ለሁለት ሺ ብር ሞባይል ሲባል የጠፋ የሰው ሕይወት

የካቲት የወር ስም ሆኖ በጥር ወርና በመጋቢት ወር መሃል የሚገኝ ከአስራ ሶስቱ ኢትዮጵያ የወራት አቆጣጠር ውስጥ ስድስተኛው የወር ስም ነው። የካቲት ከተተ ከሚለው ግስ የተባዛ ነው። ወቅቱ የመኸር ጊዜ በመሆኑ አርሶ አደሩ ሰብሉን አጭዶ ሰብስቦ እና ወቅቶ የምርቱን ፍሬ ወደ ጎተራ የሚከትበት ወር በመሆኑ ወርሃ የካቲት ተባለ።

ገበሬው ምርቱን ሰብስቦ ወደ ጎተራ በሚከትበት በወርሃ የካቲት ያለፋበትን ገንዘብ ነጥቆ ከሀብት ቋቱ ሊከት የወደደው ቀማኛ በምሽት ተነጣቂውን አደፍጦ እየተጠባበቀ ነበር። የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡00 ሰዓት ሲሆን ተደብቆ ግዳዩን ይጠባበቅ የነበረው ቀማኛ ሰዓቱ ደርሶ ግዳዩ ወደ ወጥመዱ ገባ። በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው አትላስ አካባቢ የሚባለው ቦታ ነበር ሀገር ሰላም ብሎ ቤቱ ሊገባ ጠደፍ ጠደፍ የሚለውን አቶ መኮንን መስፍንን በብረት አንገቱን በመምታት ኪሱን ፈታተሾ ያለውን ይዞ ለማምለጥ ይሮጥ ጀመር።

ቀማኛው

አምታቴ ማሞ ይባላል። ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንዲሉ አምታቴ እንደስሙ እያምታታ በሰው ላብ መክበርን ሥራው ያደረገ ሰው ነው። ዓመት ዓመትን እየወለደ ቢሄድም ከጥፋቱ ተምሮ በሀቁ ሰርቶ መክበርን ከማሰብ ይልቅ እንዴት አድርጌ በተለየ መንገድ ዘርፌ መኖር እችላለሁ እያለ ያሰላስላል። ጨለም ያሉ ቦታዎችን ምርጫው የሚያደርገው ቀማኛ ለዘረፋ ተግባሩ ድምፅ የሌላቸውን መሳሪያዎች መጠቀም ምርጫው ያደርጋል።

በትንንሽ ቅሚያዎች የጀመረው ዘረፋ እለት እለትን እየጨመረ ሲሄድ ሱሰ ሆነበት፡፡ አንድም ቀን ሳይሰርቅ መዋል ይከብደው ጀመር። ቦታ እየቀያየረ እለት እለት ልክ እንደ መደበኛ ሥራው የሰው ማጅራት እየመታ ያገኘውን ይዞ መሮጥ የእለት ከእለት ተግባሩ ሆነ።

ዛሬም ካገኘ በሰላም ዘርፎ ሊሄድ ካላገኘ ደግሞ በያዘው ፌሮ ብረት ማጅራት በመምታት ሊነጥቅ ተዘጋጅቶ ምቹ የሆነ ጨለማ ሰፍራ ተሸሽጎ ይጠባበቅ ጀመር። ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ጨለማውን ተገን አድርጎ ከለል የሚያደርገው ድንጋይ ስር ያደፈጠው ቀማኛ ብቻውን የሚመጣ መንገደኛ እስከ መጣ እየተጠባበቀ ሰዓታት አለፉ። እሱ ያደፈጠበት ቦታ ጨለም ስለሚል ይሁን ለሌላ ሰው ደፍሮ ብቻውን በቦታው ማለፍ ይፈራል።

ከዛ በኋላ ሰው ቀስ በቀስ ቤቱ ገብቶ ወደ ማለቁ ደረሰ። በግምት ከምሽቱ ሶሰት ሰዓት አካባቢ ሲሆን አንድ ዳቦና ፍራፍሬ የተሞላ ፌስታል የያዘ ግለስብ ጠደፈ ጠደፍ እያለ ሲያልፍ ከተደበቀበት ወጥቶ ከኋላው ይከተለው ጀመር።

ልቡ ቤቱ መድረስ ላይ የነበረው መንገደኛ ከኋላው ማን እንደተከተለው ልብ ሳይል መንገዱን ብቻ እየተመለከተ ይሄድ ጀመር። ረጅም ርቀት ፊትና ኋላ ከሄዱ በኋላ ጨለማው ድቅድቅ ያለበት የሰው ዘር ዝር የማይልበት ቦታ ላይ ሲደርሱ በያዘው በረት አንገቱን በማለት ይጥለዋል።

መሬት ላይ እንደወደቀ ጊዜ ሳያጠፋ ኪሱን ፈትሾ ያገኘውን ጥሬ ገንዘብ ሰባት መቶ ብር፣ ሞዴሉ ያልታወቀ ሞባይል የዋጋ ግምቱ 2 ሺ ብር የሆነ፣ በአጠቃላይ 2ሺ ሰባት መቶ ብር የሚያወጣ ንብረት ወሰዶ ተዘራፊው በወደቀበት ጥሎት ከአካባቢው ለማምለጥ ይጣደፍ ጀመር።

የናፈቀበት ሳይደርስ የቀረው አባት

መኮንን መስፍን ይባላል። ታታሪ ለፍቶ አዳሪ የሚባል ዓይነት ሰው ነው። በእለቱ ማልዶ ነበር ከቤቱ የወጣው። አስቸኳይ ሥራ ስለነበረበት ባለቤቱና ሁለት ልጆቹ እንደተኙ ድምፅ ሳያሰማ ሹልክ ብሎ ወደ ሥራው በረረ። ረፈድፈድ ሲል ባለቤቱ ጋር ደውሎ ሰላም ብሎ ማታ ቢያመሽም እንኳን ልጆቹ ሳይተኙ እንዲጠብቁት ይነግራታል።

«ተጨማሪ ገንዝብ ስላገኘሁ ለልጆቹ ምናምን ይዤላቸው እመጣለሁ ሳታስተኚ ጠብቂኝ» በማለት ካስጠነቀቀ በኋላ አምሽቶ ከወጣበት ሥራው ቤቱ እስኪደርስ ልጆቹ ዓይኑ ላይ እየተንከራተቱ፤ የሚያስፈለጋቸውን ፍራፍሬም፤ ዳቦም ሌሎች ሌሎች ነገሮችን ገዘቶ የተረፈውን ሰባት መቶ ብር ኪሱ እንደከተተ የናፈቁት ልጆቹና ባለቤቱ ጋር ለመድረስ ይጣደፍ ጀመር።

የናፈቃቸውን ልጆቹን አቅፎ ቤቱ ለመከተት የናፈቀው አባት በቀን ጎዶሎ የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡00 ሰዓት ሲሆን ያላሰበው ውርጅብኝ ወረደበት። ዘራፊው ልጆቹ ጋር ለመድረስ የተጣደፈውን አባት ንብረት ለመውሰድ እንዲመቸው ከኋላ ሆኖ በብረት አንገቱን በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርገው።

ለልጆቹ ይዞ ለመግባት ከገዛው አስቤዛ የተረፈውን ኪስ ውስጥ የነበረ ጥሬ ገንዘብ ሰባት መቶ ብር፣ ሞዴሉ ያልታወቀ ሞባይል የዋጋ ግምቱ 2 ሺ ብር የሆነ፣ በአጠቃላይ 2ሺ ሰባት መቶ ብር የሚያወጣ ንብረት ወስዶ የተነፋፈቁት ቤተሰቦች እስከ ወዲያኛው እንዳይገናኙ አደረገው።

አጋጣሚ ያመጣቸው የዓይን ምስክሮች

በአጋጣሚ ከሰፈራቸው ራቅ ያለ ቦታ የሚኖር ወዳጃቸውን ለቅሶ ለመድረስ የወጡት ወጣቶች ለቅሶ ቤት አምሸተው ሲመለሱ… « አ….» የሚል ድምፅ ተሰማ። ከዛ ከደቂቃዎች በኋላ አንድ የሚሮጥ ሰው በርከት ብለው ወደሚሄዱት ሰዎች እየሮጠ መጣ። ሁኔታው ያላማራቸው ሰዎች ተረባርበው ይዘው ድምፅ ወደሰሙበት ይዘውት ሲሄዱ የወደቀ ሰው ተመለከቱ።

ምንም ነገር እንደላየ ቢናገርም ፖሊስ ጠርተው አስያዙት። የወደቀውም ሰው ለልጆቹ የገዛው አስቤዛ ሜዳው ላይ እንደፈሰሰ አስክሬኑ ተነሰቶ በአንቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወሰደ።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ በቦታው ሲደርስ በአሳዛኝ ሁኔታ የወደቀው ምስኪን አባት፤ ልቀቁኝ አትልቀቁኝ እያለ የሚታገል ነፍሰ ገዳይ ፤ ለቅሶ አምሽተው የሚመጡ ከአስር የሚበልጡ ወጣቶች አካባቢው ደብልቅልቅ ብሎ ነበር። ፖለስ የዓይን ምስክሮችን ቃል ተቀብሎ ማስረጃውን ከያዘ በኋላ፤ የሆስፒታል ምርመራን ጨምሮ ወደ ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አቀረበ።

ንብረት ለመውሰድ እንዲመቸው ሟችን በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርገሀል ባለው ተከሳሽ ላይ ክስ ይመሰረትበት ዘንድ ወደ ዓቃቤ ሕገ የተላከው አምታቴ ማሞ የተባለው ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ወንጀል ሕግ አንቀጽ 671/2/ ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ክስ ቀርበበት፡፡

የዓቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

ማስረጃውን የተቀበለው የዓቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡00 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው አትላስ አካባቢ ንብረት ለመውሰድ እንዲመቸው ሟች መኮንን መስፍንን በብረት አንገቱን በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጎ ከሟች ኪስ ውስጥ የነበረ 1ኛ ጥሬ ገንዘብ ሰባት መቶ ብር፣ 2ኛ ሞዴሉ ያልታወቀ ሞባይል የዋጋ ግምቱ 2 ሺ ብር የሆነ፣ በአጠቃላይ 2ሺ ሰባት መቶ ብር የሚያወጣ ንብረት የወሰደ በመሆኑ በፈፀመው የከባድ ውንብድና ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል፡፡

የእምነት ክህደት ቃል

የሰውን ላብ ለመብላት ጨለማን ተገን አድርጎ የሰው ነፍስ ያጠፋው ተከሳሹ የተከሰሰበት ክስ በችሎት ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም ያለ ሲሆን ዓቃቤ ሕግም ተከሳሹ ክዶ ቃሉን የሰጠ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሚያስረዱ የሕግ ምስክሮቻችን ስላሉ ይሰሙልኝ በማለት ቀጠሮ ያስይዛል።

በቀጠሮውም ቀን በቦታው የነበሩ 10 የሰው ምስክሮችን አቅርቦ ያሰማ ሲሆን የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችና ማስረጃዎችም በተከሳሹ ላይ በክሱ መሠረት ያስረዱ በመሆኑ ተከሳሽ በቀረበበት ክስ መሠረት እንዲከላከል የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቀነ ቀጠሮ ተሰጠው።

ተከሳሹ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ቀርቦበት ወንጀሉን አልፈፀምኩም የሚል የእምነት ክህደት ቃል በመስጠቱ የምስክርነቱን ቃል የሚሽር ሃሳብ ካለው መከላከያ እንዲያቀርብ በተሰጠው ቀጠሮ መሠረት 3 የመከላከያ ማስረጃ አቅርቦ ቢያሰማም የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ማስተባበል ባለመቻሉ ተከሳሹ ይከላከል በተባለበት ድንጋጌ ስር ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ነህ ብሎታል።

በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ወንጀል ሕግ አንቀጽ 671/2/ ስር የተደነገገውን ሕግ በመተላለፍ በፈፀመው የከባድ ውንብድና ወንጀል ጥፋተኝነቱ ተረጋግጦ ለውሳኔ ቀነ ቀጠሮ ተቆረጠ።

ምሰከሮች

10 የሰው ምስክሮችን አቅርቦ ያሰማ ሲሆን የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በምሽት ያውም በጨለማ ከአንድ የሰቆቃ ደምፅ በኋላ ሲሮጥ ያገኙት መሆኑንና በወቅቱ ያልተገባ ዓይነት ሁኔታ በማሳየት ለማምለጥ ሲጣጣር መመልከታቸውን መስክረዋል።

« አንዴ አልነካሁትም፤ አንዴ ይሞታል ብዬ አላሰብኩም፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ አላውቀውም….. » በማለት ይቀበጣጥር እንደነበረ ተናግረው በወቅቱ በቦታው ላይ ማንም እንዳልነበረ ወንጀሉ ሲፈፀም በቅርብ ርቀት በመኖራቸው ነገሩ በትኩሱ እንዳለ መድረሳቸውን አብራሩ።

ከምስክርነቱም ባሻገር ማስረጃዎችንም በማቅረብ በተከሳሹ ላይ በክሱ መሠረት ያስረዱ በመሆኑ ተከሳሽ በቀረበበት ክስ መሠረት እንዲከላከል የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቢጠየቅም ያንን ሊያደርግ ባለመቻሉ ለመጨረሻ ውሳኔ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ለማስወሰን ተቀጠረ።

 ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት በተከሳሹ ላይ በእርከን 38 ስር በማሳረፍ ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል::

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You