የለውጥ አስተሳሰቦች ጠንካራ መሠረት እንዲኖራቸው መገናኛ ብዙኃን ሀገራዊ ኃላፊነት አለባቸው!

 መገናኛ ብዙኃን ወቅታዊ መረጃዎችን በጥራትና በፍጥነት እንዲሁም ከፍ ባለ የተጠያቂነት መንፈስ ለሕዝብ የማቅረብ ሙያዊ ኃላፊነት አለባቸው። ይህን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣትም በየጊዜው እራሳቸውን በመገምገም፤ ጥንካሬያቸውን አጠናክረው ማስቀጠል እና ድክመታቸውን ማረም ይጠበቅባቸዋል።

መገናኛ ብዙኃን ለሕዝቡ መረጃ መስጠት፣ ማስተማር፣ ማሳወቅና ማዝናናት፣ ለሰላም ለልማትና ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ብልፅግና ስኬት የሕዝቡን ተሳትፎ ማሳደግ እና የዜጎችን ሃሳብን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብት ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

እንዲሁም የተለያዩ አመለካከቶችን፣ አስተሳሰቦችንና አስተያየቶችን በማስተናገድ የዲሞክራሲ ባህልና ሥርዓት ግንባታ እና የብሔራዊ መግባባት እንዲጠናከር ማድረግ የዜጎችን የእርስ በእርስ ግንኙነትና ትስስር ማጠናከር፣ የሕዝቦችን ቋንቋ፣ ባህልና ዕሴት ማስተዋወቅና ማጎልበት፣ የሀገርን አጠቃላይ በጎ ገፅታ ከፍ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይህ ኃላፊነታቸው፣ በተለይም በለውጥ ላይ ባለ ማኅበረሰብ ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ክብደት፣ መረጃን በጥራትና በፍጥነት ከመስጠት፣ ከመተርጎምና ከመተንተን ባለፈ፤ ለውጡ የማኅበረሰቡን ቀልብ ገዝቶ፤ስኬታማ እንዲሆን እንደሚያስችል ይታመናል።

የለውጥ ንቅናቄዎች የቀደሙ አስተሳሰቦችንና አሁናዊ ተግዳሮቶችን መሻገር የሚያስችል አቅም በማጣታቸው ምክንያት የሚወለዱ ከመሆናቸው ባሻገር፣ አዲስነታቸው ለብዙ ፈተናዎች ይዳርጋቸዋል። ንቅናቄዎቹ የሚጠብቋቸውን ፈተናዎች ተሻግረው በማህበረሰቡ ውስጥ ተገቢውን ስፍራ እንዲያገኙ የመገናኛ ብዙኃን አስተዋፅኦ አልፋና ኦሜጋ ነው።

በተለይም እንደእኛ ያሉ ዛሬዎቻቸው በብዙ የትናንት የትርክት ፈተናዎች ችግር ውስጥ የሚገኙ እና የነገ ብሩህ ተስፋቸውም በተዛቡ ትርክቶች ጥላ ስር የወደቁ ሕዝቦች፤ ካሉባቸው አሁናዊ የትርክት ፈተናዎች ወጥተው ነገዎቻቸው ብሩህ እንዲሆኑ የመገናኛ ብዙኃን አስተዋፅኦ መተኪያ አይገኝለትም።

መገናኛ ብዙኃን የተዛቡና የተሳሳቱ ትርክቶችን ከማረምና ከመግራት ጀምሮ፤ የጋራ ሀገራዊ ትርክቶችን በማጉላትና በማስፋት፤ በሕዝቦች መካከል መተማመንን፣ መቀራረብንና መደማመጥን በመፍጠር ለጋራ ራእይ በጋራ መንቀሳቀስ የሚችሉበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር የተልዕኳቸው ዋና አካል አድርገው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

ይህን ሀገርን የማጽናት ኃላፊነታቸውን፣ ከሙያዊ ኃላፊነታቸው ባላነሰ መንገድ፣ ከፍ ባለ ትጋትና ጥንቃቄ ሊወጡት ይገባል። በተለይም በለውጥ ወቅት ዜጎችን ለለውጥ አስተሳሰቦች ተገዥ በማድረግ ለውጡ ሀገራዊ የስኬት ምዕራፍ እንዲቀዳጅ አቅም መሆን ይጠበቅባቸዋል።

አሁን ያለውን በፈተና የተሞላ ውጣ ውረድ በመቀልበስ ሀገር በተሻለ ጥንካሬ በለውጥ ጎዳና እንድትጓዝ፣ ሕዝቡ ብዙ ተስፋ ሰንቆ አደባባይ ለወጣበት የለውጥ ትሩፋት ተጠቃሚ እንዲሆን በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መግባባት መፍጠር የሚያስችል ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡

በልዩነት ጽንፍ አየሩን ከመቅዘፍ ወጥተው፣ ልዩነትን ውበት አድርጎ የሚያስተናግድ አስተሳሰብ በመፍጠርና በማስፋት ሂደት ውስጥ ሙያዊና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚያስችል ተቋማዊ ቁርጠኝነት መፍጠር ይኖርባቸዋል።

በተለይም አሁን ላይ ሀገራዊ የፖለቲካ ባህላችንን በመቀየር ሀገራዊ ፋይዳ ያለው አዲስ የፖለቲካ ትርክት ለመፍጠር፣ በዚህም ለመጪዎቹ ትውልዶች የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ዝግጅት እየተደረገበት ያለው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠርና ባላቸው አቅም ሁሉ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

የኮሚሽኑን ምንነትና ተልዕኮ፣ የውይይቶችን ጽንሰ ሃሳብና ሂደቶችን ለሕዝብ በማድረስ፤መላው ሕዝብ በውይይቱ ተስፋ ከማድረግ ባለፈ ተሳታፊ በመሆን የራሱንና የመጪዎቹን ትውልዶቹን እጣ ፈንታ መወሰን የሚችልበትን እድል ተጨባጭ ማድረግ ሙያዊ ኃላፊነታቸው ጭምር ነው።

ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በጸና መሠረት ላይ ለማቆምም ሆነ ከትናንት ችግሮቻቸው ተላቀው ነገዎቻቸውን ብሩህ ሊያደርጉ በሚችሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መረዳቶቻቸው ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ፤ ይህም ሀገራዊ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል መገናኛ ብዙኃን ማኅበራዊና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

ከዚህ አንጻር፤ ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን፤ በዚህም ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረባትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትወልድ ማስረከብ እንዲቻል፤ የተጀመረው የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲታነጽ በብዙ መትጋት ይኖርባቸዋል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You