ከሀገር ጥቅም በተጻራሪ መቆም ነውር ነው!

በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ሀገር ዜጋ ደረጃው ይለያይ እንጂ ስለ ሀገሩና ሕዝቡ የሚቆረቆር ማንነት አለው። ይህ ማንነቱ በደግ ቀናት ለሀገሩ በጎ ከማሰብ ጀምሮ በክፉ ቀን ውድ የሆነውን ሕይወቱን እስከ መስጠት የሚደርስ ነው። ይህ እውነታ ሀገራት እንደሀገር እንዲቀጥሉ ከማስቻል ባለፈ፤ የሀገርና የሕዝብን ጥቅም በማስከበር ሂደት ውስጥ ወሳኝ አቅም እንደሆነ ይታመናል።

በተለይም አሁን ባለንበት ወቅት፤ ዓለም በብዙ ፍላጎቶች እና እነዚህን ፍላጎቶች ለማስፈጸም የሴራ ፖለቲካ እንደ አንድ አማራጭ ስትራቴጂ እየተወሰደ ባለበት ሁኔታ፤ ሀገር እንደ ሀገር እንድትቆምም ሆነ፤ የሀገርና የሕዝብ ጥቅሞች ተጠብቀው እንዲቀጥሉ ዜጎች፤ ዓለም አቀፋዊ እውነታውን ተረድተው ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለሀገራቸው ዘብ ሊቆሙ ይገባል።

በተለይም ወቅታዊ የፖለቲካ ሞቅታዎች ሊፈጥሩ ከሚችለው መጠለፍ፤ ዓለም አቀፍ ሴራዎች ሊያመጡ ከሚችሉት የመለያየት አደጋዎች፤ በማንነት ላይ ከተገነባ የእልህ ፖለቲካ ራሳቸውን በማቀብ እንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ወቅቶችን በተረጋጋ መንገድና በሰከነ መንፈስ ማሳለፍ የሚያችል ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ።

ይህን አይነት ዝግጁነት ማጣት የሀገርና ሕዝብን ተጠቃሚነት አደጋ ውስጥ የሚከት፤ ሀገርን እንደ ሀገር ሊያሳጣ እንደሚችል ከዓረብ የፀደይ አብዮት ማግስት በመካከለኛው ምስራቅ የሆነውን ተጨባጭ እውነታ ማስታወስ ተገቢ ነው። ወቅቱ የፈጠረው ሞቅታ፣ የእልህ ፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ሴራ ተዳምረው የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤት የሆኑ ሀገራትን ሳይቀር መንግሥት አልባ በማድረግ ሕዝቦቻቸውን ለሞት፣ ለስቃይና ለስደት ዳርጓል ።

እኛ ኢትዮጵያውን ካለን የዘመናት የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ አንጻር በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ የመጣን፤ ዛሬም በብዙ ውጣ ውረዶች እየተፈተን ያለን ሕዝቦች ነው። ይህ እንደ ሕዝብ ትውልዶች እያለፉበት ያለው የፈተና ሕይወት በብዙ መልኩ ስለሀገራችን የበለጠ ቀናኢ እንድንሆን፤ በሀገር ጉዳይ አንድ ዓይነት ድምፅ እንዲኖረን፤ ከሀገርና ከሕዝብ የምናስቀድመው ነገር እንዳይኖረንም ትልቅ አቅም ሆኖናል ።

ከዚህ የተነሳም ጠላቶቻችን በተለያዩ ጊዜያት እንደ ሀገር ተከፋፍለዋል፤ በመካከላቸው ያለው መከፋፈል ለዓላማችን ስኬት ጉልበት ይሆነናል ብለው፤ ለከንቱ ዓላማቸው ሊያንበረክኩን በተንቀሳቀሱባቸው ወቅቶች ሁሉ ባልጠበቁት እና ባልገመቱት መንገድ የልዩነት አጀንዳዎቻችን ጥለን ስለሀገራችን በአንድነት ተሰልፈን፤ በብዙ የተጋድሎ መስዋዕትነት ሀገራችንን አስጠብቀን ቆይተናል ።

የብሔራዊ ማንነታችን አንድ አካል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሀገራዊ ትርክታችን አንድ ምዕራፍ እና ልዩ ቀለም የሆነው መገለጫችን፤ ከትውልድ ትውል እየተላለፈ ለመጣው፤ እንደ ሕዝብ የነፃነት ቀንዲል ሆነን እንድናበራ ያስቻለን ይሄው ስለሀገርና ስለ ሕዝብ ያለን የጸና ወገንተኝነት፤ ነገም ተስፋ ለምናደርጋት የበለጸገች ሀገር ግንባታ መተኪያ የሌለው አቅማችን እንደሚሆን ይታመናል።

ይህም ሆኖ ግን አሁን አሁን ከዚህ ብሔራዊ ማንነታችን ተምጠው ያልተወለዱ፤ ከሀገርና ከሕዝብ ተጠቃሚነት ባፈነገጠ መልኩ ጊዜያዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት፤ የፖለቲካ መሻታቸውን እውን ለማድረግ፣ ከዚያም አልፈው በግልጽ በባንዳነት የጠላቶቻችን መሣሪያ በመሆን ሌት ተቀን ያለ እንቅልፍ የሚዳክሩ ”ኢትዮጵያውያንን” ማየት እየተለመደ መጥቷል።

ይህ እውነታ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት፣ እንደ ሀገር በመጣንባቸው ውጣ ውረዶች ውስጥ በተጨባጭ ተስተውሏል። በእነዚህ ዓመታት እንደሀገር ለከፈልናቸው ያልተገቡ ዋጋዎችም ተጠቃሽ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ ሕዝባችን ተገቢውን ግንዛቤ መጨበጥ ካልቻለ ተስፋ ያደረግናቸውን ነገዎች ሊያጨልምብን እንደሚችልም መገመት አይከብድም።

የሀገር ዋጋ፣ የሀገር ፍቅር፣ የሕዝብ ጥቅምና ለሕዝብ ጥቅም የሚከፈል ዋጋ ምንነት በአግባቡ ያልተረዱ፤ ለመረዳትም ፈቃደኛ ያልሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች፤ አሁን አሁን ፍጹም በሆነ ጠላትነት፤ በአደባባይ ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅሞች በተጻራሪ ያለ እፍረት፣ ቆመው ማየት፤ ሲጮሁ መስማት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሆኗል ።

እነዚህ ግለሰቦች ሀገር ከጊዜያዊ ፍላጎታቸው እና ከፖለቲካ መሻታቸውን በላይ መሆኗን፣ በብዙ ትውልዶች የመስዋዕትነት ቅብብሎሽ እዚህ መድረሷን፤ ከነሱ በፊት የነበረች፣ ከነሱ በኋላ የምትኖር፤ የልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው የተስፋ አድማስ እንደሆነች አሳዛኝም አሳፋሪም ነው።

ይህ ተግባራቸው የቀደሙት አባቶቻችንን ስለ ሀገርና የሕዝብ ጥቅም ብዙ ዋጋ ከፍለው የጻፉትን ደማቅ ታሪክ የሚያደበዝዝ ፤ እንደ ትውልድ የሁላችንንም አንገት የሚስደፋ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዘመናት የምንታወቅበትን ብሄራዊ ማንነታችንን የሚያሳንስ፤ በሀገርና በሕዝብ ጥቅም ላይ የሚቀነቀን አሳፋሪና ነውረኛ ተግባር ነው!

 አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2016

Recommended For You