ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትጠቀምባቸው የቆየቻቸውን የባሕር በሮች ካጣች ወዲህ የባሕር በር ጉዳይ አንገብጋቢ ሆኖባታል። ሀገሪቱ የባሕር በር እጦቱን ወደብ በኪራይ በመጠቀም ለመሻገር ብዙ ሞክራለች። ላለፉት ከሠላሳ ዓመታት በላይም በእዚህ መንገድ ነበር የወጪ ገቢ ሸቀጦችንና ምርቶችን ስታስናግድ የኖረችው።
ለእዚህ የወደብ ኪራይም በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ስታወጣ መቆየቷን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ወጪ ለሀገሪቱ አዲስ ወጪ ነው። ለተለያዩ ልማታዊና ሰብዓዊ ጉዳዮች ልታውለው የሚገባትን ይህን ሀብትም ነው ስትገፈግፍ የቆየችው።
ወደብ ከአንድ ሀገር አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 25 በመቶውን እንደሚሸፍን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህም በእጅጉ የሚያምና አልምቶ መና እንደመቅረት የሚቆጠር ነው። የወደብ አለመኖር ይህችን ሀገር ምን ያህል እንደጎዳት እነዚህ ሁለት አብነቶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።
ሀገሪቱ የተያያዘችው የልማት አቅጣጫ የወደብ ፍላጎቷ በየጊዜው እየጨመረ እንዲሄድ የሚጠይቅ ነው። በግብርና፣ በኢንዱስትሪው፣ በማዕድን ዘርፍ የምታካሂዳቸው ሰፋፊ ልማቶች የወደብ ፍላጎቷን በእጅጉ እንደሚጨምሩት ይጠበቃል። ከእነዚህ ዘርፎች የሚገኘውን ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ፣ ዘርፎቹን ለማልማት የሚያስፈልጉትን ማሽነሪዎች፣ ግብዓቶች ወዘተ. ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የባሕር በር በእጅጉ ያስፈልጋል።
ሀገሪቱ እያደገች ስትሄድ፣ የሕዝብ ብዛቷ ሲጨምር የገቢና ወጪ ንግዱም በዚያው ልክ ይጨምራል። በዚህ እንቅስቃሴ የሚወጣውንና የሚገባውን ሸቀጥና ምርት በተሳለጠ መልኩ ማስተናገድ ያስፈልጋል። ፍሰቱ የተሳለጠ መሆን ብቻ አይደለም ያለበት፤ ደኅንነቱም የተጠበቀ ሊሆን የግድ ይላል።
በሌሎች ዘርፎች ለሚካሄዱ ልማቶች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማቅረብ ዋናው መሣሪያ የባሕር በር ነው። ቴሌኮም፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ወዘተ ለማስፋፋት፣ የግንባታውን ዘርፍ ለማሳለጥ፣ የትራንስፖርት መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት የባሕር በር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።
ኢትዮጵያ በልማቱ እያካሄደቻቸው የምትገኛቸውና የምታካሂዳቸው ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉ ልማቶች ያለወደብ ብዙ ርቀት ሊጓዙ አይችሉም፤ አትራፊነታቸውም፣ የዜጎች ተጠቃሚነትም እንዲሁ ያጠራጥራል። አርቆ ለሚያስብ፣ ያለፉትን ፈተናዎች በሚገባ ለተመለከተ መንግሥትና ሕዝብ ደግሞ የባሕር በር ጉዳይ ከምንም በላይ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተግባሮች አንዱ ነው።
ሀገሪቱ በኪራይ የወደብ አገልግሎት ማግኘትን በሚገባ ሠርታበታለች፤ የጅቡቲ ወደብን በሚገባ በመጠቀምም ልማቷን ስታሳልጥ ቆይታለች። አማራጭ ወደቦችን ለማግኘትም ብዙ ሞክራለች፤ ሶማሊያ በርበራን፣ ፖርት ሱዳንን ፣ የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን ለመጠቀም ብዙ ጥራለች። ለሀገሪቱ ሲያገለግል የቆየው የጅቡቲ ወደብ ብቻ ነው። ይህን ሁሉ ስታደርግ የቆየችው ልማቱ እንደሚጠይቃት ስለምትረዳ ነው።
