ዝማኔ እንጂ ቅንጦት አይደለም

ኪነ ጥበብ ከጊዜው ጋር እየገሰገሰ መሔዱን ቀጥሏል። የዘመን ጥበብ ከቴክኖሎጂው ጋር እጅና ጓንት ሆነው ቅልጥ ያለ ፍቅር ውስጥ ናቸው ቢባል ስህተት አይደለም። ጥበብ በቴክኖሎጂ ባትወለድም ከጥበብ ውስጥ ያለ ኪነ ጥበብ ግን ከቴክኖሎጂ ጋር ከመተቃቀፍ አልቦዘነም። ድሮ ድሮማ ሁሉም ብርቅ፣ ድንቅ ነበር። ድሮ ድሮማ ሙዚቃ ለማድመጥ መቻል ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል የራቁትን ወዳጅ ዘመድ ድምፅ እንደመስማት የሚናፍቅ ነበር፡፡ ፊልሞችን ከቴሌቪዥን መስኮት ለማየት መቻል ደግሞ ከህዋ ላይ በአካል ተገኝቶ ቬነስን እንደመመልከት ያለ መታደል ነበር፡፡ “ነው” አላልንም፤ ነው ያልናቸው እልፍ ጉዳዮች “ነበር” እየሆኑ መጥተው በነበር ቀርተዋል። ምስጋና ለቴክኖሎጂው ይግባውና ዛሬ ላይ የማይቻል የለም የምንልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ዛሬ ላይ ሙዚቃ ለማድመጥ የፈለገ እንደ ድሮው ዘመን ዝሆንና የዝሆን ልጅ የመሰሉትን ግዙፍ ራዲዮንና የካሴት ክር ፍለጋ መውጣት/መውረድ የለም። ፊልምን ለመመልከት ሽቶ የሰማይ ስባሪ የሚያህለውን ቴሌቪዥንና እንደ ድንጋይ አለት የገዘፈ ማጫወቻ አያስፈልገውም፡፡ በዘመኑ እነዚህ ሁሉ እንደ ብርቅና ድንቅ ቴክኖሎጂ ከታዩ በኋላ ቀጣዩ ጥያቄ የነበረውን የድምፅ እንዲሁም ጥቁርና ነጭ ምስልን አልፎ ዛሬ የደረስንበትን ለመድረስ በሀገራችን ረዥም ጊዜን የፈጀ ነበር፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ስለ ኪነጥበብ መውደቅና መነሳት፤ መሔድና መምጣት፤ ስለ ማደግና መቀጨጭ፤ እንዲሁም፣ ምንስ በልቶ ምን ይጠጣ በማለት፤ እያነሳን የማናፈርጣቸው ሀሳቦች የሉም። ስለ ሀገራችን ሙዚቃና ፊልሞች እድገት ካደጉ ሀገራት አኳያ እያነጻጸርን ስናወራ፤ ፊት ለፊት ለዓይን ቅርብ ስለሆኑ ጉዳዮች እንጂ ለእድገቱ ከጎደሉን ነገሮች አንዱ ዓለማት የደረሱበት ቴክኖሎጂ እንደሆነ ግን እምብዛም አናነሳውም፡፡ ስለ እንጀራው እንጂ እንጀራውን ስለምንጋግርበት ምጣድ ግድ ካለን ነገ ላይ እንጀራ ስለመብላታችን እንጃለቱ። የትኛዎቹም ሚዲያዎች (ከግዙፍ የቴሌቪዥን መስኮት እስከ ትስስር ገጾች) በቴክኖሎጂ የተወለዱ የቴክኖሎጂ የአብራክ ክፋይ ናቸው። ቴክኖሎጂ ስንል በኪነ ጥበብ ውስጥ ሦስት አንደምታዎች አሉት። የመጀመሪያው የትኛውም የኪነ ጥበብ ሥራዎች ኢንተርኔትን በመጠቀም ተደራሽነታቸውን ለማስፋት የሚያገለግሉ እንደ ማኅበራዊ ሚዲያና መተግበሪያዎች ያሉ ናቸው። ሁለተኛውና ግዙፉ ደግሞ የሳተላይት ስርጭት የማስተላለፊያ መንገድ ነው። ሦስተኛው ቴክኖሎጂ ከሁለቱ የሚለይ ሲሆን የድምፅና የምስል ጥራታቸው ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን የምንጠቀምባቸው ቴክኖሎጂዎች መሆናቸው ነው።

