ተንቀሳቃሽ ጭፈራ ቤቶች

የገባሁበት ታክሲ ከቦሌ ወደ ፒያሳ የሚያደርሰውን ነበር:: ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሊሆን የቀሩት ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ናቸው:: ወደ ታክሲው ስገባ ሠላም አልተሰማኝም:: በጣም ደመቅመቅ ያሉ መብራቶች (ዲምላይት) የታክሲውን ጥጋጥግ እንዲሁም መሐል ላይ ተለጥፈው ለዓይን ምቾት አይሰጡም:: ታክሲው ለትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ የተዘጋጀ መሆኑም ያጠራጥራል:: በጣም በከፍተኛ ድምፅ የተከፈተ ስልተ ምቱ ‹አፍሮ ቢት› ይሉት አይነት ሙዚቃ ታክሲውን ድብልቅልቅ አድርጎታል::

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ስልክ ማውራት አይሞከርም:: አጠገብ ካለው ሰው ጋር መነጋገር የሚቻለው በምልክት ብቻ ነው:: አልያ ደግሞ ወደ ጆሮ ጠጋ ብሎ መናገር ግድ ይላል:: ብቻ ምን አለፋችሁ ታክሲው አስተናጋጅ እና መጠጦች የሌሉበት ጭፈራ ቤት መስሏል:: እኔ በግሌ እንዲህ ያሉትን ታክሲዎች እና መሰል የትራንስፖርተ አገልግሎት ሰጪዎችን ‹‹ተንቀሳቃሽ ጭፈራ ቤቶች›› ብያቸዋለሁ::

ደግሞ እኮ ሙዚቃው ማቆሚያ የለውም:: የሹፌሩ አነዳድም ልክ እንደ ሙዚቃው የፈጠነ ነበር:: በመሐል አነዳዱ ሳያምረን ሲቀር ‹‹ኧረ ቀስ በል::›› ብንለው ሰሚ አናገኝም:: የምንለውን ለመስማት የግድ የሙዚቃው ድምፅ መቀነስ አለበት:: ሙዚቃው ከፍ ብሎ በመደመጡ፤ ንግግሮች ሁሉ አየር ላይ ይቀራሉ:: በጉዟችን መሐል አንድ ስልክ ለማውራት የሞከረች ሴት መደማመጥ አቃታት:: ‹‹እባክር ሾፌር ድምፁን ትንሽ ቀነስ ብታደርገው?›› ብላ በትሕትና ብትጠይቅ፤ ወይ ፍንክች:: አጠገቤ ስለነበረች የሰማኋት እኔ ብቻ ሳልሆን አልቀርም:: ያላት አማራጭ ረዳቱን መጎተት ነበር:: እርሱም ሂሳቡን ከሰበሰበ በኋላ የሚመለከተው ወደ ፊት ብቻ ነበር:: እንደ ምንም ፊቱን ወደ ኋላ አዙሮ ‹‹እእእ … ምን ፈለግሽ?›› አላት እርሷም ‹‹ወይ ቀንሰው፤ ወይ ዝጋው። መደማመጥ አልቻልኩም›› አለችው:: በመሐል ሹፌሩ ጭቅጭቅ እንደተፈጠረ ገብቶት የሙዚቃውን ድምፅ በመቀነስ ‹‹ከፈለክሽ ውረጂ›› የሚል መልስ ሰጣት:: በዚህ መሐል ብዙ ጭቅጭቅና ንትርክ ተፈጥሮ እንደ ምንም ‹‹በሠላም›› ካሰብንበት ደረስን::

የተፈጠረውን ንትርክ እያሰብኩ ለራሴ ‹‹እንኳንም አጭር መንገድ ሆነ›› አልኩ:: እንዲህ አይነቱ ችግር በብዛት በትራንስፖርት ውስጥ ያጋጥማል:: ሙዚቃዎች እና መንፈሳዊ መዝሙሮች ከመጠን በላይ ድምፅ ተከፍተው ‹‹ቀንሱ›› ከተባሉ ነገሩን ከሌላ ነገር ጋር ያይዙታል:: የሕዝብ ትራንስፖርት ሕዝቡን ለማገልገል የተዘጋጁ ናቸው:: ነገር ግን አንዳንዶቹ ከዓላማቸው ያፈነገጡ ሆነው ነው የሚገኙት::

የትራንስፖርት መጓጓዣዎች ጥቅማቸው ብዙ ነው:: አንዳንዶች ከራሳቸው ጋር ለመነጋገር ይጠቀሙበታል:: ረዘም ያለ ቦታ የሚሄዱት ደግሞ የተለያዩ መጽሐፎችን በማንበብ ይጠቀሙበታል:: በተጨማሪም የብዙ ሰዎች መተዋወቂያ ስፍራ ሲሆኑ፤ ከተነፋፈቁት ወዳጅ፣ ጓደኛ፣ ዘመድ እና ቤተሰብ ጋር ሳይቀጣጠሩ በአጋጣሚ የሚገናኙበት ዕድል ሰፊ ነው ማለት ይቻላል::

እንደ እድል ሆኖ እኔ የተሳፈርኩበት ታክሲ በስፒከር ብቻ የታጀበ ነበር:: አንዳንዶቹ ደግሞ በተንቀሳቃሽ ምስል ጭምር የታገዙ ናቸው:: የሕዝብ ትራንስፖርትን በእድሜ ከፍ ካሉ አረጋውያን ጀምሮ ሕፃናት እና ወጣቶች ይገለገሉበታል:: አንዳንድ ባለታክሲዎች የሚከፍቱት የሙዚቃ ቪዲዮዎች ፍጹም ከባሕላችን እና ከወጋችን ያፈነገጡ ናቸው:: እርቃናቸውን የሚደንሱ ሴቶችን እና አልባሌ ድርጊቶቻቸውን ላለመመልከት ገሚሱ በሀፍረት ሲሸማቀቅ፤ ገሚሱ ደግሞ ተገቢ እንዳልሆነ ለማስተማር ለመምከር ገና ከጅማሬው ስድቡን ተከናንቦ ይወርዳታል::

አንዳንድ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ለተሳፋሪዎቻቸው አስቂኝ፣ አስተማሪ እና መላ (ዘዴን) የሚያስተምሩ ቪዲዮዎችን በመክፈት ‹‹ይህም አለ ለካ?›› የሚያስብሉ መልዕክቶችን በማሳየት ተሳፋሪዎቻቸው ከቦታ ቦታ ከመጓጓዝ ባለፈ ለማስተማር የሚያደርጉትን ጥረት አመስግኖ ማለፍ ተገቢ ነው::

አሁን አሁን ታክሲ ላይ አስተያየት መስጠት ፍጹም የማይታሰብበት ሜዳ ከሆነ የዕለት ተዕለት ትዝብታችን ሆኗል:: ሰዎች ‹‹ለምን እሰደባለሁ›› ብለው መብታቸውን አሳልፈው የሚሰጡበት ቦታም ሆኗል:: የትራፊክ ፖሊሶቻችን ይሁኑ ሌሎች የሕግ ተቆጣጣሪ አካላት የሚመለከቱት ትርፍ የመጫናቸው እና ሌሎችን ሕግ ስለመተላለፋቸው ብቻ ነው::

በታክሲም ሆነ በሌሎች መጓጓዣዎች ‹‹እየተረበሽኩ ነው›› ብሎ ተሳፋሪው አይከስ ነገር ድምፅ መጨመሪያውም ሆነ መቀነሻው ያለው በሾፌሩ እጅ ነው:: ምን ይታወቃል? ዝም ብሎ ከመሳፈር ውጭ እንዲህ አይነቱን ሃሳብ ማንሳት በራሱ ቅንጦት (ቀበጥ) ያስብል ይሆናል:: ‹‹ታክሲውን እናግኘው እንጂ ለምን ከዛ በላይ አይናገሩንም›› የሚል ሃሳብ ከአንዳንድ ሠዎች እንደሚሰነዘር ይታወቃል::

በእርግጥ ስለ ሾፌሮች እና ረዳቶች ይህን አልን እንጂ በተሳፋሪዎችም የሚታየው ችግር ብዙ ነው:: ምን እንደሆነ ባይገባኝም በትሕትና ከማናገር ይልቅ ለጸብ የሚጋብዝ ንግግር ይስተዋላል:: ሁሉንም አጥፊ እና ተሳዳቢ አድርጎ በመቁጠር አገልግሎት የሚሰጡትን ሰዎች ሥነ ምግባር በጎደለው መልኩ ሲያናግሩ እና ሲያደናግሩ ይታያል:: አንዳንዶችም በስልካቸው የተለያዩ ሙዚቃዎችም በሉት ቪዲዮ በመክፈት እና በስልክ ጥሪያቸው ተሳፋሪዎችን በመረበሽ መውረጃ ቦታን ያስናፍቃሉ::

ይህን፣ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ችግር አነሳን እንጂ መረጃ አሰጣጥ ላይ ብዙ ክፍተቶች ይታዩብናል:: አንድ ጥያቄ ተጠይቆ ምላሽ መስጠትን እንደ ትልቅ ነገር ማየት በአንዳንድ ቦታዎች የተለመደ ነው:: በትሕትና ከማናገር ይልቅ በቁጣ ማስረዳት፤ ከመጨቃጨቅ እስከ መሰዳደብ ደረጃም ይደረሳል:: ሥራ እየሠሩ ሥራ ካለመሥራት የማይተናነስ፣ የመሰልቸት ስሜት የሚስተዋልባቸው አገልጋዮች ጥቂቶች አይደሉም::

ትንሽ ጩኸት የሚረብሻቸው ሰዎች ምን ዓይነት ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል መገመት ቀላል ነው:: አንዳንዶቹ የሚከፍቱት ሙዚቃ ተሳፍሮ ከሚሄደው ውጭ ለመንገደኛ እስከ መሰማት የደረሰ ነው:: ይህንን የሰማ መንገደኛም በሙዚቃ ለሚረበሸው ተሳፋሪ ከማዘን ውጭ ሌላ ምን ማድረግ ይቻለዋል?

በትራንስፖርት መጓጓዣዎች ውስጥ የሚደረጉ አንዳንድ ክንውኖች አንዳች የሚያመላክቱት የግብረ ገብ ጉድለት መኖሩን በግሌ አምናለሁ:: በዚህም ለሰው ግድ ያለመስጠት፣ ራስ ወዳድ መሆን፣ ሥራን እንደ ሥራ አክብሮ አለማየት፣ የሥነ ሥርዓት እጦት፣ እንዴት ማገልገል እና መገልገል እንደሚገባን ጠንቅቆ አለማውቅን እና ሌሎችንም ታዝቤያለሁ:: ለዚህም ይሆናል አንዳንዶቹ የሰውን መረበሽ ከምንም የማይቆጥሩት:: ብቻ ይህ ሊሆን የሚችለው በራስ ስሜት ብቻ ከመነዳት፣ ሥራን እንዴት መሥራት እንደሚገባ ጠንቅቆ ካለማወቅ የመጣ የግንዛቤ ችግር ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ::

ለማንኛውም የድምፅ ብክለት የሚከሰተው ከጭፈራ ቤቶች ብቻ ከሚወጡ ድምጾች ብቻ አይደለም፤ በተመሳሳይ ከተንቀሳቃሽ ጭፈራ ቤቶቻችን ጭምር እንጂ::

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥር 1/2016

Recommended For You