ገና፦ የፍቅር፣ የይቅርታና የትሕትና መገለጫ በዓል!

 የገና በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ/መንፈሳዊ በዓላት አንዱ እና ዋነኛው ነው። በሃይማኖቱ አስተምሮ መሠረት በዓሉ፣ በብዙ ነብያት አንደበት ሲነገርለት የኖረው፣ ለሰው ልጆች መዳን ተስፋ የተደረገው፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ውልደት ከቤተልሔም የተበሰረበት ታላቅ ቀን ነው ።

እለቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢያት ምክንያት ከፈጣሪው/ከአምላኩ ጋር ተራርቆ በጭለማ ውስጥ ለመኖር ለተገደደው ለሰው ልጅ በደሙ የኃጢያት ስርየት ይሆን ዘንድ በብዙ ፍቅር እና ትሕትና የእግዚአብሔር የመስዋዕት በግ ሆኖ ወደ ምድር የመጣበት፣ ለኃጢያት ስርየት ተስፋ ጀማሪ የሆነበት ቀን ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በአምላክ መካከል በኃጢያት/ባለመታዘዝ ምክንያት የተፈጠረውን የጥል ግድግዳ ለማፍረስ፣ ሰላም እርቆት ለነበረው የሰው ልጁ እውነተኛ ሠላም በመሆን ከሠላም እጦት ሊታደገው በከብቶች ግርግም የተወለደበት ፤ እና የሠላም ብስራት ዜማ ሆኖ የተሰማበት ዕለት ነው ።

ለክርስትና እምነት ተከታዮች የመዳናቸው ጅማሬና ብሥራት የሆነው ይህ ቀን፣ ትውልዶች በብዙ መሻት ከሩቅ እያዩ የተሰናበቱት የመዳን ተስፋቸው፤ ከተስፋ ቃልነት አልፎ ሥጋ ለብሶ የተገለጠበት፣ በዚህም ከጥልቅ ፍቅር የሚመነጨውን የአምላካችንን ይቅር ባይነት የተረዱበት የደስታ ቀን ነው ።

እንደ እምነቱ አስተምሮ፤ ይህ የሆነው በብዙ ምሕረት እና ስለ ፍቅር ነው። ይህ የሆነው፤ በብዙ ይቅርታ፤ የተወለደውን ደግሞም ስለ ኃጢያት በመስቀል ላይ የሞተውን የኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅሩ፣ የይቅር ባይነቱ፣ የትሑትነቱ፣…ወዘተ የባሕሪ ተካፋይ መሆን እንድንችል ነው ።

የእምነቱ ተከታዮች አሁን ላይ ይህንን ትልቅ ትርጉም ያለውን የገናን በዓል ለማክበር ስንዘጋጅ፣ ከሁሉም በላይ ራሳችንን ፣ ከእምነቱ አስተምህሮ አንጻር የቱ ጋር ነኝ ብለን በድፍረት ልንጠይቅ፣ ለሚያገኘውም ምላሽ ታማኝ በመሆን ራሳችንን በአግባቡ ልንመረምር ይገባል።

ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ኅብረት፤ ኅብረታችን የተገዛበትን ፍቅር፣ ትሕትናና ይቅር ባይነት ልናስተውል ያስፈልጋል ። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለሌሎች ያለንን የሕይወት ተምሳሌትነት ቆም ብለን ልናጤን ያስፈልጋል።

እንደ ሀገር ክርስትናን በመቀበል ካለን የቀዳሚነት ትርክት አንጻር፤ ያሳለፍናቸውን ብዙ አስቸጋሪ ትናንቶችን ጨምሮ፤ ዛሬ ላይ እየኖርናቸው ያሉ የፈተና ቀናቶቻችንን በአግባቡ ልንመረምራቸውና ለዚህ የሚሆን ድፍረት ልንፈጥር ይገባል።

በዓሉ መንፈሳዊ በዓል ከመሆኑ አኳያ፤ በመወለዱ፤ በመከራውና በሞቱ ከተካፈልነው የፍቅር፣ የእርቅ እና የሰላም መንፈስ አንጻር፤ እንደ ሀገር በምድራችን እየሆነ ያለውን እውነታ በመወለዱ የተስፋ ቃል ልናየው፤ ለዚህ የሚሆን መንፈሳዊ ዝግጁነት ይጠበቅብናል።

እንደ ሕዝብ አሁን ላይ እየሄድንበት ያለው የፍቅር እጦት፣ የመለያየት እና የጥል መንገድ የተገነባበት ማንነታችን ከምን መንፈስ እንደተቀዳ፤ በሰከነ መንፈስ ልናጤነው ያስፈልጋል። ወንድም በወንድሙ ላይ የጨከነበት፣ በስደት እና በሞቱ በአደባባይ የሚፈነድቅበት አስተምሮን ከየት እንዳገኘነው ልንመረምር ይገባል።

እርቅን እንደ ሽንፈት የሚቆጥረው አዕምሯዊ ስሪታችን ከየትኛው መንፈስ እንደተቀዳ፣ ለጥፋት መፎከር እና ማቅራራታችን፣ በዚህም እየደነደነ ድንጋይ እየሆነ ያለው ልባችን ወዴት እየወሰደን እንደሆነ፣ በዚህም ትውልዱን እያስከፈልነው ስላለው ዋጋ ቆም ብለን ልናስብም ይገባል።

በዓሉን ስናከብር ከመብላትና ከመጠጣት ባለፈ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ ባለፈ፣ እስከ መስቀል ሞት ድረስ የሄደበትም የማዳኑን ሀሳብ፣ በኛ ሕይወት እንዲገለጥ የወደደውን የባሕሪውን ምንነት እያሰብን፤ ለሱ ያለንን ተገዢነት እያደስን መሆን ይኖርበታል።

ይህንን ማድረግ መቻል እንደ ሀገር አሁን ላይ እየተገዳደሩን ያሉ ፈተናዎችን ተሻግረን በሃይማኖቱ አስተምሮ ተስፋ የምናደርገውን፤ እውነተኛ የፍቅር፣ የእርቅና የሠላም ሕይወት ወራሽ እንሆናለን። ከዚህም አልፈን ለመጪ ትውልዶች በሁሉም መልኩ/በመንፈሳዊም ሆነ በቁሳዊ ሕይወት የተመቸች ሀገር መፍጠር እንችላለን!

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You