ኪነ ጥበብ ያለ ቴክኖሎጂ፤ ዓሣ ያለ ውሃ እንደ ማለት አይደለም፡፡ ያለ ቴክኖሎጂ መሥራት ይቻላል፤ ያለ ቴክኖሎጂ ማደግ ግን የማይወጡት ዳገት ነው። ስለ ቴክኖሎጂው ስናነሳ ከእጅ ወደ አፍ ለመሰሉ እዚሁ በዚሁ ለሆኑ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎቻችን ሳይሆን ኪነ ጥበብን በመጠቀም በራሱ በኪነ ጥበብ፤ እንዲሁም በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን የተጫኑብንን ቀንበሮች ሰባብረን ወደ ዓለም አቀፉ አደባባይ መውጣት እንድንችል ነው፡፡ የነገሩ ወሳኝነት የገባቸው ሀገራት የኪነ ጥበብ ዘርፎቻቸውን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ጥፍጥናውን በማጣጣም ላይ ናቸው። ትምህርት ቤቶችን በመክፈትና ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችንም በተመቻቸ ሁኔታ በማስገባት ባገኙባቸው ቀዳዳዎች ሁሉ ወደ ዓለም ገበያ ይተማሉ። ወደ እኛ ስንመጣ ግን መልኩ የቅንጦት ነው የሚመስለው። ለዚህ ወሳኝ የሆኑ እንደ ካሜራና መሰል ያሉ ለምስልና ድምጽ ቅጂ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች እንኳን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የሚጣልባቸው ቀረጥ የዱላ ያህል የሚፈነክት ነው። ኪነ ጥበብ የሀገርን ገጽታ ከመገንባትም ባሻገር ኢኮኖሚውን ተሸክሞ የመሮጥ አቅም እንዳለው ዘንግተን ይሁን ችላ ብለን፤ ከመንግሥት ጀምሮ ትኩረትን በመነፈጉ፤ “አላደገም” ከሚል ትችት በስተቀር ምን ይሆን የሚያስፈልገው የሚለውን መጋረጃ ገልጠን ጓዳውን አንመለከትም። አሁን አሁን በኪነ ጥበቡ ምን ልሥራ ከማለት ይልቅ በምን ልሥራ ሆኗል ትልቁ ጉዳይ። እንደ ግለሰቦች ብቻም ሳይሆን እንደ ሀገርም የቴክኖሎጂውን ጉያ የሚኮረኩር ነው። ገና ለገና ኪነ ጥበብ “መዝናኛ ነው” ብለን እንደ ቅንጦት ከተመለከትነው ቅንጦት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ ካወቅንበትስ ቅንጦት አይደለም። ከቴክኖሎጂው ረገድ ብቻም ሳይሆን በሁሉም ነገር ኪነ ጥበብ በሀገራችን፤ የጀርባ አጥንት ተደርገው ከሚቆጠሩት እንደ አንዱ ዘርፍ ቢታይ፤ ካሉን የታሪክ የብሶች አንጻር የኢትዮጵያን ምሰሶ የምናቆምበትን ኃይል ለማመንጨት እንችል ነበር፡፡ ሆሊውድና ቦሊውድን እንኳን ብንመለከት በጊዜው በብዙዎች ጥረት በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ ተደርገው ዛሬ ላይ የሀገራቸው ዋልታና ማገር ለመሆን የበቁ ናቸው፡፡

ኪነ ጥበብ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ቴክኖሎጂው ገብቷል፤ እንደኛም በመግባት ላይ ነው፡፡ ታዲያ ጥበብ እያበበች ወይንስ እየረገፈች ነው? አንዳንድ ፍካት፤ አንዳንድ ድርቀት፤ በድምሩ ሞትና ሕይወትን ታቅፋለች። የቴክኖሎጂው ፍሬ በሀገራችን በጥቂቱ እየተበተነ ብዙ መልካም ነገሮችን መፍጠሩ እንዳለ ሆኖ በሌላ በኩል ግን ቲያትር ቤቱን አስቦዝኖታል፡፡ ዓለም በቴክኖሎጂ ሰተት ብላ ወደ ቤታችን ገባችና ከውጭ ያሉ ጉዳዮችን ፍለጋ ለመውጣት አስንፋናለች፡፡ በአንድ የእጅ ስልክ ዓለምን ከጫፍ እስከጫፍ እናዳርሳለን። ገዝተን ከቤታችን ባስገባነው ቴሌቪዥን በሀገርና በውጭ የተሠሩ ልዩ ልዩ የመዝናኛ ዘርፎችን በአንዲት ሪሞት ብቻ ምርጫና ፍላጎታችንን እንዘውራለን፡፡ እናም የቲያትር ተመልካቹም ከዚሁ ተሟሙቆ ወደ ቲያትር ቤት መሔዱን ዘንግቶታል፡፡ ዛሬ ቴክኖሎጂው በበዛበት ዘመን ጥበብ ፊቷ ገርጥቶ፤ አጥንቷ ገጦ መለመሏን ቀርታለች በማለት የድሮው ዘመን የተሻለ ስለመሆኑ የሚናገሩ ብዙ ናቸው። በርግጥ “ውሸት ነው” ለማለት ባያስደፍርም፣ ቴክኖሎጂው ያደበዘዘው ኪነ ጥበብን ሳይሆን ኪናዊ ማንነትን ነው። ከቴክኖሎጂ በፊት ኪነ ጥበብ በጥበብ መሬት ላይ ነበረች፤ ማለትም አፍቃሪዎቿን የምታገኘው በገጽ ለገጽ ነበር። በጥቂት ነገር ለጥቂቶች ብቻ ተመጥኖ ይቀርባል። ከብዛቱ ጥራቱ እንልም የለ?፤ የሚቀርቡትም እኛኑ የመሰሉ ጉዳዮች ናቸው። አሁን ግን በሁለት ነገሮች አሉታዊ መልክ ተጎናጽፏል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ፣ በቴክኖሎጂው አማካኝነት ተደራሽ እየሆኑ ያሉት የኪነ ጥበብ ሥራዎች ተደራሲያኑን ያማከለ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት አስፈላጊ የሆኑ የእድሜም ሆነ ሌሎች ገደቦችን ተግባራዊ ለማድረግ አይቻልም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አድማጭ ተመልካቹ፤ እንዲሁም፣ አንባቢያኑ ዓለማቀፋዊ እየሆኑ ሲመጡ፤ ለሁሉም የሚመጥንና አካታች የሆኑ ይዘቶችን ለመፈለግ ስንዳክር ከታች ያሉ ብዙ ነገሮችን አንመለከታቸውም፤ ወይንም፣ ጥቃቅን እየመሰሉን እናልፋቸዋለን፡፡ በሁሉም ዓይንና ጆሮ ለመግባት ስንል ከዚህም ከዚያም ስንቃርም ደግሞ ቀደም ሲል የነበረውን እንበርዘውና አጠገባችን ላለው ማኅበረሰብ ወይኑን ሆምጣጤ እናደርግበታለን፡፡ ለአብነት ያህል የሀገራችንን ሙዚቃ ድሮና ዘንድሮ ብንል፤ ሙዚቃና ሙዚቀኛ በየአይነቱ እየፈላ በተራቀቀ የቴክኖሎጂ ቅንብሮች የተንበሸበሸበትን ዘመን፤ አብዛኛዎቻችን ግን አጣጥለን ሙዚቃማ ድሮ ቀረ በማለት፤ ከአድማጩ ሙዚቀኛው በበዛበት በዚህ ጊዜም፤ ሙዚቃ ሞልቶ ሙዚቃ ጠፋ እንላለን፡፡ የምንለውም እንደ ድሮው በእኛ የማንነት ልክ ተሰፍሮ ባለመሠራቱ ነው። ከማኅበራዊ ሚዲያዎች አንስቶ እስከ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ያሉት ከየዓለም ዳርቻው በገፍ ከሚለቁብን የራሳቸው ማንነት አንጻር፤ ከማየትም አልፎ የኛም ጭምር አድርገን ስለተቀበልናቸው ነው፡፡ በቴክኖሎጂው ወደ አንድ መንደርነት እየተቀየረች ባለችው ዓለም ውስጥ ጥያቄው “የማን መዝሙር ይዘመር?″ የሚል ሆኗል። ብዙ የያዝን እኛ በሁሉ ጠንክረን መቆም ካልቻልን፤ ጥቂት ይዘው በቴክኖሎጂው ኃይል በየጆሮዎቻችን በሚጮሁት መዋጣችን አይቀርም። ዓለም አንድ ሆና ለቡና ለመጠራራት በደረሰችበት በዚህ ዘመን፤ የኛ የሆኑት የጥበብ አፍቃሪያን እንኳን በቴክኖሎጂ የበለጸጉ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በሚፈልጉት ልክ ከኛ ማግኘት ካልቻሉ፤ ፊታቸውን ወደ ውጭ በማዞር ሌላኛው ፈተና ይጋረጥበታል።

መሰላሉን ከረገጥን አይቀር በዚሁ ተንደርድረን ወደ ሌላኛው ደረጃ እንሻገር። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂ አንጻር ገና በአፍላነት እድሜ ላይ እንደመሆኗ በዚያ ዘመን ከማንም በላይ የነበራት እምቅ የኪነ ጥበብ ሀብት በዓለም ተወዳዳሪ እንዳይሆን አግዶታል። እየሞተ ያለ የመሰለንም ብዙዎች ጥቂት ይዘው ወደ ፊት ሲገሰግሱ፤ ብዙ የያዝን እኛ የቅንጦት እየመሰለን ባለንበት በመቆማችን ነው። ኪነ ጥበብን በቴክኖሎጂ ስንቃኛው ሀሳቡ ለሁሉም የኪነ ጥበብ ዘርፎች የሚሆን ቢሆንም በዋናነት ግን በፊልምና ሙዚቃዎቻችን ዙሪያ የሚያንዣብብ ነው የሚሆነው፡፡

ያሉንን እምቅ የኪነ ጥበብ ሀብቶቻችንን በቴክኖሎጂው ደግፈን ወደ ዓለም መድረክ ካወጣናቸው ባሕል፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እሴቶቻችን ከፍ በማድረግ ዓለም ፊቷን ወደኛ እንድታዞር ብቻም ሳይሆን ዓለምን መዘወር እንችላለን፡፡ ከመሳጭነቱ የተነሳ የሰው ልጆችን አዕምሮና ሥነልቦና በቀላሉ የመግዛትና የመቆጣጠር ኃይል አለው፡፡ ከኪነ ጥበብ አንዲቷን ሰበዝ መዘን በፊልሙ ዘርፍ ብንመለከት፤ ለዚህ ማሳያ የሚሆን እንደም እንኳን በአሜሪካ የለም፡፡

የአሜሪካ ኃያልነት የመጣው መች በሥራዋ ብቻ ሆነና፤ ለዚህ መብቃቷ ባላት ኢኮኖሚና ደረቅ ፖለቲካም ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ የፊልም ኢንዱስትሪው የጀርባ አጥንቷ ነው፡፡ እሷም ብትሆን “እድሜ ለፊልሞቼ” ትበል እንጂ። ልታደርጋቸው የምትሻቸውን ነገሮች አስቀድማ ለዓለም የምትናገረው በፊልሞቿ ነው፡፡ ፊልሞቿ ሁሉ ያላትን የቴክኖሎጂ ጥበብ፣ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አቅሟን በፊልሞቿ በኩል በማሳየት ዓለምን ጸጥ እረጭ ለማድረግ የምትጠቀምበት ማስፈራሪያዋም ጭምር ነው፡፡ ብዙ ጉዳዮቿም ምናባዊ ናቸው፤ ገና ለዛሬ ሀምሳና ስድሳ ዓመት ያላትን ምኞት ልክ ዛሬ ላይ የደረሰችበት ያህል አድርጎ ገጽታዋን በመገንባት እንደ ቆንጆ ኮረዳ ዓለምን ሁሉ ታማልልበታለች። አንዳንዴም፤ እሷ ሚያው! ብትል ፊልሞቿ ግን እንደ አንበሳ ስታጓራ ያለውን የሚያንቀጠቅጥ ድምፅ ከተቆጣ ፊቷ ጋር አድርገው እያሳዩ ብራቅ መስላ እንድትፈራ በማድረግ፤ የጌቶቹ ጌታ ስለመሆኗ እየነገሩ ያሳምኑናል። ዓለም በማየት የተሞላች ናትና ገጽታ ግንባታ ለሀገር ወሳኙ ነገር ነው፡፡ ኪናዊ የሆነ ፕሮፖጋንዳ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ እንገነዘብበታለን፡፡

የፊልሙ ዘርፍ ብዙ ነገሮችን የተነፈገ ቢሆንም ባለቤት አልባ ሆኖ መሰንበቱ ደግሞ ሌላ እራስ ምታት ነው። ሌላው ቀርቶ የእይታ ጊዜያቸውን ጨርሰው ከሲኒማ ሲወርዱም ቀጣይ መዳረሻቸው ከፊልም ቤቶች የዘለለ አልነበረም፡፡ ከእኛ ለእኛ ብቻ ሆኖ በቂ ገንዘብና እውቅና የሚያስገኙም አልነበሩም። በዓለም ላይ የተለያዩ የፊልምና መሰል ኢንዱስትሪዎች ገቢያቸው ከሲኒማዎቻቸው ብቻ ሳይሆን በዋናነት ለዓለም አቀፉ ተመልካቾቻቸው ከሚያደርሱባቸው ከእነዚሁ የቴክኖሎጂ መንደሮቻቸው ነው። አሁን አሁን ዘግየት ብሎም ቢሆን ከወደ እኛም የተሻሉ ነገሮችን ለማየት እየቻልን ነው፡፡ በጥቂቱም ቢሆን የሀገራችንን ኪነ ጥበብ ለማስተዋወቅ የእድል በር ከከፈቱልን የሚዲያው ቴክኖሎጂዎች መሐከል የዩቱብን ውለታ አንዘነጋውም። ቅሉ የጥበብ ሥራው ባለቤቶች የሚንቀሳቀሱበት በተናጠል ቢሆንም፡፡

