“የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ የሀገራችንን ታሪክና ባሕል እንድናውቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል”- በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን

አዲስ አበባ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ የሀገራችንን ታሪክና ባሕል እንድናውቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ሲሉ በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።

ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለመጡ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ከኔዘርላንድ ወደኢትዮጵያ የመጣው ዳንኤል ገብረማርያም፤ ጥሪው በውጭ ሀገራት የምንኖር ኢትዮጵያውያን ባሕልና ታሪካችንን እንድናውቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ሲል ሃሳቡን ሰጥቷል።

ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ ደስታ እንደተሰማው የገለጸው ዳንኤል፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ሀገሪቷ ያላትን ሀብት የበለጠ ለማስተዋወቅ የሚረዳ መሆኑን ተናግሯል።

በርካታ ሀገራት በቱሪዝም የሚያገኙት ገቢ ከፍተኛ መሆኑን ካየን ኢትዮጵያም በቱሪዝም ዘርፍ ተመጣጣኝ ገቢ እንድታገኝና የሀገራችን ገጽታዋን እንዲሻሻል ጥሪው ሰፊ ጠቀሜታ እንዳለው አንስቷል።

ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንም ለሀገራቸው አምባሳደር በመሆን በያሉበት ሆነው ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል ያለው ወጣት ዳንኤል፤ የኢትዮጵያን ባሕል፣ ታሪክና ቅርስ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆኑን አስረድቷል።

ከአሜሪካ የመጡት ወጣት ምሕረት በሪሁና ቴዎድሮስ ገብረንጉሥ በበኩላቸው፤ ጥሪው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መልካም አጋጣሚ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የተለያዩ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የቅርስ መገኛና ታሪካዊ ቦታዎች፣ ተፈጥሯዊ ፏፏቴዎችና ሐይቆችን ለመጎብኘት እቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ባሕል፣ ታሪክና ቅርስ ለማስተዋወቅ ፍላጎት አለን ያሉት ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያኑ፤ በተጨማሪም እናት አባት የሌሏቸው ሕጻናትን በመርዳት በሰብዓዊ አገልግሎት መሳተፍ እንደሚፈልጉ አመላክተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ባሕላቸውንና ታሪካቸውን እንዲያውቁ በተደረገው ጥሪ መሠረት የተለያዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተው አሁን ላይ እንግዶቻችንን መቀበል ጀምረናል ብለዋል።

እንግዶቹን ለመቀበል ከቪዛ፣ ከጉምሩክ እንዲሁም ከተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጋር ተያይዞ በትኩረት ሲሠራ ቆይቷል ያሉት አምባሳደር ናሲሴ፤ ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያኑ የአገልግሎት ክፍያ ቅናሽ እንደተደረገ አስታውቀዋል።

ጥሪው በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በኩል እንዲሳለጥ ተደርጓል ሲሉ አምባሳደር ናሲሴ ጠቁመዋል። በሦስት ዙር ለሚመጡ እንግዶች ባሕላቸውን እንዲሁም ቅርስና ታሪካቸውን የሚያውቁበትና ረክተው የሚመለሱበት ትልልቅ ሁነቶች እንደተዘጋጁ ጠቁመዋል።

በውጭ ሀገር ለሚኖሩ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የቀረበው ጥሪ በሦስት ዙሮች የሚከናወን ሲሆን፤ “ከብዝኃ ባሕል መሠረትዎ ጋር ይገናኙ” የተሰኘው የመጀመሪያው ዙር ከታኅሣሥ 20 እስከ ጥር 30 እንደሚካሄድም ታውቋል። በጥሪው መሠረት የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ የሚገኙ ብዝኃ ባሕሎችን እየተዘዋወሩ ይመለከታሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You