ከሰሞኑ በአንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ አንድ ጽሑፍ ተለጥፎ አስተዋልኩ። ጽሑፉ ለዓይኖቼ አዲስ አልመስል ቢለኝ ጠጋ ብዬ አፈጠጥኩበት። አልተሳሳትኩም። ይህን ልጥፍ ከቀናት በፊት ከምንጩ በቀጥታ አንብቤዋለሁ። በነገሩ እየተገረምኩ ፊደላቱን አንድ በአንድ አነበብኳቸው። ‹‹እባክዎ! ፈሳሽ ሳሙና ቀንሰው አይውሰዱ›› ይላል።
ባይገርማችሁ ይህን የማሳሰቢያ ጽሑፍ ከሚመለከታቸው አካላት እየተለጠፈ በነበረ ጊዜ በቅርብ የታዘብኩ የዓይን እማኝ ነበርኩ። ስፍራው መፀዳጃ ውስጥ ከእጅ መታጠቢያው አጠገብ ከሚገኝ ግድግዳ ላይ ነው። በወቅቱ ይህን መልዕክት ስትለጥፍ ከነበረች የጽዳት ክፍል ኃላፊ ጋር ጥቂት አውርቻለሁ።
እሷ እንደነገረችኝ ፈሳሽ ሳሙናውን ቀንሰው ሲወስዱ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ሠራተኞች አሉ። ይህ መቀጠል የለበትምና ማሳሰቢያውን መለጠፍ ግድ ብሏል። ጉዳዩን ስገረምበት፣ ሳፍርበትም ሰነበትኩ። ይህን መልዕክት ከዛን ዕለት ጀምሮ ለቀናት ሳየው ፊደሉንም በግርምት ስቆጥረው ቆይቻለሁ።
የሚያስገርመው ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የሆነው ጉዳይ ነበር። ይህን ጽሑፍ በካሜራቸው ያነሱ አንዳንዶች ያዩትን እውነት አሁን በስም ላልጠቀስኩት አንድ የማኅበራዊ ‹‹ዩቲዩብ›› ገጽ በቀጥታ አስተላልፈውታል። የተላከው መረጃ በትክክል ሲለጠፍ ያየሁት ምስል ስለመሆኑ አልተጠራጠርኩም። በአካባቢው የነበሩ ቁሳቁሶች ሁሉ አንድም ሳይቀሩ አብረው ተልከዋል።
ይህን ተከትሎ መነጋገሪያ ሲሆን የቆየው ጉዳይ ታዲያ ሌላውን ተመሳሳይ ድርጊት ያስታውሰኝ ያዘ። መቼም ቸግሮን ሳይሆን ዓመል ሆኖብን የምንፈጽማቸው አንዳንድ ድርጊቶች ከስማችን በላይ መለያችን የሚሆኑበት አጋጣሚ ይኖራል። በአንዳንድ ቦታዎች ‹‹እከሌ እኮ ይሉኝታ የለውም። እከሊትም ነውርን አታወቅም›› የሚል ስም የሚሰጣቸው ሰዎች አይጠፉም።
እንዲህ አይነቱ ስያሜ የሚሰጣቸው ደግሞ ያለ ምንም ምክንያት አይደለም። አንዳንዶች በአንዳንድ ቦታዎች ክብራቸውን የሚያዋርድ፣ ሰውነታቸውን ዝቅ የሚያደርግ ጉዳይ ላይ ሲተጉ ይታያሉ። ለዚህ ማሳያ አንድ ምሳሌን ልጥቀስ። በሆነ የስብሰባ ቦታ በሚኖር የእረፍት ሰዓት ለቆይታው የሚሆን የሻይ ቡና ግብዣ አይጠፋም።
ታዲያ በዚህ ስፍራ አንዳንዶችን አለማየት ነው። የሚመጥናቸውን ያህል ከማንሳት ይልቅ የእጃቸው ሞልቶ አስኪፈስ፣ የጉንጫቸውም ተወጥሮ እስኪታይ የሚሻሙበት አጋጣሚ ይበረክታል። ጉዳዩ የሚያሳፍር ቢሆንም ለአድራጊዎቹ ግን ሁሌም ትክክል ነው።
ሰዎቹ ይህ ብቻ አይበቃቸውም። ለብዙኃን መስተንግዶ ሲባል የተዘጋጀውን ቆሎና ኩኪስ በየኪሳቸው እያጨቁ፣ ሌላ ካለ ለመጨመር ዓይናቸው ይቃብዛል። እንዲህ አይነቶቹ ታዲያ በሠርግና መሰል ግብዣዎች ላይ በተገኙ ግዜ ክፉ ዓመላቸው አይለቃቸውም። የተጠሩበትን በልተው ጠጥተው እንደጨረሱ በምስጋና መውጣት ልምዳቸው ሆኖ አያውቅም።
ዓመለኞቹ ከጎረሱት ምግብ ለመቋጠር፣ ከተጎነጩት ጠላና ጠጅ፣ ቢራና ድራፍት በላስቲክ ዕቃዎች ሞልተው ለመውሰድ ወደ ኋላ አይሉም። ይህ እንግዲህ ክፉ ዓመል ካልሆነ በቀር ምንም ስያሜ አይሰጠውም። ከመብላት መጠጣት ጥጋብ በኋላ የተረፈውን ላለመተው መሻማት ከትዝብት አልፎ ጥላቻ ላይ ይጥላል። ከዚህ ባሻገር ማንነትን በክፉ አስፈርጆ ስምን በአጉል ቅጽል ያስነሳል።
ከዚሁ የግብዣ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በበርካቶች ዘንድ የሚነወር አንድ ልማድም አለ። ይህ አይነቱ ልማድ አንዳንዶች ያለ አንዳች ሀፍረት የሚደጋግሙት ነው። ሳይጠሩ ድንኳን ሰብሮ የመግባት ክፉ አባዜ።
ይህ እውነት የሰዎቹ ድርጊት እስኪታወቅ ድረስ በክብር ሊያራምድ ይችላል። ጉዳዩ ታውቆ ማንነታቸው በተጋለጠ ጊዜ ግን ሁኔታውን ያከፋዋል። ብዙ ግዜ እንዲህ አይነቶቹ ልማደኞች ጥሩ ለብሰውና፣ አምሮባቸው የሚታዩ ናቸው። ሰዓቱን ጠብቀው ከመድረስ ባለፈ የሚቀመጡበትን ስፍራ ሳይቀር ለይተው ያውቁታል።
በአለባበሳቸው አይታሙምና በሚመለከቷቸው ዘንድ ሁሌም ሚዛን ይደፋሉ። ይህ ቁመና ከሌሎች የቀደመ ቦታና አክብሮትም ሊያሰጣቸው ይችላል። እንዳሻቸው በልተውና ጠጥተው ከጠገቡ በኋላ ግን ዓይናቸው መቃበዙን አይተውም።
ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እጃቸውን ልከው የሚያነሱትን ይፈላልጋሉ። ሠርግ ከሆነ ሰዎች ቦርሳቸውን ከወንበር ጠረጴዛ ትተው ለጭፈራ ይነሳሉ። ሞባይላቸውን እንደዋዛ ጣል አድርገው በጨዋታ ይያዛሉ። ይሄኔ እነ አጅሬዎች በለስ ይቀናቸዋል። በተከበረ ሞገሳቸው እያታለሉ የሰውን ንብረት ገፈው ከስፍራው እብስ ይላሉ።
በዚሁ የሠርግ አጋጣሚ የአንዳንዶች ልማድ ደግሞ በሙሉ ዓይን ለማየት የሚከብድ ነው። ከቀረበው የምግብ ብፌ ፊት ፈጥነው ለመሰለፍ ቀዳሚ ይሆናሉ። ተራቸው ደርሶ ምግቡ በእጃቸው ሲገባ ደግሞ ምርጫ ይሉትን ጉዳይ ፈጽሞ አያውቁትም። ከእያንዳንዱ ላይ ሰሀናቸው መሸከም ከሚችለው በላይ እየቆለሉ ሌላ ለመጨመር እጃቸውን ይዘረጋሉ።