በፊልሙ ዘርፍ በተናጠል እየተደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች ውጤት በድምሩ አሁን ደግሞ ሌላ የተሻለና የዓለም አቀፉን በር ለኢትዮጵያ ፊልሞች የሚከፍተውን እድል አስገኝቷል፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በውጭ ሀገራት የሚገኙ፤ በፊልም ኢንዱስትሪው የሚሠሩ ድርጅቶች ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ በማዞር ላይ ናቸው፡፡ ሸሚዛቸውን እየጠቀለሉ እጃቸውን ለማስገባት መዳዳታቸውም፤ የኢትዮጵያ ፊልሞች ተወዳጅ እየሆኑ ከመምጣታቸውም ባሻገር ያለንን ሀብት መገንዘባቸውን የሚያሳይ ነው። ከእነዚህም አንዱ ከሁለት ዓመታት በፊት ድርጅቱን ከፍቶ መሥራት የጀመረው የፈረንሳዩ ካናል ፕላስ አንዱ ነው፡፡ ከሀገራችን የተመራረጡትን፣ የኛ ብቻ የሆኑ ፊልሞችን የዓለም አቀፍና ሰፊ የስርጭት ሽፋን ባለቤት በሆነው በዲኤስቲቪ ያሳያል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ፈቃድ አግኝቶ በዋናነት እየሠራ ያለው የፊልም ተቋም ካናል ፕላስ ይሁን እንጂ፤ በኢትዮጵያ ፊልሞች ፍላጎት ያደረባቸው በርካታ የውጭ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲዩሰሮች ማኅበር ጎራ ማለታቸው አልቀረም።

በሙዚቃው ስንመለከት ደግሞ ከአድማጭ ተመልካቹ ይልቅ ለሙዚቀኞቹ ገዘፍ ያለ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ልዩ ልዩ መተግበሪያዎች ተፈጥረዋል። ሀገር በቀል ሆነው ዛሬ ላይ ሙዚቃውን በባለቤትነት ከመምራትም፤ ነገ ላይ ከፍ ወዳለ ኢንዱስትሪ የማደግ ተስፋንም የሰነቁ ናቸው፡፡ በአሁን ሰዓት በሀገራችን እየሠሩ ካሉና የዚህ ዓይነቱ መተግበሪያ ባለቤት ከሆኑት፤ የሰዋሰው መልቲሚዲያ በዋናነት ተጠቃሽ ነው። በእነዚህ ሁለት ዓመታት በተለይም ከአንድ ዓመት ወዲህ ከበርካታ ሙዚቀኞች ጋር የስምምነት ውል በመፈጸም አጋሩ አድርጓቸዋል። ስምምነት የፈጸሙ እነዚህ ሙዚቀኞችም አዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን የሚያስረክቡት መተግበሪያውን ለሚያስተዳድረው ተቋም ብቻ ይሆናል። ተቋሙ ለሙዚቀኞቹ ክፍያውን የሚፈጽመው፤ አስቀድሞ ሥራውን በመግዛት፣ አሊያም በሥራው ተወዳጅነትና በሚያስገኘው የገቢ መጠን ተሰልቶ እንደስምምነታቸው ሊሆን ይችላል። ዓለምን ለመድረስ የሚችሉ እንዲህ አይነቶቹም ቴክኖሎጂዎች ግሩም ናቸው፡፡ በብዙ የድኅነት ችንካር ተቸንክረን በቴክኖሎጂ መበልጸግ ስላለበት የኪነ ጥበብ ዘርፍ ማውራት ቅንጦት አይደለም፤ ረሃባችንን የምናስታግስበት መድኃኒት እንጂ። ያውም ብዙዎች ለመሻማት የሚሯሯጡለት የታሪክ ሀብት ይዘንማ እንዴትስ ስለቅንጦት መስሎ ይሰማን ∙ ∙ ∙ ቅንጦት አይደለም፤ የዘመን ጥበብን አዘምኖ ከዘመኑ ዓለም ጋር ስለመሔድ ነው፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You