ወደብ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ሚና እንዳለው እሙን ነው:: በተለይ እንደኢትዮጵያ ላሉ ወደብ አልባ ሀገራት ደግሞ የህልውና ጉዳይ ነው:: ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት ወደብ አልባ መሆንዋ ለወጪ እና ለገቢ ንግድ የጅቡቲን ወደብ በመጠቀም ላይ ትገኛለች። ሀገሪቱ ለወደብ ኪራይ በየዓመቱ የምታወጣው ወጪ ከፍተኛ እንደሆነ ይ ነገራል::
ይህንን ችግር መፍታት ያስችል ዘንዳም መንግሥት በቅርቡ ከሱማሌ ላንድ ጋር ስምምነት አድርጓል:: ስምምነቱ ለሀገሪቷን የወደብ ጉዳይ ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነ ታምኖበታል:: የወደብ መኖር ለኢኮኖሚው እድገት ያለውን ሚና አስመልክቶ ያነጋግርናቸው የፖሊሲ ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ፣ ወደብ የውጪና የገቢ ንግድ ከማሳለጥ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራሉ::
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ወደብ ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገነባሉ:: ከቀረጥ እና ከግብር ነጻ አካባቢ ሆኖ ማምረቻ ቦታ ይሆናል:: ይህም እነ ቻይና እና አረብ ኤሜሪቶች ያደጉበት መንገድ ነው:: በተለይም ቀይባሕር ላይ በዓመት 160ሺ ቶን ዓሳ ማምረት እንደሚቻል የሚጠቅሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ይሁንና እስካሁን ድረስ በተወሰነ ደረጃ የሚጠቀሙበት ግብጽና ሳውዲ አረቢያ መሆናቸውን ያነሳሉ:: እነርሱ ደግሞ ኢኮኖሚያቸው ደህና የሚባሉ ሀገራት በመሆናቸውና የጎላ የኑሮ ችግር ስሌለባቸው ብዙም አይጠቀሙበትም ይላሉ:: ይሁንና ቀጣናው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረው ያስረዳሉ::
በሌላ በኩል ባህር ውስጥ ከፍተኛ የማዕድን ሀብቶች መኖራቸውን የሚጠቅሱት ባለሙያው፤ ሱማሌ ላንድና ፑንትላንድ ባሉበት አካባቢ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት እንዳለ መረጋገጡንም ያነሳሉ:: በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለው የሰው ኃይል ለመቀጠር ያስችላል ይላሉ:: ወደቦች እየተስፋፉ ሄደው ብዙ ኩባንያዎች ቢሮዎቻቸውን እዚያ የሚከፍቱ መሆናቸውን አንስተው፤ ይህም ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ስለሚሄዱ ወደቦች አካባቢ በብዙ ሺ የሚቆጠር የሰው ኃይል መቅጠር እንደሚያስችል ይጠቁማሉ::
በራስ ወደብና በኪራይ ወደብ መካካል ስላለው ልዩነት አስመልክተው፤ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ለተከራየችው ወደብ በየወቅቱ ገንዘብ የምትከልፈበት ሲሆን፤ አሁንም ለወደብ ኪራይ በየዓመቱ በርካታ ዶላር ወጪ እንደምታደርግ ያስረዳሉ:: በሌላ በኩል ቻይና በራሺያና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ያሉ ወደቦችን በሊዝ ወስዳ በማስተዳደር ለራሷ ጥቅም እንደምታውል ያነሳሉ:: ይህም ከኪራይ ዋጋ ሲነፃፀር ከፍተኛ እንዳልሆነ ነው የሚጠቁሙት::
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በሊዝ ደረጃ የሚያዝ ወደብ ሲኖር ደግሞ ለተወሰነ ዓመት በሊዝ የሚቆይ ሆኖ በየዓመቱ ሊዝ ይከፈልበታል:: ያም ቢሆን ግን ከኪራዩ አንፃር ዝቅተኛ የሚባል ነው:: በተጨማሪም በሊዝ መሬቱ ተወስዶ የራስ ወደብ የመገንባት አሰራር ያለ ሲሆን ይህም የገነባው ሃገር ወደብ ይሆናል:: ኢትዮጵያም ወደብ ብትገነባ የምትከፍለው ሊዝ ለመሬቱ ብቻ ይሆናል::
በዚህ መንገድ ወደብ ሲገነባ ሁለቱንም ሃገር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ያስረዳሉ:: ‹‹ምክንያቱም የሚቀጠረው የሰው ኃይል ከዚያው ሀገር ነው የሚሆነው:: ከዚህ ባሻገር በገቢና በውጪ እቃ በተለያዩ መንገዶች ገበያ የሚያገኙበት መንገድ አለ፤ በአጠቃላይ በወደብ አካባቢ የሚያድገው የንግድ ልውውጥና የሚገነባው ኢንዱስትሪ ሁለቱንም የሚጠቅም ነው የሚሆነው›› ይላሉ::
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ አብዛኛው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በሱማሌላንድና በጅቡቲ በኩል እንደሚካሄድ ያመለከቱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ የወደቡ መኖር ይህንን ችግር የማስቆም ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ባይ ናቸው:: ‹‹እንደ አገር የቀንድ ከብት፣ ቡና ፣ወርቅ የመሳሳሉ በኮንትሮባንድ መንገድ ስለሚካሄዱ ከፍተኛ የሆነ መዋለ ነዋይ እያሳጣን ነው›› ይላሉ::
ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሬት የተሰኘ ድርጅት ያወጣ መረጃ ጠቅሰውም፤‹‹በኮንትሮባንድ ንግድ ኢትዮጵያ እስከ 3ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ብር ታጣለች›› ሲሉ ይጠቁማሉ:: እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ወደቡ በሱማሌላንድ ውስጥ የሕግ ማስከበር ሥራ የሚሰራ በመሆኑ ለኮንትሮባንድ ምቹ ሁኔታ እንዳማይኖር ያስረዳሉ::
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ የንግድ መርከብ ድርጅት ያላት ሀገር መሆንዋን አስታውሰውም፤ እነዚህ መርከቦቻችን በከፍተኛ ገንዘብ ቢገዙም መርከቡ ማረፊያ ቦታ የሌላቸው በመሆኑ ለወደብ ኪራይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማውጣት መገደዷን ያመለክታሉ:: በዚህም ረገድ የራስ ወደብ በሊዝ መገኘቱ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ያስገነዝባሉ::
በሌላ በኩልም በኤደን ባሕረ ስላጤና በቀይ ባሕር አስቸጋሪ የጸጥታ ሁኔታ መኖሩን አስታውሰው ፤ይህንን ችግር መከላከል የሚያስችል የባሕር ኃይል መፍጠር ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ:: ለዚህም ወደቡ ወሳኝ እንደሆነ ነው ባለሙያው የጠቀሱት::
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ አሁን ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ተጨማሪ ወደብ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ለጂቡቲ የሚከፈለው ከ1 ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ሊቀንስልን ይችላል:: ይህ በአለም ውድ ኪራይ የሚከፈልበት የጅቡቲ ወደብ በየእለቱ ብዙ ትርምስ የሚያስተናግድ በመሆኑ የራስ ወደብ መኖሩ ሀገሪቱ ያለባትን እንግልት ያስቀርላታል:: የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ባደገ ቁጥርም ተጨማሪ ወደቦች ያስፈልጋሉ:: በተለይ የንግድ ልውውጡን አሁን ካለበት ደረጃ በላይ ለማዘመን የራስ ወደብ መገንባቱ የላቀ አስተዋፅኦ አለው:: በዚህ ረገድ የቻይና የመሳሰሉት ሃገራት ተሞክሮ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፤ ብለዋል::
‹‹በቅድሚያ ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ጋር የምታደርገው የስምምነት በዲፕሎማሲ መንገድ መምራት ይጠበቅባታል›› ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በመቀጠልም የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ::
በሌላ በኩል በከፍተኛ ወጪ የተሰራው ጅቡቲ የባቡር መስመር ወደዚህ ማዞር ሊያስፈልግ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ያነሳሉ:: ለዚህም ደግሞ ከሶማሌም ሆነ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ በተጨማሪም ሀገር ውስጥ ሰላምና መረጋገት እንዲሰፈን ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት::
ሌለኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ተባባሪ ፕሮፌሰር ከተማ በቀለ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ዋናው የአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚለካው በጂዲፒ ነው:: እንደ ኢትዮጵያ ሲታይ ለጂዲፒው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የግብርና ዘርፍ ነው:: የግብርናው ዘርፍ የሚውሉ አብዛኞቹ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጣ በመሆኑ፤ እንዲሁም የግብርና ምርቶችም ወደተለያዩ ሃገራት የሚላክ እንደመሆኑ የራስ ወደብ መኖሩን ይህንን የንግድ ልውውጥ ለማሳለጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው:: በተለይም በኪራይ ግብዓቶች የሚገቡ ከሆነ ዋጋቸው የሚጨምር በመሆኑ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ሚና ይኖረዋል::
‹‹አሁን ላይ ለጂቡቲ ወደብ ኪራይ የሚወጣው ወጪ ማዳበሪያ ላይ ዋጋ እንዲጨምር በማድረግ አርሶ አደሩ ጋር ሲደርስ ድረስ ዋጋው የጨመረ እንዲሆን ያደርገዋል›› ይላሉ:: ይህ ደግሞ አርሶ አደሩ ምርት ላይ ተደምሮ ሲቀርብ የዋጋ ንረት እንዲመጣ እንደሚያደርግ ይጠቁማሉ::
በተጨማሪም መዘግየት እንደሚፈጥር የሚያነሱት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ ‹‹የራሳችንን ወደቡ ቢኖር የሚፈለገው የግብርና ምርት ቀድሞ ማምጣት የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር ይቻል ነበር:: አሁን ላይ የወደቡ ላይ የሚከማችበትን ወጪ ላለመክፈል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማምጣት የሚቻልበት ስትራቴጂ ነው ተግባራዊ እየተደረገ ያለው:: ይህንን ስንል ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች መጉላላቶች ስለሚፈጠሩ ለምርት ጊዜ ሳይደርስ ይቀርና መዘግየት እንዲከሰት ያደርጋል›› ሲሉም ያስረዳሉ::
ከዚህም ባሻገር ወደ ውጭ የሚላከው ምርት ዋጋ የወደቡ ኪራይ ተጨምሮ ስለሚሰላ በተቀባይ ሀገራት ፍላጎት እንዲቀንስና ሌላ በተሻለ ዋጋ የሚያቀርቡ ሀገራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ምክንያት ይሆናል የሚል እምነት አላቸው:: በተመሳሳይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ምርት ላይ ዋጋ እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን አንስተው፤ በመሆኑም የወደቡ መኖርን በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት የሚያስተካክል እንደሆነም ነው ያስረዱት::
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ጋር ያደረገችው የወደብ ስምምነት የውጭና የገቢ ንግዱን ከማሳለጥ ባሻገር ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚያዊ ጥቅም አለው:: የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ስምምነት ሲያደርግ የሁለቱንም ሀገራት በማይጎዱ መልኩ የንግድ ሂደቱን ለማሳለጥ ያግዛል:: የዚህ ወደብ መኖር የጅብቲን ወደብ እንደሌላ አማራጭ ለመጠቀም ያስችላል:: ሁለቱንም ወደቦች በመያዝ አመቺ የሆነው አማራጭ በመጠቀም የንግድ ሂደቱን ለማቀላጠፍ ይረዳል::
‹‹መንግሥት በወደቡ ዙሪያ ከሱማሌላንድ ጋር ያደረገው ስምምነት ተከትሎ አሁን ላይ እየተነሱ ያሉ ጉዳዮች እልባት ሊያገኙ ይገባል›› የሚሉት ተባባሪ ፕሮፊሰሩ፤ የቀይባሕር ጉዳይ የቀጠናው ሀገራትን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ ሳይሆን ትልልቅ ሀገራት አጀንዳ እንደሆነ ያመላክታሉ:: ምክንያቱም ሲያስረዱ ‹‹የዓለማችን 12 በመቶ ሸቀጥ በቀይ ባሕር ስለሚያልፍ ነው፤ ስለዚህ መንግሥት ከሌሎች ሀገራት ጋር በምን መልኩ መሄድ እንደምችል በሰከነ መንፈስ በመወያየት የሚያስችል የዲፕሎማሲ ሥራዎች መስራት ያዋጣል›› ይላሉ::
ኢትዮጵያ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ከሰራች የሱማሌላንድ ወደብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ አማራጮችን በማስፋት መጠቀም እንደምትችል አንስተው፤ አማራጮችን ማስፋቷ ደግሞ ዘላቂና አስተማማን የወደብ አማራጭን ከማግኘት ጀምሮ ለኢኮኖሚ እድገቷ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ያስገነዘቡት::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥር 1/2016