እነዚህ ሰዎች ‹‹ያየነው ሁሉ አይቅርብን›› ባዮች ናቸው። የሚሹትን ምግብ በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ፊታቸው በፈገግታ ይደምቃል። ተጣድፈውና ተስገበግበውም መብላት ይጀምራሉ። በዚህ ፍጥነት ግን ጥቂት አይቆዩም።
ከእያንዳንዱ ላይ መለኳኮፍ እንደያዙ ሆዳቸው ይሞላል። ወዲያው ያነሱትን ምግብ ከአንዱ ጥግ አስቀምጠው ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ። ምግቡ በወጉ ሳይበላ እንደባከነ ይቀራል። እነሱም ከትዝብት ወድቀው አይቀሬው ገላጭ ስም ይለጠፍባቸዋል።
አንዳንዴ ደግሞ እንዲህ ይሆናል። ሰዎች ለመስተንግዶ በገቡበት ከፍ ያለ የሆቴል መፀዳጃ ከሚቀመጥ በርከት ያለ ሶፍት ላይ ዓይናቸው ያርፋል። በክፍሉ ሲቆዩ ታዲያ ተጠቅመው ለመውጣት ብቻ አይደለም። በአግባቡ ተጠቅልሎ የተቀመጠውን የመጸዳጃ ወረቀት በእጥፍ በእጥፉ እየጠቀለሉ ከቦርሳ ከኪሳቸው ያጭቁታል።
እንዲህ አይነቶቹ ይህን ድርጊት የሚፈጽሙት ሁሌም መፀዳጃ ገብተው በወጡ ቁጥር ነው። እናም ለበርካቶች ግልጋሎት የታሰበውን ጠራርገው በመውሰድ ለግል በማዋል የሚያህላቸው የለም። ከዚሁ የመፀዳጃ አገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚስተዋል ሌላም አሳፋሪ ጉዳይ አለ።
ዓመለኞቹ በዓይን ቅኝት የሚያገኟቸውንና በቀላሉ ለመፍታት የሚያመቹ ቁሳቁሶችን በኪስ ለማድረግ ፈጣን ናቸው። በግድግዳ የሚታሠሩ የሶፍት ማስቀመጫዎች፣ ጌጣጌጦች፣ በቀላሉ የሚፈታቱ የፎጣና የቀላል ነገር ማንጠልጠያዎች ሳይቀሩ ከዓይኖቻቸው አያመልጡም። ካመቻቸው ደግሞ ከኪስ ሲሆኑ የማያስታውቁ ፎጣዎችን ጭምር እንደ መሐረብ አጣጥፈው ይዘው ይወጣሉ።
ሌሎች ደግሞ በእንግድነት ውለው ካደሩበት ሆቴል አንሶላና የትራስ ልብስ ገፈው የሚወስዱ ናቸው። ነጠላ ጫማዎች፣ የሲጋራ መተርኮሻዎች፣ የቴሌቪዢን ሪሞቶችና መሰል ዕቃዎችም ከእነሱ አደን አያመልጡም። ደግነቱ አንዳንድ ነቄ ባለሆቴሎች ሁለት የተለያየ እግር ነጠላ ጫማ እያስቀመጡ ከመሰረቅ ለመዳን ይሞክራሉ።
ነገሩ ሁሉ ‹‹ሌባ ላመሉ›› ሆኖ እንጂ የሚወሰዱ ቁሳቁሶች ሕይወትን የሚለውጡ፣ ታሪክን የሚቀይሩ ሆነው አይደለም። አንዳንዶች ግን በትንሽ ነገር ‹‹ሰው›› ይሉትን ታላቅ ክብር ሊያዋርዱ ይፈጥናሉ። ካልተገባ መንገድ ተገኝተውም ስማቸውን በከንቱ ያጎድፋሉ። ልቦናውን ይስጣቸው።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም