ባለዘርፈ ብዙ አገልግሎት ሮቦት ፈጣሪው ተማሪ

ተማሪ በንያስ ወንደወሰን ይባላል። የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ታለንት ማዕከል ከታቀፉ ባለተሰጥኦዎች አንዱ ነው። ተማሪ በንያስ በማዕከሉ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች በመስራት ያለውን የፈጠራ ችሎታና ተሰጥኦውን እያሳየ ይገኛል። ቀደም ሲል ሁለት የፈጠራ ስራዎች ያሉት ተማሪው፤ በአሁኑ ወቅትም ቤት ውስጥ በረዳትነት የምታገለግልና የደህንነት ሥራ የምትሰራ ሮቦት ሰርቷል።

ተማሪ በንያስ ይህን የፈጠራ ሥራ ለመስራት መነሻ የሆኑት በአካባቢው የሚያያቸው ነገሮች ናቸው። በየቤቱ ከሚያየው ችግር ተነስቶ ሰውን ተክቶ በቤት ውስጥ በረዳትነት ሊያገለግል የሚችል ነገር መኖር እንዳለበት ያስባል። ይህን መስራት የሚያስችለውን አጋጣሚ አገኘናም ሀሳቡን ወደ ተግባር ቀየረው። በየአካባቢው ከሌባ ጋር ተያይዞ ከሚነሱ ስጋቶች ጀምሮ ሌሎች የአደጋ ስጋቶች በመነሳትም በደህንነት ላይ ትኩረት አድርጎ ሰርቷል።

በርካታ የፈጠራ ሀሳቦች በውስጡ ይዞ የሳይበር ታለንት ማዕከልን መቀላቀሉን የሚናገረው ተማሪ በንያስ፤ ማዕከሉ መግባቱ ከሳይበር ደህንነት ጋር በተያያዘ የሚያስበውን ሁሉ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንዳደረገው ይናገራል። ቀደም ሲልም ሁለት የሮቦት ፈጠራ ሥራዎች ሠርቶ እንደነበር አስታወሶ፤ ይህ ሮቦት ሦስተኛው የፈጠራ ስራው መሆኑን ይናገራል። የፈጠራ ሥራውን በማዕከሉ ጀምሮ እያሳደገ አሁን ያለበት ደረጃ እንደ ደረሰም ይገልጻል።

ተማሪው የፈጠራ ሥራውን ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ይሞክር፣ አገልግሎት ላይ ከማይውሉ እና ከወዳደቁ ነገሮች የፈጠራ ሥራዎች በመስራት በቅርቡ ላሉ ሰዎች ያሳያቸውም ነበር። ለፈጠራ ሥራዎች የተለየ ፍቅር ስለነበረው በትምህርት ቤቱ ያለውን እምቅ የፈጠራ ችሎታ በማሳየት ከማይጠበቁ ነገሮች የሚፈጥራቸውን የፈጠራ ሥራዎች ለመምህሮቹና ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ ያሳይ እንደነበርም ያስታውሳል። ይህን የተመለከቱ መምህራኖቹና የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ሞራል በመስጠት አበረታትውታል።

ሳይበር ታለንት ማዕከልን ከተቀላቀለ በኋላ ደግሞ በተሰጠው ስልጠናና ሙያዊ እገዛ የተነሳ ከፍ ያለ ሥራ መስራት እንደቻለ የሚገልጸው ተማሪ በንያስ፤ በዚህም በአንድ ጊዜ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት የምትችል ሮቦት መስራቱን ይገልጻል። ሮቦቷን የቤት ውስጥ ረዳትነት አገልግሎት እንድትሰጥና የደህንነት ሥራዎችን እንድትሰራ በማሰብ መስራቱን ጠቅሶ፤ ሮቦቷን ለመስራት ከተጠቀመባቸው ቁሳቁስ አንዳንዶቹ አገልግሎት ያቆሙ መሆናቸውን ይጠቁማል።

ተማሪ በንያስ እንዳብራራው፤ ሮቦቷ አይኗ አካባቢ የፊት ገጽን ፎቶ የሚያነሳ ቁስ ተገጥሞላታል፤ በዚህም እንደ ፈለገች እየተሽከረከረች የአካባቢውን ፎቶ በማንሳት ደህንነት የመጠበቅ ስራዋን ትሰራለች። ከዚህም በተጨማሪም ቤት ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ፤ በተለይም ሌባ ቢገባ ወይም ሌላ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ክስተት ቢፈጠር የሌባውን ወይም የክስተቱን እንቅስቃሴ በመመዝገብ በየአንድ ሰዓቱ ልዩነት ለሚቆጣጠራት አካል ሪፖርት ታደርጋለች፤ መልዕክቶችንም ትልካለች።

ሮቦቷ ሌሎች በርካታ ጥቅሞች እንዳላትም ተማሪ በንያስ ይገልፃል። ከሰዎች ጋር በአማርኛ ቋንቋ መግባባት ትችላለች። ሰዎች የሚያሰሙትን ድምጽ መልሳ ታሰማለች፤ ለሚቀርብላት ጥያቄ ምላሽ ትሰጣለች። ለምሳሌ ‘ሰላም’ ተብላ ሰላምታ ስትጠየቅ ‘ሰላም’ በማለት አጸፋውን እንደምትምልስ ነው ያስረዳው። በተጨማሪም ሮቦቷ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚፈለጉ ነገሮች ደህንነት እንዲትጠብቅ የተሰጣትን ኃላፊነት እንደምትወጣ ይናገራል።

ተማሪ በንያስ እንደሚለው፤ ሮቦቷ የሬዲዮ ሞገድ ደህንነት በመጠበቅ ረገድ የምትሰራው ሥራ አለ። ለሮቦቷ ሬዲዮ ማቋረጫ የ‹‹ሬዲዩ ጃመር›› ስርዓትም ተገጥሞላታል። ስለሆነም ሬዲዮ ማቋረጫ ሲስተም አገልግሎቱ የተወሰኑ ሬዲዮ ጣቢያዎች ያለፍቃድ እንዲቋረጥ ቢደረጉ፤ ሲስተማቸው ቢበላሽና በሌሎች ቁጥጥር ሥራ ቢገቡ የሬዲዮ ጣቢያዎቹ ትክክለኛ ያልሆነ ነገር እያስተላለፉ ከሆነ ሮቦቷ ወዲያወኑ በፍጥነት ሬዲዮ ጣቢያዎችን ከአየር ላይ በማውረድ እንዳይሰሩ ታደርጋለች።

ሮቦቷ ትክክለኛ ያልሆነውን የሬዲዮ ሞጎድ እንዲቋረጥ በማድረግ በምትኩ ራሷ የምትፈልገውን መረጃ ታስተላልፋለች። በዚያ ወቅት በአካባቢው ላይ ያለ ማንኛውም ያንን ሬዲዮ የሚያዳምጥ ሰው የሚሰማው ድምጽ ሮቦቷ የምታስተላልፈውን መረጃ ብቻ ይሆናል። ተማሪ በንያስ እንደሚለው፤ ሮቦቷ በሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ የነጣጠረ ጥቃት ሲፈጸም በፍጥነት ምላሽ በመስጠት ጣቢያው ያልሆነ ነገር ከማስተላለፍ እንዲቆጠብ ታደርጋለች። አድማጩም በተሳሳተ መረጃ ውዝግብ ውስጥ እንዳይገባ በማድረግ የምትጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።

በተጨማሪም የድምፅ መረጃችን ለመሰብሰብ የሚያስችለው ‹ቮይስ እስፖ› ተገጥሟላታል። ሰዎች በአዳራሽ ተሰብሰበው በሚያወሩበት ጊዜ ሮቦቷ እዚያ አካባቢ ላይ እየተዘዋወረች ያሉትን ሰዎች የሚነጋገሩትን በመሰማት ድምጻቸውን በመቅረጽ (ሪከርድ) ለሚቆጣጠራት አካል ታስተላልፋለች። ይህም በ‹ቮይስ እስፖ› አማካኝነት ለመስማት የሚፈለግ መረጃ ካለ የትም ቦታ ላይ ሮቦቷን በማስቀመጥ የሚፈለገውን መረጃ በመሰብሰብ ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው።

