/ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አ ገልግሎት የተሰጠ መግለጫ ሙሉ ቃል /
በኢፌዴሪ እና ሶማሌ ላንድ መካከል የተደረገው ስምምነት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ሰፋ ያሉ የትብብር አድማሶችን ያካተተ ነው። ሶማሌ ላንድ የአፍሪካ ቅርምትን ተከትሎ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ሥር የቆየች ሲሆን እ.ኤ.አ ጁን 26 ቀን 1960 ነፃነቷን አግኝታለች። በወቅቱ በርካታ ሀገራት እውቅና ሰጥተዋት እንደነበርም ይታወሳል። ሆኖም በዚያው ዓመት ከአምስት ቀናት በኋላ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ቆይታ ነፃ ከወጣችው ሞቃዲሾ ጋር በፈቃዷ ተቀላቅላለች።
በ1991 እ.ኤ.አ ዳግም ነፃነቷን አውጃ በተከታታይ ሰላማዊ ምርጫ፤ ሰከን ያለ የመንግሥት ቅይይር በማካሄድ ለ30 ዓመታት ዴሞክራሲን በመለማመድ ላይ ትገኛለች። ሀገራችንን ጨምሮ አንዳንድ ሀገራት በሐርጌሳ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ከፍተውም ይንቀሳቀሳሉ:: ነገር ግን እስካሁን የተሟላ ዕውቅና አላገኘችም። ይህም ሆኖ የወደብ አገልግሎትና ልማትን ጨምሮ ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ስምምነት ፈርማለች።
ከዚህ ቀደም በርበራ ላይ ለኢትዮጵያ የ19 በመቶ ድርሻ እንዲኖራት ይፈቀድ የነበረ የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ እንደነበርም ይታወሳል። በአሁኑ ወቅት ሌሎች ሀገራት ተመሳሳይ ሂደት እየተከተሉ መሆኑም ይታወቃል። ይሄ ሲሆን የተሰማ ኮሽታም ሆነ ቅሬታ አልነበረም። ኢትዮጵያ የወታደራዊ ቤዝና ኮሜርሻል ማሪታይም አገልግሎት በሰጥቶ መቀበልና በኪራይ ለማግኘት የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድና ሂደትም በመሠረቱ አንድና ያው ነው።
በሀገራችንና በሶማሌ ላንድ መካከል ቆየት ያለ የትብብር ስምምነት ነበረ። ሁለቱ ወገኖች ወዳጅነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ባደረጉት ጥረት የተገኘው የአሁኑ ሁሉን አቀፍ ትብብርና አጋርነት ሰነድ የሁለቱንም ወገኖች ታሪካዊ የሚባሉ ጥያቄዎችን በሚመልስ፣ ዝርዝር ፣ግልጽና ስትራቴጂክ አጋርነትን በዘላቂነት ለመገንባት የሚያስችል ነው። በሶማሌ ላንድ በኩል ማንም ሀገር እየፈለገ ሊያከውናቸው የማይችሉ ጥያቄዎቻቸውን የሚመልስ ሲሆን ከማንም ሀገር ሊያገኙት የማይችሉትን እገዛና ሽርክና ያጎናጽፋቸዋል::
የሀገራችንን መሻቶች በተመለከተ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን በግልጽ እንደሰፈረው ለጎረቤቶቻችን ቅድሚያ እንሰጣለን። በዚህም ችግራቸውን ተጋርተን ለመፍትሔው አብረን መሥራት፣ ፀጋዎቻችንን በጋራ በማልማትና በጋራ ተባብሮ ለማደግ ያለንን ራዕይና ጉጉት በተግባር ለመተርጎም ያስችላል። ሕልውናችንን እና ሀገራዊ ጥቅሞቻችንን በአስተማማኝ ለመጠበቅና ለማራመድ የሚያስችል ዕድልም ይፈጥራል።
ሀገራችን በረጅም፣ በመካከለኛና በቅርብ ዘመን ታሪኳ የባሕር በር ባለቤት ነበረች። ከቅርብም ከሩቅም በተሸረበ ተከታታይ ሸፍጥ ተገፍታም የባሕር በሯን አጥታ ነበር። በኋላም በድጋሚ የባሕር በር ባለቤት ሆነች። በስተመጨረሻም ለሦስት አሥርተ ዓመታት በዘለቀና በውስጥ ቀውስና በውጭ ሤራ በታገዘው የእርስ በርስ ጦርነት ተካሂዷል።
በእርስ በርስ ጦርነቱ ማብቂያ ላይም በሕግም በታሪክም ፊት በተፈጸመ ስሕተት የባሕር በር አልባ ሆና ላለፉት 30 ዓመታት ዘልቃለች። ይህንን የታሪክ ስብራትና የትውልድ ቁጭት ለማረም ባለፉት አምስት ዓመታት የለውጡ መንግሥት ከጦርነት በመለስና በሰጥቶ መቀበል መርሕ የሀገራችንን ቁመናና ዕድገት የሚመጥን ዘላቂና አስተማማኝ የወደብና የባሕር በር አማራጮችን ስለማስፋት ሲያውጠነጥንና ሲመክርም ሲሞክርም ቆይቷል::
በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ ይኸው ሐሳብ ዳብሮ ለኢትዮጵያውያን እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ የመንግሥት አቋም መሆኑ ተበስሯል። መንግሥት ይፋ ባደረገው ይኸው አቋሙ ከማንም ሀገር ጦርነት እንደማይገባና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አማራጮች መኖራቸውን እንደሚያምን፣ ኢትዮጵያም ያሉዋትን ጸጋዎች ለመጋራት ዝግጁ መሆኗን ሲገልጽ ቆይቷል። በዚሁ መሠረት ጆሮ መስጠት ለቻሉና ለፈለጉ ሁሉ አቋማችንን ለማስረዳት ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን።
ከሶማሌ ላንድ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ለወራት በብስለትና በስክነት ምክክር እና ድርድር ሲካሄድ ቆይቷል:: እነሆም ሁለቱንም ተጠቃሚ በሚያደርግ አግባብ የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል። ይኸው ሰነድ ለኢትዮጵያ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር ኃይል ቤዝና ኮሜርሻል ማሪታይም አገልግሎት በሊዝ የምታገኝበትን ዕድል የሚያስገኝ ሲሆን መንግሥት አስቀድሞ ይፋ ባደረገው አቋሙ መሠረት ሶማሌ ላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ እንዲኖራት ያስችላል። ከዚያም ባሻገር በሂደት ሶማሌ ላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወሰድበትን አግባብም ያካትታል ።
ቀጣናችን የተቸረው ፀጋ ለሁላችንም ከበቂ በላይ ነው። በሥጋት ይሁን በክፋት ተሸብቦ ትብብርን መንፈግ በሕዝቦች ጉስቁልና የሚመነዘር ዝቅታን እንጂ የተሻለ ነገን ለመፍጠር አይቻልም። ከሶማሌ ላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት መንግሥት የኢትዮጵያን መሻቶች ከጎረቤቶቿ ጋር በሚደረግ ትብብር፣ በሰጥቶ መቀበልና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለማሳካት ያለውን እምነት በተግባር ያሳየበት ነው። ይኸው ዕድል ለሁሉም ክፍት የነበረና ክፍት ሆኖም የሚኖር ነው።
ስምምነቱ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት ጭንቀትና ቁዘማ ለማከም የሚያስችል አጋጣሚን የፈጠረ ነው። በመሆኑም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስደስት ታሪካዊ ክስተት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም የቀጣናው ሠላም የሚገዳቸው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት ሁሉ ሊደሰቱ ይገባል።
በዚህ ስምምነት የሚጎዳ አካልም ሆነ ሀገር የለም። የተጣሰ ሕግና ተሰበረ እምነትም የለም። እውነታው ይኸው ቢሆንም ማንም እንደሚገምተው በዚህ አወንታዊ ድምዳሜ የሚከፋ፣ የሚደነግጥና ሁኔታውን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል አይኖርም አይባልም።
በመሆኑም በተለይ ኢትዮጵያውያን በርግጥም ሀገራችን በልኳና በቁመናዋ ልክ በቀጣናው፣ በአህጉራችንና በዓለም አደባባይ ተገቢ ሥፍራዋን ስታገኝ፣ ገንቢ ሚናዋን ስትወጣ፣ ጥቅሞቿንም ስታስከብር ብቻ በጋራ እንደምንከበር ማመንና ለዚህም ልዩነቶችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ በማቻቻል ተያይዘን ከፍ እንል ዘንድ ይህን አጋጣሚ እንድንጠቀምበት የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል ።
ይህ በዘመናት አንዴ የሚከሠት የታሪክ እጥፋት በመሆኑ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ሀገራችንን በጋራ እንታደግ!! ከዘመናት በኋላ በታሪክ የማንወቀስ እንድንሆን ያለንበትን ምዕራፍ ከመወራረፍና ከመጠላለፍ ተላቀን የኢትዮጵያችን ከፍታ ማብሠሪያ ለማድረግ በአንድነት አብረን እንትጋ! !
ታኅሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም አ ዲስ አበባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አ ገልግሎት
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም