ኢትዮጵያ ለስኳር ልማት ዘርፍ ትልቅና እምቅ አቅም አላት:: ሀገሪቱ ዘርፉን ለማስፋፋትና ምርታማነቱን ለማሳደግ የሚያስችል ከፍተኛ የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትም ናት:: በተለይም ለሸንኮራ አገዳ ልማት ተስማሚ የሆነው የአየር ንብረቷ፣ በመስኖ ሊለማ የሚችል እስከ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር የሚደርስ ሰፊ የእርሻ መሬቷ እንዲሁም ‹‹የአፍሪካ የውሃ ማማ›› ያሰኛት በቂ የውሃ ሀብቷ፣ በስኳር ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት እንድታስመዘግብ የሚያስችሏት አጋዥ ግብዓቶች ናቸው::
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስኳር ኢንዱስትሪ ልማት የተጀመረው በ1943 ዓ.ም ነው:: በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ‹‹ኤች. ቪ.ኤ›› (HVA) ከተባለ የኔዘርላንድስ ኩባንያ ጋር የአክስዮን ስምምነት በመፈራረም ዘመናዊ የስኳር ልማት ሥራ እንዲጀመር አድርጓል:: ኩባንያው ሥራውን የጀመረው አምስት ሺ ሄክታር የሸንኮራ አገዳ ማልሚያ መሬት ተረክቦ ሸንኮራ አገዳ በማልማትና ‹‹የወንጂ ስኳር ፋብሪካ››ን በመገንባት ነበር::
ኢትዮጵያ ለስኳር ልማትና ንግድ አዋጭ መሆኗን የተረዳው ይኸው ኩባንያ፣ የ‹‹መተሐራ›› ስኳር ፋብሪካን ደግሞ በ1962 ዓ.ም ገንብቶ ሥራ አስጀመረ:: በመቀጠልም ‹‹ቡከርስ አግሪካልቸራል ኢንተርናሽናል ሊሚትድ›› የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ በፊንጫኣ አካባቢ ዝርዝር የስኳር ልማት ጥናት አደረገ:: በጥናቱ መሠረት ‹‹ኤፍ.ሲ.ሼፈርና አሶሽየትስ›› እና ‹‹ድዌቶ ኢንተርናሽናል›› የተባሉ የአሜሪካና የኔዘርላንድስ ኩባንያዎች እንዲሁም በርካታ ሀገር በቀል ድርጅቶች ባከናወኑት የፋብሪካና ኤታኖል ማምረቻ ግንባታ አማካኝነት፣ በ1991 ዓ.ም የ‹‹ፊንጫኣ›› ስኳር ፋብሪካ የምርት ሥራ እንዲጀምር ተደረገ::
የስኳር ልማትን የማሳደጉ ጥረት ቀጥሎ፣ በምርትና በግንባታ ላይ በሚገኙት ሌሎች የስኳር ፋብሪካዎች (‹‹ተንዳሆ››፣ ‹‹አርጆ ዲዴሳ››፣ ‹‹ከሰም››፣ ‹‹ጣና በለስ›› ‹‹ኦሞ ከራዝ›› እና ‹‹ወልቃይት›› ፋብሪካዎች) አማካኝነት ሀገሪቱን የስኳር ፍላጎት ለማሟላት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል::
የፋብሪካዎቹ የአስተዳደር ሁኔታም ከሀገሪቱ የመንግሥታት መለዋወጥ ጋር እየተለዋወጠ ዘልቋል:: በወታደራዊው መንግሥት ዘመን የስኳር ፋብሪካዎቹ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ይዞታ ስር ሆነው፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሕግ ክፍል ማስታወቂያ ቁጥር 58/1970 የተቋቋመው ‹‹የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን›› ፋብሪካዎቹን ያስተዳድር ነበር::
ከ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ በኋላ ‹‹የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን›› በሕግ ፈርሶ፣ ፋብሪካዎቹ ራሳቸውን የቻሉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሆነው እንዲቋቋሙ ተደረገ:: በ1990 ዓ.ም ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ድጋፍ ሰጪ ማዕከል አክስዮን ማኅበር›› የተሰኘ ድርጅት ለስኳር ፋብሪካዎቹ የጋራ አገልግሎት እንዲሰጥ ተቋቋመ:: ከስምንት ዓመታት በኋላ ደግሞ በዚህ ማዕከል ምትክ ‹‹የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኤጀንሲ›› በአዋጅ ቁጥር 504/98 ተመስርቶ የስኳር ፋብሪካዎቹን በመቆጣጠር፣ በፕሮጀክት ልማት፣ በምርምር፣ በስልጠናና በግብይት ረገድ ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል::
ኤጀንሲው በ2003 ዓ.ም ፈርሶ፣ ‹‹ስኳር ኮርፖሬሽን›› በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 192/2003 ተቋቋመ:: በፕሮጀክት አፈፃፀምና በገንዘብ አስተዳደር ረገድ አነጋጋሪ የነበረውና በርካታ ጥያቄዎች የተነሱበት ኮርፖሬሽኑ በመጋቢት 2014 ዓ.ም ፈርሶ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ›› ተቋቁሟል::
ኢትዮጵያ ለስኳር ልማት ዘርፍ ትልቅና እምቅ አቅም ያላት ሀገር ብትሆንም፣ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የስኳር ፍላጎቷን የምታሟላው ከውጭ በመግዛት ነው:: የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ወቅት ያለው አጠቃላይ ዓመታዊ ሀገራዊ የስኳር አቅርቦት መጠን ከአምስት ሚሊዮን እስከ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ነው:: ከዚህ ውስጥ ባለፉት ዓመታት በዓመት ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ስኳር በሀገር ውስጥ የተመረተ ሲሆን፣ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለው ከአንድ ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ስኳር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በየዓመቱ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ይገኛል:: በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የአንድ ሰው ዓመታዊ የስኳር ፍጆታ ከ10 ኪሎ ግራም በላይ እንደሚደርስ ቢገመትም፣ እየቀረበ ያለው መጠን ግን ስድስት ኪሎ ግራም ያህል ነው::
ምንም እንኳ ኢንዱስትሪው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም፤ በኢንዱስትሪው በሚፈለገው ፍጥነት አለማደግ፣ ሀገሪቱ በተከታታይ ባስመዘገበችው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ምክንያት የኅብረተሰቡ የስኳር ፍላጐት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር፣ ነባር የስኳር ፋብሪካዎች የሚያመርቱት የስኳር መጠን እያደገ የመጣውን የሀገር ውስጥ ፍላጎት ማርካት አለመቻሉ፣ የሕዝብ ቁጥር ማደግ እና ስኳርን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋት ለስኳር ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ዋና ዋና ምክንያቶች ተደርገው ይጠቀሳሉ::
በርካታ የስኳር ፋብሪካዎችን በአንድ ጊዜ ለመገንባት ተጀምሮ የነበረው እቅድ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ ዳርጓታል:: በስኳር ልማት ዘርፍ ላይ የተጋረጡ በርካታ መሰናክሎች ቢኖሩም የግብዓት አቅርቦት፣ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ እጥረት፤ የአመራር ድክመት እንዲሁም ከንግድና ግብይት ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች የሀገሪቱ አቅምና የማምረት መጠን እንዲራራቅ ያደረጉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው:: በመሆኑም ሀገሪቱ ለስኳር ልማት ያላትን እምቅ አቅም በተገቢው ደረጃ ጥቅም ላይ ለማዋል መንግሥት አምስት የስኳር ፋብሪካዎችን (ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ እና ፊንጫኣ) በአዋጅ ቁጥር 500/2014 ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ አድርጓል::
ይህ የመንግሥት ርምጃ ፋብሪካዎቹ ያሉባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲቃለሉና በተሻለ አቅም እንዲያመርቱ እድል በመፍጠር፣ የስኳር ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣምን ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዝ ታምኖበታል:: በዚህ ርምጃም አንዳንድ ፋብሪካዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማየት ጀምረዋል:: በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ከሆኑት ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ‹‹ወንጂ ሸዋ›› ስኳር ፋብሪካ ነው::
በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የሆነው ፋብሪካው፣ በዓመት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር እና 31 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው:: ይሁን እንጂ አሁናዊ የምርት አቅሙ ከ300ሺ ኩንታል ብዙም የተሻገረ አይደለም::
የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አማን እንደሚገልፁት፣ ስኳር ፋብሪካዎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ከተወሰነ በኋላ የፋብሪካው ሥራ አመራር ቦርድ ለፋብሪካው ምርታማነት ማደግ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል:: ዘንድሮ 327ሺ ኩንታል ለማምረት ያቀደ ሲሆን፣ በ2017 የምርት ዘመን ደግሞ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ለማምረት አቅዷል::
«ፋብሪካው በ2007 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን 158ሺ ኩንታል ስኳር አምርቷል:: በአሁኑ ወቅት እያመረተ ያለው ግን ከ300ሺ እስከ 400ሺ ኩንታል ብቻ ነው፤ ይህ ደግሞ ፋብሪካው ካለው አቅም 31 በመቶ ብቻ ነው» ሲሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ይገልጻሉ:: የዚህ ምክንያቱ የአገዳ ሽፋኑ በሚፈለገው ልክ በቂ አለመሆኑ ላይ እንደሆነም ይጠቅሳሉ:: ችግሩ ለቦርድ ቀርቦ ቦርዱም ድጋፍ አድርጎ የአገዳ ሽፋን የማሳደግ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ መሠረተ ልማቶችን የማደስ ተግባራትም ተከናውነዋል:: የፋብሪካውን የምርት መጠን የሚወስነው የአገዳ አቅርቦት ነው:: መንግሥት እያደረገ በሚገኘው ድጋፍ አማካኝነት ፋብሪካው በ2017 አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር የማምረት እቅዱን ለማሳካት ጥረት እያደረገ ነው::
ፋብሪካው ከስኳር ምርት በተጨማሪ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አቶ ጀማል ይጠቁማሉ:: በፋብሪካው አማካኝነት ሰፋፊ የስንዴ ልማት ሥራዎች ተሰርተዋል:: በዘመናዊ የከብት ማድለቢያው ባለፈው ዓመት 500 ከብቶችን አድልቦ ለገበያ ማቅረቡን ጠቅሰው፤ ዘንድሮም በመጀመሪያው ዙር ከ300 በላይ ከብቶችን እያደለበ ነው:: ከሶስት ሺ 500 በላይ ዶሮችንም እያረባ ይገኛል ብለዋል::
«የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ» ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብዱራህማን ኢድ በበኩላቸው፣ ፋብሪካዎቹ ራሳቸውን ችለው እንዲደራጁ ከተደረገ ወዲህ ተጨባጭ ለውጥ ካሳዩ ፋብሪካዎች መካከል «ወንጂ ሸዋ»› ስኳር ፋብሪካ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ የፋብሪካው የምርት መጠን እየተሻሻለ ነው፤ በ2017 አንድ ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የአገዳ ምርትን የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል::
ፋብሪካው ባለው የራሱ ስድስት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ከሚያለማው ሸንኮራ አገዳ በተጨማሪ ከአርሶ አደሮች ጋር በገባው ውል አማካኝነት ያገኝ የነበረውን የአገዳ ምርት በሚፈለገው ልክ አለማግኘቱ በምርቱ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮበት መቆየቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል:: የአመራር ማስተካከያ በማድረግ የፋብሪካዎችን አፈፃፀም ለማሻሻል ጥረት መደረጉንም አቶ አብዱራህማን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ፋብሪካዎቹ ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች የመፍትሔ አማራጮችን በማስተባበርና በማቀናጀት እገዛ እንደሚያደርግም ገልጸዋል::
ሀገሪቱ ለስኳር ልማት ያላትን እምቅ አቅም በተገቢው ደረጃ ጥቅም ላይ ለማዋል አምስት የስኳር ፋብሪካዎችን (ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ እና ፊንጫኣ) ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ሲወሰን ከተተገበሩ አሰራሮች መካከል አንዱ ፋብሪካዎቹ የየራሳቸው የሥራ አመራር ቦርድ እንዲኖራቸው መደረጉ ነው:: የሥራ አመራር ቦርዶቹ የፋብሪካዎቹ ችግሮች በጥናት እንዲለዩ በማድረግ ችግሮቹ የሚፈቱበትን መንገድ እያመቻቹና ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ::
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አወሉ አብዲ፣ የፋብሪካው ችግሮች በጥናት ተለይተው ለችግሮቹ የመፍትሔ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ይገልፃሉ:: «‹ፋብሪካው ሰፊ የሆነ መሬትና የሰው ኃይል አለው:: ነገር ግን በሙሉ አቅሙ እንዳያመርት መሰናክል የሆኑበት ችግሮች ምን እንደሆኑ ለመለየት በባለሙያዎች ዝርዝር ጥናት ተደርጓል›› ሲሉም ተናግረዋል::
የቦርዱ ሰብሳቢ እንዳሉት፤ ከችግሮቹ መካከል አንዱ የአመራር ድክመት ነው:: ከቦርድ እስከ ታችኛው ፈፃሚ ድረስ፣ በየደረጃው ያለው አመራር ችግሮቹን ለይቶና አውቆ ፋብሪካውን በመምራትና በማስተዳደር ረገድ መጠነ ሰፊ የአቅም ውስንነት ይታይበት ነበር:: የድጋፍና ክትትል ውስንነት እንዲሁም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ችግር ነበር:: ለማሳ ዝግጅትና ከእንክብካቤ፣ ለማዳበሪያ፣ ለውሃና ለሌሎች ግብዓቶች አቅርቦት የተሰጠው ትኩረት በጣም ዝቅተኛ ነበር::
ችግሮቹን በመሠረታዊነት ለመፍታት ከአርሶ አደሩ ጋር በመወያየት የግብዓት አቅርቦት እንዲሻሻል መደረጉን አቶ አወሉ አስታውቀዋል:: ‹‹የፋብሪካውን አቅም ባገናዘበ መልኩ ለሠራተኛው ማበረታቻ ተሰጥቷል:: በዚህም ለሌሎች ፋብሪካዎችም ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ እና ኢንዱስትሪውን መሠረታዊ በሆነ መልኩ ለመቀየር የሚስችሉ ጅምር ውጤቶች ተገኝተዋል›› ሲሉም ገልጸዋል:: እነዚህን ተግባራት አጠናክሮ ማስቀጠል ከተቻለ፤ አርሶ አደሩም ሆነ የፋብሪካው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እና በ2017 አንድ ሚሊዮን ኩንታል የማምረት እቅድን ማሳካት እንደሚቻል አቶ አወሉ አስታውቀዋል::
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም