ኢትዮጵያ የራሷ ድንቅ ባህል፣ ትውፊት፣ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች፣ ባህላዊ የዳኝነት ስርአቶች፣ ሀይማኖታዊና ባህላዊ በአላት፣ ጥበባት፣ ቋንቋዎች፣ ታሪክ …. ወዘተ ያሏት ታላቅ ሀገር መሆኗ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይነገራል። እነዚህ ከሀገር አልፈው አለምን ጭምር ያስደመሙ ባህላዊ ትውፊቶችና ሀይማኖታዊ ስርአቶች ማህበረሰቡን በመልካም ስነ-ምግባር በማነፅና በዘመን ሂደት ስርአቱን ጠብቆ እንዲሄድ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፤ እየተጫወቱም ይገኛሉ። የማህበረሰብ አውቀትና ስብዕና በዘመናዊ የቀለም ትምህርት ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ባህላዊ ትውፊቶችና ልዩ ልዩ ሀይማኖታዊ ስርአቶችም ጭምር እንደሚገነባ አሳይተዋል፤እያሳዩም ነው።
ነገር ግን እነዚህ ኢትዮጵያዊ መልካም ባህሎችና እሴቶች በዘመን አመጣሽ የውጪ ባህሎች እየተወረሩና ህልውናቸውም ጭምር አደጋ ላይ እየወደቀ መጥቷል። በተለይ በዚህ ዘመነ ግሎባላይዜሽን አለም ወደ ትንሽ መንደር እየተቀየረች ባለችበት ግዜ በሀገራት መካከል ከፍተኛ የባህል መወራረስ ይስተዋላል። በርግጥ በግሎባላይዜሽን በሀገራት መካከል መልካም ተሞከሮዎቸና አሰራሮች ይወረሳሉ። የዛኑ ያህል ደግሞ በምእራባዊያኑ በኩል እንደ ዘመናዊነትና ስልጣኔ የሚቆጠሩ ባህልና ልምዶች መልካምና ማህበረሰብን የሚያርቁ ባህል ባሏቸው ሀገራት እየተወረሱ በብዙ መልኩ ጉዳት እያመጡ ነው።
በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያን የመሰሉ የመልካም ባህልና እሴት ባለቤት የሆኑ ሀገራት የእነሱ ባልሆኑና ከወግና ስርአት ባፈነገጡ፣ መጤ ባህሎች ክፉኛ እየተወረወሩ ይገኛሉ። የዚህ ዘመን ትውልዳቸውም ወግና ስርአቱን ለቆ የውጪ ባህል ወርሶ አስተሳሰቡ፣ የኑሮ ዘይቤውና ሌሎቹም ድርጊቶቹ ተለውጠዋል። ጠንካራ ወግና ስርአት የነበራት ኢትዮጵያ ዛሬ ዛሬ ትውልዷ በመጤ የውጪ ባህል ተሸብቦ አነጋገሩ፣ አካሄዱ፣ አስተሳሰቡ፣ አበላሉ፣ ሁለንተናዊ ድርጊቱ፣ ሁሉ ነገሩ የውጪዎቹን ሆኗል። ክፋቱ ደግሞ ትውልዱ እነዚህን የውጪ ባህሎችና አስተሳሰቦች ሳይመረምርና በቅጡ ሳይረዳ፤ እንዲሁ በግርድፉ ሳያላምጥ መዋጡ ነው።
ይህ ክስተት ነው እንግዲህ መልካሙን ሀገራዊ እሴትንና ባህልን እየጎዳ ያለው። ይህ ነው በተለይ ወጣቱን ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እየመራ ያለው። ድሮ ድሮ ታላላቆችን ማክበር ማንኛውም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ግራ ቀኝ ሳያይና ሳያመነታ የሚተገብረው በጎ ባህል ነበር። በፀብ መሀከል ገላጋይ ቢገባ ይሰማል። ጠብ ወይም ግጭት ተነስቶ ሽማግሌዎች ኧረ ሀይ! ቢሉ ተሰሚነት ነበራቸው። ሰው ሲቸገር መረዳት፣ ሲያጣ ማገዝ፣ ሲራብና ሲታረዝ ማብላትና ማጣት፣ የጋራ ጠላትን በጋራ መመከት፣ አንድነት፣ መተባበርና መረዳዳት ድንቅ ኢትዮጵያዊ ባህል ነበር።
ነገር ግን፣ አሁን ላይ እንደ ፋሽንና ስልጣኔ ተቆጥሮ ሰውን መናቅ፣ ማንቋሸሽ፣ መስደብና ማዋረድ ባህል እየሆነ መጥቷል። ሰብአዊነትን አስቀድሞ ሰውን መረዳትና ማገዝ እንደ ኋላቀርነት እየቶጠረ ነው። ሰው ሲጣላ መገላገል ‹‹ጎመን በጤና″፣ “ከመሞት መሰንበት››ን በመሳሰሉ አባባሎች ተተክቷል። አብሮ መብላትና መጣት ኢትዮጵያዊ ባህል መሆኑ ከቀረ ሰንብቷል። ሽማግሌ መስማት ቀርቷል። አንድነትና በጋራ ችግሮችን መጋፈጥ የማይሞከር ሆኗል።
መልካም ባህላቸውንና ስርአታቸውን ጠብቀው ትውልዳቸውን በስርአትና በመልካም ስብእና የገነቡ ሀገራት ዛሬ በሁለንተናዊ መልኩ ለሌች ሀገራት ምሳሌ መሆን ችለዋል። ስነ ምግባር ላይ ትኩረት አድርገው ትውልዳቸው ላይ በመስራታቸው በምንም የማይለወጥ ጠንካራ ማህበረሰብ መገንባት ችለዋል። ይህም አሁን ለደረሱበት የኢኮኖሚ እድገትም ሆነ በቀጣይ ሀገራቸውን የሚፈለገው የእድገት ደረጃ ላይ ለማስቀመጥ በእጅጉ ጠቅሟቸዋል።
ከዚህ በተቃራኒ ጥሩ የባህል፣ እውቀትና ማንነት መሰረት የነበራቸው ሀገራት የራሳቸውን ትተው እርባና ቢስና መጤ ባህሎችን በመውረሳቸው በግራ መጋባት ውስጥ እየናወዙ ነው። ይህ መጤ ባህል በራሳቸው መንገድ ራሳቸውን ከመለውጥ ይልቅ የእነርሱ ባልሆነ መጤ ባህል እንዲያስቡ፣ እንዲራመዱና እንዲወስኑ እያስገደዳቸው ይገኛል። የመጥፎ ባህሎች ቁራኛ ሆነው ወዴት አቅጣጫ መጓዝ እንዳለባቸው እንኳን ካርታው ጠፍቶባቸዋል። ትውልዳቸውም የውጪ ሀገር ባህል ናፋቂ ሆኖና የራሱን ባህልና ማንነት ረስቶ ራሱን እንደ ዘመናዊ እየቆጠረ ጉዞዬ ሁሉ በዚሁ አዲስ ባህልና ማንነት መሰረት ነው የሚቀጥለው፤ በቃ! አሻፈረኝ ካለ ሰነበተ። ኢትዮጵያም ትውልዷ የዚሁ መጤ ባህል ሰለባ ከሆነ ሰነባብቷል። ተውልዱ ኢትዮጵያዊ ማንነቱ እስኪቀየር ድረስ የዚሁ መጤ ባህል አምላኪ ከሆነ ውሎ አድሯል።
አለም ላይ ባደጉት ሀገራት የተፈጠሩና ህይወትን በሁለንተናዊ መልኩ ሊቀይሩ የሚችሉ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የፈጠራ ግኝቶች፣ አዳዲስ አሰራሮችና ጠንካራ የስራ ባህሎች ተበርክተዋል። እነዚህ ለየትኛውም ሀገር የሚጠቅሙና በልዩ ልዩ መልኩ ህዝብና ሀገርን ሊለውጡ የሚችሉ በመሆናቸው ጥቅም ላይ መዋላቸው አይከፋም። ግን ደግሞ ለማህበረሰቡ የማይጠቅሙና ሀገርንና ህዝብን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የሚመሩ መጤ ባህሎችና የማይሆኑ አስተሳሰቦች መገፋት እንጂ በትውልዱ መወረስ የለባቸውም። ትውልዱም መልካም የሚባሉ ኢትዮጵያዊ ባህሎችንና እሴቶችን አውቆና መርምሮ በእነዚሁ እሳቤ ተቀርፆ፣ ጉዞውን አስተካክሎ መራመድ ይኖርበታል።
ስለዚህ አሁንም ቢሆን አልረፈደም። ትውልዱን ወደራሱ ማንነት የመመለስ እድል አለ። ትውልዱ ወደ ራሱ ኢትዮጵያዊ ማንነትና አስተሳሰብ እንዲመጣ ግን ሁሉም የየራሱ ሀላፊነትና ድርሻ አለው። ለዚህም ወላጆች፣ መምህራን፣ ቤተሰብና ጎረቤት፤ ብሎም ራሱ ትውልዱ የየራሳቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ደግሞ መምህራንና ወላጆች ትውልዱ በስነ ምግባር ተቀርፆ እንዲያድግና መልካም ስብእናን ተላብሶ ለሀገርና ህዝብ ጠቃሚ ስራ ሰርቶ እንዲያልፍ ከፍተኛ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል።
ከዚህ በዘለለ፣ ከዚህ ትውልድ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ጎረቤቶች፣ ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፋሎች ትውልዱን በጨዋ ደምብ ገስፆና ሸንቁጦ የማሳደግ ሀገራዊ ሀላፊነት አለባቸው። የሃይማኖት አባቶችም ቢሆኑ ሀይማኖታዊ ስርአቱ በሚፈቅደው ልክ ትውልዱን በስነ ምግባር የማነፅ፣ የማስተማርና በትክክለኛው አቅጣጫ እንዲጓዝ የማድረግ ድርብ ሀላፊነት አለባቸው። መንግስትም ቢሆን ለሀገር አሳቢና ተቆርቋሪ ትውልድ በመገንባት ረገድ የራሱ ሀላፊነት እንዳለበት ተረድቶ ትውልዱ ከዚህ መጥፎ መጤ ባህል መጠናወት እንዲላቀቅ ታላቅ ሀገራዊ ሀላፊነት አለበት። ተውልዱን ወደ ቀልቡ የመመለስ ጉዳይ ግን ለነገ የማይባልና አሁኑኑ ሊሰራበት የሚገባ ተግባር ነው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን 2016 ዓ.ም