አካል ጉዳተኛ እንደ መሆኗ የሌሎች አካል ጉዳተኞችን ሕይወት ጠንቅቃ ታውቀዋለች። የእርሷ ሕይወት በብዙ ፈተና ያለፈ ቢሆንም ስለፈተናዎቹ ከመናገር ይልቅ ሰርቶ ማሳየትን ትመርጣለች፡፡ ለሌሎች ለመትረፍ እና የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣት አለበት በሚል ቅን ሃሳብ ብርቱ ጥረቷን ቀጥላበታለች – ሠዓሊ እና መምህርቷ ዓለም ጌታቸው፡፡ ሠዓሊዋ፣ ‹‹ዓለም ጋለሪ እና ቡና›› ብላ በከፈተችው የሥነ ጥበብ ማዕከል ታዳጊ ልጆችን እና ፍላጎቱ ላላቸው ሰዎች ሥዕል ታስተምርበታለች። ቡና፣ ሻይ … ለሚፈልጉትም ማዕከሉ ክፍት ነው፡፡
ማዕከሉ ከተመሰረተ 14 ዓመታትን አስቆጥሯል። እስካሁን ድረስ ከአራት ሺህ በላይ፣ ዕድሜያቸው አራት ዓመት የሞላቸውን ጨምሮ፣ በርካታ ታዳጊዎችን ሥዕል ማስተማር ችሏል፡፡ ወደ ጋለሪው ሲገባ የተሰቀሉ የተለያዩ መልዕክት ያላቸውን ሥዕሎች ቡና እና ሻይ እያሉ እንደልብ መመልከት ይቻላል፡፡ ወደ ጋላሪው ለሚመጡ ወጣቶችም ይሁን ተገልጋዮች ‹‹ምን ይምጣላችሁ? ሻይ ወይስ ቡና?›› የሚለውን ትዕዛዝ ከተቀበሉ በኋላ የማይቀር ጥያቄም አለ፡፡ እርሱም ‹‹መጽሐፍ ማንበብ? ወይስ ሥዕል መሳል?›› የሚል ነው፡፡ ሥዕል (ባይችሉ እንኳን መሞኮር) አልያም እያነበቡ ሻይ ቡና ከማለት ውጭ ተሰብስቦ ያለ ሥራ መቀመጥ በፍጹም የተከለከለ ነው፡፡ ለዚህም በየጠረጴዛዎቹ ላይ ሥዕል ለመሳል የሚያግዙ ቀሳቀሶች ተቀምጠዋል፡፡ ማንበብ ፍላጎታቸው ለሆኑት ደግሞ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የተለያዩ ይዘት ያላቸው መጻሕፍትም ዝግጁ ናቸው።
ትውልድን ለመቅጽ እና ለማፍራት እንዲሁም ለየትኛውም ነገር ራሳቸውን ተጠያቂ እንዲያደርጉ ኃላፊነትን የሚሰማው መልካም ትውልድ እንዲመጣ እርሷ እና ሌሎች መምህራኖች በሥራ ላይ ናቸው፡፡ ሀገር ያለችው ልጆች ላይ ነውና በሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ እና ስለ ሀገራቸው ገጽታ በሚገባ እንዲረዱ ለማድረግም የልጆች መጻሕፍትንት ትጽፋለች፡፡
አንዳንዶቹ ወደ ጋለሪው ሥዕል ለመግዛት ፈልገውም ይሁን ልጆቻውን ሥዕል ለማስተማር ሲመጡ ድንገት እርሷ ብቻ ሆና በዊልቸር ስትንቀሳቀስ ያዩት ‹‹ሰው የለም እንዴ?›› ብለው መጠየቃቸውን ያስታወሰችው ሠዓሊዋ እና መህርቷ ዓለም፤ ከቅያሜ ይልቅ ይህ አንዱ የአስተሳሰብ ችግር መሆኑን በማስገንዘብ አጋጣሚውን ተጠቅማ ታስተምርበታለች፡፡
እንደ ሠዓሊዋ ማብራሪያ፤ ዓለም ጋለሪ ከሥነ ጥበብ ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎችን ይሠራል። ወጣቶች ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ይልቅ መጥተው ሥዕል እንዲስሉ ያበረታታል፡፡ ያላቸውን ሰዓት አብቃቅተው መጻሕፍት ያነባሉ። ማዕከሉ የእውቀት መገኛ ቦታ በመሆኑ፣ ሰዎች መጥተው የአእምሮ ምግብ የሚያገኙበት ሥፍራ ለመሆን በቅቷል፡፡
ሌላው ነገር አካል ጉዳተኞች ጥሩ አስተሳሰብ ያለው ማሕበረሰብ ካልገጠማቸው ከአካላቸው ይልቅ አእምሯቸው እጅጉን ይጎዳል፡፡ ከባዱ ችግርም ሆነ ጉዳት ይህ ነውና።
ሠዓሊዋ ‹‹አብረን›› የተባለ ምግባረ ሠናይ ድርጅት መሥርታለች፡፡ ድርጅቱ አካል ጉዳተኞችን ለማሰልጠን፣ ተምረው የአንድ ሞያ ባለቤት ሆነው ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው። እስካሁን ድረስም ከ40 በላይ አካል ጉዳተኞችን አሰልጥሎ በማእከሉ እና በሌሎች ቦታዎች ለሥራ ማብቃቱን ታስረዳለች፡፡
በተደጋጋሚ አፅንኦት ሰጥታ እንደምትናገረው፣ ማዕከሉ በተለይ በተለይ አስተሳሰብ ላይ ይሠራል። የአስተሳሰብ ሕክምናም ያደርጋል፡፡ አካል ጉዳተኞች ላይ ያለውን የአስተሳሰብ ችግር ለመቅረፍ ወደ ተለያዩ ተቋማት በማቅናት፤ እንዲሁም የሻይ ሰዓትን ብቻ በመጠቀም አስተሳሰብ ላይ የበለጠ ለመሥራት እቅዷ እና ፍላጎቷ እንደሆነ ትናገራለች።
