እናንተዬ ሰልፍ አልበዛም ? ከለውጡ በኋላ በተደረጉ ሰልፎች አገራችን ሪከርድ ሳትሰብር አትቀርም፡፡ ሰልፍ መውጣት እንደዛሬ ከመርከሱ በፊት እንደ አንድ ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጠራ ይታይ ነበር፡፡ ገዢው ፓርቲ አንበሳና ሃይገር ባስ አቅርቦልህ ሃምሳ ብር አበል ካስጨበጠህ በኋላ ነበር መፈክር የምትጨብጠው፡፡ ሌላ መልክ ያለው ሰልፍ ካደረክም ዱላ የጨበጡ የጸጥታ ኃይሎች መቀመጫህን በእጅህ ያስጨብጥህ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሁለቱም ቀርቷል፡፡
ምክንያቱም እንደ ህዝብ ሽግግር ላይ ነን፡፡ መንግሥትን ከመፍራት ወደ ማስፈራራት፤ ከድጋፍ ሰልፍ ወደ ተቃውሞ ሰልፍ፤ ከመሸበር ወደ ማሸበር እየተሸጋገርን ነው፡፡ ከስጋት ያልተላቀቀ ለውጥ ላይ ባለችና ስንት ችግሮች በተሰለፉባት አገር በየሜዳው መሰለፍ ፈሊጥ ሆኗል፡፡ መቼ ነው የሰልፍ ጋጋታ ቀንሶ አደባባዮች እፎይ የሚሉት ? በበኩሌ የሰልፍ አምሮታችን እስኪወጣልን “ፀሐይ አርፍዳ ወጣች” እያልን መሰለፋችን የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡
አንዳንዱ የራሱን መብት ለማስከበር የሌላን ህዝብና ግለሰብ መብትና ክብር የሚነኩ መፈክሮችን ይዞ አደባባይ ይወጣል፡፡ በኢትዮጵያ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ “ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስምን ለመጠበቅ፤ የጦር ቅስቀሳዎችን እንዲሁም ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል ተጠያቂ ከመሆን አያድንም” ይላል፡፡
አሁን የምናያቸው አንዳንድ ሰልፎች በተጠቀሰው አንቀጽ ያስጠይቃል የተባለውን ሁሉ የሚያሟሉ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ሰልፎች ጋብ ብለው ሹፌሮች፣ ሀኪሞችና መምህራን ሰልፍ ሲወጡ እያየን ነው፡፡ መሰለፍም ሆነ መብትን መጠየቅ የየትኛውም ዜጋ ህገ- መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት ሰልፍ በስራ ማቆም አድማ መታጀቡ ተገቢ አይመስለኝም፡፡
የአገሪቷ የመጨረሻ ሰው በሰጡት መልስ ያልረካ ወገን ጥያቄውን በሰከነ መንገድ በድጋሚ ማቅረብ መብቱ ነው፡፡ ይህን ካልመረጠ ግን አዋራ ከማስነሳት ይልቅ ወደ በላይ አካል (ኢጋድና አፍሪካ ህብረት ጋር) ቢሄድ ይሻለዋል፡፡ ለአንድ ጥያቄ ከማን እንዴት ያለ መልስ እንደሚጠበቅ የተገነዘብን አይመስለኝም፡፡
ኃላፊነት መብት ሲነካ ችላ የሚባል፤ ሲከበር ደግሞ ግዴታ የሚሆን መደራደሪያ አይደለም፡፡ ለአገሩና ለወገኑ ፍቅር ያለው ሙያተኛ ነገሮች፣ ሁኔታዎችና ሰዎች መስመር ቢለቁ እንኳን መስመር ሳይለቅ ታጋይ ነው፡፡
በኃይል በመግፋትና በመልካም ተጽዕኖ በማነሳሳት መካከል ልዩነት አለ፡፡ በስልጣን መደገፍና ባዳበርነው ተቀባይነት መደገፍ ለየቅል ነው፡፡ ፍርሃትን መልቀቅና ፍቅርንና አክብሮትን መስጠትም እንዲሁ፡፡ ስህተት ፈጻሚን መፈለግና ስህተትን ማረም አይገናኝም፡፡ እኔ ማለትና እኛ ማለት ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ነው፡፡ አክብሩኝ ማለትና በአቀራረብ መከበር ይለያያሉ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም እንጉርጉሩ በተሰኘ የግጥም መድብላቸው ባካተቱት “መሰላል” የተሰኘ ግጥማቸው
ዘርግተው የረገጡትን መርገጥ፤
የመውጣት ሕግ ነው የማይለወጥ
ሲወርዱ ግን ያስፈራል ፤
የረገጡትን ያስጨብጣል፡፡
ሲሉ የገለጹትን የአገራችንን የፖለቲካ ባህል የሚቀይር አዲስ አመራር ብቅ ማለቱ ደራሽ ሰልፎች እንዲጎርፉ በር ከፍቷል፡፡ በተከፈተው በር መውጣት ያለብን በማስተዋል መሆን አለበት፡፡
ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር በአንድ ወቅት ከቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ “እጣ ፈንታችን መወለድና መሞት ላይ ነው፡፡ መሀሉ የኛ ምርጫ አለበት፡፡ እንደ ካርታ ጨዋታ ነው፡፡ ካርታ ተሰጥቶ ስትጫወት መጫወቱ ያንተ ፋንታ ነው፡፡ የሚሰጥህ ካርታ ግን እጣ ፈንታ ነው፡፡” ብሎ ነበር፡፡ እንግዲህ አገራችን ስጦታችን (እጣ ፈንታችን) ከሆነች ለውጡን ተጠቅመን እሷን መገንባት የእኛ ፈንታ ነው፡፡ እርግጥ ተቃራኒውን ማድረግም በእጃችን ነው፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2011
የትናየት ፈሩ