የባሕር በር ጉዳይ በእጅጉ ሲያሳስበው የቆየው መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎታል፤ በቅርቡም ጉዳዩ አንገብጋቢ መሆኑን በመጠቀስ ዜጎች የባሕር በር በሰላማዊ መንገድ ማግኘት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ እንዲወያይ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም ሕዝቡ ፊትም የባሕር በር አጥብቆ ሲጠይቅ የኖረ እንደመሆኑ የባሕር በር ጉዳይን አጀንዳው አድርጎታል።
መንግሥት በቅርቡ ደግሞ የባሕር በር በሊዝ ማግኘት የሚቻልበትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር ተፈራርሟል። ስምምነቱም ለባሕር በር የሚያስፈልገውን ቦታ በሊዝ ማግኘት የሚያስችል ነው። ስምምነቱ በአጸፋው የሶማሌ ላንድ ከኢትዮጵያ የልማት ድርጅቶች የአንዱ ባለድርሻ እንድትሆን ያስችላታል።
ይህ ሀገሪቱ ዘላቂ በሆነ መልኩ የባሕር በር ባለቤት እንድታገኝ የሚያስችል ውሳኔ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ይዞ እንደሚመጣ ከወዲሁ መናገር ይቻላል። ይዞት የመጣው ዕድል ብዙ ነው። የሀገሪቱን ዕድገት ዘላቂ ማድረግ ያስችላል፤ ሀገርን ከወደብ ኪራይ ይታደጋል፣ ሀገሪቱ ባሕር ላይ የምትንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለደህንነትም ዋስትና ይሆናል። በአካባቢው ካሉ ሀገሮች ጋር አብሮ መልማት እንደሚቻልም ማሳያ ሊሆን ይችላል።
የሀገሪቱ የባሕር በር በሊዝ የመያዝ ስምምነት በዓለም አቀፍ ደረጃም ይሠራበታል። የተለያዩ ሀገሮች የባሕር በር በሊዝ ይዘው እየሠሩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ያደረገችው ይህንኑ ነው። መንግሥት ይህን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ አምጥቶ ለሀገር የሚበጅ ዘላቂ የወደብ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል ውሳኔ ላይ መድረሱ በወሳኝ ወቅት የተወሰደ ትክክለኛ ርምጃ ነው።
120 ሚሊዮን ሕዝብ ይዞ በአንድ ወደብ ላይ ተረጋግቶ መኖር ይከብዳል፤ ለዚያውም በኪራይ። በግብርናው በኢንዱስትሪውና በማዕድን ዘርፍ የሚደረጉ ልማቶች የሚያስገኙትን ውጤት እንደልብ ማውጣት፣ ለብልጽግና ጉዞ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት የሚያስችል የባሕር በር በሌለበት ሁኔታ ልማቱን ዘላቂ ማድረግም ፈታኝ ይሆናል።
የባሕር በር አለመኖር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ሊገፋ እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ይሄ ደግሞ ዓለም የሚሻማበትን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መግፋት ይሆናል። ኢንቨስተሮች የባሕር በር፣ የሸቀጣቸው ደህንነት እንዲጠበቅና ርካሽ የማጓጓዣ አገልግሎት ይፈልጋሉ፤ ርካሹ የማጓጓዣ ትራንስፖርት ከሆነው የባሕር ትራንስፖርት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያደርጋል። የባሕር በር መኖሩ እነዚህን ችግሮች ሁሉ ይፈታል።
የምጣኔ ሀብቱን እድገት የሕዝብ ብዛቱን እየጨመረ መምጣት ተከትሎ የሚፈጠሩ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ልማቶችና አገልግሎቶችን ለማድረስም ዘላቂ የባሕር በር መኖሩ የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከሶማሌ ላንድ ጋር የደረሰበት ስምምነት ፋይዳ ከፍተኛና ለዘላቂ ልማትም ዋስትና ነው!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2016