የገና እና የጥምቀት በዓላት በክልሉ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ያስችላሉ

አዲስ አበባ፡- የገና እና ጥምቀት በዓላት በክልሉ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የሚያስችሉ መሆኑን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ እምቢአለ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የገና እና ጥምቀት በዓላት በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አማራ ክልል በቀደምትነት ይጠቀሳል። እነዚህ በዓላት በክልሉ ተቀዛቅዞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የሚያችሉ በመሆናቸው በትኩረት እየተሠራ ነው።

በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት የከተማው ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ መቀዛቀዝ አሳይቷል ያሉት አቶ አበበ፤ ሁለቱን በዓላት በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ክልሉን ብሎም ሀገሪቱ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በደመቀ ሁኔታ ለማክበርም የዝግጅት ሥራዎችን እየተሠሩ ነው ብለዋል።

ዘንድሮ በታኅሣሥ 28 የሚከበረውን የገና በዓል በላሊበላ ከተማ ለማክበር የከተማው አስተዳደር ኮሚቴ ከማቋቋም ጀምሮ የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደርና የቱሪዝም ቢሮ ከክልሉ ጋር በመሆን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይም በደመቀ መልኩ በጎንደር የሚከበረው የጥምቀት በዓል እንደክልል ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፈው ዓመት በሁለቱ በዓላት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በእያንዳንዳቸው ላይ የተገኘ መሆኑን አቶ አበበ አስታውሰዋል። በዚህ ዓመትም ተመሳሳይ መልኩ በደመቀ መልኩ ለማክበር እና ቀጣይነት እንዲኖረውን ይሠራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገና እና ጥምቀትን በዓላትን ታሳቢ በማድረግ በክብረ በዓሉ ለመታደም የሚመጡ ጎብኚዎች ከባሕርዳር ላሊበላ እና ከጎንደር ላሊበላ ለመንቀሳቀስ በቀጥታ የአየር ትራንስፖርት መፍቀዱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ፓኬጁን ቁጥርን እንዲጨምር ለማድረግ የክልሉና ፌዴራል ቱሪዝም ቢሮ እየሠራ መሆኑን አቶ አበበ አስታውቀዋል።

የእነዚህ በዓላት ብሎም የሠላም ባለቤቱ ሕዝብ በመሆኑ በክልሉ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በማስቀጠል እንግዶች በዓላቱን ከማክበር ባለፈ የሚጎበኙ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።

በክልሉ የሚገኙ ሆቴሎች፣ ትራንስፖርት፣ አስጎብኚ ማኅበራትና መሰል አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በጋራ እየተዘጋጁ መሆኑን አቶ አበበ ገልጸዋል።

አቶ አበበ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ እና የሠላም ችግር ምክንያት በክልሉ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር መቀነስ ያሣያል። ለዚህም ቢሮው የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት በማድረግ ያለውን የጎብኚዎች እጥረት ለማካካስ እየሠራ ነው።

በክልሉ ያሉትን ሰፊ የባሕልና የቱሪዝም መዳረሻዎች ምቹ በማድረግ እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመደገፍ ዘርፉን በድጋሚ የማንሰራራትና የሚገኘውን ተጠቃሚነት ማሳደግ ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ቢሮው ከመንግሥት እና በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

አቶ አበበ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላቱን ለማክበር የሚመጡ እንግዶች በክልሉ በነፃነት መንቀሳቀስና መጎብኘት የሚቻል መሆኑን ታሳቢ በማድረግ እንዲጎበኙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You