ሮቦቷ ያለማንም አጋዥ በራሷ ወዲያውኑ መሄድ እንድትችል ተደርጋ መስራቷን የሚገልጸው ተማሪ በንያስ፤ ሮቦቷ ራሷን ችላ በምትሄድበት ጊዜ አንዳንድ ያልተፈቀዱ ቦታዎች እንዳትገባ ለማድረግም መቆጣጠሪያ ተገጥሞለታል። ለሮቦቷ የመቆጣጠሪያ ስርአትም ተገጥሞላታል፤ ሲስተሙ የሚያገለግለው ማንኛውም ሰው ሮቦቷን እንደፈለገ መቆጣጠር እንዳይችል ለማድረግ እንደሆነም ተማሪው ይገልጻል።

እንደእሱ ማብራሪያ፤ አንድ ሰው ሮቦቷን ለመቆጣጠር ሲፈልግ የግድ ፍቃድ ማግኘት አለበት። ፍቃዱን ለማግኘት ደግሞ ለሮቦቷ የተሰጠውን የተጠቃሚ ስምና የሚስጥር ቁጥር ማወቅን ይጠይቃል። ሮቦቷን ማንኛውም ሰው ፍቃድ አግኝቶ የተጠቃሚ ስም እና የሚስጥር ቁጥሩን እስካላወቀ ድረስ ሮቦቷን ሊያዛት እንደማይችል ነው ያመለከተው።

ሮቦቷ የተሰጣትን ትክክለኛ የተጠቃሚ ስም እና የሚስጥር ቁጥር ከገባለት ግን ሥራዋን ወዲያውኑ እንደምትጀምር የጠቆመው ተማሪ በንያስ፤ ‹‹ሥራ ስትጀምር ሥራ መጀመሯን ለማሳወቅ አይኖቿ አካባቢ ያሉትን አረንጓዴ መብራት ታበራለች›› ይላል። ይህንን የምታደርገውም ‹ንቁ ነኝ፤ ለማገለገል ዝግጁ ነኝ’ ለማለት መሆኑን ይገልጻል። ይህም የምትጠቀምበት መገለጫ ቋንቋዋ እንደሆነ ነው ተማሪ በንያስ የሚያስረዳው።

በአጠቃላይ ይቺ ሮቦቷ ሁሉን የሬዲዮ ጃመር አይነቶች፣ ቮይስ እስፖ እና የተለያዩ የደህንነት መጠበቂያ ስርአቶች ስለተገጠመላት ሰዎች እነዚህን ስርአቶች ለሌላ ሕገወጥ ተግባሮች እንዳይጠቀሙባቸው ለማድረግ ደህንነቷን ለመጠበቅ የሚያስችል ሶፍትዌር ተገጥሟላታል ሲልም ያብራራል።

በሃርድ ዌር በኩልም የበር ላይ ቁልፍ በማዘጋጀት በሩ በሚከፈትበት ሰዓት ለባለቤቱ የሚጠቁም አሠራር እንደተገጠመላት ጠቅሶ፤ በባለቤቱ ስልክ ላይ በቀጥታ የመጠቆሚያ ድምጽ ለማሰማት መደወል የምትችልበትና ማስታወሻ የምትልክበት ስርአት የተገጠመላት መሆኗንም ነው ተማሪ በንያስ ያብራራል።

እንደተማሪው ገለፃ፡ ሮቦት አብዛኛው ኀብረተሰቡ ተጠቅሞባቸው አያፈልጉም ብሎ ከጣላቸው ቁሳቁስ የተሰራች ናት፤ እነዚህን ቁሳቁስ መልሶ መጠቀም እንዲቻል አድርጎ በመገጣጠም ለሮቦቷ መስሪያነት አውሏቸዋል። ለምሳሌ ፕሮግራምድ የሚደረጉ ቦርዶች አሉ። እነዚህን ቦርዶች መልሶ በማደስ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚቻሉትን ሁኔታ ፈጥሯል፤ መልሶ መጠቀም የማይቻሉትን ደግሞ ገዝቶ ተጠቅሟል። የተጣሉ ሆነው ምንም ጥገና ሳይደረግላቸው መልሶ አግልገሎት ሊውሉ የሚችሉትን የተጠቀመበት ሁኔታም አለ።

