ዲፕሎማሲ ተስፋ ያደረግናቸውን ነገዎች ማሳኪያ ትልቅ አቅም ነው!

እንደ ሀገር ከማኅበራዊ ማንነታችን የሚመነጨው የረጅም ዘመን የዲፕሎማሲ ጉዟችን ትናንት ሆነ ዛሬ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ ያለ ስፍራ አጎናጽፎናል ፤ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆነን ብሄራዊ ጥቅሞቻችን አስጠብቀን እንድንጓዝም ረድቶናል ።ዛሬ ላይ ለጀመርነው እና ተስፋ ሰጪ እየሆነ ለሚገኘው የለውጥ ጉዟችን ስኬት ትልቅ አቅም እየሆነንም ይገኛል ።

በመከባበር እና ሰጥቶ በመቀበል ላይ የተመሰረተው የሀገሪቱ የረጅም ዘመን የዲፕሎማሲ ታሪክና ትርክት ፤ ለሀገር እና ለሕዝብ ክብር የተገዛ ፤ ለሰብአዊነት እና ለሰብአዊ እሴቶች ቅድሚያ የሚሰጥ፤ በሀገር ሉአላዊነት እና በብሄራዊ ጥቅም ላይ መቼም እና በየትኛውም ሁኔታ የማይደራደር፤ እንደ ሀገር ካለን ማኅበራዊ ስሪታችን የተቀዳ ነው።

በዓለም ገናና ሆነን ካለፍንባቸው የደመቁ የታሪክ ምዕራፎቻችን ጀምሮ ፤ በብዙ ውጣ ውረዶች በተፈተንባቸው ዘመናት ፤ የዲፕሎማሲ መንገዳችን / መርሆዎቻችን ምንም ዓይነት መዛነፍ ሳያሳዩ ፤ በመከባበርና ሰጥቶ በመቀበል ላይ ተመስርተን ረጅም ዘመን መጓዝ እንድንችል ረድተውናል። ይህም እንደ ሀገር ከፍያለ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንድናገኝ አድርጎናል ።

በቀደመው ዘመን ፤ ለብሄራዊ ክብራችን ፣ ለሉአላዊነታችን እና ጥቅማችን ከፍ ያለ መስዋዕትነት በመክፈል ከማኅበራዊ ማንነታችን ለሚመነጩት የዲፕሎማሲ መርሆዎቻችን የቱን ያህል የተገዛን እንደሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተጨባጭ ማሳየት ችለናል።

በዚህም መላው ዓለም ስለ ማኅበራዊ ማንነታችን በተሻለ መንገድ እንዲረዳ ከማድረግ አልፈን፤ ለብዙዎች ፋና ወጊ በመሆን ደምቀን የምናበራበት ትርክት ባለቤት ሆነናል። በዚህ ደማቅ ታሪክም አንገታችንን ቀና አድርገን መሄድ የምንችልበትን የስነልቦና ከፍታ መጎናጸፍ ችለናል።

በትውልዶች ቅብብል በብዙ ተግዳሮቶች እና ፈተናዎች እየተናጠ ዘመናትን በደማቅ ቀለማት አሸብርቆ ዛሬ ላይ የደረሰው ሀገራዊ የዲፕሎማሲ ጉዟችን ፤ በተግዳሮቶች እና ፈተናዎች ወቅትም ሆነ ማግስት ሀገር እንደ ሀገር ጸንታ እንድትቆም ፤ከመቆምም አልፋ መራመድ እንድትችል ስትራቴጂክ አቅም በመሆን አገልግሏል ፤ ዛሬም እያገለገለ ነው።

ወቅት የሚፈጥራቸውም ሆኑ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከፍ ባሉ ማንነቶች እና ማንነቶቹ በፈጠሩላቸው አቅሞች ሜዳ ሞልተው ለያዥ ለገላጋይ አንመች ባሉባቸው ወቅቶች ሳይቀር ፤ ብሄራዊ ክብራችንን ፣ ሉአላዊነታችንን እና ጥቅማችንን አስጠብቀን ለመጓዝ የመረጥነው የዲፕሎማሲ መንገድ ከብዙ ኪሳራ ታድጎን አትራፊ አድርጎናል።

ከሕዝባችን ማኅበራዊ እሴቶች የሚቀዱት የዲፕሎማሲ መርሆዎቻችን ፤ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የሕዝባችን የዕለት ተዕለት ህይወት አካል የመሆናቸው እውነታ ፤ ዜጎች በተፈጠረው አጋጣሚ ሁሉ ለሀገራቸው ዲፕሎማት የሚሆኑበትን የተሻለ አጋጣሚ ፈጥሯል ፤ በየወቅቱ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን/ ፈተናዎችን አሸንፎ ለመሻገር ትልቅ ሕዝባዊ አቅም መፍጠር አስችሏል ።

ይህንን ሀገራዊ አቅም ፣ የደመቀ ትርክት ለጀመርነው የለውጥ ጉዞ ስኬት ጉልበት እንዲሆን ለማስቻል ፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ከፍ ባለ መነቃቃት ወደ ሥራ ተገብቷል ። መነቃቃቱ በዘርፉ ያሉትን የትናንት ተሞክሮዎችን በአግባቡ ማወቅ ፤ ዛሬን መገምገምና ነገን ብሩህ አድርጎ መጠበቅ የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ነው።

ይህ ዝግጁነት በተለይም ለውጡ እንደ አንድ ትልቅ የታሪክ ትርክት ይዞት ሊመጣው ከሚችለው ሀገራዊ ተጠቃሚነት አንጻር ፤ ሊያጋጥሙት የሚችሉትን የተለያዩ ተግዳሮቶች /ፈተናዎች በስኬት ለመሻገር ብርቱ አቅም ሆኖ ማገልገል የሚያስችል ነው።

እኛም ሆንን የቀደሙት ትውልዶች ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር መንፈስ ተፈጥራ ማየት የምንፈልጋትን የበለጸገች ሀገር እውን ለማድረግ ፤እንደ ሀገር ለጀመርነው በልማት ድህነትን ታሪክ የማድረግ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ስትራቴጅክ አቅም በመሆንም ያለው አስተዋጽኦ ከግምት ያለፈ ነው ።

ዲፕሎማሲ ከፈረጠመ ወታደራዊ አቅም ባልተናነሰ መጠን ትልቅ ዋጋ እያገኘ ባለበት በዚህ ዘመን ፤ በዘመናት ያካበትናቸውን የዲፕሎማሲ አቅሞች ፤ ዘመኑን በሚዋጅ የዲፕሎማሲ እውቀት ፣ ጥበብ እና ቴክኖሎጂ በመታገዝ፣ በዘርፉ ይዘነው የመጣነውን ዓለም አቀፍ ከፍታ በማስቀጠል ፤ ብሄራዊ ጥቅሞቻችንን ማስከበር የዚህ ትውልድ ዋነኛ ኃላፊነት ነው።

ትውልዱ የቀደሙት አባቶቹ በዲፕሎማቲክ ዘርፍ የነበራቸውን ዓለም አቀፍ ከፍታ በአግባቡ በማጤን ፤ ከከፍታው በስተጀርባ ያለ፤ ብሄራዊ እሴቶቻችንን በማጎልበት ፤ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚመጥን አዲስ የዲፕሎማሲ ትርክት መፍጠር ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ በሁሉም መልኩ ለሀገር ዲፕሎማት ሊሆን የሚያስችለውን ማንነት መገንባት ይጠበቅበታል!

አዲስ ዘመን ጥር 3/2016

Recommended For You