የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 12/65 2014ዓ.ም ከተቋቋመ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል። ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ሥራዎችን እየሰራ ቢቆይም ወደፊት ግን ሰፊ ሥራ ይጠብቀዋል። የተሰጠው ጊዜ ደግሞ ሶስት ዓመት ነው። ሁለት ዓመት ሊሞላው የቀረው ጥቂት ጊዜ ነው። የሚሰራቸው ሥራዎችና የተሰጠው ጊዜ በቂ ስለመሆኑና አጠቃላይ እንቅስቃሴውን በተመለከተ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚዲያ ኮሙዩኒኬሽንና አጋርነት ዘርፍ አስተባባሪና የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን:- በቅድሚያ ኮሚሽኑ እስካሁን ያለፋቸውን ሂደቶች ቢያስታውሱን?
አቶ ጥበቡ:- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ጊዜ የሚቆጠረው ኮሚሽነሮች ተሰይመውለት ሥራውን በይፋ ከጀመረበት ጊዜ መሆኑን በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በግልጽ ተቀምጧል። በዚሁ መሠረትም ኮሚሽኑ ሥራውን ከጀመረ ሁለት ዓመት ሊሆነው የቀረው ጥቂት ጊዜ ነው።
ሥራዎች በአራት ምዕራፍ ተከፍለው እየተሰሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ነው። በዚህ ምዕራፍ ሀገራዊ ምክክር በራሱ ምንነትና ሥራውንም ለማከናወን በአዋጅ የተቋቋመው ኮሚሽን የተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች ምንድናቸው? አጠቃላይ የአዋጁስ መንፈስ ምንድነው? የሚለውን የመገንዘብ ሥራዎች ነው ሲሰሩ የነበረው። ምክንያቱም ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት የመጀመሪያው ምዕራፍ ያስፈለገው ምን እንደሚሰራ፣ ለምን እንደሚሰራና እንዴት እንደሚሰራ በአግባቡ መረዳት ይጠይቅ ስለነበር ነው።
ኮሚሽኑ ያሉት በተለያየ የሙያና የትምህርት ዘርፎች ላይ የሚገኙ 11 ኮሚሽነሮች ነው። እነዚህ ኮሚሽነሮች ተግባብተውና ተናብበው ለመሥራት እንዲችሉ እርስ በርሳቸው መተዋወቅ ይኖርባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ኮሚሽኑ ሥራውን ሲጀምር በነባር ተቋም ሳይሆን፤ በአዲስ መልክ የተቋቋመ ነው። በዚህ ምክንያት የመፈፀም አቅም አልነበረውም። የመፈፀም አቅም እንዲፈጥር የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ነበር። እነዚህ በቅድመ ዝግጅት ሥራ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። አጠቃላይ ሁኔታውን የማጤንና የማንበብ የምክክር ሂደቱን በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት እንዲወጣ የሚያስችሉ ሥራዎች ናቸው።
ሁለተኛው ደግሞ የዝግጅት ምዕራፍ ነው። በዚህም በሃሳብ ደረጃ የተቀመጠና ወደ ሕግም የተቀየረ ነው። ተቋም ተቋቁሞለት ኮሚሽነሮች የሚሰየሙለት ሥራ በምን አግባብ ነው ወደ መሬት ማውረድና መተግበር የሚቻለው በሚሉ ጉዳዮች ላይ ወደትግበራ ከመገባቱ በፊት የዝግጅት ሥራ ያስፈልግ ነበር። አንዳንዶቹ ከቅድመ ዝግጅት ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ሥራ የዞሩ አሉ። ለምሳሌ የኮሚሽኑን የመፈፀም አቅም የመገንባት ሥራ ይጠቀሳል።
በተጨማሪም ምክክሩ በሂደቱ አሳታፊ፣ አካታችና ግልጽም መሆን አለበት የሚሉ የመሳሰሉ መርሆዎች አሉት። ሰፋፊና ሲተገበሩም ብዙ ጥረትን የሚጠይቁ ናቸው። ስለዚህ በዚህ መርህ መሠረት ምክክሩን ለማካሄድ የሚያስችሉ ነገሮች ለማምጣት ኮሚሽኑ ብቻውን የሚሰራው ሥራ አይሆንም ማለት ነው። ከዚህ አኳያ በሂደቱ ሊሳተፉ የሚገባቸውን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትንና የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማማከር ሥራ መሠራት ነበረበት።
ምክንያቱም ይሄ ምክክር አሳታፊና አካታች መሆን አለበት ስንል መጨረሻ ላይ በአንድ አዳራሽ ተሰባስበው የአጀንዳ ሃሳቦችን በሚሰጡ ወይንም ደግሞ በምክክሩ በሚሳተፉ ሰዎች ብቻ የሚገለጽ አይደለም። አካታችና አሳታፊ መሆን ያለበት ሂደቱ ሁሉ ነው። ለምሳሌ ተሳታፊዎች በምን አግባብ ቢለዩ ነው የተሻለ የሚሆነው? በሚሉ የተለያዩ ሃሳቦች ላይ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ምክክሮች ተደርገዋል። ይህ ምክክር ከትግራይና አማራ ክልሎች ውጭ በሌሎች ክልሎች ተካሂዷል። በዚህ መልኩ ከኅብረተሰቡ ግብዓት ከተሰበሰበ በኋላ መጨረሻ ላይ ወደ አሰራር ሥርዓት የተቀየረው።
ስለዚህ በዝግጅት ምዕራፉ ለምሳሌ ተሳታፊዎች በምን መንገድ ይለያሉ ለሚለው ምላሽ ለመስጠት የራሱ የሆነ የአሰራር ሥርዓት መቅረጽ ነበረበት። ይህን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል። ምክክሩ አሳታፊና አካታች መሆን ስላለበት እንዲሁም ኮሚሽኑ ይህን ሰፊ ሥራ ለብቻው የሚወጣው ባለመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ የመግባቢያ ስምምነቶችን የማድረግና አቅምንም የማጎልበት ሥራዎች ተሰርተዋል።
ተቋማዊ አቅምን በሰው ኃይልም በግብዓትም የማጠናከር ሥራዎች በዚህ ምዕራፍ ተጠናክረው የቀጠሉበት ነው። ወደ ተግባራዊ ሂደት የተገባው እነዚህ ዝግጅቶች ከተደረጉ በኋላ ነው። ወይንም ወደ ሶስተኛው ምዕራፍ የተሻገረው። በዚህ የሂደት ምዕራፍ ላይ የሚከናወኑ በርካታ ተግባራት አሉ።
አንደኛው በምክክሩ ውስጥ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን በአዋጁ ላይ በተቀመጠው መሠረት አካታችና አሳታፊ በሆነ መንገድ የመለየት፤ ሁለተኛ ደግሞ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሥራ ይጠይቃል። ምክንያቱም በአዋጁ ላይ በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ እንመካከራለን፣ በምክክሩ የሚሳተፉ እነዚህ ናቸው የሚል በግልጽ አልተቀመጠም። መርሆዎቹ ናቸው ያሉት። በመርህ ደረጃ ግን ምክክሩ መደረግ ያለበት እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነቶች ወይንም ደግሞ አለመግባባቶች ያላቸው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ምሁራንና የፖለቲካ ማኅበረሰቡ መሳተፍ እንዳለበት ብቻ ነው አዋጁ ላይ ደንግጎ የሚያልፈው። አጀንዳዎቹንም በተመለከተ እንዲሁ አቅጣጫ ብቻ ነው ያስቀመጠው። የምንመካከርባቸው ጉዳዮች ሰፊ በመሆናቸው የምንመካከርባቸው ጉዳዮችም እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ መሆን ነው ያለባቸው ተብሎ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ስለዚህ እነዚህ ማለት ምን ማለት ናቸው? አጀንዳዎቹስ ከየት ነው የሚመጡት? የሚሉትን የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ይዞ ሥራ መሥራት የሚጠይቅበት ምዕራፍ ነው ማለት ነው። ይሄ የሂደት ምዕራፍ፤ የአጀንዳ ሃሳቦቹ ከተሰባሰቡ በኋላ ከተለያዩ ምንጮች አንድም ከማኅበረሰቡ፤ ሁለተኛ ደግሞ ኮሚሽኑ በራሱ በሚያካሂደው ጥናት፣ ሶስተኛ ደግሞ የተለያዩ አካላት ወይም ከዚህ ቀደም እነዚህ ናቸው ለሀገሪቱ ያለመግባባት የሃሳብ ልዩነቶች ምክንያት ናቸው ብለው ያስቀመጧቸውን ሰነዶች በመፈተሽ፤ ወይንም ደግሞ አሁንም እነዚህ አካላት በቀረበው ጥሪ መሠረት የአጀንዳ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ በማድረግ ጭምር ነው ከነዚህ ሁሉ ምንጮች የአጀንዳ ሃሳቦች የሚሰባሰቡት።
በዚህ መልኩ የአጀንዳ ሃሳብ ከተሰበሰበ በኋላ ቀጣዩ የሚሆነው አጀንዳ የመቅረጽ ሂደት ነው። ስለዚህ የሚመጡ በርካታ ሃሳቦች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህን ሃሳቦች መልክ የማስያዝ፣ የማደራጀትና ከነዚህም ከመጡ ሃሳቦች መካከል እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ ናቸው የሚባሉትን መለየት ቀጣይ የኮሚሽኑ ሥራ ይሆናል ማለት ነው። ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ ምክክሩ ነው። በምክክሩ መሠረት የተደረሰባቸው መግባባቶች ተግባራዊ የሚደረጉበትን ምክረ ሃሳብ አዘጋጅቶ መስጠት ቀጣዩ ተግባር ይሆናል ማለት ነው።
አሁን ባለንበት የሂደት ምዕራፍ በዋናነት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ያለነው የተሳታፊ ልየታ ሥራ ነው። ሌላው ከዚህ ውጭ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራው እነዚህ ሥራዎች የሚመሩበትን የሕግና የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ነው። ይህን የሚመለከትም ዘርፍ ተቋቁሟል። ዘርፉ በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።
ከነዚህ ሁሉ በላይ ግን ይህ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገና ውጤታማም ሊሆን የሚችለው ሃሳቡን ሕዝቡና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሲገዛው ነው። ወይም ተቀባይነት ሲኖረው ነው። ተቀባይነት ለማግኘት ደግሞ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች በስፋት ሲሰራ ነው። ከኮሚሽኑ በሚሰነዘሩ ሃሳቦች ብቻ ሳይሆን፤ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚመጡ ሃሳቦችንም በመያዝ ሰፊ የሆነ የማንቃት ግንዛቤ የመፍጠርና ኅብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት የሂደቱ ባለቤት እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎችም እንዲሁ በስፋት እየተካሄደ ነው።
እነዚህን የቅድመ ዝግጅት፣ የዝግጅትና የሂደት ምዕራፎች እንዲሁም ገና በሂደት ላይ ያለው የትግበራ ምዕራፍን ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው፤ ኮሚሽነሮች ተሰይመው ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ዋና ዋና ሥራዎች ተከናውነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ሊሞላው በቀረው ጥቂት ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸውልናል። በሥራዎቹ እንደ ጥንካሬ እና ክፍተት የሚነሱትንም ቢያብራሩልን?
አቶ ጥበቡ፡- በተሰሩት ሥራዎች በስኬት ከሚነሱት ውስጥ አንዱ አቅምን ለማጎልበት የተከናወነው ነው። በርግጥ አቅምን ማጎልበት በአንድ ጀንበር የሚጠናቀቅ አይደለም። የሆነ ቦታ ላይም አቅም ተፈጥሯል ይበቃል የሚባልም አይደለም። ኮሚሽኑ ሥራውን እየሰራ ነው አቅም የሚፈጥረው። ነገሮችን ጎን በጎን በማስኬድ እንጂ አቅም እስኪፈጠር ተብሎ መቀመጥ አይቻልም። ሥራ እየተሰራ የሚፈለገው አቅም እየተገነባ ይሄዳል። ኮሚሽኑ ሲመሰረት ከነበረው አቅም አኳያ በሰው ኃይል፣ በግብዓት፣ በአሰራርና በመሳሰሉት ሁኔታዎች ሲገመገም ዛሬ ላይ በተሻለ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ መሬት ወርዶ ሥራዎችን እየሰራ የሚገኘው አቅም በመፍጠሩም ነው። ውጤት እየተመዘገበ ቢሆንም የመፈፀም አቅሙን አሁን ካለው በላይ ማጎልበት ይኖርበታል።
ሁለተኛው እንደ ስኬት የሚወሰደው ግንዛቤን ለመፍጠር የተሰራው ሥራ ነው። ትናንትና እና ዛሬ ያለው ሁኔታ ፍጹም የተለያየ ነው። በዚህ ላይ የተሰራው ሥራ የተሻለ ነው በሚል የሚወሰድ ቢሆንም ሰፊ ክፍተት እንዳለው በግምገማችን እንገነዘባለን። ክፍተቶችን በመለየት ከውስጥም ከውጭም ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን በመጀመሪያ አካባቢ ላይ የምክክር ኮሚሽኑ ያስፈልጋል ወይ ከሚሉ ጥያቄዎች ጀምሮ ክፍተቶች ነበሩ። በሂደት መግባባትና ልዩነቶችን ወደ ማጥበብ ተመጥቷል። ሀገራዊ ምክክር የሚባለው ጉዳይ በራሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል። በተለያዩ ባለድርሻ አካላትና በኅብረተሰቡም ሃሳቦች እየሰረጹ ነው።
አሁን ላይ ተሳታፊዎች የመለየት ሥራ መሥራት የተጀመረው እነዚህ ሁሉ ተግባራት ተከናውነው ነው። ይህም ሥራ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተሞች፣ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሐረሪ እና ሲዳማ ክልሎች ሙሉ ለሙሉ በወረዳ ደረጃ የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ሃሳብ የሚሰጡ ተወካዮችን የማስመረጡ ሂደት ተጠናቅቋል። በአፋርና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የተሳታፊ ልየታ ሥራ ተጠናቅቆ የአጀንዳ ሃሳብ የሚሰጡ ተወካዮች የማስመረጥ ሂደት ላይ ይገኛሉ።
ሶማሌና ደቡብ ክልሎች ላይ ደግሞ ለአጀንዳ ማሰባሰቡ ተወካዮቻቸውን የሚመርጡ ከኮሚሽኑ ጋር ለሚሰሩ ተባባሪ አካላት ስልጠና ተሰጥቶ ዝግጅት ተደርጓል። የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ሃሳብ የሚሰጡ ተወካዮችን የማስመረጡ ሥራ እየተገባደደ ነው።
ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ከሚኖርባቸውና በርከት ያሉ ወረዳዎች ካሉባቸው ክልሎች አንዱ በሆነው ኦሮሚያ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ካሉት ዞኖች ውስጥ ወደ ስምንት በሚሆኑት ዞኖችና ስድስት ከተሞች ላይ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር የሚሰሩ ተባባሪ አካላት ሰልጥነው አሁን ላይ ተሳታፊ ልየታ ሂደት ላይ ነው የሚገኙት። በክልሉ የተሰራው ሥራም አሁን በደረስንበት ደረጃ ትልቅ ስኬት ነው ብለን እንወስዳለን። በቀሪዎቹም በተመሳሳይ ተግባራት ይከናወናሉ።
በተጨባጭ ሥራ ውስጥ ያልገባንባቸው የትግራይና የአማራ ክልሎችም ቢሆኑ የተሳታፊ ልየታ ሥራ ስላልተጀመረባቸው እንጂ አስፈላጊ የሆኑ የዝግጅት ሥራዎች ግን እየተሰሩ ይገኛሉ። ተቋማትና ግለሰቦች ኮሚሽኑ ድረስ በአካል በመምጣት የሰጡትንም የአጀንዳ ሃሳብ በማሰባሰብ ረገድም ተጨማሪ ሥራዎች እየተሰሩ በመሆናቸው በዚህ በኩል ያለው ሥራ በውጤት ይገለጻል።
አዲስ ዘመን፡- አማራና ትግራይ ክልሎች ወደኋላ የቀሩት በምን ምክንያት እንደሆነ ቢገልጹልን?
አቶ ጥበቡ፡- መሠረታዊው ጉዳይ የፀጥታ መደፍረስ ነው። ትግራይ ክልል ግን ከጦርነት ውስጥ ወጥቶ አሁን ላይ በማገገም ላይ የሚገኝ እንደሆነ ይታወቃል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ክልሉ በጦርነቱ የተጎዳ እንደመሆኑ፣ ኅብረተሰቡም ሆነ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ይህ ምክክር ደግሞ አሳታፊና አካታች እንደመሆኑ መጠን ክልሉ ከነበረበት ውጥረት ወጥቶ ኮሚሽኑ የሚሰራቸውን ሥራዎች ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታ እስኪፈጠር ነው።
በአማራ ክልል ግን ወደ ሥራ ያልተገባው ግጭት በመኖሩ ነው። እንደሀገር ወደ ምክክር ተገፍተን የገባነውም አለመረጋጋትና ጦርነት በመኖሩ ምክንያት ነው። የሃሳብ ልዩነትና አለመግባባቱ በሰፋ ቁጥር የሚያመራው ወደ ግጭት ነው። ብዙ ታሪካችንም ይህንኑ የሚያሳይ ነው። አለመግባባቶችንና ልዩነቶችን በኃይል አማራጭ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ማለት ነው። ምክክሩ አሳታፊና አካታች ሆኖ እንዲከናወን ከተፈለገ ቢያንስ አንጻራዊ ሰላም ያስፈልጋል።
ምክክር፤ ጥሞናን፣ መደማመጥን እርጋታን ይፈልጋል። እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች ባልተፈጠሩበት ያለያዩንና ያልተግባባንባቸው ነገሮች አሉ የሚለውን የአጀንዳ ሃሳብ አምጥቶ ተመካክሮ ዘላቂ ሃሳብ ለማምጣት ያስቸግራል። ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት አካባቢው እስኪረጋጋ እየጠበቀ ነው። ለዚህ ምክክር ኮሚሽኑ ብቻ ሳይሆን መንግሥት፣ በግጭት ውስጥ የሚገኙ ወገኖችም ያላሰለሰ ጥረት ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- በኦሮሚያ ክልል ያለው ነባራዊ ሁኔታ የኮሚሽኑን ሥራ ለማሳካት የሚያስችል ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ጥበቡ፡- በክልሉ በተወሰኑ ዞኖች ግጭቶች አሉ። በተወሰኑ ዞኖች ደግሞ አንጻራዊ ሰላም አለ። የምናመጣው ውጤት ተመሳሳይ መሆን እንዳለበት እናምናለን። የሥራ ሂደታችንም ለሁሉም እኩል መሆን አለበት። ግጭት ስላለ አሳታፊነትና አካታችነት መጎዳት የለበትም። እንደየአካባቢው ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መጠቀም ይኖርብናል ማለት ነው።
በሥራችን ላይ እንደተግዳሮት እየገጠመን ያለው ግጭት ብቻ አይደለም። ለአብነት ለማንሳት አዲስ ክልል የሆኑ አካባቢዎች በሁለት እግራቸው እስኪቆሙ ድረስ ጊዜ ይወስዳሉ። እንዲህ ያለውና ሌላም ምክንያት ነው ለሥራችን መዘግየት ምክንያት እየሆነ ያለው።
ኮሚሽኑ የሚከተለው መርህ ችግሮች ወይንም ግጭቶች ስላሉ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አያስፈልግም። ኮሚሽኑ ችግሮች አሉ ብሎ ሥራዎችን ሳይሰራ ቀርቶ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት መፈጸም ባልቻለ ነበር። የእስካሁኑ ሥራም ለቀሪው ሥራ አቅምን አጠናክሮ ለመሥራት ዕድል ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን፡- ለኮሚሽኑ ሥራ እንቅፋት እየሆኑ ያሉት ግጭቶችና የተለያዩ ተግዳሮቶች በእቅዱ እንዳይመራ አያደርጉትም?
አቶ ጥበቡ፡- ምንም ጥርጥር የለውም ሥራን ያጓትታል። አሁንም ለሥራው እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮች አልተወገዱም። ኮሚሽኑ ሥራውን እንዲያጠናቅቅ በአዋጁ የተቀመጠው የሶስት ዓመት ጊዜ ነው። ሆኖም ግን እንዳስፈላጊነቱ የሥራ ጊዜው ሊራዘም ይችላል የሚለው እንደተጠበቀ ነው። ምክክሩ አሳታፊና አካታች ነው። ወረዳ ድረስ ዘልቆ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍልን ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም በሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በዓለም የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያንን ማካተት አለብን ብለን እየሰራን ባለንበት ሁኔታ በሆነ ምክንያት ዘልሎ ሀገራዊ ምክክር ማድረግ አይታሰብም። ምክንያቱም አካታችና አሳታፊ መሆን ስለማይችል ማለት ነው። ይህ ከመሠረታዊ መርሁ አኳያ ሲፈተሸ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርም።
ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ተቋቁመው ሥራ ሲጀምር በትግራይ ክልል ጦርነት እየተካሄደ ነበር። የዝግጅትና ሌሎችም ሥራዎች ሲሰሩ የነበረው በዚህ ሁኔታ ነበር። መሬት ላይ ወርዶ ሥራዎች መሥራት በማይቻልባቸው ሁኔታ ነበር ወደፊት ለሚከናወኑ ሥራዎች ሲሰራ የነበረው። ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ የነበረው ተጽዕኖዎችን ማስወገድ ባይቻል ቢያንስ ሥራው መቆም የማይችልበት ደረጃ ላይ ማድረስ ይቻላል በሚል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው? ወይስ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንም ያካተተ ነው?
አቶ ጥበቡ፡- እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ ጉዳዮቻችንን መፍታት ከቻልን ሌሎች ችግሮች በራሳቸው ሊፈቱ ይችላሉ። ወይም ይከስማሉ። ትልልቆቹ ችግሮች ሲፈቱ አብረው ሊፈቱም ይችላሉ። ካለው ጊዜ አንጻርም ከፍተኛው ላይ ማተኮሩ የተሻለ ነው። አሁን ላይ ሆነን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ይዘት ያላቸው መሆናቸውን ማወቅ አንችልም። ወደፊት በሚሰበሰቡት የአጀንዳ ሃሳቦችና ኮሚሽኑ ደግሞ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት አጀንዳዎች በሚቀረጹበት ወቅት የሚታወቅ ነው የሚሆነው። ነገር ግን ገዥው ነገር እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ ጉዳይ መሆን አለባቸው ነው።
ኅብተሰብንም ሆነ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ ያስፈለገውም፤ የአጀንዳ ሃሳቦቻችንን ከሥር ከመሠረቱ ማውጣት ወይንም መለየት አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ ይመለከታቸዋል በተባሉ በተወሰኑ አካላት አጀንዳዎች ተቀምጠው ውይይት ተደርጎ ነበር። ውይይቱ እንደ አሁኑ ኮሚሽኑ እንደተከተለው አቅጣጫ ስፋትና ጥልቀት አልነበረውም። አንዱ የማንግባባት ጉዳይ በአጀንዳዎቻችን ላይ ጭምር ነው። ለአንዱ ትልቅ ጉዳይ የሆነው ለሌላው ደግሞ ላይሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ። መግባባቱ መፍጠር ያለበት ከአጀንዳ ቀረፃ ጀምሮ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በተለያየ ዓለም ላይ የሚኖረውን ዳያስፖራ በምን መልኩ ነው ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ ያለው?
አቶ ጥበቡ፡- በሀገሩ ጉዳይ ላይ ይመለከተኛል የሚል በየትኛውም ዓለም የሚኖር ሁሉ ተሳታፊ እንዲሆን ነው የሚፈለገው። ልክ ሀገር ውስጥ እንደሚከናወነው ሁሉ ዳያስፖራውም እንዲሳተፍ በእቅድ እየተሰራ ነው። የትኩረት ቦታ ተብለው የተለዩ አሉ። አንዱ ወረዳዎችን ጨምሮ ክልልና ከተማ አስተዳደሮች፣ሁለተኛ ደግሞ በፌዴራል ደረጃ ነው። ሶስተኛው ዳያስፖራዎች ናቸው።
ዳያስፖራ ወገኖቻችን በምን ሁኔታ ቢሳተፉና ቢካተቱ የተሻለ ይሆናል የሚለውን ከእነርሱ ጋር እየተመካከርን ነው። እስካሁን ባለውም በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በበይነመረብ (ኢንተርኔት) አማካኝነት ምክክር እየተደረገ ነው። ስለሀገራዊ ምክክሩ ግንዛቤ መፍጠር፣ ስለኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነትም የማስተዋወቅ፣ ወይም ማስረዳት ጭምር በምን መልኩ ማሳተፍ እንደሚቻል ግብዓት ከእነርሱ በመወሰድ ጭምር እየተሰራ ነው። በተመሳሳይ በሌሎች ሀገሮች ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች ጋርም ሥራው ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ የያዘው ሥራ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሰጠው ጊዜ በቂ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ጥበቡ፡- የሆነ ሥራ ተሰርቶ የሆነ ነገር ላይ የሚቆም ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ልዩነቶቻችንና የማያግባቡንን ነገሮች በምክክር የመፍታት ባህል ልናዳብር ይገባል። እንዲህ ያለውን ባህል ኮሚሽኑ ለሶስት ዓመት በሚሰራው ሥራ ብቻ ማምጣት አይቻልም። ያሉት ችግሮች ውስብስብና ለዘመናትም የተከማቹ ናቸው። አሁንም የቀጠሉ በመሆናቸው በአንድ ጊዜ እልባት ላይ ላይደርስ ይችላል። ጊዜ ይጠይቃል።
ኮሚሽኑ በተሰጠው ጊዜና በአዋጅም በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት ተልዕኮውን ለመወጣት በተቻለው መጠን ጥረት እያደረገ ይገኛል። ሆኖም ግን በእቅዱ መሠረት መፈፀም ካልተቻለ ሕጉ ክፍት ነው። ሕጉን ያወጣው አካል ወይንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚሽኑ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገዋል ብሎ ካመነ የማራዘም ሥልጣን አለው። የጊዜው ጉዳይ በአንድ በኩል ያሳስባል። ምክንያቱም ተጨማሪ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ሥራዎች ቶሎ ቶሎ መሠራት አለባቸው።
በሌላ በኩል የተጀመረው የምክክር ሥራ በማያዳግም ሁኔታ መሠራት ስላለበት በጥንቃቄና በእርጋታ መሠራት ይኖርባቸዋል። የኮሚሽኑ ሥራ እዚህም እዛም የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማስቆም አይደለም ተልዕኮው፤ ለግጭት መንስኤ የሆኑትንና ሌሎችንም ችግሮች ከሥር ከመሠረቱ በማጥናት ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ ማስቻል ነው። ይህ ደግሞ ጊዜ ይጠይቃል።
በጥቅሉ እየተሰራ ባለው ሥራ ውጤታማ ነው ውጤታማ አይደለም ብሎ ለማስቀመጥ ብቻ አይደለም። ሂደቱ በራሱ ወሳኝ ነው። በሂደቱ ውስጥ ልምድ እየተገኘ ነው። አቅምም እየተፈጠረ ነው። ችግሮች ሲያጋጥሙ የምንፈታባቸው ጥሩ የሆኑ የባህል እሴቶች አሉን፤ ነገር ግን እንደ ሀገር በአዋጅ ተቋቁሞ የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ በስፋትና በጥልቀት መንቀሳቀስ የተለመደ አይደለም። ይህ መልካም ጅምር ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ ሂደት ማለፍ እንደ ሀገር ትልቅ ዕድልም ነው።
እየተሰራ ባለው ሥራ ፈጣን የሆነ ውጤት ማስመዝገብ ባይቻልም። ፈታኝ በሆኑ ነገሮች ውስጥ የተሰሩት ሥራዎች ተስፋ የሚሰጡ ናቸው። ጊዜ ቢወስድም በጠረጴዛ ዙሪያ ምክክሩ መካሄዱ አይቀሬ በመሆኑ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ዝግጁነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል። በምክክሩ ለሌሎች ሀገሮችም ጭምር ተምሳሌት መሆን ይጠበቅብናል። በኮሚሽኑ አካሄድ ላይ ጥያቄዎች ካሉ በግልጽ ማቅረብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ ጥበቡ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም