የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከመቋቋሙ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የሎተሪ ጨዋታ በተለያየ መልኩ ይካሄድ ነበር፡፡ ህግ ከመውጣቱ በፊት የሚካሄዱት ቁማር መሰል ጨዋታዎች በህብረተሰቡ ዘንድ “ኪሳራ” በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ በ1938 ዓ.ም ህገወጥ ሎተሪዎችን የሚያግድ አዋጅ ከወጣ በኋላ “ኪሳራ” የሚባሉት የቁማር ጨዋታዎች እንደቀሩ ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።
ከዚህ በኋላ ደግሞ አንዳንድ ግለሰቦች ፈቃድ ከመንግስት እያወጡ ሎተሪ ማጫወት ጀምረው የነበረ ሲሆን፤ እነዚህ ግለሰቦች አንዳንዴ ገንዘቡን እየሰበሰቡ የሚጠፉበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በ1945 ዓ.ም መንግስት ይሄንን ችግር በመገንዘብ ሎተሪ እንዲያካሂድ የሚፈቅድ አዋጅ አወጣ፡፡ በመጨረሻ በ1954 ዓ.ም የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ ታወጀ፡፡
በዚህም መስከረም 1954 ዓ.ም የመጀመሪያው ሎተሪ ገበያ ላይ የዋለ ሲሆን፤ ዕጣው 50ሺ ብር የሚያሸልም መደበኛ ሎተሪ ነበር፡፡ ሎተሪው አምስት ክፍልፋዮች ያሉት ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው አስር ሺ ብር የሚያሸልሙ ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው ሎተሪ ዕጣው የወጣው የመዲናዋ ኗሪዎች በታደሙበት በጃንሜዳ ታህሳስ 29 ቀን 1954 ዓ.ም የገና ዕለት ነበር፡፡
ብሔራዊ ሎተሪ ከተመሰረተበት ጀምሮ እድልን ከዕድለኞች እያገናኝ ዘመንን እየተሸጋገረ ሲሆን፤ በብሔራዊ ሎተሪ ከተለመደው የዕጣ አወጣጥ ሂደት ለየት ባለ መልኩ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ተንቀሳቃሽ የዕጣ ማውጫ የፈጠራ ስራ አቶ ጌታሁን ደምሴ ይዘውልን ብቅ ብለዋል። እርሳቸውንም ስለፈጠራ ስራቸው ምንነትና ፋይዳ እንደሚከተለው ይናገራሉ።
አቶ ጌታሁን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ዲፕሎማቸውን በ1974 ዓ.ም በማግኘት የሂሳብ ባለሙያ ቢሆኑም ባላቸው የተፈጥሮ ዝንባሌ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ይሰራሉ። ከአሁን በፊትም ሦስት የፈጠራ ስራዎችን በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የፈጠራ ባለቤትነት መብት ማግኘት ችለዋል። እንዲሁም አሁን ላይ የሰሩትን በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ተንቀሳቃሽ የዕጣ ማውጫ ማሽን መጋቢት 6 ቀን 2010 ዓ.ም ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የፈጠራ ባለቤትነት መብት አግኝተውበታል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ የፈጠራ ስራው አንድ ሜትር ርዝመትና አርባ ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፤ ሁሉም በራሳቸው ዛቢያ ላይ የሚሽከረከሩ የዕጣማውጫ ክብ አሀዞች (ዲጂቶች) ከ 0 እስከ 9 ድረስ ቁጥር ተጽፎባቸዋል። አሀዞቹ (ዲጂቱን) ከስድስት እስከ 16 ድረስ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ ከዛ በላይ ማድረግ የሚቻል ሲሆን፤ እነዚህን ክብ አሀዞች (ዲጂቶች) በኤሌክትሪክ ኃይል አማካኝነት በሚመነጭ የንፋስ ኃይል በራሳቸው ዛቢያ እንዲሽከረከሩ በማድረግ በዕጣ ማውጫ ማሽኑ ላይ የተገጠመውን ማቆሚያ ማንኛውም ሰው ተጭኖ በሚያቆምበት ወቅት ማሽኑ ሁሉንም የባለ እድለኛውን የዕጣ ቁጥሮች በአንዴ ይዞ በመውጣት እድለኛውን የሚያበስር ይሆናል ብለዋል።
የዕጣ ማውጫ ማሽኑ ዲጂታል ወይም አናሎግ ስላልሆነ ከፍተኛ የሰው ኃይል አይጠይቅም፤ ከእጅ ንክኪ የጸዳ፣ ከቴክኖሎጂ እጸጾችና ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ፣ ከጊር ሲስተምና ከኮምፒውተር ሲስተም የጸዳ በመሆኑ፤ የዕጣ አወጣጥ ሂደቱን ግልጽና ተአማኒ በሆነ መልኩ በማካሄድ ለትክክለኞቹ እድለኞች ሽልማታቸውን ለማድረስ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የፈጠራ ባለቤቱ በአገር ውስጥ በቀላሉ በሚገኙና የውጭ ምንዛሬ በማይጠይቁ እንደ ብረት፣ ኩሽኔታ፣ ሸራ የመሳሰሉ ግባቶችን በመጠቀም የፈጠራ ስራውን እንደሰሩ ጠቁመው፤ የዕጣ ማውጫው ማሽን የሚወስደው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ትንሽ በመሆኑ፤ የኃይል መቆራረጥ በሚኖርበት ሰዓት በሶላር ኃይልና በጀኔሬተር ማንቀሳቀስ ስለሚቻል የዕጣ ማውጣት ሂደቱና ስነ ስርዓቱ ሳይቆራረጥ በተፈለገው ጊዜና ቦታ ማካሄድ እንደሚቻል ገልጸዋል።
አቶ ጌታሁን የፈጠራ ስራውን ከአራት አመት በፊት የሰሩት ሲሆን ስራውን ከሰሩ በኋላ ያዩትን ነባራዊ ችግር በተጨባጭ በመመልከትና ለማህበረሰቡ ለዕይታ በማቅረብ በሰበሰቡት አስተያየቶች መሰረት አራት ጊዜ አሻሽለው በመስራት እንዳዘመኑት ተናግረዋል። በአጠቃላይ ማሽኑን ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ፣ ከእጅ ንክኪ በጸዳ መልኩ፣ በተፈለገው ፍጥነት ጊዜንና ወጪን ቆጥቦ የዕጣ አወጣጥ ሂደቱን ግልጽና ተአማኒ በሆነ መልኩ ለማካሄድ የሚያገለግል በማድረግ እንደሰሩት ተናግረዋል።
አቶ ጌታሁን እንዳጫወቱን የፈጠራ ስራውን ለመስራት የተነሳሱት በኢትዮቴሌኮም አማካኝነት በአጭር የጽሁፍ መልዕክት የሚካሄዱ የተለያዩ የሎተሪ ጨዋታዎች የዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓቱ በይፋ ለማህበረሰቡ ስለማይታይ ማህበረሰቡ ጥርጣሬ ውስጥ ስለሚገባ ተሳትፎው ከዕለት ዕለት እየቀነሰ አሁን ላይ የለም በሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ። ስለዚህ ይሄንን ተንቀሳቃሽ የዕጣ ማውጫ ማሽንን በመጠቀም በየሆቴሉ፣ በየገበያው፣ በኳስ ሜዳዎች (ስታዲየሞች) እንዲሁም በተለያዩ አዳራሾች የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓቱን ህዝቡ በአይኑ እንዲያይ በማድረግ አሁን ላይ የተቀዛቀዘውን የአጭር የጽሁፍ መልዕክት የሎተሪ ጨዋታ ዳግም እንዲያንሰራራና ተሳታፊው ማህበረሰብ እንዲጨምር ለማድረግ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንዲሁም ማህበረሰቡ በተደጋጋሚ ወደ ስልኩ በሚላኩ አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመሰላቸቱ ሰው ወደ ስልኩ የሚገቡትን አጭር የጽሁፍ መልዕክት ሳያነብ ሁሉ የሚያጠፋበት ሁኔታ እንዳለ የጠቆሙት አቶ ጌታሁን፤ የፈጠራ ስራውን ተጠቅመው የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓቱን በቀጥታ በመገናኛ ብዙሀን በማስተላለፍ ተአማኒነትን ከመጨመር ባሻገር ወደ ማህበረሰቡ የሚላኩ አጭር የጽሁፍ መልዕክትን ለመቀነስ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የአጭር የጽሁፍ መልዕክት የሎተሪ ጨዋታ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ አዲስ አሰራር በመዘርጋት የማህበረሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ መንግስትን፣ ኢትዮቴሌኮምን፣ ማህበረሰቡንና በዚህ ስራ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍልን የስራ እድል ለመፍጠር ታሳቢ በማድረግ የፈጠራ ስራውን እንደሰሩ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ጌታሁን ማብራሪያ የፈጠራ ስራው የተቀዛቀዘውን አጭር የጽሁፍ መልዕክት የዕጣ ጨዋታ ለማነቃቃት፤ በአገሪቱ የሚካሄዱ የዕጣ አወጣጥ ሂደት ግልጽና ተአማኒ በማድረግ የሰዎችን ተሳትፎ በማሳደግ፤ የፈጠራ ስራው ወደ ስራ ሲገባ ቢያንስ ለ45 ሰዎች የስራ እድል በመፍጠር፤ ማህበረሰቡን በተለያዩ የዕጣ ጨዋታዎች ላይ በማሳተፍ ለተለያዩ ልማቶች የሚውል ገቢን ለማሰባሰብ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
እንዲሁም የፈጠራ ስራው በአጭር የጽሁፍ መልዕክት የሎተሪ ጨዋታ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ እንዲሳተፍ በማስቻል ኢትዮቴሌኮም ከዘርፉ ከፍተኛ ገቢ እንዲያገኝ የሚያደርገው ሲሆን፤ መንግስትን ደግሞ ከፍተኛ የቀረጥ ገቢ እንዲያገኝ ያስችለዋል ብለዋል።
በማሽኑ በግል መስራት፣ ማከራየትና አምርቶ በመሸጥ የፈጠራ ስራውን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ጌታሁን፤ የፈጠራ ስራው በህብረተሰቡ ዘንድ እውቅና እንዲያገኝ መጀመሪያ ተግባር ላይ መዋል እንዳለበት በማመናቸው፤ ከኢትዮቴሌኮም አጭር የጽሁፍ መልዕክት አድራሻ በማውጣት በዚህ አድራሻ አማካኝነት ህብረተሰቡን በዕጣ ጨዋታ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን በማድረግ፤ የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓቱን ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ህዝቡ በአይኑ እያያ እንዲካሄድ ከማድረግ ባሻገር የእጣ አወጣጥ ስነስርዓቱን በቀጥታ በቴሌቪዥን መስኮት እንዲተላለፍ ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
አቅመደካሞችን ለመደገፍና ቤታቸውን ለማደስ እንዲሁም ወጣትና ታዳጊ የፈጠራ ባለሙያዎች የፈጠራ ስራቸው እውን እንዲሆን ይህን ስራ ወደ ተግባር በማስገባት ከሚገኘው ገቢ ላይ በቋሚነት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል የገቡት የፈጠራ ባለሙያው፤ እነዚህን ድጋፍ የሚያሻቸውን የህብረተሰብ ክፍል በቴሌቪዥን መስኮት በሚተላለፍ የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት ላይ በመጋበዝ ያለውን የመተባበር መንፈስ ለማህበረሰቡ እንዲያጫውቱ በማድረግ፤ ለሌሎች በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ባለሀብቶች መሰል በጎ አድራጎቶችን እንዲያደርጉ አርአያ በመሆንና ለማነሳሳት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በመሆኑም የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓቱን በቴሌቪዥን መስኮት በማስተላለፍ፤ ፕሮግራሙ ከማዝናናት ባሻገር አስተማሪ ለማድረግ አራት ለሚደርሱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ማመልከታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ጌታሁን የፈጠራ ስራውን በሚሰሩበት ወቅት የባለሙያ እገዛ ማጣት፣ የተሟላ ወርክሾፕ አለማግኘት ፣ የገንዘብና የጊዜ እጥረት፣ ከማህበራዊ ህይወትና ኑሮ መራቅ የገጠማቸው ችግር እንደነበር ይናገራሉ።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፈጠራ ስራቸው እውቅና ማግኘቱን የሚናገሩት አቶ ጌታሁን፤ ባለሀብቱ አየር በአየር ትርፍ የሚያስገኙ ንግዶች ላይ ትኩረት የሚያደርግ በመሆኑ የተለያዩ የፈጠራ ሀሳቦችን በመደገፍ ነገ ላይ ትርፍ አገኛለሁ የሚል አመለካከት የለውም ብለዋል። በመሆኑም ይሄንን የፈጠራ ስራ አብሮ ለመስራት ፍቃዳቸውን ለባለሀብቶች ቢያሳዩም ከባለሀብቱ በኩል የተደረገላቸው ድጋፍ እንደሌለ ተናግረዋል።
ማህበረሰቡ የፈጠራ ስራ የሚሰሩ ሰዎችን የማበረታታት ባህሉ ዝቅተኛ በመሆኑ እና ከአገር ውስጥ ምርት ይልቅ ለውጪ ምርት ከፍተኛውን ቦታ የሚሰጥ በመሆኑ፤ የፈጠራ ስራቸውን ለመስራት በሚጥሩበት ወቅት በማበረታታት ፋንታ ተስፋ አስቆራጭ ቃላቶችን እንደሚሰነዝሩ ባቸው በአጠቃላይ ስራውን ሲሰሩ ከመንግስትም ሆነ ከማህበረሰቡ የተደረገላችው ድጋፍ እንደሌለ ፤ በራሳቸው የወር ገቢና በቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ስራውን እውን እንዳረጉት ተናግረዋል።
አቶ ጌታሁን የፈጠራ ስራ የሚሰሩ ወጣቶች ተስፋ ሳይቆርጡ በመስራት ዛሬ ላይ ስራቸው ስኬታማ ባይሆን እንኳን መጪው ትውልድ ሀሳቡን እውን ሊያደርገው ስለሚችል ተስፋ ቆርጠው አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ማህበረሰቡ የፈጠራ ስራ የሚሰሩ ሰዎችን ተስፋ አስቆራጭ ቃላትን በመናገር ወደ ኋላ ከማስቀረት በመቆጠብ በአንጻሩ በሚችለው ነገር ድጋፍ በማድረግ በአገሪቱ የተሻለ የፈጠራ ስራ እንዲሰራ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።
አዲስ መዘን ግንቦት 23/2011
ሶሎሞን በየነ