ሁላችንም የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ ስለ ኢትዮጵያም ዲፕሎማት እንሁን!

 ሀገር በሕዝቦቿ ተግባር ልክ ትገለጻለች፡፡ መልካም ዜጎች መልካም ሀገርን ይገነባሉ፤ ካልሆነው የሀገር መገለጫው ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያንም በየዘመኑ ትውልዶች እሳቤና ተግባር ልክ ኢትዮጵያን ሠርተናል፡፡ በዓለም የሚታየው ገጽና ስሟንም ፈጥረናል፡፡

ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ቀደምትነቷም፤ የነጻነት አርነቷም፤ የጥበብና ባህል ማዕከልነቷም፤ የድህነትና ጦርነት ታሪኳም፤ የረሃብና ስደት ገጿም መነሻና መሥሪያ ማዕከሏ እኛው ዜጎቿ ነን፡፡ ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገን በሠራን ልክ፤ ስለ ኢትዮጵያ ተጨንቀን በተንቀሳቀስን መጠን የኢትዮጵያን ገጽ እናስውባለን፡፡ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያን ልክ እናጠይማለን፡፡ የልዕልናዋንና የጉስቁልናዋም ገጽ የመሳሉ እውነትም በዚሁ አግባብ የተገለጠ ነው፡፡

ይሄን የኢትዮጵያን ገጽ የመግለጥ፤ ልዕልናዋን የማረጋገጥ መንገድ ደግሞ የተለያየ ፈርጅ አለው፡፡ ሰላሟን በማጽናት፤ ልማቷን በማሳለጥ፤ የዴሞክራሲ ግንባታ መንገዷን ቀና በማድረግ፤ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር በመፍጠር፤ ብቁ (በእውቀትም በጤናም) የሰው ኃይልን በመፍጠር ሂደት ውስጥ የሚገለጽ የእያንዳንዱ ዜጋ ተግባር ድምር ውጤትን ይፈልጋል፡፡

ከዚህ የውስጥ የቤት ሥራዎች በተጓዳኝ ግን ኢትዮጵያን በሠራናት ልክ ለውጪው ዓለምና ማኅበረሰብ የማሳወቅ፤ ከውጪው ዓለም ጋር የሚኖራትን ግንኙነትና ትብብር ቀና የማድረግ፤ ከውጪው ዓለም ጋር በሚኖራት ግንኙነት ተጠቃሚነቷን የማረጋገጥ፤ ከፍ ያለ የአምባሳደርነት ተግባር ከዜጎች ይጠበቃል፡፡ ይሄ ደግሞ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛትና ድንበር ባሻገር የመሥራት የዲፕሎማትነት ልዕልና መጎናጸፍን ይጠይቃል፡፡

አምባሳደርነት፣ የሀገርን ስምና ገጽ ይዞ መንቀሳቀስ፤ በዛ ልክ ራስን ቀርጾ መትጋትን መጎናጸፊያ ማዕረግ ነው፡፡ ይሄን ማዕረግ በልኩ መጠቀም፤ ኢትዮጵያን በሚገልጸው ስዕል ልክ መጠቀም ይገባል፡፡ ይሄን ለማድረግ ግን የግድ የአምባሳደርነት ማዕረግን ከመንግሥት አካል ማግኘት የግድ አይልም፡፡ ምክንያቱም አምባሳደርነት ሀገርን የመውደድና ሀገርን የማክበር የውስጥ ስሜት የሚፈጥረው ማንነት ነው፡፡

ይሄ ማንነት ደግሞ ለሀገር ጥቅም የመቆምን፣ ስለ ሀገር ገጽታ ማንንም ሳይጠብቁ የራስን ተግባር መወጣትን በጥቅሉ ስለ ኢትዮጵያ በውጪው ዓለም መልካም ገጽ መሳልን እውነት ለመግለጥ የሚያስችል የዲፕሎማሲ ሥራ የመፈጸም የኢትዮጵያ አምባሳደር መሆንን ያጎናጽፋል፡፡

ዲፕሎማትነት ደግሞ በአንድ ሁኔታና ሁነት ውስጥ ተቀንብቦ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ዲፕሎማትነት ሀገርን መስሎም፣ ሆኖም መገለጥን የሚሻ ነው፡፡ ሀገርን መምሰል የቻለ ዜጋ፣ ሀገሩን የመግለጥ አቅም አለው፡፡ አንድ ዜጋ ደግሞ ሀገሩን በእርሱነቱ ውስጥና ገጽ መግለጥ ከቻለ የሀገሩ ጥቅም አስከባሪ ዲፕሎማት ሆነ ማለት ነው፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ የሚገልጧት ዲፕሎማቶች ትሻለች፡፡ በብዙ ፈተና፣ በብዙ ችግር፣ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ እያለፈች ባለችበት በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ከእነዚህ ችግሮች ባሻገር የሚመለከታትንና ለብልጽግናዋ የሚያግዛትን ዓለም ለመፍጠር የሚያስችል ሥራን የሚከውን ትውልድ ትፈልጋለች፡፡

