የዲፕሎማሲ ሳምንትን አስመልክቶ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ ሙሉቃል
አዲሰ ዘመን፦ የዲፕሎማሲ ሳምንትን የማክበር ዓላማና አስፈላጊነቱን ቢገልጹልን?
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ፦ አሁን የታቀደው የዲፕሎማሲ ሳምንት ዝግጅት ዋናው ዓላማ በሦስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። አንደኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደተቋም ከተደራጀ ጀምሮ 116 ዓመት ሆኖታል። ስለዚህ ያለፉት ዓመታት የዲፕሎማሲ ጉዟችን በየዘመኑ ያሳረፉት ዐሻራ፤ ያሉት ወረቶች እና የምንማራቸውን ትምህርቶች በማየት ያንን የዲፕሎማሲ ጉዞ የሚዳስስ ይሆናል።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አሁናዊ ሁኔታችን በዲፕሎማሲ መስክ ምን ይመስላል? ምን ዕድሎች አሉ? ምን ፈተናዎችስ አሉ? ብሔራዊ ጥቅማችንን አስከብረን ለመሻገር ምን መደረግ አለበት? የሚለውን ለማየት በእጅጉ ይጠቅማል።
ሦስተኛው ደግሞ የመጭው ዘመን ዲፕሎማሲን ያማተረ የዲፕሎማሲ ሳምንት ዝግጅት ነው። ታሪክንም፣ አሁናዊ ሁኔታንም፣ የመጪው ዘመንም፤ ሦስቱም ጉዳዮች በአንድ ላይ በማስተሳሰር ይህንን የዲፕሎማሲ ሳምንት በኤግዚቢሽን፣ በፓናል እና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ብናከብረው ለመጪው ጊዜ የተሻለ ሀገራዊ ንቅናቄ መፍጠር ይቻላል በሚል ነው ዲፕሎማሲያችን የሚለው ዝግጅት እያደርግን ያለነው፡፡
ሁለተኛ ከዛሬ 116 ዓመት በፊት ጥቅምት 4 ቀን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ ተቋም የተደራጀው፤ ከዚያም በፊት በልዩ ልዩ መልክ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አልነበረም ማለት አይደለም። ቀደምት የሆኑ ግንኙነቶች ሃይማኖታዊ መልክ ያላቸው፤ ኢኮኖሚያዊ መልክ ያላቸው፤ ባህላዊ እና የፀጥታ ገጽታ ያላቸው፤ ኢኮኖሚያዊ፣ በንግድ፣ በልዩ ልዩ መልክ የሚታዩ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያሉትን ቁም ነገሮች መዳሰስ፤ በደረስንበት ልክ ለዚህ ትውልድ በእጅጉ ይጠቅማል፤ እንደወረትም ይወሰዳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ አንድ የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሆኖ ከተቋቋመ ጀምሮ ያለው ተቋማዊ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? የሚለው ተያይዞ ሲወሰድ ትልቅ ትርጉም አለው። ልክ ከሁለት ሳምንት በፊት ጥቅምት 4/2016 ዓ/ም የመከላከያ ሚኒስቴር በተመሳሳይ ጊዜ የ116 ዓመት ምሥረታውን አክብሮ ለመጪው ዘመን ተልዕኮ ዝግጅት እንዳደረገ ሁሉ የውጭ ጉዳይ የዲፕሎማሲያችን እቅድ እና መነሻም በዚህ ዙሪያ ያጠነጠነ ነው ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ቀጣይነቱስ ምን ይመስላል?
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፦ በእኛ በኩል የምናስበው ይኸ የዲፕሎማሲ ሳምንት ዘንድሮ በእነዚህ በሦስት አውዶች ላይ አተኩሮ የመጀመሪያው ዝግጅት ይሆናል። በየዓመቱ የዲፕሎማሲ ሳምንት እንደዚህ ሰፋ ባለ ዝግጅት ባይሆንም እየታሰበና ዓመታዊ ተልዕኮዎችን ቆጥሮ እያስቀመጠ ሁሉም ዜጋ በዲፕሎማሲ ተሳትፎ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ የሚያስችል አጀንዳ አድርጎ ለመቀጠል እንሠራበታለን።
በየዓመቱ በጥቅምት ወር ዓመታዊውና ያለፈው ሥራ ሲገመገም፤ ለመጪው ሥራ ዕቅድ ሲዘጋጅ ይኸንን ያሰበ ቢሆን ሥራውን የበለጠ ያጠናክረዋል፤ የሕዝብ አጀንዳ ያደርገዋል የሚል እምነት ነው ያለን፤ እናም ይቀጥላል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የለውጡን ማዕቀፍ ተከትሎ በውጭ ጉዳይ፣ በውጭ ግንኙነታችንም እንደዚሁ በግልጽ የተቀመጡ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉ። የዲፕሎማሲው አንጓዎች ዋና ዋና የትኩረት መስኮችም፦አንደኛ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮረ፤ በሁለተኛ ደረጃ፣ በአጠቃላይ ፖለቲካ የባለብዙ ወገን፣ የሁለትዮሽ ወገን ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ማዕቀፍ ላይ ያተኮረ፤ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የዜጋ ዲፕሎማሲን እንደአንድ ትልቅ ማዕቀፍ አድርጎ የያዘ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ያሉት፡፡
ሁለተኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ማጠንጠኛው በመጀመሪያ ደረጃ ከሀገራዊ ፍላጎቶች፣ ከሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ይነሳና ውጭ ጉዳይ ወይም የውጭ ግንኙነት ሲባል ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ ነው፤ ሉኣላዊነትን ማስከበር ነው። በሁሉም መስኮች ጥቅማችንን የማረጋገጥ ጉዳይ ስለሆነ ከሀገራዊና ከውስጣዊ ሁኔታ ይነሳል ማለት ነው። ከዚህ ተነስቶ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ለጎረቤት ሀገራት ይሆናል። ጎረቤት ሀገራት ጋር የሚሰጠው ትኩረት እና ሚዛን እንዳለ ሆኖ ደግሞ ወደ አፍሪካ አህጉር ይሻገራል፤ ከዚያ ወደዓለም አደባባይ፡፡
በባለብዙ ወገን (Multilateral) የሚባለውም፣ በሁለትዮሽ ግንኙነትም እየሰፋ የሚሄድ የዲፕሎማሲ የግንኙነት ማዕቀፍ ነው ያለው ማለት ነው። ቀደም ካሉት ዓመታት ሥርዓቶች የነበሩ አዎንታዊ ልምዶችን መነሻ በማድረግ በለውጡ ማዕቀፍ ልዩ ልዩ የለውጥ ፓኬጆች ሲዘጋጁ የውጭ ግንኙነታችን የቱ ላይ የበለጠ ቢያተኩር? ካለፈው የትኛውን ቢያሻሻል? ለመጭው የትኛውን ቢያጠናክርና ቢያጠብቅ ይሻላል? የሚል መነሻ ተወስዶ ነው የተዘጋጀው፡፡ በእነዚህ ማጠንጠኛዎች ጎረቤት ላይ አተኩሮ፤ ወደአህጉር ዘል እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ተደማጭነት፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና በዓለም ውድድር ጥቅማችንን ባስከበረ ሁኔታ እውን እንዲሆን የሚያደርግ ነው ማለት ነው።
አዲስ ዘመን ፦ከተገኙ ውጤቶች፣ ዋና ዋና የሚባሉት ምንድን ናቸው ?
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፦ በቅድሚያ በእነዚህ ዓመታት ያለው ጉዞ፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፤ የተገኘው ውጤት እና ለመጪው የምንማረው ምንድን ነው? የሚለውን ብናየው የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
እንግዲህ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ በየዘመኑ ብዙ ፈተናዎች እያጋጠሙ ያንን በየዘመኑ መሪዎች፣ በየዘመኑ ባለድርሻ አካላት በሕዝቡ ዋና አቅም ያንን እየተሻገረች አገራችን ብዙ አሻራዎችን አስቀምጣ እዚህ ደርሳለች። ቀደም ብለን በቅኝ ግዛት ዘመን ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የጥቁር ሕዝብ ተወካይ ሆና በ”ሊግ ኦፍ ኔሽን” የታደመችበትንና የተጫወተችውን ታሪካዊ ሚና ስንመለከት፤ ከእርሱም ጋር ተያይዞ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን ስናይ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በሁለትዮሽ ግንኙነት ለራሷ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ሕዝቦችም የተጫወተችውን ሚና በደንብ አድርጎ መመልከት ያሻል ማለት ነው።
ያጋጠሙ ፈተናዎች ምን ያህል ፈታኝ እንደነበሩና በየዘመኑ ዐሻራዎች እያሳረፍን የዘለቅንበት የ116 ዓመታት ጉዞ አለ። በእነዚህ የጉዞ ሂደቶች ውስጥ ደግሞ በዚህ በለውጡ ዘመን በተለይ የሦስቱን ዓመታት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ስንመለከተው ምናልባት በጣም የከፋና ፈርጀብዙ የሆነ ጫና በኢትዮጵያ ላይ ያረፈበት፤ ያንን ለመሻገር ኢትዮጵያውያን፣ መንግሥት እና ወዳጆቿ ከፍተኛ ርብርብና ተጋድሎ ያደረጉበት ዘመን ነው። በየዘመኑ ለነበሩ ብዙ ፈተናዎች እና ያንን ለመሻገር ለተሠሩ ጥበቦች በየራሳቸው ሚዛን እውቅናና አክብሮት መስጠት በእጅጉ ያስፈልጋል። ያለፉት ጥቂት ዓመታት ሂደትን ስንመለከተው ደግሞ እንዲያው ትውልድ እንዲማርበት ዘርዘር አድርጎ በእንዲህ ዓይነት የጥያቄና መልስ ጊዜ ብቻ ሊዳሰስ የማይችል ጥልቅ የሆኑ ገጠመኞች አሉት።
ለዚህ ውይይት እንዲሆን እንዲያው ለማሳያ አንዳንድ ጉዳዮችን እንናንሳ፣ ለውጡ የተለያዩ የሪፎርም አጀንዳዎችን አውጆ ወደሥራ ሲገባ የውጭ ጉዳይ የግንኙነት ማዕቀፎቹን አሻሽሎ በዜጋ ዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካው እና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ሲቀጥል በፊት ከነበረው ተሻጋሪ የሆኑ ጉዳዮች እንደዚሁም ደግሞ ለውጡ ራሱ ያመጣቸው የለውጥ አጀንዳዎች በራሱ የዲፕሎማሲውን ሁኔታ ወደልዩ ልዩ ፈተናዎች እና እድሎች እንዲገባ አድርጎታል። ለምሣሌ፥ የህዳሴ ግድብን ብንመለከተው ከለውጡ በፊት ዓመታትን ያስቆጠረና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር እየተረባረበ እያሸጋገረው የነበረ ፕሮጀክት ነው። የለውጡ ዘመንም ይኸንን በመረከብና ያሉበትን ማነቆዎች በመፍታት ወደተሻለ እንቅስቃሴ እንዲገባ ያመቻቸ ነው። ህዳሴ ግድቡ በራሱ በዲፕሎማሲው ላይ ቀደም ብሎ የተጀመረ፤ በለውጡ ዘመን ደግሞ ከፍተኛ ጫና እንዲያርፍብን ያደረገና ብዙ ፈተናዎች ኢትዮጵያ ያለፈችበት ነው።
አንደኛ፣ ከሕዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ ጫና በኢትዮጵያ ላይ ወርዶባታል። ሁለተኛ ለውጡን ባለመቀበልና በልዩ ልዩ ምክንያት በሀገር ቤት ከፍተኛ የጦርነትና ሀገርን የሚፈታተን ችግር አጋጥሞ ነበር። ከእርሱ ጋር የተያያዙ ፈርጀብዙ ጫናዎች እንደበረዶ ኢትዮጵያ ላይ የሚወርዱበት ሁኔታም ነበር። አንዳንድ ጎረቤት ሀገራት ያንን አጋጣሚ ተጠቅመው ለምሣሌ ሱዳን ጊዜውን ተጠቅማ ወረራ አካሂዳ የተወሰኑ ቦታዎችን የያዘችበት፤ ለአንዳንድ ሸማቂ ኃይሎች ጥግ ሰጥታ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃቱ እንዲስፋፋ ያደረገችበት ጊዜ ነበር።
ግብጽና ሱዳን የጋራ ወታደራዊ ስምምነት እያደረጉና ስምምነት ብቻ ሳይሆን በድንበር አካባቢ እንቅስቃሴ እያደረጉ የመጨረሻውን የጦር ቃታ ለመሳብ እያንዣበቡ ያለበት ሁኔታ ነበር። በዓለም አደባባይ በሴኩሪቲ ካውንስል ብቻ ” ከ13 ጊዜ በላይ በአማካይ በወር አንድ ጊዜ ኢትዮጵያ አጀንዳ እየተደረገች ፋታ ያጣንበት ዘመን ነበር። በዚያን ወቅት የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮችም በእጅጉ ኢትዮጵያን ይፈትኑ ነበር። ለምሣሌ፥ የኮቪድ ዘመን፣ የዓለም ችግር ሆኖ ኢትዮጵያም ላይ የነበረው ፈተና በራሱ የዲፕሎማሲውን ሂደት ያወሳሰበ እና የራሱ ጫና የነበረው ነው። ሌሎች የተፈጥሮ ችግሮችም በኢትዮጵያ ተከስተው ነበር። ልዩ ልዩ ማዕቀቦች፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉት ከሰብዐዊ መብት ጋር የተያያዙ ክሶችና በጄኔቫ በተከታታይ በኢትዮጵያ ላይ ይደረግ የነበረውን ጫና ማንሳት ይቻላል፡፡
በዩኤስ በኩል ከፍተኛ ጫና ያሳደሩ የኢኮኖሚና የልዩ ልዩ የማዕቀብ ውሳኔዎች የተላለፉበት፤ ኢትዮጵያን ሊፈትኑ የሚችሉ አጀንዳዎች በሙሉ በኢትዮጵያ ላይ የተጫነበት፤ ከአንዳንድ ሀገሮች በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች በአንዴ ከዚያ አገር አስወጥቶ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ከፍተኛ ጫና እንዲያድርብን የተደረገበትም ነበር፡፡ ሀገር ቤት በሚካሄደው ጦርነት የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ለዲፕሎማሲ ያልተመቸችና ለደህንነት ስጋት ስለሆነች ብዙ አገሮች “ውጡ፣ እንውጣ” አድማ የገቡበት፤ ኤምባሲያቸውን እየዘጉ ለመውጣትና ሁሉንም ነገር ለማጨለም የተሠራበት ወቅት ነበር። ሌሎች በዚህ በዝርዝር ያላካተትኳቸው ጉዳዮችን ስንጨምር እነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያን በእጅጉ የፈተኑና ኢትዮጵያን ከፍተኛ ፈተና ውስጥ የጣሉ ጉዳዮች ነበሩ።
የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከአፍሪካ አጀንዳ ወጥቶ ወደሌሎች አካላት እንዲሄድ፤ የሰላም ድርድር ተብሎ የተያዘው አጀንዳ ከአፍሪካዊ አጀንዳነት ወጥቶ ሌሎች አካላት ሊቆጣጠሩት የፈለጉበት፤ የሰብዓዊ ድጋፍ እንቅስቃሴና ሌሎች የአገልግሎት አጀንዳዎች ከሌሎች የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ ፍላጎቶች ጋር ተያይዘው ኢትዮጵያን ለማንበርከክ እና እጅ ለመጠምዘዝ እንደመሣሪያ የተወሰዱበት ነበር፡፤ በአጠቃላይ ጫናዎቹ ተቆጥረው የሚያልቁ አይደሉም ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ፦እነዚህን ጫናዎች እንዴት መሻገር ቻልን ?
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ፦ የመጀመሪያው የድሉ ምንጭ እና ሀብት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጽናት፣ የኢትዮጵያ እንደሀገር ብርታት እና የተዋናዮቹ ጥበብና ብልኀት እንዲሁም የወዳጆቻችን አብሮ መቆም ይሆናል ማለት ነው። በእነዚህ አራት ጭብጦች ውህድ ውጤት ኢትዮጵያ ይኸን ፈተና ተሻገራ ዋናውን መስመሯን ሳትለቅቅ በታሪክ በየዘመኑ የተሻገርንባቸውን የአገር ሉአላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር ይኸንን በረዶ ለመሻገር ችላለች። ይኸ ድል እንደትልቅ ድል እና ስኬት ሊወሰድ ዋናው ባለቤት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ማለት ነው።
እንደትምህርት ይኸን ለመሻገር ይሠራ የነበረው ሥራ ምንድን ነው? በሰፊው የሕዝብ አቅም ውስጥ ሆኖ ዲፕሎማሲው ሲንቀሳቀስ አንደኛ የኢትዮጵያን ትክክለኛ አጀንዳ፣ ኢትዮጵያ ራሷን መግለጽ አለባት። ራሷን (ዲፋይን) ማድረግ አለባት። ስለዚህ ማስገንዘብ ለተለያዩ አካላት ለተለያዩ ወገኖች የኢትዮጵያን አቋም ማስገንዘብ፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በስሜት፣ በልዩ ልዩ ጫና የሚመጡ ነገሮችን የማለዘቡ ሥራ ትልቅ ጥበብ ሆኖ ነው የታየው፤ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በእንዲህ ዓይነት ፈታኝ ጊዜ ወዳጅ ማብዛት ያስፈልጋል።
ወዳጆች በትክክል ተገንዝበው አብረው እንዲቆሙ፤ ኢትዮጵያን ሆነው ለጥቅማችን ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ በሚያስችል ሥራ ታስገነዝባለህ፤ ጫናውን ታለዝባለህ ሁሉንም በማካረርና ክሩ እንዲበጠስ በማድረግ ሳይሆን የሚያሻግርህን ጥበብ በመከተል ወዳጅ ታበዛለህ። በሀገር ቤት ባለው አቅም በእነዚህ የግንኙነት ጥበቦች በየደረጃው በተሠራው ሥራ ይኸንን የማሻገር፣ ዲፕሎማሲው ወደነበረበት እንዲመለስ (ሪኢንጌጅመንት) የሚል ታክቲክ ተዘርግቶ በዚያ ነው ይሠራ የነበረው፤ ሁኔታው ወደተሻለ ምዕራፍ ሲሸጋገር ደግሞ ከዚያ አለፍ ብሎ የነበረው ግንኙነት የተሟላ የማድረግና እና ወደላቀ ግንኙነት ደግሞ ልንሄድ ይገባል። ክንዳችንን እያበረታን፤ እጃችንን እያስረዘምን በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በጎረቤት ሀገር፣ በሁለትዮሽ፣ በዓለም አቀፍ አውድ ላይ የቆምንበት እና የተሻገርንበት ነው።
የህዳሴ ግድባችንን የሦስትዮሽ ድርድር ከአፍሪካ በማውጣት ቀደም ሲል ዋሽንግተን በዘመነ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጊዜ ከፍተኛ ጫና እየተካሄደ፤ ከዚያ ቅርቃር ውስጥ አውጥቶ አፍሪካዊ እና የኢትዮጵያና አፍሪካዊ በለቤትነት ያለው ድርድር እንዲካሄድ ማድረግ በጣም ትልቅ ስኬታማ ሥራ ነው ማለት ነው። በሌሎች መገለጫዎች ሊጠቀሱ የሚችሉ ሥራዎችም እንደዚሁ ተሠርተዋል ማለት ነው።
ያንን በማጠንከር ራሳችንን የማሳወቅና የማስገንዘብ ሥራ ስንሠራ፤ የማለዘቡ ሥራ ሲከናወንና ወዳጅ ማስፋቱ በስፋት ሲሠራ ቀደም ከነበሩት ታሪካችንና ከሀገራችን የፍትሕ ጥያቄ ጋር እያያያዙ አንዳንድ አገሮች መልሶ የማስተዋልና ኢትዮጵያን ቆም ብለን እናዳምጣት፤ እውነትም የፍትሕ ጥያቄ አላት ብለው በይፋ የገፉበትና ከእኛ ጋር የቆሙበት ነው።
በዚህ ሁሉ ሥራ የሕዝባችን ጥንካሬ ግሩም ነበር። ዲያስፖራው በ#No more እንቅስቃሴ ርብርብና ዘመቻ ሲያካሂድ እያንዳንዱ ዜጋ ያለውን ወርውሯል። አገሩን ለመታደግ ማለት ነው። በእነዚህ ጉዞዎች ነው ይህ ውጤት የተረጋገጠው፤ እዛም ላይ እየቀጠልን፤ እየቀጠልን ለኢትዮጵያ መያዣ ተብለው የተዘየዱት ወይም የተቀመሩት የማነቆ መሣሪያዎች እንዲነሱ በዓለም አደባባይ ላይ ያደረግንበት፤ እንዲያውም ከዚያ አልፈን እንደነ ብሪክስ ዓይነት አዳዲስ የትብብር ማዕቀፎችም ውስጥ ኢትዮጵያ አባል ሆና የገባችበትና በዩኤንም በአውሮፓ ኅብረትም በልዩ ልዩ መስኮች የተሻለ ግንኙነትና የተሻለ እንቅስቃሴ ውስጥ የገባንበት ሁኔታ አለ ማለት ነው፣ በአጭሩ ጉዞው ፈተናዎቹ፣ስኬቶቹም የድሉም ምንጭ ይህ ነው ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ለመጪው ዘመን የዲፕሎማሲ ሥራችን ሀገራዊ ዝግጅታችን ምን ይመስላል፣ ምንምን ሥራዎችስ እየተሰሩ ነው፣ ኢትዮጵያ ያላት ተስፋና እድል ምንድ ነው?
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ፦ ኢትዮጵያ ያላት ተስፋና ዕድል የሚለውን ጭብጥ ስታነሳ አንዳንድ ነገር መጡብኝ፣ እኔ በዚህ የስራ አጋጣሚ በውጭ ግንኙነት ስራ ጥቂት ዓመታት ስንቀሳቀስ የተገነዘብኩት ብዙ ሀገራት አፍሪካውያን፣ በታሪክ በመጣንባቸው በልዩ ልዩ መልኮች ለኢትዮጵያ ያላቸው ክብርና ግምት በጣም የላቀና ትልቅ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኛ በልዩ ልዩ አጀንዳ ተወጥረን በአለንበት ዓለምን የሚፈትኑ ጉዳዮች ሲመጡ በዩናይትድ ኔሽን ሌላ ቦታ አቋም የሚወሰድባቸው፣ድምጽ የሚሰማባቸው፣ ጊዜያት ሲመጡ ኢትዮጵያ በራሷ ብዙ ችግርና ብዙ ጫና ያለባት ቢሆንም ፣ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፣ ኢትዮጵያ በዩናይትድ ኔሽን፣ በአፍሪካ ህብረት ትልቅ ቦታ ያላት ሀገር ናት፡፡
የኢትዮጵያ ድምጽ፣ የኢትዮጵያ መልዕክትና ተጽዕኖ ተባዥ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ነው ሚናችሁን መወጣት ያለባችሁ፣ይህን አቋም ውሰዱ፣ እንዲህ ዓይነት እርምጃ ውሰዱ፣እንዲህ ዓይነት ድምጽ አሰሙ በሚል ትልቅ ግምት ሰጥተው ነው የሚነግሩን። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ምናለች ይባላል፡፡ አፍሪካውያን ፣የላቲን አሜሪካ ሀገራት እና ብዙ የዓለም ሀገራት ለኢትዮጵያ ያላቸው አተያይና እይታ በጣም ከፍያለ ነው፡፡ ይህ የሚሆነውም በታሪክና በልዩ ልዩ ገጠመኝ የኢትዮጵያን ቦታ ስለሚያውቁ ነው፡፡
ይህ ትልቅ ዕድልና ሀብት አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዚህ ፈታኝ ጊዜም፣ በየዘመኑም በነበረውም ምንያህል በጽናት ለነጻነታቸውና ለክብራቸው ተዋድቀው ይህን አገር ለዚህ እንዳበቁ ለሌሎችም የጥቁር ህዝብ ነጻነት መገለጫ ሆነን የመቆም ሌጋሲ አለ፡፡ ይህ የሕዝባችን ውጤት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ዕድል እያለ በተለያዩ ስሜቶችና ፍላጎቶች ቅርብ አዳሪ በሚመስል ደረጃ ልዩ ልዩ አጀንዳዎች እያጣቀስን እኛው ራሳችን በሀገር ቤት ውስጥ የምንናቆርበት፣ የምንቋሰልበትና ኢትዮጵያን የምንገዘግዝበት አጋጣሚ ያሳዝነኛል፡፡
ለኢትዮጵያ ጠንካራ ዲፕሎማሲ ይኑር ከተባለና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ ይስፋ ይደግ ከተባለ፣ ማጠንጠኛው መጀመሪያ ሀገር ቤት ውስጥ የሚኖረን አብሮነትና አንድነት ነው። በሀገርቤት ውስጥ የሚኖር ጥንካሬ ተባዥነቱ በየትኛውም የፕላኔቷ ማዕዘናት ውስጥ ያርፋል፡፡ ስለዚህ የትኛውንም ሃሳብ፣ የትኛውንም ልዩነት፣ የትኛውንም ፍላጎት በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ጥፋት ሳናስከትል ስልጡንና በሰላማዊ ሁኔታ የመፍታትን ባህል ማዳበር አለብን፡፡ ጠንካራ ሀገር መገንባትና ፣ አብረን መቆም ነው የኢትዮጵያ ትልቁ ተስፋና መሰረቷ፡፡ ይህ ነው ዋናው ማዕዘን። በታሪክም በልዩ ልዩ ስሜትም የምናሳንሳት፣ የማናቆስላትና የምንገዘግዛት፣ ልጆቿ ነን እንጂ በዓለም አደባባይ በብዙ ማዕዘናት ለኢትዮጵያ ያለው ግምትና ክብር ትልቅ ነው፡፡ ለዚያ ክብር እኛው ባለቤቶቹ መሪ ሆነን ጠንክረን መራመድና መቆም አለብን ማለት ነው፡፡
ለመጪው ዘመን ውስጣዊ አብሮነት፣ አንድነት፣ በኢኮኖሚ ከድህነት መውጣት፣ ሀገርን መውደድ ላይ አተኩረን መሥራት ይገባል፡፡ በራሱ የሚኮራ፣ ከድህነትና ጠኔ የተላቀቀ፣ ማኅበረሰብና ሕዝብ እንዲኖርም መስራት ያስፈልጋል፡፡ ይህን
የቤት ሥራ ከሠራን የመጪውን ዘመን ዲፕሎማሲ በስኬትና በማማ ላይ ሆኖ መቀጠል ይቻላል። የመጪው ዘመን ዲፕሎማሲን የምንተነብየውም ከወዲሁ በእይታ ውስጥ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሀገርና ሀገራት አስካሉ ድረስ ዲፕሎማሲ ይኖራል። የዲፕሎማሲው አውድና ስልቱ ምን ይሆናል የሚለው ደግሞ እንደየዘመኑ መሰለፍና መታጠቅ ያስፈልጋል፡፡
ለመጪው ዘመን ዲፕሎማሲ ከወዲሁ አስቦ አሁን ያለው ዓለማዊ ሁኔታ፣ ጂኦፖለቲካውና የሀገራት ፍላጎት፣ ምንድነው እያሉና እያነበቡ፣ የዲፕሎማሲውን መንገድ መቃኘት ይገባል፡፡ አሁን ስናይ የጂኦፖለቲካው ሁኔታ በጣም ተገማች ባልሆኑ ሁኔታዎች ይቀያየራል፡፡ አይቀራረቡም በምንላቸው ሀገራት መካከል የበለጠ የመቀራረብ ነገር እናያለን። በትብብር ማዕቀፍ ይታወቁ የነበሩ የትብብር ማዕቀፎች መልካቸውን እየቀየሩ በሌላ አግባብ ይስተዋላሉ፡፡ እና የመጪውን ዘመን ዲፕሎማሲ ፍኖተ ካርታ ለማስቀመጥ አሁን ያለውን ተለዋዋጭ ሁኔታ መነሻ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ዲፕሎማሲ ስንል በመጪው ዘመን የሚለዋወጠውን ሁኔታ ከራስ ሁኔታ ጋር አጣጥሞና ተወዳዳሪ ሆኖ መቆም ይጠይቃል፡፡ በየዘመኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ ዲፕሎማሲ አለቀለት፣ በሌላ ተተካና ብዙ የሚባሉ አንዳንድ ሊትሬቸሮች እንደዚያ ይታያል፡፡ የተለያዩ የግንኙነት መስኮች፣ የዓለም ውድድር እና ሀገራት እስካሉ ድረስ፣ ዲፕሎማሲው መልኩን እየቀየረ እንደሚቀጥል ማወቅና ለዚያ የሚበቃ ዝግጅት ማድረግ ይገባል ማለት ነው፡፡
አሁን እንኳ ስናየው ድሮ ከነበረው የመደበኛ ወይም ኮንቬንሽናል የምንለው ዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን አሁን መታገያው፣ ዲጅታል ዲፕሎማሲ ተጨምሮበታል። የሶሻል ሚዲያው ሁኔታና ላንድ ስኬፑም ተቀይሯል። ዝምብለህ ረጅም ቀጠሮ እየያዝክ እና ፊት ለፊት እየተገናኘህ የከረትሲ ኢንጌጅመንት አሁን ላይ በቂ አይደሉም፡፡ ፈጣን፣ በእጅ ላይ በያዝነው ሞባይል ቴክኖሎጂው ኮንቨርጅ አድርጎ ሁሉም መረጃ በአንድ ጊዜ የሚደርስበት፣ እያንዳንዱ መሪ፣የውጭ ጉዳይ አምባሳደሩ ሁሉም ቲዊት አድርጎ በልዩ ልዩ መሣሪያዎች ግንኙነት የሚያደርግበት ነው ዘመኑ።
ያንን የሚመጥን ዝግጅትና ስራ ካልተሰራ የዲፕሎማሲ ሥራው ከእጃችን ወጥቶ ሌሎች በፈለጉት መልክ ዲፋይን እያደረጉ የሚቀጥሉበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ስለሆነም ያነን የሚመጥን የዲጂታል ዲፕሎማሲ ስርዓት አቅም መገንባትና ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ አሁን እየመጣ ያለው የጂኦ-ዲጂታል ኢኮኖሚ ሁኔታ የወደፊት የግንኙነቱ አግባብ በኢኮኖሚ ግብይትና ግንኙነት ዲፕሎማሲውን ለመጠቀም የበለጠ ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ የዩኤስ ሲል ካምፓኒ ላይ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና እዚያ ላይ ያለ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አንዳንድ ሀገሮች የራሳቸውን አምባሳደር ለዚያ ተልዕኮ ብቻ መድበው የሚከታተሉበትና ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚሰሩበት ሁኔታ አሁን ይስተዋላል፡፡
ለአንድ ሀገር አንድ ሚሽን የማቋቋም ብቻ አይደለም፡ በዓለም ላይ ባሉት የሴኩሪቲ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሌሎች የግንኙነቶች አውዶች ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የምሰማራበት ገበያ የት ቦታ ነው፣ የሀገሬን ፍላጎት በትክክል ለመጠቀም የሚያስችለኝ ስምሪት ምንድነው፣ እያሉ እያሰቡና ተለዋዋጭ የሆኑ ሁኔታዎችን እየቀጠሉ ለዚያ የኢኮኖሚ ሁኔታ ስራዬ ብለው መድበው የሚሰሩበት አለ፡፡ እንደአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዓይነት አብዮቶች አሁን እየመጡና እየተስፋፉ ባሉበት ሁኔታ የዲፕሎማሲው ውሎና ተወዳዳሪነት ምን ይሆናል የሚለውን ማሰብና ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
የድርድር የስምምነት ፣የሌሎች የኢንጌጅመንት ሁኔታዎች በምን አግባብ ነው ሊቀጥሉ የሚችሉት የሚለውን ለመመለስ ቴክኖሎጂው የሚሰጠውን እድል በአግባቡ መጠቀም፣ የሚፈጥረውን አሉታዊ ጫና የሚመክት ሀገራዊ አቅም መገንባትና መሥራት ያስፈልጋል። ከዚህም ባለፈ የዲጂታል ኢኮኖሚ የኢኖቬሽን መሰረተ ልማት አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከውጪ ጉዳይ የፖሊሲ ማዕቀፍ ጋር መቃኘትና መተሳሰር አለባቸው፡፡
