‹‹የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕጎች የሚደግፉት ነው ›› አቶ በፈቃዱ ድሪባ – በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር

በኢትዮጵያ አዲስ የመንግስት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በትኩረት ከሰራባቸውና ለውጥ ካመጣባቸው ጉዳዮች አንዱ የባህር በር ጥያቄ ነው። መንግስት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባህር በር ጣያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። ለ27 አመታት ያህል ፈርሶ የቆየውን የባህር ኃይል እንደገና በማደራጀት ኢትዮጵያ እንደገና የባህር ኃይል እንዲኖራት አድርጓል።

ሰሞኑንም ከሶማሊ ላንድ ጋር ስምምነት በማድረግ ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝባቸውን አማራጮች አስፍቷል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ያነሳችው የባህር በር ጣያቄ ከዓለም አቀፉ የህግ እሳቤ አንጻር እንዴት ይታያል?ተቀባይነቱስ እንዴት ይረጋገጣል? ከሶማሊ ላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ(Memorandum of understanding) ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል? ስንል በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር የሆኑትን አቶ በፍቃዱ ድሪባን አነጋግረናል።

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የነበራት የባለቤትነት ድርሻ እንዴት ይገለጻል ?

መምህር በፍቃዱ ድሪባ፦ ኢትዮጵያን ያለቀይባህር ፤ቀይባህርንም ያለኢትዮጵያ ማሰብ አይቻልም። ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንደነበረች በመጀመር የታወቀው ከ100 እስከ 150 ዓ.ም የተጻፈው ተህ ፒሪፒለስ ኢቭ ዘኤርትርያን ሲ በተሰኘው መጽሃፍ ነው። ይህ መጽሃፍ የአክሱም መነግስት በቀይባህር መጠነ ሰፊ ንግድ ሲያከናውን እንደነበር ያትታል። አዶሊስም ዋነኛው ወደን እንደነበረም ያስረዳል። እስከቀርብ ጊዜ ድረስም ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ዋነኛ ተዋናይና ገናና እንደነበረች የሚያስረዱ በርካታ የታሪከ ድርሳናት አሉ።

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የነበራትን የባለቤትነት ድርሻ እንድትዘነጋ የተደረገው በተሳሳተ ትርክት ነው። ይባላል ይሄንን ቢያብራሩልን ?

መምህር በፍቃዱ ድሪባ፦ በትርክት የነበረን እውነታ መቀየር ባይቻልም ማንሻፈፍ ግን ይቻላል። ከባህር በር ተያይዞ ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር የትርክ መንሻፈፍ ነው። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ላይ ይዞታ የነበራትና ቀይ ባህርንም ስታዝበት የኖረች ሀገር ነች። 1ሺ800 ኪሎሜትር የሚረዝመውን የቀይ ባህር ይዞታ በቁጥጥሯ ስራ ያኖረችና ለወጭና ገቢ እቃዎች ሁለት ወደቦች የምታስተዳደር ሀገር ነበረች። ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ውጪ ቀይባህርንም ከኢትዮጵያ ውጭ ማሰብ አይቻልም ነበር።

ሆኖም የኢትዮጵያን ማደግ የማይፈልጉ ኃይላትና በየጊዜውም በውስጥ በነበሩ ቅራኔዎች በተፈጠረ ክፍተት ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትወገድ ተደርጓል። ለዘመናትም ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ምንም ድርሻ እንዳልነበራት ሆን ተብሎ በተሰራጨው ትርክት መብቷን እንኳን ለመጠየቅ ስትሸማቀቅ ቆይታለች። ለዚሁ አንዱ ማሳያ ባለፉት 30 አመታት ሰለወደብና ባህር በር ማውራትም ሆነ የኢትዮጵያን የባለቤትንት መብት መጠይቅ እንደነውር ከማስቆጠሩም በላይ አደጋም የሚያስከትል ነበር።

በእነዚሁ አመታት ከባህር በር ጋር የተያያዙ ጥናቶችና ምርምሮች ሁሉ ታግደው ቆይተዋል። ስለባህር በር የሚያወሩ ሰዎችም እንደሀገር ጠላት ይታዩ ነበር።

በተሰራባት ሴራና ሆን ተብለው በተፈጠሩ ትርክቶች ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ተጋልጣለች። ይህም ባለፉት 30 አመታት የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድም ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል። ለበርካታ መሰረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ልማቶችን ይውል የነበረውን ከ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየአመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለኪራይና ለመጓጓዣ ከፍተኛ ዶላር ስለምታፈስ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።

በዲፕሎማሲ እና በተጽዕኖ ፈጣሪነትም ረገድ የኢትጵያ ሚና አሽቆልቁሏል። ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ በአለም እጅግ ተፈላጊ ከሆኑትና የሃያላን ሀገራትንም ቀልብ የሚስብ በመሆኑ እድገቷን የማይፈልጉ አካላት በተቀነባበረ ሴራ ከቀይ ባህር እስኪያርቋት ድረስ ገናና እና በሁሉም ዘንድ ተፈላጊ ሆና ቆይታለች። ሆኖም ሀገሪቱ ወደብ አልባ ከሆነች ጀምሮ ተፈላጊነቷ አሽቆልቁሏል፤በምትኩም ጅቡቲን የመሳሰሉ ትናሽ ሀገራት የበለጠ ተፈላጊና ተደማጭ ሆነዋል።

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ የባህር ለማግኘት የተለያዩ አማራጮችን እየፈለገች ነው ለመሆኑ ኢትዮጵያ ያነሳችው ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ህጎች አንጻር ምን ያህል ተቀባይነት አለው?

መምህር በፍቃዱ ድሪባ፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑት16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ህጋዊ መሰረት የሌላቸው ናቸው። ኢትዮጵያ በውሃ ሃብት በአለም ላይ ከሚታወቁት ሀገራት አንዷ ስትሆን አፈጣጠሯም ከውሃ ጋር የተያያዘ ነው። የዓባይ ወንዝ መነሻና በቀይባህር ዳርቻ መገኘቷ የዚሁ አመክንዮ ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ በአለም ላይ የባህር በር ከሌላቸው 44 ሀገራት አንዷ ነች። በአፍሪካም ካሉት 16 የባህር በር ከሌላቸው ሀገራትም ታርታ ትሰለፋለች። ሆኖም ኢትዮጵያ ከእነዚሁ ሀገራት የሚለዪዋት በርካታ ነገሮች አሉ። አንደኛው የህዝብ ቁጥሯ ነው። በአሁኑ ወቀት የኢትዮጵያ ህዝብ 126 ሚሊዮን ደርሷል። በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የሚኖረው ህዝብ የባህር በር የሌላቸውን ሀገራት ህዝብ 1/3ኛውን ይሸፍናል።

ይሄንን የሚያህል ህዝብ ይዞ የባህር በርና ወደብ የተነፈገ ሀገር የለም። ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ በባህር በር የተከበበች ሀገር ነች። ከላይ እንደጠቀስኩት በሴራ እና በተሳሳተ ትርክት ከቀይ ባህር እንድትርቅ ከመደረጓ በስተቀር በአፈጣጠሯ ለቀይ ባህር የቀረበ ነው። በሶስተኛ ደረጃ በታሪክም በቀይ ባህር ላይ ለዘመናት የበላይ ሆና መቆየቷን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ያሏት ሀገር ነች።

ስለዚህም ኢትዮጵያ በግፍ ከይዞታዋ እንድትነቀል ከመደረጓ ውጪ ባለቤተነቷን የሚከለክላት አንዳችም ዓለም አቀፍ ህግ የለም። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችበትም ሆነ ከቀይ ባህር እንድትወገድ የተደረገበት አካሄድ ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት የሌለው ነው። ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትወገድና ወደብ አልባ እንድትሆን የተደረገውበ1900፤ 1902 እና 1908 ከቅኝ ገዚዎች በተደረጉ ውሎች አማካኝነት ነው። እነዚህ ውሎች ደግሞ በተባበሩት መንግስታት መመስረቻ ቻርተር ህጋዊነታቸውን አጥተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲቋቋም ካወጣቸው ድጋጌዎች አንዱ ሀገራት የቅኝ ግዛት ውሎችን የመቀበል ግዴታ እንደሌለባቸው የሚደነግገው አንቀጽ አንዱ ሲሆን ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሀገር ካለመሆኗም ባሻገር በቅኝ ገዢዎች የተረቀቁትን የ1900፤ 1902 እና 1908 ውሎችን የመቀበል ግዴታም የለባትም።

በዚሁ መሰረት አንደኛ ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብት አላት(Access to the sea) ። ሁለተኛ ደግሞ የባህር በር ባለቤትነት መብት (Maritime sovernity) ያላት ሀገር ነች። ኢትዮጵያ እነዚህ መብቶች የመጎናጸፍ መብት ያላት በመሆኑ ያነሳቻቸው ጥያቄዎች ህጋዊ መሰረት ያላቸው ናቸው።

ሆኖም እነዚህን መብቶች ለማረጋገጥ አለም አቀፍ ህጎች ምን ይላሉ የሚለውን መፈተሽ ተገቢ ነው። አለም አቀፍ ህጎች በሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚዳኝ እና የሚያስተዳደሩ ህጎች ናቸው። በሁለት ሀገራት መካለል ያለውን ግንኑነት የሚዳኙና ችሮችም ሲያጋጥሙ ውሳኔ የሚሰጡ ናቸው። አለም አቀፍ ህጎች የሚመነጩት ሀገራት ካደረጓቸው ውሎች ነው።

የአለም አቀፍ ውሎችን ስንመለከት ኢትጵያን የባህር በር የሚያሣጣት ወይም እንዳታገኝ የሚያግዳት አንዳችም ነገር የለም። በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት መመስረቻ ጽሁፍ አንቀጽ 38 ላይ በግልጽ እንደተደነገገው አንድ ሀገር በተዛባ መልኩ ኢፍትሃዊ ውሳኔ ተወስኖብኛል ብሎ ካሰበ ጥያቄውን ማቅረብና መሟገት ይችላል።

ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ከሆነችባቸው ውሎች መካከል የቅኝ ግዛት ውሎች ተጠቃሾች ናቸው። ከአጼ ሚኒሊክ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከቅኝ ገዚዎች ጋር ያደረገቻችው ስምምነቶች የባህር በሯን እንዳሳጧት ይነገራል። የቅኝ ግዛት ስምምነቶች በባህሪያቸው ቅኝ ሲገዙ የነበሩ ኃይሎች በአስገዳጅ መልኩ ቀኝ ገዢዎች ላይ የፈጸሙት ደባ ነው። ስለዚህም ውል ከማለት ይልቅ በጉልበተኛና በደካማ መካከል የተፈጸመ አስገዳጅ ስምምነት ነው ማለት ይቻላል። እነዚህ ውሎች የቅኝ ገዢዎችን እንጂ የተገዢዎችን ሙሉ ፈቃደኝነት የያዙ አይደሉም።

ስለዚህም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው የ1900፤የ1902 እና የ1908 ውሎች ገዢ ውሎች አይደሉም፤ስለዚህም ተፈጻሚነት አይኖራቸውም። እነዚህ ውሎች በተባበሩት መንግስታት ማቋቋሚያ ቻርተር ላይም ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው በግልጽ ተደንግጓል። ለዚህም በዋነኝነት ምክንያት ተደርገው ከተቀመጡት ውስጥ አንደኛ የቅኝ ግዛት ውሎች ያለቅኝ ተገዢው ፍላጎት በጉልበት የተፈጸመ መሆኑ ነው። ቅኝ ገዢዎች ኃይልን በመጠቀምና አንዲት ሉኣላዊ ሀገርን በማስገደድ ውል ሲፈጽሙ ኖረዋል። ይህም በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት ሲቋቋም መጀመርያ ውድቅ ካደረጋቸው የህግ ክፍሎች መካከል የቅኝ ግዛት ውሎችና ስምምነቶችን በተመለከተ ነው።

ጣሊያንና ኢትዮጵያ የ1900፤የ1902 እና የ1908 ውሎችን ሲፈራረሙ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት ክፉኛ የተንቀሳቀሱበት ውቅት ነበር። በዚሁ ጊዜ እንግሊዝ፤ፈረንሳይና ጀርመን የበኩላቸውን ድርሻ ሲይዙ አንድም ቅኝ ግዛት ያላገኘችው ጣሊያን ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ አዞረች። ጣሊያንንም በመደገፍ እንግሊዝና ፈረንሳይም በኩላቸውን ድጋፍ ያደርጉ ነበር። የወልወሉ ጥቃትም የዚሁ አንዱ መሳያ ነው።

በበርካታ ቦታዎች የተወጠረችው ኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳ ለማግኘት እነዚህን ውሎች በአስገዳጅነት ለመፈረም በቃች። አጼ ሚኒሊክ እነዚህን ውሎች የፈረሙት በነበረባቸው ጫና ተገደው ነው። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፤በጦር ኃይልና በዲፕሎማሲ እነዚህን ኀይላት የመገዳደር በቃት አልነበራትም። ስለዚህም ተገዳ ስምነቶችን ለመፈረም በቃች። አንድን ተዋዋይ አስገድዶ ማስፈረም ህገወጥ ከመሆኑም በላይ በህግ ፊትም ተቀባይነት አይኖረውም። እኤአ በ1994 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተደነገገው የውል ህግ አንቀጽ 39 አንድ ተዋዋይ ውል ውስጥ እንዲገባ ማስፈራራት ውሉ ፍርስ እንደሚሆን ይደነግጋል።

አዲስ ዘመን፦ ቅኝ ግዛት ውሎችን አሁንም እንደሚሰሩና ኢትዮጵያም የባህር በር እንዳታገኝ እንቅፋት እንደሚሆኑባት የሚከራከሩ ወገኖች አሉ፤እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?

መምህር በፈቃዱ ድሪባ ፦ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ አንዳንድ ግለሰቦች ቅኝ ግዛት ውልን እንደመተማመኛ በመውሰድ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ዋጋ እንደሌለው ሲሞግቱ ይደመጣሉ። ሆኖም ይህን ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ካለማወቅ ነው ብሎ መደምደም ያስቸግራል። የ1900፤1902 እና 1908 ውሎች የሞቱና ተፈጻሚነት እንደሌላቸውም እየታወቀ እነሱን እንደመተማመኛ መውሰድና ሀገርን የሚጎዳ ውሳኔ ማሳፍ ታሪክ ይቅር የማይለው ነው።

የዚሁ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማቋቋሚ አዋጅ ጨምሮ እንዳሰፈረውም ቅኝ ገዢዎች ሀገራትን ወክለው የፈረሟቸው ውሎችና ስምምነቶችም የህግ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው አድርጓል። እዚህ ላይ ጣሊያን ኤርትራን ወክላ የፈረመቻቸው ውሎች በሙሉ ተቀባይነት የማይኖራቸውና ተፈጻሚነትም የሌላችው ናቸው።

በሌላም በኩል የተፈረሙ ውሎች በተደጋጋሚ የሚጣሱ ከሆኑም ተዋዋዮቹ በውሎቹ የመገዛት ግዴታ የለባቸውም። ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር የፈረመቻቸው የ1900፤የ1902 እና የ1908 ውሎች በጣሊያንና በኢትዮጵያ መካከል ውዝግብን በማስቀረት ሰላማዊ ሁኔታን ለማስፈን በማቀድ ነበር። ሆኖም ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረርና በማጥቃት እነዚህ ውሎች በተደጋጋሚ እንዲጣሱ አድርጋለች። ስለዚህም ኢትዮጵያ ጣሊያን በተደጋጋሚ በጣሰቻቸው ውሎች የመገዛት ግዴታ የለባትም። እነዚህ ሶስት ስምምነቶች ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ቅጽበት ዋጋ የሚያጡ ናቸው።

በሌላም በኩል አንድ ሀገር ከቅኝ ግዛት ነጻ ሲወጣ ቅኝ ገዢው የገባቸውን ግዴታዎች እንደገና ተደራድሮ ግዴታውን ካላደሰ ቀኝ ገዢው ከገባው ግዴታ አዲሱ ሀገር ነጻ መሆኑን ወይም እንደማይመለከተው የ1978 የቪና ኮንቬንሽን አንቀጽ 16 ይደነግጋል። ስለዚህም በ1900፤በ1902 እና 1908 ጣሊያንና ኢትዮጵያ የተፈራረሙዋቸው ውሎች በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ሊያስገድዱ አይችሉም። በእነዚህ ውሎች ተመርኩዞ የሚሰጥ ማንኛውም ዳኝነት መሰረታዊ የህግ ስህተት ሰላለበት ውሳኔው በህግ ፊት ዋጋ አይኖረውም።

በሌላም በኩል እኤአ በ1967 ሀገራት በካይሮ ተሰባበስበው ከቅኝ ግዛት የወጡ ሀገራት የነበራቸውን ይዞታ ሳይጨምሩም ሳይቀንሱም ይዘው መጓዝ አለባቸው የሚል ህግ አውጥተው ነበር። ይህ ስምምነት በርካታ ሀገራት ቅኝ ከመገዛታቸው በፊት የነበራቸውን ይዞታ የሚያሣጣ ከመሆኑም በሻገር አንድ አንድ ሀገራት ደግሞ ከሌሎቹ ተወስዶ እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ስምምነት ነው።

በዚህ ስምምነት አንዳንዶች በብዙ ተጠቅመዋል፤አንዳንዶች ደግሞ በብዙ ተጎድተዋል። የአንዳንድ ሀገራት ህዝቦች ግማሽ ለግማሽ ተከፍለው አንዱ ህዝብ በአንድ ሀገር ሌላው ህዝብ በሌላ ሀገር ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል። ኢትዮጵያም የባህር በሯንና ወደቦቿን የምታጣው በዚህ ህግ መሰረት ነው በሚል የሚነሱ የመከራከርያ ነጥቦች አሉ።

ይህ መርህ ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር ምን ያህል ተቀባይነት አለው የሚለውን ግን መፈተሸ ያስፈልጋል። ይህ ስምምነት በተለይ ኢትዮጵያን በተመለከተ ገዢ ሊሆን አይችልም። አንደኛ የኢትዮጵያና የጣሊያን ግንኙነት የቀኝ ገዢና ተገዢ አልነበረም። ኢትዮጵያ ቅኝ የተገዛች ሀገር ባለመሆኗ በዚህ ህግ የመገዛት ግዴታ የለባትም። እንዴው የቅን ግዛት ስምምነቱን ሙጥኝ ብለው የሚይዙ እንኳን ቢኖሩ አሰብ የኢትዮጵያ አካል የሆነና ራስ ገዝ ሆኖ የቆየ በመሆኑ ኤርትራ ነጻ ስትወጣ በምንም አይነት መልኩ ከኤርትራ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚገባው አልነበረም።

ይህንኑ ስምምነት ተከትሎ የመጣውም የአልጀርስ ስምምነት የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎትና መሻት እስከመጨረሻው የዘጋ ነው በሚል የሚነሳው ውዝግብ ውሃ እንደማይቋጥር ማሳያ ነው። የአልጀርስ ስምምነት ተብሎ የሚገለጸው ኢትጵያ በማትገደድባቸው ውሎችና ስምምነቶች ላይ ተመስርቶ በተዛባ መልኩ የተሰጠው ውሳኔ በመሆኑ ኢትዮጵያ ልትቀበለው የማትችለው ነው።

አዲስ ዘመን፦በአልጀርሱ ስምምነት ኢትዮጵያ ወድብና የባህር በር ማግኘት መበቷን ተነጥቃለች የሚሉ ወገኖች አሉ፤በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?

መምህር በፈቃዱ ድሪባ፦ የአልጀርስ ስምምነት በራሱ አደንደማስረጃ የሚያቀርበው ኢትዮጵያ በ1900፤በ1902 እና በ1908 የተፈራረመቻቸውን ውሎችን ነው፡፤እነዚህ ውሎች ደግሞ በተባበሩት መንግስታትማቋቋሚያ ቻርተር ላይ የተሻሩና ተቀባይነትም ሌላቸው ናቸው። ስለዚህም በተሻሩ ውሎችና ስምነቶች ላይ ተመርኩዞ የተሰጠ ብያኔ በራሱ ዋጋ ቢስ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን መነሳት ያለበት የባህር በር ጉዳይ ሲነሳ ሁልጊዜም አብሮ መነሳት ያለበት ሰብአዊ ርህራሄና ፍትህ የሚባሉ ጽንሰ ሃሳች ናቸው። ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው ሰብአዊ ርህራሄና ፍትህን በተነፈገ መልኩ ነው። ኢትዮጵያ ከ100ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያዘች ፤ኢኮኖሚዋ እያደገ የሚሄድና በተዛባ ፍትህ ምክንያት የባህር በሯንና ወደቦቿን ያጣች ሀገር ነች። በአጠቃላይም ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ የተሰጠው ውሳኔ ኢፍትሃዊ ከመሆኑም ባሻገር ከ100 ሚሊዮን በላይ የሆነ ህዝቧን የወደፊት ዕጣ ፋንታ ያላገነዘበና ሰብአዊ መብትን የገፈፈ ነው።

ለአብነት በካሜሮንና በናይጄሪያ መ ካከል የነበረው የድንበር ወዝግብ ሲፈታ 33 የሚጠጉ መንደሮች ወደ ካሜሮን እንዲካለሉ ተደርጓል። ይህ የተደረገው መንደሮቹ ለካሜሮን የሚገቡ ሆነው ሳይሆን በእነዚህ መንደሮች የሚኖሩ ነዋሪዎች ተገነጣጥለው በሁለት መንደር መኖር ስለሌለባቸው ነው። በአጠቃላይ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ስለሆነ ነው። በኢትዮጵያ ግን ግማሹ የአፋር ህዝብ ኤርትራ ግመሹ ደግሞ ኢትዮጵያ እንዲኖር ተፈርዶበታል። ከዚህ በላይ ሰብአዊ መብት ጥሰት ሊመጣ አይችልም።

አለም አቀፉን ልምድ ስንመለከት የባህር በር ጉዳይ በቀላሉ የሚፈታባቸውን ልምዶች እናገኛለን፡ በቨርሳይለስ ስምምነት ጀርመን ለፖላንድ የራሷን መሬት ቆርሳ ሰጥታለች። ፖላንድ ተቆልፎባት መኖር ስለሌለባት ጀርመን ለፖላንድ መሬቷን አሳልፋ በመስጠት እና ፖላንድ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን በማድረግ ዘላቂ ሰላምን ማረጋጥ ችላለች። በኒኳራጓና በኮሎምቢያ፤በቼክና በፔሩ ኢትዮጵያ ካጋጠምት ችግሮች በላይ ችግሮች ተፈትተው ሀገራት የባህር በር ባለቤት መሆን ችለዋል።

አዲስ ዘመን፦ ሌሎች አለም አቀፍ ህጎችስ ኢትዮጵያን ምን ያህል ይደግፏታል ?

መምህር በፈቃዱ ድሪባ፦ የተባበሩት መንግስታት የባህር በር ህግ (United nation cooperation the low of the sea) አንቀጽ 69 የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢው ያለውን የባህር በር የመጠቀም እና የመሸጋገር አለም አቀፍ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ይህ መብት የባህር በር በሌለው ሀገር፤የባህር በር ባለቤት በሆነው ሀገር እና በቀጠናው መካከል በሚደረግ ስምምነት ሊፈጸም እንደሚገባ በዚሁ አንቀጽ ላይ ተመልክቷል። የአፍሪካ ህብረትም ይህን ድንጋጌ የሚያጸና አንቀጽ በመተዳደርያ ድንቡ ውስጥ አካቷል።

የተባበሩት መንግስታት የባህር በር ህግ (United nation cooperation the low of the sea) አንቀጽ 27 ደግሞ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በስምምነት ካልተደረገ በስተቀር ለተገለገሉበት የባህር በር ምንም አይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁ ይደነግጋል።

ስለዚህም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ህጎችን በመጠቀም በቅርቧ የሚገኘውን የባህር በር የማግበኘት መብቷን ማስከበር፤ኢትዮጵያ የባህር በር እንደምትፈልግ ሁሉ የባህር በር ያላቸው የአካባቢው ሀገራት የእርሻ መሬትና ሌሎች የሚያስፈልጓቸው ሃበቶችን በመለዋወጥ ሰጥቶ የመቀበል መርህን ተግባራዊ ማድረግ፤ሀገራት ወደቦችን እኩል በማልማት የሚጠቀሙባቸውን ስልቶች መንደፍና የመሳሰሉት ስልቶችን በመጠቀም የባህር በር ባለቤትነቷን ማስከበር ይገባታል።

አለም አቀፉ ህግ በባህር በር የመጠቀምንም ሆነ የባህር በር ማግኘትን መብት ያረጋግጣል። በአለም አቀፍ ህግ መሰረት አንድ ሀገር ከጠረፏ እስከ 23 ኪሎሜትር ብቻ ነው የእሷ የሚሆነው፡፤ከዚያ ውጭ ያለው የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ሃብት ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ሃብትና ንብረት የመጠቀም መብት አላት።

አዲስ ዘመን- ሰሞኑን ኢትዮጵያና ሶማሊ ላንድ ያደረጉት ስምምነት ያለው አለም አቀፍ ተቀባይነት ምን ይመስላል ?

መምህር በፈቃዱ ድሪባ– ኢትዮጵያና ሶማሊ ላንድ የተፈራረሙት የ መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) ነው። የመግባቢያ ሰነድ ደግሞ ሁለት ሀገራት የሚያደርጉት ስምምነት እንጂ በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ ሰነድ ሆኖ የሚያገለግልና ኣሳሪ አይደለም። ኢትዮጵያና ሶማሊ ላንድ ያደረጉት በሰጥቶ መቀበል ምርህ የሁለቱን ጥቅም የሚያረጋገጥ የመግባቢያ ሰነድ ነው የፈረሙት። የመግባቢ ሰነዱ ከህግ ሰነድነቱ ይልቅ አካባቢያዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ሆኖም በዚህ ስምምነት የማይደሰቱ ሀገራት እንዳሉ መረዳት ግን ይገባል። በዋነኝነት ሶማሊ ሪፐብሊክ የመጀመርያዋ ቅሬታ አቅራቢ ሆና መቅረቧ ገና ከመጀመርው የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ የሚቃጥላቸውና እድገቷን የማይመኙ ሀገራት በማያገባቸው ገብተው ጩኸት ለመፍጠር መሞከራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህንን ደግሞ ግብጽ፤የአረብ ሊግና የመሳሰሉት በማያገባቸው ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ሲጮሁ ተሰምተዋል።

ነገር ግን ኢትዮጵያና ሶማሊ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ማንንም የሚጎዳ አይደለም። ይልቁንም አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው። ከሁሉም በላይ አለም አቀፍ ህጉና ተቋማት ጭምር ፍትሃዊ የሆነ የባህር በር ተደራሽነት እንዲኖር ስለሚፈልጉ በኢትዮጵያና በሶማሊ ላንድ መካከል ተደረስ የመግባቢያ ስምምነትን የሚደግፉት እና ተቀባይነትም ያለው ነው።

አዲስ ዘመን – አሁን ተጀመረው የባህር በር የማግኘት ጥረት ግቡን እንዲመታ ከኢትጵያውያን ምን ይጠበቃል ?

መምህር በፈቃዱ ድሪባ– እንደመታደል ሆኖ አሁን ያለው መንግስት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ለመመለስ ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ባለፉት ሰላሳ አመታት በነበረው አገዛዝ ስለባህር በር የሚያነሳ እንደጸብ አጫሪ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። አልፎ ተርፎም ለእስርና እንግልት ብሎም ህይወት የሚያሳጣ ነበር፡የባህር በር ጥያቄ ያነሱ ምሁራን ጭምር ለብዙ ውጣውረድና እንግልት ተዳርገዋል።

አሁን ግን መንግስት እራሱ ተነሳሽነቱን ወስዶ የኢትዮጵያውያንን የባህር በር የዘመናት ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ጥረቶችን እያደረገ ነው። ሰሞኑንም ከሶማሊ ላንድ ጋር የተፈረመውም የመግባቢያ ሰነድ የዚሁ ጥረቱ ማሳያ ነው። ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ መንግስት የጀመረውን ጥረት ሊያግዝና ኢትዮጵያም ወደ ታሪካዊ መበቶቿ እንድተመለስ የበኩሉን ጥረት ሊደርግ ይገባል።

የተጀመሩት ጥረቶች ፍሬ ሊያፈሩ የሚችሉት ደግሞ በሀገር ውስጥ ሰላም ሲኖር ነው። እዚህም እዚያም ያሉ ግጭቶች ሊቆሙ ይገባል። የኢትዮጵያን እድገት የማይሹ ወገኖች ክፍተቶቻችንን ተጠቅመው የጀመርነውን የባህር በር የማግኘት መብት እንዳያሰናክሉብን አንድነታችን ሊጠናከር ይገባል። የባህር በርን በተመለከተ አሁን ኢትዮጵያ በትክክለኛ መስመር ላይ ትገኛለች። ስለዚህም ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት የመጀመርያው እንጂ የነመጨረሻው አይደለም።

ከላይ እንዳብራራሁት ኢትዮጵያ ያነሳችውን የባህር በር የማግኘት መብት አለም አቀፍ ህጎች በሙሉ የሚደግፉት ነው። ሆኖም ግን እስካሁን እነዚህን አለም አቀፍ ህጎች አልተጠቀምንባቸውም። ይልቁንም ሆን ተብሎ በተቃራኒው የህግ ትርጉም በመስጠት ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳይኖራት ተደርጓል። ዛሬ ግን ሁሉም ነገር ወደ ትክክለኛ ቦታው የተመለሰ ይመስላል። ስለዚህም ሰላማችንን እስካስጠበቅንና አንድነታችንን እስካጠናከርን ድረስ የባህር በር የማግኘት መብታችንን ማስከበር እንችላለን።

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ

አቶ በፈቃዱ ድሪባ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You