ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ በተለያየ መንገድ በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወንድም እህቶቻችን ጋር ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በአካልም በመሄድ፣ እንዲሁም ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ጥሪዎችን በማድረግ።

ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያዊያን የተደረገው ጥሪም የዚያው ቀጣይ ክፍል ነው ብለን መውሰድ እንችላለን። በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር እንዲገቡ ጥሪ ተደርጎ በጣም ጥሩ ውጤት አይተንበታል። ለምሳሌ የ2014ቱን ማንሳት ይቻላል፤ በጣም ትልቅ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው መጥተው ከሀገራቸው ጎን ቆመው አንደኛ ከሀገራቸው ጋር መሆናቸውን ለውጭው ዓለም አሳይተዋል። ሁለተኛ ሀገራቸው አንፃራዊ ሰላም እንዳለና ሰዎች መምጣት እንደሚችሉ አሳይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከወገኖቻቸው ጋር ተሳስረው በተለያየ መልኩ ወገኖቻቸውን ደግፈዋል። የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍል ጎብኝተው የቱሪዝሙ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል የተሻለ እድል ፈጥረዋል።

ከዚሁ ቀጥሎ በ2015 ዓ.ም የተለየ ጥሪ ተደርጓል። አሁንም ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ተደርጓል። ዋና ዓላማው የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር ማድረግ ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዓመታት በውጭ ሀገራት ኖረዋል። ልጆች አፍርተዋል። ልጆቻቸው የማንነት ጥያቄ አለባቸው። የመጡበትን የእናት የአባቶቻቸውን አያቶቻቸውን ሀገር ማወቅ ይፈልጋሉ።

እንደሚታወቀው ደግሞ የሚያኮራ ታሪክና ባህል አለን። ውብ የሆነ ተፈጥሮ ያላት ሀገር አለቻቸው። ይህ እደመሆኑ መሰል ትስስር መፍጠር አስፈላጊ ነው። እነሱም መነሻቸውን ያውቃሉ። ኢትዮጵያ የሁሉም መነሻ ነች። የሰው ልጅ መገኛ ነች። የእናት የአባቶቼ የአያቶቼ ሀገር የሚለው ስሜት ደግሞ በጣም ከፍተኛ ነው። እንደ ሰው ልጅ ሁላችንም መነሻችንን ማወቅ እንፈልጋለን። ይህ ትልቅ ስሜት ነው። ይንን ለማወቅ ያስችላል።

ሁለተኛ መጥተው ባህልና ታሪካቸውን እንዲያውቁ እንዲሁም ለወገኖቻቸው መስጠት እንዲችሉ መቀራረብ እንዲችሉ መንገድ ለመፍጠር ነው። ስለዚህ የጥሪው ዓላማ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን መጥተው ሀገራቸውን እንዲያውቁ ነው። ይህንን በሶስት ፌዝ ከፍለነዋል። የመጀመሪያው ከብዝሃ ባህል መሠረት ጋር ይተዋወቁ ብለነዋል።፡

ምክንያቱም ይህ ወቅት ብዙ ፌስቲቫሎች ያሉበት እንዲሁም በተለያየ መልኩ ሀገራቸውን ባህላቸውን ለማወቅ የተመቸ አጋጣሚ የሚፈጠርበት ነው። ለዚህም የተለያየ ሁነቶች ተዘጋጅተዋል። ባህላቸውን ያውቃሉ። ይማራሉ። ወደተለያዩ የሀገራችን ክፍል ሔደውም ራሳቸው ለራሳቸው ዲስከቨር ያደርጋሉ።

ሁለተኛው ዙር ከታሪክ መሠረቶች ጋር ይታዋወቁ የሚል ነው። ይህ የዓድዋ ሰሞን የሚጀምር ነው። ከዓድዋ መጀመሩ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ወቅትና ሁኔታ ስለታሪካቸው ኢትዮጵያ ለዓለም በተለይ ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ያበረከተችው አስተዋፅኦ ውይይት የሚደረግበት ነው። ታሪካችንን ወደ ኋላ መለስ ብለን የምናይበት ወቅት በመሆኑ ከታሪካቸው ጋር እንዲተዋወቁ፤ ይህ እድል እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው።

በእነዚህ ዙር የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍሎች ተዘዋውረው የጉብኝቱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ በሶስተኛው ዙር ሲመጡ ደግሞ ረዘም ያለ ጊዜ ስላላቸው በሚገባ ባህሉንም ታሪኩንም እንዲያውቁ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ነው። እንደሚታወቀው በዚህ ወቅት እንደ ሀገር ከአረንጓዴ ዐሻራና እና ከበጎ አድራጎት ጋር ተያይዞ የተለያየ ኢንሺየቲቮች አሉን።

ይህ የእረፍት ወቅታቸውን እንደመሆኑም በእነዚህ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉና ይበልጥ የተሳሰሩ እንዲሆኑ ለማስቻል ታሳቦ የተጠራ ጥሪ ነው። ስለዚህ ሁሉም ሰው ይህን በመልካም ወስዶ በጣም በትልቅ ቁጥር ወደ ሀገር እየገባ ነው። ቁጥሩንም ወደፊት አንድ ላይ ደምረን የምናሳውቅ ይሆናል። ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ እኛም እየተቀብልን ነው።

ጥያቄ፡-በተጠናቀቀው በፈረንጆቹ ዓመት 2023 በተለይም ዓለም አቀፍ ቅርሶችን በማስመዝገብ ረገድ ከፍተኛ ሥራ የተሠራበት እንደሆነ በተለያየ መገናኛ ብዙሃን ሲገለፅ ነበር። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ተቋም የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቻችን ቁጥር እያሻቀበ መጥቷል። በዚህ ረገድ የተሠሩ ሥራዎች ምንድ ናቸው?

አምባሳደር ናሲሴ፡- አንድን ቅርስ አዘጋጅቶ ለዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ በጣም በብዙ ውጣ ወረዶች መሃል ያልፋል። ብዙ ሀገራት ለብዙ ነገር ይጠቀሙበታል። የመጀመሪያው የሀገራቸውን ገፅታ ለመገንባት ይጠቀሙበታል። ያላቸውን ለማውጣትና ለዓለም የሚያበረክቱትን ነገር ለሀገር ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላለው ለእሱ ይጠቀሙበታል።

ሁለተኛው የቱሪስት መዳረሻ ከማልማትና ከማስተዋወቅ አንፃር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ስለሆነ የቱሪስት መዳረሻዎቻቸውን ከማስፋት አንፃር ይጠቁሙበታል። እኛ እንደ ሀገር ብናስመዘግብ ከሞላ ጎደል ሙሉ ኢትዮጵያን ማስመዝገብ እንችላለን ብለን በድፍረት መናገር እንችላለን።

እኔ በግሌ ይህን መናገር እችላለሁ። ለምን ሌሎች እንደ ዓለም ቅርስ የሚያስመዘግባቸውን ጉዳዮች በቅርበት ስለምመለክት ማለት ነው። ስለዚህ የተለያዩ ጉዳዮችና ቦታዎችን እንደ ዓለም ቅርስ የሚያስመዘግቡት አንደኛው ምክንያት እንደ ቱሪስት መዳረሻ ለማልማትና ሰውን ወደ ሀገር ለመሳብ ነው።

እንደሚታወቀው ዩኔስኮ አንድን ቅርፅ ሲመዘግብ ከፍ ያለ ዓለም አቀፍ አሴት “አውትሳንዲንግ ዩኒቨርሳል ቫሊው” አለው ፤ ለዓለም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለው፤ ከሌሎቹ የተለየ ዋጋ አለው ብሎ ነው የሚመዘግበው። ይህ ትልቅ እውቅና ስለሆነ ቀደም ሲል እንዳልኩት የሀገር ገፅታን ይገነባል።

ሁለተኛ ደግሞ ዓለም አቀፍ እውቅና ከመስጠትና የቱሪስት ፍሰት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲጨምር ከማድረግ አንፃር የራሱ አስተዋጽኦ አለው። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የጥበቃና የእንክብካቤ ሥራ ነው። ይህ ሥራ ለቅርሶች ከፍ ያለ ይሆናል። ሀገራት በሚገባ ይንከባከባሉ ይጠብቃሉ። ይህን መሰል አስተዋጽኦ ስላለው ብዙ ሀገራት ከፍ አድርገው የሚያዩት በመሪ ደረጃም መጥተው እውቅናው የሚቀበሉት ነው።

ወደሀገራችን ስንመጣ አሁን የተመዘገቡ ቅርሶች ቅድም እንደጠቀስኩልህ ማስመዝገብና ማስተዋወቅ አለብን ብዬ የምልበት ምክንያት አንደኛ ከአርባ ዓመት በኋላ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለትና ሶስት ቅርስ ስናስመዘግብ። እንደሀገር ደግሞ ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ምንም ዓይነት ቅርስ አላስመዘገብንም።

ዶክሜንቶቻችንን እንልካለን በተለያዩ ምክንያቶች ዶክሜንቶቻችን አያልፉም። ብዙ ጊዜ ከዶክሜንት ዝግጅት ጥራት፣ ከማስረዳትና ሎቢ ከማድረግ ጉድለት ዶክሜንቶች አያልፉም። በዚህ ዓመት ተጠሪ ተቋማቶቻችን የቅርስ ባለሥልጣን፣ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም ሌሎችም አካላት በሠሩት ከፍተኛ ሥራ ሶስት የዓለም ቅርሶችን ለማስመዝገብ ዕድል አግኝተናል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው።

ይህ እንደሀገር እንድምታው ምንድነው ካልክ አንደኛ የሀገር ገጽታ ይገነባል። ሁለተኛ ፍሪ ፕሮሞሽን ነው። ኢትዮጵያ ያሏት ቅርሶች ሁሉም ቱሪስት መጥቶ ሊያያቸው የሚፈልጋቸው የሚያጓጓ ቅርሶች ናቸው። ስለዚህ ከዚያ አንጻር ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ስለሆነ ሁሉም መጥቶ ሊመለከታቸው ይፈልጋል።

ወደሀገር ቤት የቱሪስት ፍሰትን ከመጨመር አንጻር የራሱ አስተዋጽኦ አለው። ከቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ አንጻር የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው። እነዚህን ቅርሶች እንድንከባከብ እንድናለማ መንገድ ይከፍታል።

እንደ ሀገር እነዚህ በዓለም አቀፍ ቅርስ ሆነው የተመዘገቡ የዓለም ቅርሶችን ማልማትና ወደመዳረሻነት መቀየር የቤት ሥራችን ነው። ለምሳሌ የተለያዩ ቦታዎች በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል። የተወሰኑት የቱሪስት መዳረሻ ናቸው፤ የተወሰኑት የቱሪስት መዳረሻ አይደሉም።

ለዚህም እነጥያን ማንሳት ይቻላል። ሌሎችም ኦሞ፣ ሎሮባሺ እያልን ማንሳት እንችላለን። እነዚህን ወደ መዳረሻነት መቀየር ኃላፊነት አለብን፤ ከዚህ እውቅና አስፈላጊውን ጥቅም ለማግኘት። ስለዚህ የቤት ሥራ አለብን ሁሉም ሰው ያለውን ፋይዳ ተገንዝቦ እዚህ ላይ መረባረብ ይኖርበታል።

ጥያቄ – በቀጣይ ምናልባት በዚህ ረገድ የተያዙ ጊዜያዊ ሊስቶች ይወጣሉና የተያዙ ቅርሶች ካሉ?

አምባሳደር ናሲሴ፡– እንደሀገር የመጀመሪያው የቤት ሥራችን የተያዙ በዚህ ዓመት በተለይ በሚቀጥለው ዓመት ሩብ ዓመት ጊዜያዊ ሊስቶቻችንን መከለስ ለዚህም ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁመናል። ብሔራዊ ኮሚቴ ወደ ሥራ አስገብተን ያሉንን ጊዜያዊ ሊስት ውስጥ ያሉትን ለቅርስነት የታጩትን እንከልሳለን። ስንከልስ አንዱ የምናተኩርበት ነገር የወል የሆኑ፣ የጋራ የሆኑ ሀብቶቻችን ላይ ነው።

የኢትዮጵያውያን የጋራ መገለጫ የሆኑ ቅርሶች ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደሌሎች ቅርሶቻችንን ማስመዝገብ እንሄዳለን። ይሄን ባማከለ መልኩ ክለሳ የሚካሄድ ይሆናል። ከዚያ ደግሞ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ለቀጣይ አምስት፣ አስር ዓመታት ልታስመዘግባቸው የምታስባቸውን ሀብቶች ሁሉም ሰው እንዲያውቃቸው፣ ሁሉም ሰው እንዲረዳቸው፣ ሁሉም ሰው በተቻለ መጠን ለመመዝገባቸው ርብርብ እንዲያደርግ መንገድ ይከፍታል።

ምክንያቱም አንድ ቅርስ ሲመዘገብ በጣም ብዙ ሥራ ነው የሚጠይቀው። ዶክሜቱን የማዘጋጀት፣ የማጥራ፣ ከቋንቋው አቀራረብ ከመሳሰሉት ስታንዳርድ ከማስጠበቅ አኳያ አንዱ ሥራ ነው። ሁለተኛው በየጊዜው የሚጠየቁ ጥያቄዎችን መመለስ ዶክሜቱን አሜንድ የማድረግ ሥራ አለ።

ሶስተኛ ሥራ ደግሞ በዶክሜንቱ ላይ ያለው ነገር መሬት ላይ አለ ወይ ብሎ የሚያይ፣ የሚያጠራ ቡድን ይላካል። ይህን ቡድን አምጥቶ በደንብ አስረድቶ ያለውን ተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን ጉዳይ በሚገባ አሳይቶ መመለስ ይፈልጋል። ሥራው በዚህ አያበቃም በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የማስረዳት የማሳመን እንዲሁም ሎቢ የማድረግ ሥራ ደግሞ ይቀጥላል። እነዚህ ሥራዎች ሁሉ ተያይዘው ስላሉ ሥራዎቹ ላይ የብዙ ሰዎች ርብርብ ስለሚያስፈልግ ይፋ እንዳደረግን የተለያዩ አካላትን አሰባስበን ፑል አድርገን ይሄን ሥራ የምንጀምር ይሆናል።

/ይቀጥላል/

አዲስ ዘመን ጥር 3/2016

Recommended For You