ሆሊውድ ወለድ ወረራ በኢትዮጵያ

ለዚያ ጥቁር ምስጋና ይግባውና ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ አንድ አፍሪካዊ ወጣት ነበር።

ከቀናት በፊት የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ትስስር በሆነው ዩቱብ፣ አንድ ጥቂር አፍሪካዊ ወጣት የአንድ የሆሊውድ ፊልምን ምስል እያሳየ ደጋግሞ ኢትዮጵያ . . . አቢሲኒያ እያለ ስሟን ይጠራል። ይህንን ወጣት በስሜታዊነትና በልበ ሙሉነት ሲያወራ ለተመለከተ አንድ ኢትዮጵያዊ የታሪክ ምሁር እንጂ አንድ ጥቁር ዩጋንዳዊ የሚዲያ ዘዋሪ አይመስልም። የሚያወራው ነገር ከጆሮዬ ቀድሞ ልቤን ሰርስሮ የገባ መሰለኝ። ኢንግሊዛዊው ደራሲ ቶልኪን “ሎርድ ኦፍ ዘ ሪንግስ የተሰኘው ፊልም ታሪክ ምናብ የተቀላቀለበት የጥንት የእንግሊዝ ታሪክ ነው ብሎ ነበር፤ ግን ውሸቱን ነው። ቶልኪን ውሸታም ነው፤ ይህ የአቢሲኒያዊያን፤ የአፍሪካዊቷ ሀገር የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። . . . ይህን ተመልከቱ . . . ይህ በጥንታዊቷ ሀገር የነበር ነው . . . ይህ ደግሞ አሁንም ያለ . . .” እያለ ወጣቱ ጥቁር ገለጻውን ይቀጥላል። ይበልጥ ቀልቤን እየሳበው መጣ። በጥቂት የነካካቸው ታሪኮች የኛ ስለመሆናቸው ጥርጥር ባይኖረኝም ፊልሙን ለመመልከት ጓጓሁ። ጓጉቼም አልቀረሁ፤ በብዙ ክፍሎች የታጨቀውን ይህን ፊልም በከፊል ተመለከትኩት። ወጣቱ አልተሳሳተም። እንዲያው እሱ ያልጠቀሳቸው በርካታ ነገሮችን ለማስተዋል ቻልኩኝ። የነገሩን ጅራት ይበልጥ ለማዳበር የኛን ሀገር የማህበራዊ ሚዲያ ድረገጾችን ብበረብረም የታሪክ አዋቂ ነን በማለት ታሪክ እያቦኩ፣ እዚህም እዚያም ከሚመርጉ የሚዲያ አብዮተኞች ለበስመአብ ያህል አንድ እንኳን ሳላገኝ ቀረሁ። ከዚያ ይልቅ ወጣቱን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ አፍሪካዊያንና እራሳቸው ነጮቹም በፊልሙ ውስጥ የታሪክ ሽሚያ ስለመካሄዱ ሲቀባበሉት ተመለከትኩ። ልቤን ደስ እንደመሰኘት ነሸጠውና መልሶ የሀፍረት ስሜት ቸለሰብኝ። እራሳችንን ታዘብኩበት። ውስጣዊ ጉዳይ ሲሆን ከሰው ኪስ ወድቆ ቅጭል! ያለችዋን ሳንቲም የኔ ነው፣ የኔ ነው እያልን በመነጣጠቅ ሚዲያውን በአንድ እግሩ የምናቆም እኛ ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታችን አይ ነዶ! . . . የሚያስብል ነው። ይሄኔ ታሪኩ የአንዱ ብሔር ነው ተብሎ ቢሆንማ . . . ብዬ ለማሰብ ሞከርኩና አለማሰብ ይሻላል ብዬ ተውኩት።

‘ሎርድ ኦፍ ዘ ሪንግስ’ አስቀድሞ መጽሐፍ የነበረ ሲሆን ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተነባቢነትን ከማግኘቱ የተነሳ ወደ ፊልም ስክሪፕት ተቀይሮ የተሠራ የሆሊውድ ፊልም ነው። ጸሐፊው ኢንግሊዛዊው ደራሲ ቶልኪን ነው። ታሪኩ ለእንግሊዝ መረቅ፤ ለሆሊውድ ደግሞ ሙዳ ሥጋ ሆኖላቸዋል። ከፊልሙ በተገኘው ከፍተኛ ገቢ ሆሊውድ የገንዘብ ጎተራውን ሞላበት። የዝና ገመዱንም ይበልጥ ዘለለበት። በተለያዩ ሽልማቶችም ተንበሸበሸ። በማን? ያው በኛው ታሪክ። እንግሊዝም በብዙዎች ዘንድ የምትታወቅበት አንድ ባህሪ አላት። እንኳንስ እንዲህ ዓይነቱን የታሪክ አልማዝ ቀርቶ ያየች የተመለከተችውን ሁሉ የመሰብሰብ አባዜ የተጸናወታት መሆኗ ነው። ሰብስባም አታበቃ ድንገት መልሺልኝ ላላት፣ “ዓይኔን ግንባር ያድርገው፤ የኔ ነው” በማለት ምላ፣ ተገዝታ ትክዳለች። በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ የቤተ መንግሥቱን ጓዳ ጎድጓዳ ሳይቀር በርብራ የዘረፈቻቸው ቁጥር ሥፍር የሌላቸው መጻሕፍትን ጨምሮ በየዘመናቱ የምትሰልባቸውን ልዩ ልዩ ቅርሶችን አሁንም የሙጢኝ ብላ አልሰጥም ማለቷ ለዚህ ማስረገጫ ነው። እንኳንስ የምድራችንን የእውቀት በር መግቢያ የያዙትን ቅርሳ ቅርሶች ቀርቶና ከራስ ላይ ፀጉር ሳይቀር ቆርጣ መውሰዷ፤ በእኛ ላይ እጅጉን ከመጎምዠቷ የተነሳ ልቧ በዚህ መታወሩን የሚያሳይ ነው። የተጸናወታት በሰው ወርቅ የመድመቅ አባዜ አለቅ ቢላት ከኛ በሰበሰበቻቸው ቅርሶች ሙዚየሞችን ከፍታ ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ጎብኚዎቿንና እኛኑ ታስጎበኘናለች። እንግዲህ ደርሳችሁ ባትነኩትም ቢያንስ እዩት ማለቷ ነው። ደራሲው ቶልኪንም የአብራኳ ክፋይ ነውና ሽንጡን ገትሮ ታሪኩ የእንግሊዝ እንጂ የማንም አይደለም ማለቱ ከእርሷው እግር ስር ቁጭ ብሎ የተማረው ነው። የእንግሊዝንና የመጽሐፉን ጉዳይ በአንድ እግር እረግጠን እንለፈውና ነገር ግን ፊልሙ እንዴት በኛ የታሪክ አጥር እንደዘለለ እንመልከት።

በመጀመሪያ፤ ግልጽና ቀላል ወደሆኑትና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲህ አይቶ ሊገነዘባቸው ወደሚችላቸው ነጥቦች እንሂድ። በዚህ ጉዟችንም በፊልሙ ውስጥ የተጠቀሱትን የቦታ ስያሜዎችን እናገኛለን። በ’ሎርድ ኦፍ ዘ ሪንግስ’ የተካተተው አንደኛው ከተማ ‘ጎንዶር’ የሚል ስያሜ ያለው ነው። በገጽታ አሳሳሉ ከነመልክና ወዘናው ጎንደርን ይመስላል። 2ኛ. ‘ሐራድ’፤ በኢትዮጵያ. . . ሐረር 3ኛ.’ባራዱር’፤ የኛው ባሕርዳር . . . 4ኛ.’ሮሐን’፤… ሮሐ ወይንም ላሊበላ 5ኛ.’ጎርጎሮት’፤ . . . ጎርጎራ 6ኛ.’ሊበነን’፤ . . . ሊባኖስ ወይም ደብረ ሊባኖስ ናቸው። ስማቸው ብቻም ሳይሆን ሁለመናቸው ከኛ ከተሞች ጋር ልክክ ብሎ መግጠሙ አጋጣሚ ከተባለ የሚያስነውር ነው።

‘ጎንዶር’ በሲንዳሪያን ቋንቋ የድንጋይ መሬት እንደማለት ሲሆን፤ ከተማው የተዋቀረውም በድንጋይ ነው። ቤተመንግሥቱ ሳይቀር የጎንደርን የመሰለ ነው። አለፍ ሲል አንዳንድ ቅርጻቅርጾችንም እናስተውላለን። አጼ ፋሲለደስ ጎንደርን ከመመስረታቸው አስቀድሞ በድንጋይ የተሞላች፤ በከርሰ ምድሯም ውድ ማዕድናትን የተሸከመች ከተማን አምላክ እንዳሳያቸው በነገሥተ ጎንደር የብራና መጽሐፍ ላይ ተቀምጧል። ከኛ ከባለቤቶቹ ይልቅ መጻሕፍቱም የሚገኙት እነርሱ ዘንድ በመሆናቸው ከኛ ጋር አንድ ዓይነት ሆኖ የሚታየን የትኛውም ታሪክ ቢኖር አያስገርምም። በ’ጎንዶር’ እና ጎንደር መሃከል ተመሳስለው የሚታዩ ሌሎች በርካታ ነገሮችም አሉ። ሰሜናዊቷ የጎንደር ከተማ በሰባት ቁጥር አሐዛዊ ቀመር የተሠራች ናት። ‘ጎንዶር’ም እንዲሁ . . . ለምሳሌ አጼ ፋሲለደስ ሰባት የወንዝ ድልድዮችን በዙሪያዋ አሠርተዋል። በመጀመሪያ ያነጹት ሰባት አቢያተ ክርስቲያናትን ነበር። የጎንደር ከተማን ሠርቶ ለመጨረስ ሰባት ዓመታትን ፈጅቷል። ለዚህም ተገንብታ ስታልቅ ለሰባት ቀናት ያህል ነጋሪት እየተጎሠመ ተጨፍሯል። ታዲያ በፊልሙ የምንመለከተው የ’ጎንዶር’ ከተማም በሰባት ቁጥር አሐዛዊ ስሌት የቆመ መሆኑን እንመለከታለን። ለከተማውና ለነገሥታቱ እንደ መለያ አሊያም እንደ ባንዲራ የሚያገለግለው ጠፍጣፋ ጦር መሳይ፣ ዙሪያው በሰባት አብረቅራቂ ክዋክብት የተዋቀረ ነው።

ጻጉድ በይ ሀገር” ብለን አለፍ ልንል ስንል ደግሞ የጃንተከልን ዋርካን ዘርፈፍ ብሎ እንደቆመ እንመለከተዋለን። በፊልሙ ውስጥ፤ ይህ ግዙፍ ዋርካ የሚገኘው ከቤተመንግሥቱ ፊት ለፊትና ከዋናው መግቢያ በር ሲሆን በጎንደር ከተማም ይህን እድሜ ጠገብ ዋርካ የምናገኘው ከፋሲለደስ ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት መሆኑ ነው።

ከመሬት ገጽታና አቀማመጥ አንጻር ደግሞ በፊልሙ ላይ የሚታየው ‘አንገረን ሪቨር’ በቀጥታ የአንገረብ ወንዝን መልክ የያዘ ነው። ‘ሚስት ማውንቴን’ እያሉ የሚጠሩት ከተራራ አናት የሚወጣው እሳታማ ጎሞራ ቅርጽና ባህሪው ከኤርታሌ ጋር ተመሳስሎሽ ያለው ነው። ሌላው ‘ማውንት ዱም’ ሲሆን ደብረ ዳሞን ወክሎ የተቀመጠ ነው። ‘አይዘንጋርድ’ በዚህ ፊልም ላይ የነገሥታቱን ገጽታ የሚያሳይ በእጅጉ ወሳኙ ስፍራና ከረዥም የድንጋይ ጡብ የተሠራና የተለያዩ ቅርሶችን የያዘ ስፍራ ነው። ይህ ደግሞ ከዲዛይንና ቅርጹ ጀምሮ በአክሱም ነገሥታት የተሠራውን የአክሱምን ሐውልት ምንነት የያዘ ነው። ‘ሎርድ ኦፍ ዘ ሪንግስ’ን ለተመለከተ ለአንድ ታሪክ አዋቂ ኢትዮጵያዊ፤ ከፊልሙ ውስጥ የኛ የሆኑትን ነገሮች አበጥሮ ማውጣት ከጤፍ ክምር ውስጥ አሸዋ እንደመልቀም ነው። ከዚያ ይልቅ የኛ ያልሆኑትን ነገሮች መለየቱ እምብዛም ጊዜ የማይፈጅ ነገር ነው።

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኢትዮጵያ የነበሩት የነገሥታት የዘር ሐረግ ወይም ስርወ መንግሥትን ስናይ ሦስት ነበሩ። እነዚህም የአክሱም (የዛግዌ)፣ የላሊበላ (ሮሐ) እና የጎንደር ነገሥታት ናቸው። ‘ሎርድ ኦፍ ዘ ሪንግስ’ ይህንንም አልተወልንም። እንደዋነኛ የታሪክ መነሻ ጭብጦች የተካተቱት የስርወ መንግሥታቱ አላባዊያን ሦስት ሲሆኑ፤ እነሱም ‘ኪንግ ኦፍ አርሎን’፣ ‘ኪንግ ኦፍ ሮሐ’፣ እና ‘ኪንግ ኦፍ ጎንዶር’ ናቸው። ከፊልሙ ውስጥ ከሚገኙ ገቢሮች ከአንደኛው ትንሿ ቆንጠር ስናደርግ፤ . . . በ’ጎንዶር’፤ የኢልሲደር የነገሥታት የዘር ሐረግ ከተቋረጠ በኋላ በመጨረሻ በመጣው አገዛዝ ሕዝቡ ደስተኛ ስላልነበረ የተለያዩ አመጾችን ያስነሳል። በዚህ ጊዜ ጋንዳልቭ ዘ ግሬይ በተባለ ጠቢብ አማካኝነት ሌላ ንጉሥ ተሹሞ ሥርዓቱ ወደ ትክክለኛው የሕዝብ ተወዳጅነት ሲመለስ ይታያል። ይህ ታዲያ በሀገራችን እንዲህ ነው፤ . . . የሰለሞን ነገሥታት የዘር ሐረግ ከተቋረጠ በኋላ የመጣው የዛግዌ ስርወ መንግሥት ላይ ሕዝቡ ደስተኛ አልነበረም። የዚህን ጊዜ አቡነ ተ/ሃይማኖት ተነሥተው ይኩኖ አምላክን በማንገሥ ዙፋኑ ዳግም እንዲጠነክር አደረጉ . . . የጋንዳልቭ ዘ ግሬይና የአቡነ ተ/ሃይማኖት ተመሳሳይ ተግባር በዚህ አያበቃም። በአቡነ ተ/ሃይማኖት ገድል ውስጥ ማርያን የተባሉት አጋንንት ሳቢዎች በእሳቸው አማካኝነት ወደ ጥልቁ የእሳት ባህር እንደገቡና እንደወደቁ ተጽፏል። የፊልሙ ግሬይም ‘ባህሮግ’ የተባለውን የጥንቱ ዓለም አጋንንትን ወደ ጥልቁ የእሳት ባህር ሲከተው ያሳያል . . . አጃኢብ ነው! በ’ሎርድ ኦፍ ዘ ሪንግ’ የአቢሲኒያ ምድር ያልሆኑ ነገሮች ቢኖሩ፤ ተዋንያኑ ብቻ ናቸው ቢባል ማጋነንም ሆነ ቅጥፈት አይደለም። በአክሱም ውስጥ ኢዛናና ሲዛና የተባሉ ሁለት ወንድማማቾች ስለመንገሣቸው አይዘነጋም፤ ፊልሙም አልዘነጋውም፤ ኢሲልደርና አርኖን በሚል።

ከሥነ ፍጥረትና ስልጣኔ አንጻር ብንመለከት ይህን እናገኛለን። ‘ጎለም’ በመካከለኛው የምድር ክፍል የሚገኝና በአራት እግር የሚንቀሳቀስ፤ በገጽታውም ሰውን ወደ መምሰል የቀረበ ልዩ የሆነ አፈ ታሪካዊ ፍጡር ተደርጎ ቀርቧል። ይህ ደግሞ በጥንት አባትና እናቶቻችን ዘንድ ጎለም/ጎለምሸት እየተባለ የሚጠራው የክፉ ዛር መንፈስ ስለመሆኑ ከነስያሜው ያመላክተናል።

በፊልሙ ውስጥ ‘5 ዊዛርድስ’ የተባሉ በሰውነት ግዝፈትም ሆነ በእውቀት ከሰው ልጆች ላቅ ያሉና በሰው አምሳል የተቀረጹ አምስት ፍጡራን አሉ። በእውቀት እጅግ የመጠቁ፣ አስተዋዮች፣ አስታራቂና የመምራት ክሂሎታቸው ከፍ ያለ ነው። መነሻቸው ደግሞ ማያ ከሚባሉ ከአነስተኛ ጎሣና የዘር ሐረግ ነው። እናም ማያዊያን በጥንቱ ዓለም የስልጣኔ ማማ የነበሩና በሰሜናዊ ሜክሲኮ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች ደግሞ ቀደም ሲል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በዝዋይ ሐይቅ አካባቢ በዌጅ ውስጥ ስለመኖራቸው የራሳቸው የታሪክ ምሁራን በአሥር ጣቶታቸው ፈርመው ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። በዚህ ፊልም ውስጥ አምስቱ ጠቢባን ማያዊያን መሆናቸው፤ እንዲሁም፣ የተገለጹበት መንገድ በቀጥታ በኢትዮጵያ ምድር ወደነበሩት ጠቢባን ይመራናል። ታዲያ ሆሊውድ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪኮች አልዘረፈም? . . . ዘርፏል! ከምትል አንዲት ቃል ጋር እንደ ግል ጠባቂ በቆመ ቃለ አጋኖ ብቻ መግለጽ የልብን አያደርስም። “ቃላቶች ያጥሩኛል” ማለትም ይሄኔ ነው። ይህ ፊልም የተጻፈው በአንድ እንግሊዛዊ ሳይሆን፤ ምናልባትም በአንድ ጎበዝ ኢትዮጵያዊ ደራሲ መስሎ ቢሰማንም አይፈርድብንም። እነዚህ ታሪኮች የተጻፉባቸው የብራና መጻሕፍት አሁንም ድረስ በነጮቹ በተለይም በእንግሊዝ እጅ መሆናቸው የሚያንገበግብ ነው። በነገራችን ከኢትዮጵያ የታሪክ ማህደር ተሰርቆ የተሠራው ‘ሎርድስ ኦፍ ዘ ሪነግ’ ብቻ አይደለም። “አቫተር”ን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ፊልሞችም አሉ። በፊልም ውስጥም ሆነ በገሀዱ ዓለም የመሰወር ጥበብ ምን እንደሆን ሳይታወቅ በፊት የኛ የጥንት አባቶች ግን እጸ መሰውርን ተጠቅመው እንኳንስ ሰውንና ግዙፎቹን ከተሞችንም ይሰውሩበት ነበር። እንግዲህ “ያልተነጠቅነው ጥበብ፤ ያልተለቀመብን እውቀት ምን አለ?” ከተባለ መልሱ ከ“ምንም” በስተቀር ሌላ ሊሆን አይችልም።

ዛሬ ላይ፤ ጀርመኖቹ በግዕዝ ቋንቋ ለመግባባት የቀራቸው ጥቂት ነው። በሀገራቸው ግዕዝን የሚያስተምሩ ዩኒቨርሲቲዎችንና ኮሌጆችን ከፍተው በማስተማርና በማስፋፈት ላይ ይገኛሉ። ባለቤቶቹ የሆንን እኛስ? እኛማ የእነርሱን የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት ቤቶችን የመክፈት ዜና በኩራት እንደጀብዱ እያወራን አለን። አናሳዝንም? ኧረ በጣም! . . . እንዲያውም ለገባንስ “እናሳፍራለን” ማለቱ ይቀላል። ህልም ለማየት የተሳነን ህልም ፈቺዊች . . . በውሃ ጥም የምናልቅ የዓባይ ልጆች . . . መቼ ይሆን ለራሳችን የምንሆነው? የአባቶቻችንን ታሪክ መድገሙ ቀርቶ ታሪክን መያዙ እንዴት ይሳነን? ሀገርን አይደለም መላውን ዓለምን የሚቀይር ምስጢራዊ ሀብቶችን በእጃችን ይዘን፤ እኛ ግን በረሀብ እየተቆላን ለእነርሱ ማዘን ምን የሚሉት አዚም ይሆን . . . የግዕዝ ቋንቋን በሥርዓተ ትምህርታችን ውስጥ በማካተት ወደኋላ ዞረን ከዚህ የእውቀት ባህር ልንጠልቅ ይገባል። ወተቷን ለመጠጣት ላሟን መቀለብ የግድ ነውና። ቋንቋው ለአንደበታቸው ስለሚጣፍጥ ሳይሆን የሚጣፍጠውን ወተት የሚያገኙበት የላሟ አራት ጡቶች ግዕዝ በመሆኑ ነው። ዜጎቻቸውን በማስተማር የሀገራቸውን ሁለተኛና ሦስተኛ ቋንቋ ማድረግ አላማቸው ነው። እንግዲህ በዚህ ከቀጠልን እነርሱ በግዕዝ ሲግባቡ ምን አልከኝ? . . . እያልን በገዛ ቋንቋችን ለጆሮ ባዳ ሆነን መደናቆራችን የማይቀር ነው። በኛ የታሪክና የቅርስ እርሾ፤ እነርሱ ፊልም መስራታቸው የልብ ኩራት እንዲሰማን የሚያደርግ ቢሆንም የኛ ስለመሆኑ እውቅና ሳይሰጡ በድፍረት ክደው ቁጭ ማለታቸው ግን ቅስም የሚሰብር ነው። የኛ ስለመሆኑ የምናውቀውም እኛ ብቻ ነን። “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ” ሆነና በኛ የታሪክ ላምባ የሚበራው የእንግሊዝ ቤት ነው። በኛ የሀብትና ቅርስ እንጀራ የሚሞላውም የሆሊውድ ሆድ ነው። ከብዙ ማዛጋት የቀረችንን ጉልበት አሟጠን ዛሬም በዓለም አደባባይ ብንጮህ ምናልባትም አልረፈደብን ይሆናል። የፊልም ኢንዱስትሪያችን ንቃተ ህሊና እነዚህን በመሳሰሉና ባልተነኩ ታሪክና ቅርሶቻችን የተቃኘ መሆን አለበት። ጥያቄው መሆን ያለበት “ሆሊውድ ለምን ሠራው?” ሳይሆን “እኛ ለምን አልሠራነውም?” ነው።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You