የተማሪ በንያስ የፈጠራ ሥራ የሆነችው ይቺ ሮቦት ከሌሎች በውጭ ኀገራት ከተሰሩ ሮቦቶች በብዙ መልኩ ልዩነት አሏት። ተማሪ በንያስ እንደሚለው፤ እስካሁን የተሰሩትና አገልግሎት ላይ የዋሉት ሮቦቶች የተሰሩት አንድ አይነት አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቦ ነው፤ በመሆኑም አንድ አይነት አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ናቸው። ለምሳሌ ለቤት ውስጥ ደህንነት አገልግሎት እንዲሰጥ የተሰራ ሮቦት አገልግሎት የሚሰጠው ለቤት ውስጥ ደህንነት መጠበቅ ብቻ ነው። ሌላ ተጨማሪ ሥራዎችን ሊሰራ አይችልም። ይቺ ሮቦት ግን በአንድ ጊዜ ብዙ አገልግሎቶች መስጠት ትችላለች። ‹‹የፈለግነውን ትዕዛዝ በመስጠት እንድትሰራ የምንፈልገውን ሥራ ማሰራት እንችላለን ››ይላል።

ሮቦቷ ውጭ ሀገር ከሚመረቱት ሮቦቶች አንጻር ስትታይ በዋጋም በኩል ቢሆን በተመጣጣኝ ዋጋ የምትሰራ መሆኗን ጠቅሶ፣ በአብዛኛው ጥቅም ላይ ከዋሉ ቁሳቁስ መሰራቷም በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሰራቷ እንዱ ምክንያት መሆኑን ይገልጻል። ይቺን ሮቦቷን ሰርቶ ለማጠናቀቅ እስከ 50ሺ ብር ወጪ እንደተደረገም ተማሪ በንያስ አስታውቋል።

ይህ ታዳጊ የፈጠራ ባለሙያ በሳይበር ታለንት ማዕከሉ ከገባ በኋላ የሰራትን ይህችን ሮቦት ሰርቶ እንደ ጨረሰ እዚያ ላሉት የማዕከሉ አካላት አሳይቷል፤ ‹‹ሮቦቷን ሰርቼ ስጨርስ በማዕከሉ ላሉት አካላት ሳሳያቸው፤ በአድናቆት ተመልክተዋታል›› ሲልም ይገልጻል። ከዚያም ለሮቦቷ አስፈላጊ የሆኑ ፍተሻዎችና ሙከራዎች ተደርገው ጥቅም ላይ መዋል እንደምትችል ተረጋግጧል›› ይላል። ሮቦቷ የፍተሻ ሥራዋን እንደጨረሰች አገልግሎት ላይ መዋል እንደምትችል ታሞኖበት ለእይታ እንድትበቃ መደረጉንም ነው ያመለከተው።

በቀጣይ ሮቦቷን በማምረት ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ እንደሚሰራ የተናገረው ተማሪ በንያስ፤ ‹‹ሮቦቶቹ ተምረተው በእያንዳንዱ ሰው ቤት በቤት ውስጥ ረዳትነት አለያም በተለያዩ የደህንነት ጥበቃ ሥራ ላይ አገልግሎት ሊሰጡ ይቻላሉ ብሎ አምናለሁ›› ይላል።

አሁን የሰራት ሦስተኛዋ ሮቦት ቀደም ሲል በሙከራ ደረጃ ከሰራቸው ሁለት ሮቦቶች በብዙ መልኩ የተሻለ እውቀትና አቅም የታከለባት መሆኑን ይናገራል። ወደፊትም የተሻለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተሻለ ሥራ ለመስራት እቅድ እንዳለው ጠቅሶ፤ ልክ እንደሰው ልጅ ስሜትን የሚጋሩ እንደነሶፊያ ያሉ ሮቦቶችን የመስራት ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2016

Recommended For You