ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮጵያየዲፕሎማሲ ጉዞ !

 ኢትዮጵያ ጥንታዊ የዲፕሎማሲ ታሪክ ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በሃይማኖት በባሕልና በንግድ እንቅስቃሴ ከበርካታ ሀገራት ጋር የጠነከረ ግንኙነት መሠረት የጣለችና በዲፕሎማሲው መስክም ተጠቃሽ ተሞክሮ ማዳበር ከመቻሏም ባሻገር ከንግሥት ሳባ እስከ ዘመነኛው የዲጂታል ዲፕሎማሲ ድረስ ዕምቅ ታሪክና ተሞክሮ ያላት ሀገር ነች፡፡

በየዘመናቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎችም ሀገሪቱን ከውጭው ዓለም ጋር የሰመረ ግንኙነት እንዲኖራትና አልፎ ተርፎም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችን ሲመሠርቱ ቆይተዋል፡፡ በዘመነ አክሱም የዲፕሎማሲ ዘመን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ መሠረቶች ተጥለዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በንጉሥ ኢዛና ዘመን ንግድና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግንኙነቶች ተፈጥረዋል፡፡

ወደ መካከለኛው ዘመን ስንመጣ የዲፕሎማሲው ዋነኛ አቅጣጫ የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነትን ማጽናት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም የሚመጡባትን የሉዓላዊነት አደጋዎች በመጋፈጥና አንድነቷን አስጠብቆ መሄድ የዲፕሎማሲው ቁልፍ አቅጣጫ ነበር፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚያጋጥማትን የሉዓላዊነት ፈተናዎች በማለፍ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ በተለይም እንደሀገር ለዲፕሎማሲና ለውጭ ግንኙነት ትኩረት ከተሰጠ 116 ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት በርካታ ፈተናዎችንና ስኬቶችን በማስመዝገብ ኢትዮጵያን ከነሙሉ ክብሯ ለዛሬው ትውልድ ለማስረከብ ተችሏል፡፡

116 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት አዳዲስ ገጽታዎችን በመላበስ አድማሱን አስፍቶ ቀጥሏል፡፡ በተለይም ለቀጣናዊ ግንኙነት የመጀመሪያውን ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራት ተደርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ወደ ሥልጣን በመጡ በጥቂት ቀናት ውስጥ የመጀመሪያ የውጭ ጉዟቸውን ያደረጉት ወደ ጎረቤት ሀገር ጂቡቲ ነው፡፡ ጂቡቲ ለኢትዮጵያ 95 በመቶ የወደብ አገልግሎት የምትሰጥ በመሆኗ እና ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚው መስክ ከፍተኛ ትስስር ያላቸው ከመሆናቸው አንጻር ከጎረቤት ሀገራት ጂቡቲን ማስቀደማቸው ተገቢ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀኑት ወደ ሱዳን ሲሆን በቀውስ ውስጥ የነበረችውን ሀገር ወደ ተሻለ መረጋጋት የሚወስድ የአስታራቂነት ሚና ተጫውታለች፡፡

ለ20 ዓመታት ያህል በጦርነት ስጋት ውስጥ የቆዩትን ኢትዮጵያንና ኤርትራን በማስታረቅና ግንኙነታቸውንም ወደ ተሻለ ደረጃ በማድረስ ቀጣናዊ ዲፕሎማሲው ወደ ከፍታ እንዲሸጋገር ኢትዮጵያ የመሪነቱን ሚና ተጫውታለች፡፡

ሌላው ባለፉት አምስት ዓመታት በዲፕሎማሲው መስክ ላይ የታየው እምርታ ኢትዮጵያ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መከተሏ ነው፡፡ አዲስ በሆነው በዚህ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በክብር ለመመለስ ችለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) በሱዳን በነበሩበት ወቅት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በእስር ቤት ይኖሩ የነበሩትን በማስፈታት በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳቸው በተሳፈሩበት አውሮፕላን ከልዑካቸው ጋር ወደ ሀገር ቤት እንዲጓዙ ማድረጋቸው መንግሥታቸው ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ ነበር፡፡

ለበርካታ ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስና የዘመናዊ ዲፕሎማሲ አዲስ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ አንዱ ክስተት ኢትዮጵያ የተከተለችው አረንጓዴ ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ32 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለዓለም ውለታ ውላለች አስደንቃለች፡፡ በእነዚሁ ዓመታት አረንጓዴ አሻራ የአካባቢው መድኅን መሆኑን በመረዳት ከራሷ አልፎ የጎረቤት ሀገራትም ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክና አብሮ በመትከልም የጋራ አካባቢን በጋራ የመጠበቅ መርሕ እውን እንዲሆን መሠረት ጥላለች፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም የጎረቤት ሀገራት በኃይል አቅርቦት እንዲተሳሰሩ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለችውም ተግባር አንዱ የኃይል አቅርቦት ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዓባይ ግድብ እና ከግልገል ግቤ ሦስት የኃይል ማመንጫዎች የምታገኘውን ኃይል ከራሷ አልፋ የጎረቤት ሀገራትን ልማት እንዲያቀላጥፍ ለኬንያ፤ ለጅቡቲ፤ ለሱዳን፤ ለደቡብ ሱዳን ኃይል በማቅረብ ላይ ትገኛለች፡፡

ዘመናትን የዋጀው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ ሀገርን አጽንቶ ሕዝብን ማዕከል አድርጎ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ዛሬም ግስጋሴውን ቀጥሎ ከሀገር አልፎ ቀጣናዊ ትስስርን ማዕከል አድርጎ ዕይታውን አስፍቷል፡፡ ከመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት አልፎ ወደ ኢኮኖሚያዊና ቀጣናዊ ትስስር የሰፋው ዲፕሎማሲዊ ግንኙኘትም አዲስ ገጽታ የተላበሰ ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያጎላ ነው!

አዲስ ዘመን ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You