ዓለም የምትሠራቸው ሥራዎች አብዛኞቹ ከሥነ ጥበቡ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በቅርቡ ደግሞ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ 50 ተፅዕኖ ፈጣሪ አካል ጉዳተኞች የሚያቀርቡት ‹‹ነገን አብረን እንሳል›› የተሰኘ የሥዕል ዓውደ ርዕይ ለማዘጋጀት እርሷና ጓደኞቿ ሽር ጉድ እያሉ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ተፅእኖ ፈጣሪ አካል ጉዳተኞች መካከል አንጋፋ መምህራን፣ ጋዜጠኞች፣ የሕግ ባለሙዎች፣ ሠዓሊያን፣ የህክምና ባለሞያዎች፣ በመንግሥት ሥራ በኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ ኃላፊዎች እና ሌሎችም ተሳትፈውበታል። እነዚህ የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ያሉ አካል ጉዳተኞች ስራዎቻቸውንም ያቀርባሉ፡፡
50ዎቹ የሀገር ባለውለታዎች ብዙ ችግሮችን ተጋፍጠው ለዛሬ በቅተዋል፡፡ ‹‹አሁን በትንሹም ቢሆን ይሻላል፡፡›› በማለት ከአካል ጉዳተኞች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች በትንሹም ቢሆን ከትናንት ዛሬ እንደሚሻል ያመላከተችው ሠዓሊዋ፤ አገራቸውን ለረዥም ዓመታት ያለገሉ መሆናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት ለእነርሱ እውቅና መስጠት እና ማበረታታት እንደሚገባ በማመን ዓውደ ርዕዩን ለማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡
ሀገራችንን ጨምሮ ሕይወታችን በእጃችን ነው ያለው፡፡ ከችግራችን ይልቅ ያለን ነገር ብዙ ነው። ስለዚህ እነርሱን ነገሮች እናጉላቸው በሚል ሃስብ ሰዓሊ ከሆኑት ውጭ ያሉ አካል ጉዳተኞች ሃሳባቸው ተጠይቆ በሸራ እና በቀለም እንዲያሰፍሩ በማድረግ ከሠዓሊያኑ ውስን ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ በዕለቱም ማስተላለፍ የፈለጉት ሃሳብ ላይ ገለፃ እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡
ከዓውደ ርዕዩ በተጨማሪም የእነዚህ 50 ተፅዕኖ ፈጣሪ አካል ጉዳተኞች ግለ ታሪካቸው ተሰንዶ በመፅሐፍ መልክ በማዘጋጀት በችግር ውስጥ አልፈው ሀገራቸውን እንዴት እያገለገሉ እንደሆነ ለማሳየት እየተሠራ ነው፡፡ አሁን ላይ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ላለው ትውልድ ከማስተማር በሻገር፣ ብቁ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ግንዛቤ ለመስጠት ያስችላል፡፡ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ከራስ ጀምሮ ሲሠራ እና ራስን በማነሳሳት እንደሆነ የምትናገረው ሠዓሊዋ፣ እጅን ወደ ሌላ አካል መጠቆም እንደማይገባ ለማስተማር ያግዛል ባይ ናት።
ማዕከሉ የትውልድ ማዕከል ነው፡፡ በውስጡ ትምህርተ ቤት፣ ጋለሪ፣ የሀሳብ መድረክ የሚካሄድበት ዓለም ዓውደ ሃሳብ፣ የቤተ መጽሐፍት እና የበጎ አድራጎት አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ነው፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት እና ሁሉም ሰው ተሰባስቦ የሚገለገልበት ቦታ እንዲሆን ለማድረግ ግን የመንግሥት ድጋፍን ትሻለች፡፡
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም