ጥቁር ና ነጭ

እማማ ሸጌ ሰፈሩ ውስጥ የታወቁ አረቄ ነጋዴ ናቸው። ከእጃቸው ላይ ማንቆርቆሪያ፤ ከፊታቸው ላይ ፈገግታ ጠፍቶ አያውቅም። ቀይ ናቸው፣ በቀይ መልካቸው ላይ ተመዞ የወጣው አፍንጫቸው ማንም ሳያየው ዓይን ውስጥ ይገባል። እንደ ቀለበት መንገድ አንገታቸው ላይ የተጥመለመለው ንቅሳት በነጭ ብራና ላይ የተነደፈ ሥዕል ይመስላል።

ከወገባቸው ጠፍቶ የማያውቀው መቀነት በሀገር ባንዲራ ተሸልሞ ሲታይ ሀገር ወዳድነታቸውን ያሳብቃል። እማማ ሸጌ በሁለት ነገር አይታሙም፤ አንደኛው ቁጥር ነው . . . የትኛውም ጠጪ ምንም ያክል ቢጠጣ ከእማማ ሸጌ ስሌት አያመልጥም። በጓዳ ጎድጓዳው እየተዋከቡ ጭንቅላታቸው ግን የእያንዳንዱን ጠጪ መለኪያ ይቆጥራል። ሁለተኛው ደግሞ ፍራንክ ነው . . . እማማ ሸጌን ከማታለል ከጆ ባይደን ቢሮ መረጃ መስረቅ ይቀላል። የአንድ ጠጪን ሂሳብ ለማስላት ምንም አይነት የቴክኖሎጂ ውጤት አይጠቀሙም፤ ለጥቂት ደቂቃ ዝም በማለት በጭንቅላታቸው ካወጡ፣ ካወረዱ በኋላ የማይጠጋጋ ሂሳብ ይነግሩሀል።

ይሄ ልዩ ብቃታቸው ነው። የሚገርመው ደግሞ ምንም አይነት የትምህርት ደረጃ የሌላቸው መሆናቸው ነው። በሦስት መንግሥት ላይ ተረማምደው መጥተው እንኳን ለሀገሬ ሕዝብ ባለውለታ ለሆነው መሠረተ ትምህርት ባይተዋር ናቸው። የጭንቅላታቸው “አይኪው″ (ችሎታ) መዛኝ ቢያገኝ ኖሮ በሂሳብ ስሌት አቻ የሌላቸው እድሜ ጠገቧ አዛውንት በሆኑ ነበር።

አስረሳህኝ የእማማ ሸጌ የረጅም ጊዜ የአረቄ ደንበኛ ነው። አስረሳህኝን ከሌሎቹ ጠጪዎች ለየት የሚያደርገው አረቄን እንደ ውሀ መጠጣቱና ራዕይ ያለው ሰካራም መሆኑ ነው። አረቄ ሲጠጣ ዓለም ላይ ጣፋጩን መጠጥ የሚጠጣ ነው የሚመስለው። አያቃጥለው፤ አይጎረብጠው፤ በቃ አንስቶ ዥው . . . ምጥጥ፣ ሽምጥጥ። ከእማማ ሸጌ ቤት ሌላ ሕይወት ያለ አይመስለውም።

እማማ ሸጌ እግዜሩ ናቸው . . . ምንም ፈልጎ የማያጣባቸው፤ ከእሳቸው ውጪ እስትንፋስ የሌለው ይመስል ውሎና አዳሩ እዛው ነው። ሰፈር ሲለቁ ሰፈር እየለቀቀ፤ ሀገር ሲለቁ ሀገር እየለቀቀ በሄዱበት በመሄድ ዛሬም ድረስ ምርጥ ደንበኛነቱን አስመስክሯል። ከወገቡ ጎበጥ ያለ ነው። እድሜ ግሳንግሱን ጭኖበት ወደ መሬት ጎንበስ ያለ . . .። በግንባሩ ሜዳ ላይ ዘመን ያሰመራቸው ቀጫጭን መስመሮች ይታያሉ። በዘመን የተኳሉ . . . በጊዜ የተቀለሙ አለላ መልኮች።

የአስረሳህኝ ሌላው ስሙ ባለራዕዩ ነው። በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ከመጠሪያ ስሙ በላይ በዚህ ስሙ ይታወቃል። አስረሳህኝና ራዕይ ተነጣጥለው የማይታዩ፣ የአንድ እጅ መዳፍና አይበሉባ ናቸው። ገና እግሩ ደፍ ሳይረግጥ ቀድመውት የመጡት የአረቄ ቤት ወዳጆቹ ባለራዕዩ ሲሉ በጭብጨባ ይቀበሉታል። ያልኖረው፣ ወደ ፊት እኖረዋለሁ ብሎ የሚያስበው ሕልም አለው። እውነት ለመናገር እየኖረው ያለውን ሕይወቱን አይወደውም።

አረቄ ቤት ከመዋልና ሰክሮ የትም ወድቆ ከማደር ባለፈ ለዚች ዓለም ያበረከተው አስተዋፅዖ የለም። በዚህ ይበሳጫል . . . ነገ ላይ ሌላ ሰው ሆኖ ራሱን ማየት ይፈልጋል። ከዚህ የበዛ እምነቱ በመነሳት ጓደኞቹ ባለራዕዩ አሉት . . . ባለራዕዩ ሆኖ ቀረ። ሕልሙ የሚጀምረው ግን እማማ ሸጌ ቤት ሲደርስና አንድ ሁለት መለኪያ አረቄ ሲደረግም ነው። ከዛ በኋላ ሌላ ነው . . . ባለቢጫ አይኖቹ ጓደኞቹ በወሬው እስኪሰለቹ ድረስ ስለ ሕልሙ ይዘባርቃል።

እማማ ሸጌ ከነማንቆርቆሪያቸውና ከነፈገግታቸው ከእቃ ቤቱና ከሳሎኑ አዋሳኝ ላይ ቆመው መለኪያው የጎደለበትን ይቃኛሉ። በዚህ መሐል ጎጃም አዘነ የለበሰ አንድ አዙሮ አደር “ሎተሪ . . . ነገ የሚወጣ . . ∙ አስር ሚሊዮን ብር″ እያለ ወደ ውስጥ ገባ።

አስረሳህኝ የሎተሪ አዟሪውን እጅ አፈፍ አድርጎ … “አ . . አን . . ንድ ስጠኝኝኝ″ አለው . . . ስካር ባነቀው ንግግር። እጁን ሱሪው ኪስ ከቶ ፍራንክ ሊያወጣ እየተፍጨረጨረ። ባለሎተሪው ከትከሻው የተንሸራተተ ጎጃም አዘነውን ሽቅብ እያጣፋ እንደተባለው አንድ በጥሶ ሰጠው።

አስረሳህኝ ሎተሪውን አፍጦ እየተመለከተ “እድለ ቢስ ነኝ፤ ግን ደግሞ ባለራዕይ . . ያልተኖረ፣ ያልተነካ ድንግል ራዕይ። ″ አለ ለራሱ።

ከቀናት በኋላ አስረሳህኝ እማማ ሸጌ ቤት አምሽቶ ሰክሮ ቤቱ ሲገባ ጠዋት የከፈተው ሬዲዮ እያወራ ያገኘዋል። ጫማውን ሊያወልቅ ሲንደፋደፍ ሬዲዮው የምሽቱን የሎተሪ አሸናፊ ቁጥር ሲናገር አንድ ሆነ። እጁን ወደ ኪሱ ከቶ ሎተሪውን አወጣ . . .። የሰዓቱ ዜና አንባቢ የመጀመሪያውን ቁጥር ተናገረ፤ አስረሳህኝ እጅ ላይ ካለው የሎተሪ ቁጥር ጋር ተመሳሳይ ነበር። አስረሳህኝ አላመነም . . . ስካሩ ለቀቀው።

ዜና አንባቢው ቀጥሎ ያለውን ተናገረ . . . አሁንም ተመሳሰለ። ሰካራሙ ሰው እየሆነ ያለውን ነገር ማመን አልቻለም። በዜና አንባቢው አፍ ያልተጠሩ የመጨረሻ አራት ቁጥሮች ይቀራሉ። አስረሳህኝ ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም።

በመሐል ሬዲዮኑ ቀጠለ . . . የአስረሳህኝን የሎተሪ ቁጥር እያየ የሚናገር ይመስል ቁጥሩ ከቁጥሩ ጋር አንድ ሆነ። አስረሳህኝ ሳያስበው ጮኽ። ከዚህ በኋላ የሆነውን አያስታውሰውም . . .። የመጨረሻ ሁለት ቁጥሮች ይቀሩታል። ከነዚህ ሁለት ቁጥሮች በኋላ የአስረሳህኝ ታሪክ ይቀየራል። ዜና አንባቢው ገና አልጠራቸውም . . . ልቡ ድም . . . ድም አለ።

ከሁለቱ አንዷ በዜና አንባቢው አፍ ተጠራች። በደስታ ውስጥ ሆኖ አንዷን ሰማት . . . እሱ እጅ ላይ ካለችው ጋር ተመሳሳይ ነበረች። አስረሳህኝ ደስታ አሸነፈው . . . የመጨረሻዋን ቁጥር ሳይሰማት በደስታ መሬት ላይ ተዘረረ።

ሌሊት ሲነጋጋ አስረሳህኝ ራሱን ከሳተበት ነቃ። ምን ተከስቶ እንደነበር ለማስታወስ አልተቸገረም። እስኪነጋ በደንብ አሰበ። እማማ ሸጌ አረቄ ቤት ላይደርስ፤ መርካቶ ጠጅ ቤት ላይገባ፤ ሰባተኛ ጉሮኖ ውስጥ ላይገኝ፤ መዋያውን ዱባይና ሙባይ ከቆነጃጅት ጋር ሊያደርግ ከወዲሁ አሰበ። ሌሊቱ ራቀበት. . . ንጋት ተሰወረበት። ነግቶ እየመሸ እንጂ መሽቶ እየነጋ፤ ሰዓቱም ወደ ኋላ እንጂ ወደ ፊት የሚቆጥር አልመስልህ አለው።

12 ሰዓት ላይ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ሄደ . . . የሥራ ሰዓት እስኪደርስ እየተንቆራጠጠ መጠበቅ ግድ ነበረበት።

“ምን ልርዳህ?″ አሁንም አሁንም መነጽሩን ወደ ቅንድቡ የሚገፋ ሰው ጠየቀው።

“አስረሳህኝ እባላለሁ . . . እ . . .″ አስረሳህኝ ያልተጠየቀውን መለሰ።

“እኮ ምን ልርዳህ?″ መነጽሩን እየገፋ በድጋሚ ጠየቀ።

“የሎተሪ አሸናፊ ሆኜ፣ አንደኛ እጣ ደርሶኝ፣ ገንዘቤን ልቀበል መምጣቴ ነው። ″ በታላቅ ጉራና መኩራራት መለሰ።

“ሎተሪውን ልታሳየኝ ትችላለህ?″

አስረሳህኝ በቅድሙ መኩራራት በእጁ ጨምድዶ የያዛትን የሎተሪ ትኬት ዘረጋለት። ዓለም ፊቱ ላይ ትታየዋለች . . . ተዘርግታ ልትቀበለው።

መነጽሩን ወደ አፍንጫው ካልገፋ ሕይወት ያለው የማይመስለው ሰውዬ የሎተሪውን ቁጥር በደንብ ካየ በኋላ አጠገቡ ያለውን ኮምፒውተር መጎርጎር ጀመረ።

አስረሳህኝ . . . ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ስላለው አስደናቂ ሕይወቱ በማሰብ ላይ ነበር።

“አቶ አስረሳህኝ . . .″ ከኮምፒውተሩ ላይ ቀና ብሎ ጠራው።

አስረሳህኝ ከሀሳቡ ባኖ እየወጣ . . . “አዎ ነኝ . . . አስር ሚሊዮን ብር . . . አቤት . . . አቤት″ እየዘላበደ ወደ ሰውዬው ተንደረደረ።

‹አዝናለሁ! ሎተሪው አልደረሰህም . . .″

አስረሳህኝ ነፍስ ላይ ረጅም ዝምታ ሰፈረ . . .

“የመጨረሻዋ አንድ ቁጥር የተለየች ናት″ መነጽሩን ወደ አፍንጫው እየገፋ ተናገረ።

በአስረሳህኝ ገጽ ላይ ጀምበር ተሰወረች። ከተስፋው ምሥራቅ ላይ ጀምበር ጠለቀች። የፈገግታው፣ የጽናቱ፣ የሁሉ ነገሩ ፀሐይ ዳመነች። ከእምነቱ ጋር ተኳረፈ . . .

ወደ ኋላው መሬቱ ላይ ሲዘረር . . . ዳግም ላለመነሳት የማለ ይመስል ነበር።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2016

Recommended For You