በጎነት የሚታይ ፍሬ ነው። የሕይወትን ጎተራ የሚሞላ ለግለሰብና ለሀገር የሚተርፍ ተግባር፤ በጎነት ከማሰብ በዘለለ፤ አብዝቶ ከመልካም ሥራዎች ጎን መሰለፍን፣ ሌሎችን ማገዝ ላይ ማተኮርን ከሰው ምላሸ ሳይጠብቁ ከራስ በላይ ለሌሎች ማድረግን የሚጠይቅ የንፁህ ልብ ክዋኔ ነው።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ደግሞ ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነትና መልካም ፈቃድ በኅብረተሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በማሳተፍ ነፃ አገልግሎት የሚያበረክቱበት ተግባር ነው፡፡ ይህ አገልግሎት የሰው ልጅ ምንም ዓይነት ክፍያ የማያገኝበት ያስደስተኛል፣ የህሊና እርካታ ያስገኝልኛል፣ ይበጀኛል ብሎ ያለምንም ቀስቃሽና ጎትጓች በእራሱ ተነሳሽነት የሚፈፅመው ተግባር ነው፡፡
ይህ ተግባር ማንኛውንም ዜጋ የሚያሳትፍ ቢሆንም በዋናነት ግን ወጣቶችን በስፋት የሚመለከት ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ማኅበራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ፍቅርን የበለጠ እንዲጠናከር የሚያደርግ ስለመሆኑም ይነገራል፡፡ ከወጣት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪዎች መካከል ወጣት ሄኖክ ፍቃዱ አንዱ ነው፡፡
ሄኖክ ተዋልዶ ያደገው በመዲናችን አዲስ አበባ ኮልፌ አካባቢ ነው። ወጣቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ በጎ አድራጎት ሥራ የገባበትን አጋጣሚ ሲያስታውስ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ተማሪ በነበረበት ወቅት አዲስ ሕይወት የበጎ አድራጎት የሚባል ክበብ ውስጥ አብሮ በሚሰራበት ወቅት በአካባቢው ለአቅመ ደካሞች እና ለሕፃናት ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡ ለሕፃናት የመማሪያ ቁሳቁስ እንዲሟላላቸው ሲያደርግ ባየው የሕፃናቱ ደስታና ሳቅ በተሰማው ሀሴት መነሻ በጎነትን የሕይወቱ አንድ አካል አድርጎ ለመሥራት እንደወሰነ ይናገራል።
በመቀጠል ከባይሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ማህበር መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ሄኖክ ስለማህበሩ አመሠራረት ሲናገር፤ በኢኮኖሚ አቅማቸው እጅግ ደካማ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተቻለው አቅም ድጋፍ ለማድረግ በማሰብ እንደተመሠረተ ይናገራል። በመኖሪያ ሰፈሩ አካባቢ ካፍቴሪያ ውስጥ ተቀምጦ ጊዜ ከማባከን ለማኅበረሰብ ለሀገር የሚጠቅም ቁም ነገር ያለውን ሥራ ለምን አንሰራም? በማለት ከሰፈር ጓደኛሞች ጋር በመነጋገር አስር ከሚሆኑ አብሮ አደጎቹ ጋር አንድ ላይ በመሆን የተመሠረተ ስለመሆኑ ይናገራል።
ወጣት ሄኖክ እንደሚገልፀው፤ 20 ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ዩኒፎርም በማልበስ፣ ደብተርና እስኪርብቶ በመስጠት የተጀመረው ባይሽ ኮልፌ በኋላም ልጆች ወልደው ልጆቻቸው የሞቱባቸውን ወይም መሃን የሆኑ እናትና አባቶችን በማገዝ ቀጥሎ ዛሬ ላይ በብዙ መልኩ ለብዙዎች የሚተርፍ የበጎነት ቤት ሆኗል ይላል።
በአሁኑ ወቅት በባይሽ ኮልፌ ወርሃዊ አስቤዛ የምገዛላቸው በቋሚነት የሚረዱ ከሰማንያ በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦች እንዳሉ የሚናገረው ሄኖክ፤ በሌላ መልኩ ከእነዚህ ቤተሰቦች ጋር በክርስቲያንም ሆነ በሙስሊም በዓላት ላይ አብሮ በመሆን እንደሚያሳልፉ፣ በተጨማሪም የጠፉ ሰዎችን በማገናኘት፣ እነዚህ በቋሚነት የሚረዱትን ህመም በሚያጋጥማቸው ጊዜ የሕክምና ርዳታ እንዲያገኙ በማድረግ፣ መኖሪያ ቤታቸው በተለያየ ምክንያት የፈረሰባቸውን ሰዎች ቤታቸውን በማደስ፣ ጎዳና ላይ ያሉ ዜጎችን ደግሞ ከተለያዩ ማዕከላት ጋር በመነጋገር ወደ ማዕከል የሚያስገቡበትን ሁኔታ መመቻቸት፣ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ደግሞ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ደጋግ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር በውጭና በሀገር ውስጥ የሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኙ በማድረግ እየሠራ እንደሆነ ይናገራል።
ጎዳናን ቤታቸው ያደረጉ በባይሽ ኮልፌ አማካኝነት ከጎዳና የራሳቸውን ቤት የሰሩና ሥራ ፈጥረው እርሳቸውን ከመቻል ባለፈ ሠራተኛ ቀጥረው ለሌሎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ፣ ለራሳቸው ጥሩ ኑሮ ከመምራት በዘለለ ለሌሎች መትረፍ የቻሉ እንዳሉ የሚናገረው ሄኖክ፤ በዚህም ትልቅ ደስታና እርካታ እንደሚሰማው ይገልጻል።
ወጣት ሄኖክ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበረው ቆይታ ወጣት ሆኖ በበጎ አድራጎት ላይ መሳተፍ ምን ዓይነት ስሜት እንዳለው ሲናገር፤ በጎነት በቃላት የማይገለጽ ትልቅ ደስታና ዋጋ ያለው ነገር እንደሆነ ይገልፃል። የተከፉ ፊቶች በደስታ ሲሞሉ ማየት፣ ጠያቂና አጋዥ ለሌላቸው ሰዎች ጊዜ በመስጠትና አብሮ በማሳለፍ የሚገኘው ውስጣዊ ደስታ ትልቅ እንደሆነ ይናገራል።
በዚህ የበጎ አድራጎት ሥራ ውስጥ ብዙ ደስ የሚያሰኙ በዛው ልክ የሚያስከፉ አጋጣሚዎች ይኖራሉ የሚለው ወጣት ሄኖክ፤ ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው በገንዘብ እጥረት ምክንያት ግን ሕክምና ማግኘት ተስኗቸው ሞታቸውን የሚጠባበቁ ሰዎች ለበጎነት በተዘረጉ እጆች እርብርብ ታግዘው ለሕክምናቸው የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ ተሟልቶ ታክመውና ድነው ደስተኛ ሲሆኑ ማየት ያለው ስሜት በቃላት የማይገለጽ እንዳልሆነ ይናገራል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከፍተኛ እርብርብ ተደርጎ በብዙ ዋጋ መክፈል ለሕክምና የሚያስፈልጋቸው በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር የገንዘብ ወጪ አሁንም ለደግነት በተዘረጉ እጆች ድጋፍ ተሟልቶ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ይኖራሉ የሚለው ሄኖክ፤ እነዚህ አጋጣሚዎች ደግሞ ልብ የሚያሳዝኑ እንደሆኑ ይናገራል።
በጎነት የሚጀምረው ከሰፈርና ከጎረቤት ነው የሚለው ወጣት ሄኖክ፤ በጎ አድራጎትን በተመለከተ አሁን ላይ ያለው የሰው አመለካከት እየተሻሻለ የመጣና ይበል የሚያሰኝ ነው፤ ለዚህም አሁን ባይሽ ኮልፌ ያለበት ሁኔታ ዓይነተኛ ምስክር መሆን የሚችል ነው ይላል። ብዙ ቁጥር ያለው ድጋፍ የሚደረግለት ሰው ቅን ግለሰቦች በሚያወጡት ገንዘብ መሆኑን በማስታወስ፤ ለበጎ ሥራ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሰዎች እንደሚተጉ ይናገራል።
አሁንም ግን ጎዳና ለወደቁ ዜጎች ማኅበረሰቡ የሚያደርገው አስተዋፅኦ ማደግ ያለበት ነው የሚለው ወጣት ሄኖክ፤ በኢትዮጵያ ካለውና ርዳታ ከሚያስፈልገው የሰው ቁጥር አንፃር በሀገር ደረጃ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት ጥቂት ናቸው፡፡ ይህ ማለት ተቋማቱ የያዙት የሰው ቁጥር ትንሽ ነው ብሏል። በየጎዳናው የወደቀው ሰው ደግሞ ብዙ ነውና ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት ተቋማትና መንግሥት በዚህ ዓይነት ሥራዎች ላይ በስፋት መሥራት የግድ የሚልበት ሁኔታ መኖሩን አስረድቷል፡፡
የተረጂው ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ከማኅበረሰቡም ሆነ ከመንግሥት ብሎም ከሕዝቡ ብዙ የሚጠበቅ መሆኑን በማስታወስ፤ ለበጎ ሥራዎች በእኔነት ስሜት መተጋገዝ እና መረዳዳት ከሁሉም የሰው ልጆች የሚጠበቅ የውዴታ ግዴታ እንደሆነም ያስረዳል። አሁን ላይ ባይሽ ኮልፌ ለአንዳንድ የሥራ ጉዳዮች ማስፈፀሚያ የሚጠቀምበት ቢሮ እንጂ በቋሚነት አረጋዊያን የሚረዳበት ቦታ እንደሌለው የሚናገረው ወጣት ሄኖክ፤ ‹‹ማህበሩ ህልውና ኖሮት መቆየት እንዲችል እና የሄኖክም ሆነ የሌሎች መስራቾች ተሞክሮ እንዲሰፋ፤ ካለፍን በኋላም ማህበሩ ለብዙዎች ማረፊያ እንዲሆን ለማስቻል እየተሰራ ነው፡፡›› ሲል ተነግሯል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁን ላይ የባይሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ማህበር ትልቁ ዓላማ ለማህበሩ ቋሚ የሆነ ቦታ እንዲኖረው ማስቻል ነው የሚለው ሄኖክ፤ ለዚህም እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፤ ይህንኑ ዓላማ ከመልካም ነገር ጋር ለመተባበር ሁልጊዜም ከማይሰንፉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር እውን ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነ ተነግሯል።
የ2014 ዓ.ም የዓመቱ የበጎ ሰው እጩ ተሸላሚ የነበረው ወጣት ሄኖክ፤ ለሚያከናውነው የበጎ አድራጎት ሥራ ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ዕውቅና የተሰጠው ቢሆንም፤ የተሰጡት ዕውቅናዎች ተጨማሪ የቤት ሥራ ይዘው የሚመጡ እንጂ ባለበት እንዲቆም የሚያደርጉ አለመሆናቸውንም ይናገራል።
በጎነት ሽልማት የሚያሻው ባይሆንም፤ ከብዙ ሰው መካከል ከአንድ እስከ ሶስት ውስጥ መግባት በራሱ የሚሰጠው ትርጉም የሰው ፍቅር ምን ያህል እንደሆነ ማሳያ ነው የሚለው ወጣት ሄኖክ፤ ይህ ለእርሱ እንደ ሸክምም ብዙ የቤት ሥራ የመስጠት ያህል መሆኑን ይናገራል፡፡ «የሚሰማኝ ከአንተ ብዙ እንጠብቃለን የማለት የአደራ ምልክት እንደሆነ ነው» የሚለው ወጣቱ፤ «በሠራሁት ሥራ ስለሚገባኝ የተሰጠኝ ሽልማት ነው ብዬ አላምንም፤ ምን ሰርቼ ነው ብዬ አስባለሁ ለተሰጠኝ ዕውቅና፣ ሽልማትና ፍቅር ግን ትልቅ ክብር አለኝ፡፡ ዕውቅናውም ከሁሉም የባይሽ ኮልፌ አባላት ጋር በጋራ ያገኘነው ነው። ይህ መሆኑ ማኅበራችንን የሚያበረታታ ነው» ይላል።
ባይሽ ኮልፌ የብዙ ሰው የጠብታ ውጤት ነው የሚለው ወጣት ሄኖክ፤ ከመጀመሪያው ጀምሮ አብረውኝ ለነበሩ ድጋፍ ከማድረግ እጃቸው ያልተሰበሰበ ብዙ ደግ ልቦች አሉና ያገኘው ዕውቅና ለእነዚህ ለመልካምነት ለተዘረጉ እጆች ሁሉ የተሰጠ ማበረታቻ እንደሆነ ነው ሲል ይናገራል።
የዚህ የመልካም ተግባር ባለቤት የሆኑት ወጣቶች የሚያከናውኑት ማኅበረሰብ ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው፡፡ ስለሆነም ለጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች አቅማቸው በፈቀደ መጠን የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስልቶችን በመጠቀም እንደ ልብስ፣ ምግብና መሰል መሠረታዊ ፍላጎቶችን ከማሟላት ጀምሮ ሌሎች ድጋፎችን ስለማድረጋቸው ወጣቱ ይገልፃል።
ወጣት ሄኖክ እንደሚናገረው፤ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመስጠታቸው በተጨማሪ አሁን በሀገራችን ላይ ያለው የሰላም እጦት መፍትሔ እንዲያገኝ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ሚናቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ከእነዚህ ሚናዎች መካከል በዋናነት ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተጓዳኝ በማኅበራዊ ሚዲያ ድህረ ገፆች አማካኝነት ሰላም ጠፍቶ ግጭት፣ ልማት ጠፍቶ ጥፋት፣ እድገት ሳይሆን ውድቀት እንዲነግስ ለማድረግ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት የሀገርን ሰላም የዜጎችን ወጥቶ መግባት አደጋ ላይ ለመጣል የሚጥሩ ኃይሎችን መላ ሊባል ይገባል ይላል።
ወጣት ሄኖክ እንደሚገልጸው፤ በባይሽ ኮልፌ የ13 ዓመታት ጉዞ ባላቸው ነገር ሁሉ ከጎን የሚቆሙ ጥቂቶች እንዳልሆኑ ይናገራል። ሕሙማን ላይ ለውጥ ሲታይ ደግሞ ያሉት ለውጦች አስደሳች እና ተስፋ አጫሪ ስለሚሆኑ የሌለውንም መዳን በመመኘት መንቀሳቀስ ይመጣል ይህ ደግሞ ጥንካሬ የሚሰጥ ነገር ነው ይላል። በሕመም ውስጥ የነበሩ ሰዎች ተሽሏቸው ከራሳቸው አልፈው ለሰው ማሰብ እና መጨነቅ ሲጀምሩ ማየት፣ ትናንት ጎዳና ላይ ወድቀው የነበሩ ሰዎች ለሌላ ለመትረፍ ጥረት ሲያደርጉ ሲመለከት ልቡ እንደሚነካ እና ጎዳና ላይ ወድቆ ያለ ሰው ሁሉ ድኖ ማየት ምኞቱ መሆኑን ይናገራል፡፡
በሚያገግሙ ሰዎች ላይ ያለው ለውጥ ለሌሎችም ለመድረስ በሚደረገው ጥረት ስንቅ ሆኖ እንደሚያገለግለው የተናገረው ወጣት ሄኖክ፤ ይህም በሥራው እንዲቀጥል እና እንዲበረታታ ሌሎች ሰዎችም ዓላማውን እንዲከተሉ ያደረገው መሆኑን ወጣት ሄኖክ ይናገራል።
በጎነት ዓይነቱ የበዛና አከናወኑም የተለያየ ነው የሚለው ሄኖክ፤ ሀገር ማለት ሰው እንደመሆኑ ሀገር የሚለውጥ መልካም ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ሀገራቸውን ለማቅናት በበጎ አድራጎት ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ የወጣትነት ትኩስ ጉልበት ለበጎነት ሲውል ደግሞ እንደ ሀገር ትርጉሙ ብዙ እንደሆነ ይናገራል።
ለመልካም ሥራ ረፍዶ አያውቅም የሚለው ሄኖክ፤ በጎነትን ዛሬ መጀመር ይቻላል። ካለን ነገር ለማካፈል የግድ ሀብታም መሆን ወይም ሚሊየነር መሆን አያስፈልገንም፤ ማንኛውም ሰው በጎ ነገር ማድረግ ይችላል። ስለዚህ የወደቁትን ለማንሳትና ጠያቂና አጋዥ የሌላቸውን ሰዎች አለንላችሁ ለማለት ሁሉም ሰው በተለይ ወጣቱ እጁን መዘርጋት እንዳለበት ይናገራል።
በመጨረሻም ሄኖክ ባስተላለፈው መልዕክት፤ ባይሽ ኮልፌ እስከ አሁን በቆየባቸው 13 ዓመታት ውስጥ ጫማ ከመጥረግ፣ ሶፍትና ቁልፍ መያዣ ፀሐይ ወይም ብርድ ነው ሳይሉ ሁልጊዜም ከማህበሩ ጋር አብረው ለነበሩ፣ ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር በስደት ላይ ሆነው ስለ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ግድ ብሏቸው ለሚጨነቁ ድጋፍ በማድረግ ከማህበሩ ጎን ለቆሙ በጎ ፈቃደኛ የባይሽ ኮልፌ አባላት በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋናን ማቅረብ እንደሚፈልግ ተናግሯል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2016