ኢትዮጵያ በጤናው፣ በቱሪዝሙ፤ በኢኮኖሚው እና በጂኦ ፖለቲካው እንዲሁም በቴክኖሎጂው ዘርፍ፤ ብሎም በሳይንስና ሌሎችም መስኮች ከፍ ያለ ገጿን የሚገልጡላት አያሌ ዲፕሎማቶችን ትናፍቃለች፡፡ እነዚህ ዲፕሎማቶች ደግሞ የትናንቶቻቸውን (ቀደምቶቻቸውን) የሚመስሉ መሆን አለባቸው፡፡

ቀደምት ኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን ከፍ አድርገው የሳሉ፤ የኢትዮጵያን ገጽ በግርማ ሞገስ የገለጡ፤ በዲፕሎማሲው ጎራ የኢትዮጵያን ተጽዕኖ ፈጣሪነትና ቅቡልነት ያረጋገጡ ናቸው፡፡ አዲስ አበባን ሦስተኛዋ የዓለም ዲፕሎማሲ መዲና ማድረግ የቻለን ሥራ የከወኑም ናቸው፡፡

የዛሬው ትውልድም ይሄንን እውነት ተገንዝቦ በቀደምቶቹ መንገድ መጓዝን፤ ከዚህም በላቀ መልኩ ዘመኑን የዋጀ አቅም ፈጥሮ መራመድን መላበስ አለበት፡፡ ኢትዮጵያን የሚወክል የአምባሳደርነት ክብርን በላዩ ሊደርብ፤ ኢትዮጵያን የሚገልጽና በዓለምአቀፍ መድረኮች ጥቅሟን የሚያስጠብቅ የዲፕሎማትነት ፍላጎትንና ግብርን ሊጎናጸፍ ያስፈልጋል፡፡

ምክንያቱም ኢትዮጵያ በጥቂት መንግሥት በሰየማቸው አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ተግባር ብቻ በከፍታዋ ልክ ልትገለጽ አትችልም፡፡ እነዚህ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችን ማስፈጸምና መፈጸም ቢችሉ እንኳን፤ ኢትዮጵያን በልኳ እና በቱባ ማንነቷ ልክ አመላክተው ጥቅሟን ያስጠብቃሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል፡፡

የታሪክ ሂደት፣ የዲፕሎማሲው እውነት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከንግሥተ ሳባ የዲፕሎማሲያዊ ጉዞ ጥንስስ ጀምሮ እስካሁኑ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ሁነት የነበራት ሂደትም፤ አምባሳደሮቿም፣ ዲፕሎማቶቿም በዜጎቿ ከፍ ያለ ተግባር ታግዘው የተጓዙና ውጤት ያመጡ ናቸው

የሩቁም እውነት፤ የቅርቡም ሁነት ይሄንኑ የዜጎችን የአምባሳደርነት እና የዲፕሎማትነት መንገድ ከገለጠ፤ የዛሬው እና የነገው የዲፕሎማሲ ጉዞም በዚሁ አግባብ ሊመራ እንደሚገባው መገንዘብ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊም፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌሎች ከሁለትዮሽና ከባለብዙ ወገን ትብብር መስኮች የም ታገኛቸውን ጥቅሞች ማስጠበቅ የሚቻለውም ይሄንኑ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡

እነሆ ዛሬ በሳይንስ ሙዚየም “ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን!” በሚል መሪ ሃሳብ የተከፈተው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይም ይሄንኑ በዓለም መድረክ የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ የሚችል ትውልድን የመፍጠር መንገድ ነው፡፡ አውደ ርዕዩም ዜጎች ከትናንቱ መንገድ የሚማሩበት፤ ከዛሬው ሁነት ልምድ የሚቀስሙበት፤ የነገውን መንገድ የሚመለከቱበት ሲሆን፤ እኛም ይሄንኑ በመገንዘብ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች፣ ስለ ኢትዮጵያም ዲፕሎማቶች የምንሆንበትን የዜግነት ከፍታ ልንጨብጥ የተገባ ነው!

አዲስ ዘመን  ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You