ዲፕሎማቶቻችን ያንን የሚመጥን ትጥቅ ያስፈልጋቸዋል፡ ፕሮፌሽናሊዝም ያስፈልጋቸዋል፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ብቃት ይጠይቃቸዋል። በቴክኖሎጂው አውድ ውስጥ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ኢትዮጵያን ለብሔራዊ ጥቅሟ የሚያበቃትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸቸዋል፡፡ ወደ ፊት እጅግ ተገማች ያልሆነ የዲፕሎማሲ አውድ እየተፈጠረ መሄዱ አይቀርም፡፡ ዲፕሎማሲ ሲባል አንድ ቦታ የሆነ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽ/ቤት በመክፈት፣ አምባሳደር በመሾም፣ ዲፕሎማት በመመደብ፣ በአንድ መንገድ ብቻ የሚንቆረቆር የዲፕሎማሲ ጉዞ ብቻ በቂ አይደለም፡፡
በዓለም ላይ ተደራሽ ለመሆን የሚያስችለን ዘመኑ የሚጠይቀውን አሰላለፍ እና ስምሪት ይጠይቃል፡፡ መደበኛ ያልሆነ ዲፕሎማሲ አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል። ምናልባት አንዳንድ ጊዜ አንድን ኢትዮጵያን ወክሎ አንድ ቦታ መልዕክተኛ በመሆን ፣የመሪን መልዕክት ለማድረስ፣አንዳንድ ጉዳዮችን ለማስፈጸም፣ለዚያ ሀገር ፣ለዚያ አጀንዳ፣ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ፣ በዲፕሎማሲው መስክ ያልተሰማራ ግን ሌላ ዜጋ የበለጠ ጠቃሚ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ በአትሌቲክስ መስክ የታወቀ፣በቢዝነስ መስክ የታወቀ፣ በሌሎች አጀንዳዎች ተጽዕኖ የፈጠሩ በሙሉ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ እየፈጠሩ መሄድ ያስፈልጋል፡፡
ዘመቻው፣ ከበባው፣ ውሎው፣ በአንድ ጠባብ መንገድ ብቻ የሚፈስ ሳይሆን፣ በሁሉም አቅጣጫ የእኛን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስምሪቶችና እንቅስቃሴዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ለየዘመኑ የሚጠይቀውን ብቃትና ቴክኖሎጂ መላበስ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ የዲፕሎማሲያችን ሳምንት አንድ ትልቅ ቦታና ግምት የሰጠው ለመጪው ዘመን ዲፕሎማሲ እንዴት እንዘጋጅ፣ አሁን ያሉት አመልካች ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ፣ በዚህ ዙሪያ የአደጉ ሀገራት ቀድመው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስንና ሌሎቹን በመጠቀም ምን ምን እየሰሩ ነው የሚለውን በመረዳት ሁልጊዜ እኛ ሌላው ተጠቅሞበት ፣ውሎበት ያንን እየተከተልን የምንኖር መሆን የለብንም የሚለውን ነው። ተከታዮች መሆን የለብንም፣ ሁሉም እኩል ተሰልፎ የሚዋኝበት፣የሚተውንበት፣ጥቅሙን ለማስከበር የሚንቀሳቀስበት፣ዘመን ነው መሆን ያለበት፡፡
በዘመናት ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ቀድመው ሀገራቸውን ወደ ሌላ ማማ አሸጋግረዋል፡፡ እኛ ከብዙ ጊዜ በኋላ ተከትለንና መንዝረን ለመከተል ሞክረናል። በዚህ መንገድ ግን መጪው ዘመን መሸከም አይቻልም። ይኸ አገር የሚመጥነው እና ማድረግ ያለብን አዳዲስ የዓለም መዋጊያ፣ መሰማሪያ አውዶችን በሙሉ ፈጥነን የማወቅ፣ አገራዊ አቅም የመገንባት በዚያ ደረጃ ጥቅማችንን የሚያስከብር ስምሪት እና ውሎ ነው። እና አዲሱ ዲፕሎማሲ በዚህ አቅጣጫ የሚገራ፤ ለዚህ የሚያስፈልጉ ፍኖተ ካርታዎች፣ በደንብ ቆጥሮ የሚያስቀምጥና ሁሉንም የሚያሰልፍ መሆን አለበት፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር የትኛውም ፍላጎት ቢኖር ለአንድ የጋራ ሀገር አምባሳደር ሆኖ መንቀሳቀስ እና በቅቶ መገኘትን ይጠይቃቸዋል ማለት ነው። መጪው ዘመን በዚህ ነው መቃኘት ያለበት፤
ዲፕሎማሲያችን ቀደምት ታሪኮች አሉት። ቀደም ብዬ እንዳልኩት 116 ተቋማዊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች አሉት። ስለሆነም ይኸንን በትክክል መዘከር፤ በትክክል መቀመር እና ወረቶቹን ማወቅና መጠቀም ያስፈልጋል። እኛ ሀገር ብዙው ችግር በየዘመኑ የምንመጣ ኃላፊዎች፣ መሪዎች እና የፊት ተዋናዮች የዱሮውን በማፍረስና እንደፍርስራሽ በመጣል ከአዲስ መሠረት ለመነሳት ብዙ እንጥራለን። ነገር ግን ከቀድሞው መማር፣ ወረቶቹን መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም ከቀድሞ አንጋፋ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች እና ተዋናዮች ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል።
በእነከተማ ይፍሩ ዘመን ምን ተሠራ? ምን ጥሩ ነገር አለ? በእነአክሊሉ ሀብተወልድ ዘመን ምን ምን ጥሩ ነገር ተሠራ? በእነኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ዘመን ምን ጥሩ ነገር ተሠራ? በውጭ ጉዳይ ቤት ውስጥ በእነስዩም መስፍን ዘመን ምን አዎንታዊ ጥሩ ነገር ተሠራ? በእነብርሃኑ ዲንቃ ዘመን ምን ጥሩ ነገር ተሠራ? በማለት ክፍት ሆኖ፤ በጎ ነገሮቹን ሁሉ መስጥሮ ለሀገር የሚጠቅመውን ማሻገር ያስፈልጋል ማለት ነው።
ውጭ ጉዳይ በዚህ ደረጃ ሁልጊዜ የሚማር፤ ሁልጊዜ የሚበቃ ተቋም እያደረጉ መምራትና ሁሉንም አቅሞች የሚያንቀሳቅስ መሆን ይኖርበታል። እንደ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትነቱ አምባሳደሮቹ ሚሊዮኖች እንደሆኑ ማወቅና ማሰብ ያስፈልጋል።ዲፕሎማሲ፣ የውጭ ግንኙነት ሥራ በሰባቱ ቀናት በ24 ሰዓት ውስጥ በጣም ብዙ ተለዋዋጭአዳዲስ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙበት ነው። ሁልጊዜ መማርን ያስፈልጋል። ሁልጊዜ ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል። ሁልጊዜ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የሚያስችል ዝግጁነት ይፈልጋል።
እኔ በሕይወት ዘመኔ በብዙ የሥራ መስኮችን ለመሳተፍ ሞክሬአለሁ። ባልሳተፍበትም ደግሞ ሁልጊዜ ትምህርት፣ ሁልጊዜ ሐላፊነት፣ ሁልጊዜ ዝግጅት የሚጠይቁ መስኮችን ለመለየት በትዝብቴ አይቻለሁ። መምህር ለማስተማር ሁልጊዜ ያነብባል፤ ሌሰን ፕላን ያዘጋጃል፤ ከዚያም በሳምንታዊ ሌሰን ፕላኑ የቀናቱን ያስተምራል። ጋዜጠኝነት እንደፕሮፌሽን እንደሥራ ሲወሰድ ሁልጊዜ ለዛ የሚመጥነውን ዝግጅትና ተልዕኮ ማድረግ አለበት።
ዲፕሎማትነት ከዚህ አኳያ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል። ስለኢትዮጵያ ምን ተባለ? ኢትዮጵያ ምንድን ነው የምታጋራው? የራሷን ተፅዕኖ ለማሻገር የሚስችላት ምንድነው የሚለውን ማወቅ ይጠይቃል ማለት ነው። እንዲህ ዓይነት ዝግጁነት በሰፊው አውድ ውስጥ ሆኖ መሥራትን እና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የዲፕሎማሲ ሥራው ከዚህ አኳያ ካለፉት ወረቶች እየተጠቀመ ውስጣዊ አብሮነትንና አንድነትን እያጎለበተ መጓዝን ይጠይቃል፡፡
በዓለም ላይ ኢትዮጵያን ታሪኳን፣ አዎንታዊ ሚናዋን፣ እና ሕዝቧን የሚመጥን የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲቀጥል ማድረግ አስፈላጊ ነው። ያ ሲሆን ብሔራዊ ጥቅም ይረጋገጣል። ሉአላዊነት ከፍ ባለ ደረጃ ይከበራል። በየትኛውም ቦታ የኢትዮጵያ ተደማጭነት እና የኢትዮጵያ ጉልህ ሚና ቦታውን ይይዛል። ያንን እውን ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናውን እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል ነው የምለው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ስለነበረን ቆይታ እጅግ በጣም እናመሰግናለን ።
አዲስ ዘመን ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም