የትምህርት ነገር ሲነሳ ተያያዦቹ ብዙ ናቸው። ከጥቁር ሰሌዳና ነጭ ጠመኔ ጀምሮ ለትምህርት አስፈላጊ ያልሆነ ነገር የለም ማለት ይቻላል። በተለይ የመርጃ መሳሪያ (ቲቺንግ ኤይድ)ን ወሳኝነት እንመልከት ካልን ለትምህርት በግብአትነት የማያገለግል ምንም አለመኖሩን እንመለከታለን።
የዛሬውን ዝቅ ብለን የምንመለከተው ሆኖ፣ ድሮ ከመማር-ማስተማሩ ተግባር ጎን ሆኖ (ወይም፣ ሳይነጣጠል) የሚገኝ አንድ አቢይ ተግባር ቢኖር የተጓዳኝ ትምህርት መርሀ ግብር ነበር ነው የሚሉት በወቅቱ የመማር-ማስተማር ተግባር ንቁ ተሳታፊ የሆኑት ሰዎች ሲናገሩ።
እነዚሁ ባለሙያ ሊቃውን እንደሚናገሩት ከሆነ ተማሪዎች ከመደበኛው የመማር-ማስተማር ሂደት ባልተናነሰ መልኩ ከተጓዳኝ ትምህርት ፕሮግራምም አስፈላጊውን እውቀት ይዘው ነበር የሚወጡት። በክፍል ውስጥ የሚሰጠውን ንድፈ ሀሳብ (ነቢብ) ወደ ገቢር የሚቀይሩት፤ ወይም በተግባር ላይ የሚያውሉት በእነዚሁ ተጓዳኝ ትምህርቶች (ክበባት) አማካኝነት እንደ ነበር ነው ከሊቃውንቱ በተጨማሪ የተለያዩ መረጃዎች የሚያሳዩት።
ጉዳዩን እንደ አንድ በትምህርት አለም ውስጥ እንዳለፈ ሰውም ሆነ፣ እንደ ተመልካችና ታዛቢ ሆነን ከገመገምነው ከተጓዳኝ ትምህርት አኳያ ዘንድሮና ድሮ እጅጉን የተለያዩ ናቸው።
ድሮ በየትምህርት ቤቱ የግብርና ትምህርት መኖሩ ብቻ ሳይሆን የቃል ትምህርቱ ሰርቶ ማሳያ የ“እርሻ″ ቦታዎች ነበሩ። ተማሪዎች ካሮት ይተከላሉ፤ ቀይ ስር እንደ ልብ ነበር። ጎመን (ሁለቱም፣ ጥቅል ጎመንና የአበሻ ጎመን) ሲደርስ መገንጠል ነው። ቃሪያ ሁሉ ይተከል እንደ ነበር ላስታወሰ የድሮ ተማሪ እውነትም ዘንድሮና ድሮ አራምባና ቆቦ ናቸው ከማለት ምንም አይመልሰውም። በውድዎርኩ (እንጨት ስራው)፣ ባልትናው (ሆም ኢኮኖሚክስ)፣ ሙዚቃው ወዘተርፈ ሁሉ የተግባር ትምህርት አለ። ዛሬ እራሳቸው፣ ትምህርቶቹ አሉ ወይም ይሰጣሉ? አይመስለኝም።
ድሮ የትምህርት ሱፐርቫይዘሮች ለሱፐርቪዥን ስራ ወደየ ትምህርት ተቋማት ሲሄዱ (የሱፐርቫይዘሮቹ ቼክሊስትም ይህንኑ ያካተተ ነውና) ያ የሚሄዱበት የትምህርት ተቋም ከመደበኛው የመማር-ማስተማር መርሀ ግብር ጎን ለጎን የተጓዳኝ ትምህርት ፕሮግራምንም እያካሄደ ይገኝ ዘንድ ይጠበቅበታል። ያ ካልሆነ የግምገማ ውጤቱ በጎደሎ ይመዘገብበታል፤ “አፈፃፀሙ″ም የደካሞች ምሳሌ ከመሆን አይዘልም። በሂደት ግን “አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ″ የተጓዳኝ ትምህርትን በመጠየፍ ተግዳኝ ትምህርትን አለመስጠት በጥንካሬ ይመዘገብ ዘንድ ፈቀደ። ርእሰ መምህራንም የተጓዳኝ ትምህርት ፕሮግራማቸውን በነጭ ሰረዙት (በምትኩ ምን እንደ ተተካ ባይታወቅም)።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከሁለት አመት በፊት በዚሁ ጋዜጣ ላይ አንድ ጽሑፍ ለንባብ አብቅተን ነበር። የተወሰኑ ትምህርት ቤቶችን በማሳያነት ወስደንም የክበባት መዳከምን አደጋ ጠቋቁመን ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን አሳስበን ነበር። እሚያበረታታ እንቅስቃሴ እያየን ነውና አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን።
ለመንደርደሪያ ያህል ይህንን ያህል ካልን፣ ወደ ከመደበኛው ትምህርት ጋር የሚተሳሰሩና በትምህርት አመራር፣ በመምህራን፣ በተማሪዎችና ወላጆች ንቁ ተሳትፎ የሚተገበሩ ልዩ ልዩ ክበባትን የሚያጠቃልለው “የተጓዳኝ ትምህርት ፋይዳ″ እንምጣና ጥቂት እንበል።
የዛሬው እንግዳችንን ጨምሮ፣ “ሁሉም″ በሚባል ደረጃ፣ በመስኩ ባለሙያዎች እንደተረጋገጠው ተጓዳኝ ትምህርት የትምህርቱ አካል እንጂ ግንጥል ጌጥ አይደለም። ተጓዳኝ ትምህርት ቃል ወደ ተግባር የሚቀየርበት፤ ተማሪዎች የተለያዩ ኃላፊነቶችን የሚወጡበት (ለምሳሌ፣ ሰብሳቢ፣ ሊቀመንበር፣ ጸሐፊ ወዘተ)፣ ውሳኔ ሰጪነትን የሚለማመዱበት፣ ዝንባሌያቸውን አድነው የሚያገኙበትና ለይተውም የሚያውቁበት (የሚያገኙበት) እንጂ የትርፍ ሰአት ስራ፣ ወይም ተማሪዎች አስተማሪ በሌለበት ሰአት (ክፍለ-ጊዜ) እንዳይረብሹ ታስቦ የሚሰማሩበት ትርጉም የለሽ የጊቢ ውስጥ እንቅስቃሴ አይደለም።
ትምህርት ሚኒስቴር በየቋንቋና ተጓዳኝ ትምህርቶች ስርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር በርሄ አማካኝነት “የተማሪዎች በተጓዳኝ ትምህርት የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸው የአዲሱን ስርዓተ ትምህርት ጽንሰ ሀሳብ ተረድተው ወደ ተግባር እንዲለውጡ እንደሚያስችላቸው″ መግለፁም ይህንን እየተነጋገርንበት ያለውን የሚያረጋግጥ ነውና ተጓዳኝ ትምህርት ፋይዳው ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም።
ተማሪዎችን ከመደበኛው ትምህርት ባሻገር በተጓዳኝ ትምህርቶች በማሳተፍ ችሎታቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ ማድረግ እንደሚገባ፤ በተጓዳኝ ትምህርቶች አማካኝነት ተማሪዎች እውቀታቸውን፣ አመለካከታቸውንና የህይወት ክሂሎታቸውን በማሳደግ ድንበር ተሻጋሪ የባህል ግንኙታቸውን እንዲያዳብሩ አስተዋጽኦ ማድረጉ ለተጓዳኝ ትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ወዘተ ሁሌም በዘርፉ ባለሙያዎች ሲመከር የቆየ ምክረ ሀሳብ ነው።
የአንድ ሕዝብ ተራማጅ ባህል፣ ተራማጅ አስተሳሰብ በትምህርት ቤቱ ተጓዳኝ ትምህርት ፕሮግራም የሚንፀባረቅ፣ የሚዳብር ወዘተ መሆኑንም ጠለቅ ባለ መልኩ የሚናገሩ ወገኖች፣ በተለይም የትምህርት ባለሙያዎች መኖራቸውንም እዚህ ጋ ሳይጠቅሱ ማለፍ አይቻልም።
የተጓዳኝ ትምህርት የየትምህርት ተቋማቱን የውስጥ ገቢ ከማዳበር አኳያም ላለው ፋይዳ ከፍተኛ ግምት ሰጥተው ሊቀዛቀዝ የሚገባው ፕሮግራም እንዳልነበረ የሚናገሩ ባለሙያዎችም አሉ።
በጉዳዩ ላይ ይህንን ያህል ካልን አንድ ጉልህ ማሳያን ወስደን ማብራሪያችንን ወደ መሬት እናውርደው።
“ተጓዳኝ ትምህርት በትምህርት ቤቶች ያለው ወቅታዊ ይዞታና ሁኔታ ምን ይመስላል?″ የሚለውን ለማየት በአቅራቢያችን ወደ እሚገኘው፣ ወደ አንጋፋው ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አቅንተን የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር የሆኑትን፣ አቶ ተፈሪ ንጉሴን አነጋግረናቸው ነበር።
ከእኛ ጋር በቢሯቸው ቆይታ ያደረጉት ርእሰ መምህር ተፈሪ ንጉሴ እንዳጫወቱን ከሆነ ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ባሉት የትምህርት እርከኖች ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተናግደው ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሁለት ፕሮግራሞች የመማር-ማስተማር ተግባሩን የሚያከናውን ሲሆን፤ በመደበኛው (የቀን) እና በማታው መርሀ ግብር ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይከታተላሉ።
በትምህርት ቤቱ አካቶ (ልዩ ፍላጎት)ን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በመደበኛው 2ሺህ 251፣ በማታው ደግሞ 500 ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ።
አካቶን በተመለከተ ጠይቀናቸውም፣ ማየት የተሳናቸው፣ መስማት የተሳናቸውና ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ የሚከታተሉት ትምህርት ነው። መምህራን አሏቸው፤ አስተርጓሚዎችም አሏቸው። “አስተርጓሚዎችም አሏቸው″ ሲባል አጠቃላይ አስተርጓሚ እንጂ ለኬሚስትሪ የኬሚስትሪ፣ ለጂኦግራፊ የጂኦግራፊ ወዘተ አስረተርጓሚዎች አሏቸው ማለት አይደለም። ከዚህ አኳያ ይቀረናል። አካቶዎችም በየክበባቱ በሙሉ አቅማቸው ይሳተፋሉ። ሲሉ መልሰውልናል።
አቶ ተፈሪ ንጉሴ እንደሚናገሩት ከሆነ የዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ተማሪዎች በተለያዩ የተጓዳኝ ትምህርት አካላት በሆኑት ክበባት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ያደርጋሉ።
በመሀል መቀዛቀዙ ትክክል አለመሆኑን፣ ተጓዳኝ ትምህርት ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የተማሩትን በውጪ የሚያንፀባርቁበት የዋናው ትምህርት አካል እንደሆነ፤ ተጨማሪ ሳይሆን የትምህርቱ “ኮር″ (ዋና አካል) እንደሆነ፣ ስርአተ ትምህርቱን ከማበልፀግ አኳያ ወሳኝ የሆነ፣ ልዩ ትኩረትም ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ወዘተ የሚናገሩት ርእሰ መምህር ተፈሪ፣ በአሁኑ ሰአት በአገር አቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረትን አግኝቶ ለተግባራዊነቱ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም የትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ደረጃ ዳግም በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውንም ይገልፃሉ።
ርእሰ መምህር ተፈሪ፣ ትምህርት ሚኒስቴር በስምንት አቢይ ዘርፎች፣ እንዲሁም በ21 ንኡስ ክበባት ውስጥ ተማሪዎች ይሳተፉ ዘንድ ሰርኩላር ደብዳቤ መፃፉን፤ በተላለፈው ሰርኩላር ደብዳቤ መሰረትም በአገሪቱ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ወደ ተግባር የተገቡ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። ትምህርት ቤታቸውም እቅድ አውጥቶ፣ ተጓድኝ ትምህርትን በእቅዱ ይዞ በዛው መሰረት እየሰራ መሆኑንም እንደዛው።
በትምህርት ቤታችን ተጓዳኝ ትምህርት በያዝ ለቀቅ የሚሰራ የአንድ ወቅት ስራ አይደለም፤ በእቅድ ተይዞ ነው እየተሰራ ያለው። መምህራን እንደ መምህርነታቸው ሌላውም እንደየ ሀላፊነተቱ፤ ሁሉም ይገመገምበታል። ይጠየቅበታል። ክንውኑ ሪፖርት አለው፤ የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ይቀርባል የሚሉት ርእሰ መምህር ተፈሪ “ተጓዳኝ ትምህርት የትምህርቱ አካል ነው″ ሲሉ ይገልፁታል።
ሚኒ ሚዲያ፣ ድራማና ሥነጽሑፍ፣ ስብእና ግንባታ፣ የእርሻ ክበብ ወዘተ በዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚከናወኑ፣ በተጓዳኝ ትምህርት ስር የሚገኙና ተማሪዎች እንደየ ፍላጎትና ዝንባሌያቸው የሚሳተፉባቸው ክበባት መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ተፈሪ ንጉሤ ገና በመመስረትና መጠናከር ላይ ያሉትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ክበባትም በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
መደበኛው ትምህርት ሕይወት የሚዘራው በተጓዳኝ ትምህርት መሆኑን፣ ተማሪዎች መሆን የሚፈልጉትንም ሆነ የሚሆኑትን ከወዲሁ የሚያዩበት መነሻቸው መሆኑን፤ ራሳቸውን በማዳመጥ ዝንባሌያቸውን የሚከተሉበት እንደ ሆነ፤ መልካም ሰብእናን የሚያጎለብቱና የሚላበሱበት መሆኑን፤ ከአመራር ሰጪነት ጀምሮ በርካታ ክሂሎችን የሚያዳብሩበት እንቅስቃሴ እንደ ሆነ የነገሩን ርእሰ መምህር ተፈሪ በጎነት፣ ደም መለገስ፣ የቋንቋ ክሂሎችን ማዳበር (በቋንቋ መግባባትና መፃፍን ጨምሮ)፣ የጋዜጠኝነት፣ ደራሲነት ወዘተ ማንነታቸውን ከወዲሁ የሚቀርፁበት መሆኑንም ይናገራሉ። እራሱን የቻለና ሌሎች ትምህርት ቤቶች የሌለ፣ በኮለኔል ሲሳይ የሚሰለጥንና የሚመራ የማርሽ ባንድም በዚሁ ትምህርት ቤት መኖሩንም ነግረውናል።
በመጨረሻም “የሚሉት፣ ለሌሎች የሚያስተላልፉት መልእክት ከለዎት?″ ብለናቸውም “ለትምህርት መበልፀግ የክበባት ሚና የሚየተካ አይደለም። ያለ ክበባትና የተማሪዎች የክበባት ተሳትፎ የመደበኛው ትምህርት እንቅስቃሴ፣ የመማር-ማስተማሩ ተግባር ፍሬያማ ሊሆን አይችልም። ተጓዳኝ ትምህርት በክፍል ውስጥ የተማሩትን እዛው ጊቢ ውስጥ በተጨባጭ የሚያሳዩበት ነው። ለምሳሌ፣ አንዱ አለቃ፣ ሌላው ደግሞ ታዛዥ ሆኖ ሲሰራ የአመራር ክሂሎታቸውን ያዳብሩበታል። ተማሪዎች በበጎነት ክበብ አማካኝነት በጎነትን፤ በስብእና ክበብ አማካኝነት ሰብአዊነትን፣ ዜግነትን ወዘተ የሚሩዳበት፤ ክፍል ውስጥ የተማሩትን የቋንቋ ትምህርት በሚኒ ሚዲያ ክበብ አማካኝነት ወደ ተግባር ቀይረው ችሎታቸውን የሚያሳድጉበት ወዘተ ነው። ባጭሩ ክበባት ተማሪው የክፍል ውስጥ ትምህርቱን በተግባር የሚያይባቸው ላቦራቶሪዎች ናቸው። በመሆኑም፣ ትምህርት ቤቶች ለተጓዳኝ ትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ቢንቀሳቀሱ ትውልድ የሚፈለገውን ባህርይ ይዞ ይወጣ ዘንድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው። በማለት አብራርተውልናል። እኛም በዚሁ፣ በርእሰ መምህር ተፈሪ ንጉሤ መልክእክት ዝግጅታችንን እናጠናቅቃለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን 2016 ዓ.ም