የቀበሌው ንግድ ቤት ኪራይ ውዝግብ – በመርካቶ ሙሉቀን ታደገ እና ክፍለዮሐንስ አንበርብር

የዛሬው ‹‹የፍረዱኝ ዓምድ›› ዝግጅታችን በመዲናችን አዲስ አበባ የተፈጠረን አንድ ውዝግብ ያስመለክተናል። ውዝግቡ የተፈጠረው በቀድሞው የመጠሪያ ስሙ ዞን አንድ ወረዳ 5 ቀበሌ 06 በአሁኑ መጠሪያው ደግሞ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 በተለምዶ መርካቶ ይርጋ ኃይሌ ዙሪያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ ወይዘሮ ሙሉ ወይንሀረግ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በተለምዶ መርካቶ ይርጋ ኃይሌ ዙሪያ እየተባለ በሚጠራው ሰፈር የንግድ ቤት ቁጥር 1004 የሆነውን የቀበሌ ቤት ተከራይ ናቸው። እናም ወይዘሮ ሙሉ ወይንሀረግ፣ «በውል እና ማስረጃ የገዛሁትን እንዲሁም ከወረዳ 08 የግንባታ ፈቃድ ተሰጥቶኝ በራሴ የጉልበት እና የገንዘብ ወጪ የገነባሁትን፤ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን ሳከናውንበት የነበረን የቀበሌ ቤት ምክንያቱ በውል ባልታወቀ አግባብ በወረዳ 8 አመራሮች ተነጥቂያለሁ፡፡ ሕዝብን እንዲያገለግሉ መንግሥት ባስቀመጣቸው ሹመኞች የደረሰብኝን በደል ተመልክቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ» ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ዝግጅት ክፍል አቤት አሉ።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድንም የባለጉዳዩዋን ቅሬታ አድምጦ፤ ሰነዶችን አገላብጦ እና የሚመለከታቸውን አካላት አናግሮ፤ በጥቅሉ ስለጉዳዩ ከሰዎች እና ሰነድ ያገኛቸውን መረጃዎች እና ማስረጃዎች በጥልቀት መርምሮ የደረሰበትን ውጤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራና ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ እነሆ ብሏል፤ መልካም ንባብ፡፡

ከአቤቱታ አቅራቢዋ አንደበት

“በደል ተፈጸመብኝ” ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን አቤቱታ ያቀረቡት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሙሉ ወይንሀረግ እንደሚናገሩት፤ ውዝግብ የተነሳበት ቤት በዓዋጅ 47/67 የተወረሰ ሲሆን፤ ቤቱም ለንግድ አገልግሎት የሚውል ነው። በዚህ ቤት ከ1968 ጀምሮ እስከ መስከረም ወር 1987 ዓ.ም ድረስ አቶ ሰይፉ አርጋው የተባሉ ግለሰብ የንግድ ሥራ ያከናውኑበት ነበር፡፡

በመስከረም ወር 1987 ዓ.ም ድንገት በተፈጠረ የእሳት አደጋ ምክንያት ቤቱ ወደ ዓመድነት ተቀየረ። ይህን ተከትሎ በቦታው ላይ ግንባታ ለማከናወን የገንዘብ አቅም ያጡት አቶ ሰይፉ የቤቱን ቁልፍ ለወይዘሮ ሙሉ ሸጡ፡፡ ወይዘሮ ሙሉም ባዶ ቦታውን የገዙት ወደፊት አልምተው ለመጠቀም ባላቸው ተስፋ ነው፡፡

ቤቱን ገዝተው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት በአካባቢው ሌባ ይበዛበት እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮ ሙሉ፤ በወቅቱ ንብረታቸውን ተዘርፈው ባዶ እጃቸውን የቀሩ በርካቶች መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ አካባቢው ያልለማ እና የቆሸሸ ስለነበርም ዘመዶቻቸው እና የቅርብ ጓደኞቻቸው ቦታውን እንዳይገዙት መክረዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ቦታው ወደፊት የሚኖረውን ተፈላጊነት በማጤን እንደገዙት ይናገራሉ፡፡

እንደ ወይዘሮ ሙሉ ገለጻ፤ ምንም እንኳን ወዳጅ ዘመዶቻቸው ቦታውን እንዳይገዙ ያላደፋፈሯቸው ቢሆንም፤ እርሳቸው ግን በቦታው ላይ ሰርቶ የመለወጥ ከፍ ያለ ሕልም ስለነበራቸው ሕልማቸውን ለማሳካት ከባንክ ብድር ወስደዋል። ይሄም አልበቃ ሲላቸው ከግለሰቦች በአራጣ እስከመበደር ደርሰዋል፡፡ በወቅቱ 200 ሺህ ብር የሚገመት ገንዘብ ወጪ አድርገዋል፡፡ የተቃጠለውን ቤት ቁልፍ ግዥ ሲፈጽሙም ሁሉም የግዥ ሂደት የተከናወነው በውል እና ማስረጃ ነበር፡፡

አቶ ሰይፉ፣ የንግድ ሥራ ሲያከናውኑበት የነበረውና በመስከረም ወር 1987 ዓ.ም የተቃጠለው ቤት የጭቃ እና ከእንጨት የተሰራ ነበር የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ የቤቱን ቁልፍ ከአቶ ሰይፉ ከገዙት በኋላ የግንባታ ፈቃድ ከወረዳ 8 በማውጣት ቤቱን በብሎኬት መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የተሰጣቸው የግንባታ ፈቃድም በርካታ ቤቶችን መሥራት እንዲችሉ የፈቀደ ስለነበር ቤቱን ሲገነቡ ሁለት ዓይነት የንግድ ሥራ ማከናወን የሚያስችል አድርገው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ሙሉ ማብራሪያ፣ በዚህ መሠረት አንደኛው ክፍል የመኝታ/አልጋ ቤት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሲሆን፤ በመኝታ ቤቶቹ ዙሪያ የተሰሩት ደግሞ የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን ለመሸጥ የሚያስችሉ ሱቆች ነበሩ፡፡ የግንባታ ፈቃዳቸው የሰጣቸውን እድል ተጠቅመውም ወይዘሮ ሙሉ በቤቱ (በቤት ቁጥር 1004) ሁለት የንግድ ፈቃድ አወጡ፡፡ አንደኛው ቤት የመኝታ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ብትን ጨርቅ ለመሸጥ የሚውል ነበር፡፡

ይሄን ተከትሎም ሥራውን ሊያግዛቸው ገበያቸውን ሊያሰፋላቸው የሚችል ሰው ስላስፈለጋቸው፤ የልብስ ቤት ፈቃድ ባወጡባቸው ቤቶች ጨርቅ እንዲያሻሸጡላቸው በማሰብ ከመርካቶ አካባቢ የነበሩ የተወሰኑ ልብስ ሰፊዎችን በነጻ በቤታቸው ውስጥ እንዲሰፉ ይፈቅድላቸዋል፡፡ በወቅቱ ልብስ እንዲያሻሽጡላቸው የተፈቀዱላቸውን ግለሰቦች ቤታቸው ውስጥ እንዲሰፉ የመረጧቸው ልብስ ሰፊዎች ደግሞ ብዙ ደንበኛ ያላቸው ነበሩ፡፡

እንዳሰቡትም ሥራውን በጀመሩበት ጊዜ የንግድ ሥራቸው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነበር፡፡ በሁሉም ሱቆች ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝ የንግድ ሥራ እያከናወኑ ነው በሚልም በመንግሥት ከፍተኛ ግብር ተጥሎባቸው በዚያ ወቅት እስከ 60ሺህ ብር መክፈል ችለውም ነበር።

በወቅቱ በጨርቅ መሸጥ እና የመኝታ አገልግሎት በመስጠት የተሰማሩት ወይዘሮ ሙሉ «ጥምር ንግድ» በሚል ፈቃድ ተሰጥቷቸው ነበር። ግብርም የከፈሉት የጥምር ንግድ ሥራ በሚል ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ግን በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ አግባብ ጨርቅ እንዲያሻሽጡላቸው ሲንጀር የልብስ ስፌት ማሽን ይዘው ከንግድ ቤታቸው ያስጠጓቸው ሰዎች በራሳቸው የገንዘብ እና የጉልበት ወጪ የሰሩትን ቤት በተለይም የጨርቃጨርቅ ፈቃድ አውጥተው ይሰሩባቸው የነበሩባትን ቤቶች እንዲወርሱ ተደረገ፡፡

እዚህ ጋ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ግን፣ በወቅቱ ለጨርቃ ጨርቅ ሽያጭ ተብሎ የተለየው አንድ ቤት ዘጠኝ ቦታ የተሸነሸነ እንጂ፤ እነዚህ የተከፋፈሉት(ሽንሽን) ክፍሎች ራሳቸውን ችለው የተሰሩ አይደሉም፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ ያሉ ሌሎች ትናንሽ ክፍሎች ነበሩ፡፡

በኋላም ወይዘሮዋ ቅሬታ ስላቀረቡ፣ ከተነጠቁት ሽንሽን ቤቶች መካከል አንድ ቤት ተሰጣቸው፡፡ የተሰጠቻቸውን አንድ ክፋይ ክፍል 1004/ለ የሚል ስያሜ ሰጧት፡፡ ይሄን የተመለከቱት ወይዘሮ ሙሉም ይህ ለምን ይሆናል? እንዴት በአንድ ቤት ሁለት የቤት ቁጥር ይሰጣል? ብለው ቢጠይቁም ሰሚ አላገኙም። አሁንም ድረስ «ከተሸነሸኑት ዘጠኝ ጠባብ ቤቶች የተሰጣቸው ቤት 1004/ለ መባሉ አግባብ አይደለም። እንዴት በአንድ ቤት ሁለት ቁጥር ይሰጣል?» ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ፣ ምንም እንኳን በዚህ መልኩ ክፍሎቹ የተወሰዱባቸው ቢሆንም፣ እነዚህ ክፍሎች የሰሩት ቤት አንድ አካል ስለሆኑ ኪራይ የሚከፈሉት ራሳቸው ወይዘሮ ሙሉ ናቸው፡፡ ክፍሎቹን መነጠቃቸውም ሆነ በተነጠቋቸው ክፍሎች ኪራይ መክፈላቸው ትክክል አለመሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ሙሉ፤ ሌላው ቢቀር የተነጠቋቸው ክፍሎች (የተቀነሱት ቤቶች) ስፋት ተሰልቶ የቤት ኪራይ ሊቀነስ፤ ካልሆነም ክፍሎቹ ሊመለሱላቸው እንደሚገባ ቅሬታቸውን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ ወይዘሮ ሙሉ ኪራይ ለሚከፍሉባቸው ቤቶች፣ 1004 እና 1004/ለ ብሎ ሁለት የቤት ቁጥር የተሰጣቸው ናቸው፡፡ በዚህም አቤቱታ ወይዘሮ ሙሉ ሁለት የንግድ ፈቃድ እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ ይህም ሕግን ያልተከተለ ከመሆኑ በሻገር፣ የግለሰቦችን የመሥራት ሞራል የሚጎዳ ነው በማለት ስለ ሁኔታው አስረድተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ሙሉ ገለጻ፤ የድርጅቱ (የንግድ ቤታቸው) ሴፕቲክ ታንከር የተገነባው በወረዳው ከተወሰዱባቸው ስምንት ቤቶች የግንባታ መሠረት ሥር ነው፡፡ ይህ ሴፕቲክ ታንከር ባለፈው ጊዜ ፈንድቶ አካባቢውን በማወኩ የአካባቢው ማኅበረሰብ ወይዘሮ ሙሉን ከሶ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ቦታው ድረስ በመሄድ ሁኔታውን ከተመለከተ በኋላ «ሴፕቲክ ታንከሩ ካልተሰራ የአቤቱታ አቅራቢዋ ድርጅት መሥራት አይችልም» ብሎ ቤቱን ዘጋ፡፡ ወይዘሮ ሙሉም ሥራቸውን ቶሎ ለመጀመር በማሰብ ሁለት መቶ ሺህ ብር አውጥተው ሴፕቲክ ታንከሩን ማሰራታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች

ከላይ በቀረበው አግባብ ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰውን የወይዘሮ ሙሉ ቅሬታ መነሻ በማድረግ የመልካም አስተዳደር እና የምርመራ ዘገባ ቡድኑ በርካታ ሰነዶችን ለመመልከት ጥረት አድርጓል። በዚህም ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በምርመራ የተገኙ ሰነዶች በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሰነዶች መካከልም የተወሰኑት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-

ሰነድ አንድ፡- የክልል 14 መስተዳደር በቁጥር ክ14/ዞ1/ከኛ3ለ/ሰ-11/28/87 በቀን 26/04/87 የጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ ይሄ ደብዳቤ፤ በክልል 14 መስተዳደር ዞን 1 ወረዳ 5 ቀበሌ 06 በተከራይ አቶ ሰይፉ አራጋው   ስም ተመዝግቦ የሚገኘው የቤት ቁጥር 1004 የሆነ የቀበሌ ቤት ቀደም ብሎ ከነበረው ቤት የተሻለ አድርጎ ለመገንባት ተከራዩ አዲስ ግንባታ አቀማመጥ ንድፍ በማቅረብ የግንባታ ፈቃድ እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ይህን ተከትሎ የቀረበው ንድፍ ተቀባይነት በማግኘቱ ቤቱ በአቶ ሰይፉ አርጋው እና በወይዘሮ ሙሉ ወይንሀረግ ስም እና ፊርማ የብሎኬት ቤት መገንባት እንደሚችሉ ፈቃድ የሰጠ ነው። በዚህ የግንባታ ፈቃድ አሁን ላይ ወይዘሮ ሙሉ የተወሰዱባቸው ቤቶች «ተለጣፊ ክፍሎች» በሚል የግንባታ ፈቃድ ተሰጥቷቸው እንደነበር ተመላክቷል፡፡

ሰነድ ሁለት፡- በክልል 14 መስተዳደር የወረዳ 5 ቀበሌ 06 መስተዳደር ጽህፈት ቤት በቁጥር 1589/መ15/ወ5/ቀ06/88 በቀን 24/9/88 በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ በዚህ ደብዳቤ ደግሞ፤ አቶ ሰይፉ አርጋው የተባሉ ግለሰብ የቤት ቁጥር 1004 የሆነውን ድርጅታቸውን ለወይዘሮ ሙሉ ወይንሀረግ ኅዳር 28 ቀን 1988 ዓ.ም ባቀረቡት የሸያጭ ውል መሠረት በክልል ፍርድ ቤት ውል ክፍል ቀርቦ የጸደቀላቸው ስለመሆኑ እና አቶ ሰይፉ ይጠበቅባቸው የነበረውን ግብር ከፍለው በማጠናቀቃቸው ባስገቡት የሽያጭ ውል መሠረት ድርጅቱ ወደ ወይዘሮ ሙሉ እንዲዞር መደረጉን የሚገልጽ ሃሳብ ሰፍሯል፡፡

በዚህ ደብዳቤ እንደተመላከተው፤ ወይዘሮ ሙሉ የውል ማዘዋወሪያ ገንዘብ በደረሰኝ ቁጥር 565921፣ 10ሺህ ብር ከፍለዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ቀደም ሲል በአቶ ሰይፉ አርጋው ስም ኪራይ ሲከፈልበት የነበረው የቀበሌ ንግድ ቤት ወደ ወይዘሮ ሙሉ ወይንሀረግ ዞሮ ወይዘሮ ሙሉ በቤቱ ኪራይ መክፍል እንደሚችሉ የቀበሌው ሥራ አስፈጻሚ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ሰነድ ሶስት፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብ መድኃኒት፣ ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ጽህፈት ቤት በቀን 09/11/2010 ዓ.ም እና በቁጥር አ/ከ/ከ/ከ/ም/መ/ ጤክ/አ/ቁ/0442010 ለወይዘሮ ሙሉ በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ ይሄኛው ደብዳቤም፣ በወረዳ 08 በወይዘሮ ሙሉ ሀረገወይን ስም ተመዝግቦ የሚገኘው የቤት ቁጥር 1004 የንግድ ሥራ የሚካሄድበት የድርጅት ቤት መሆኑን ገልጾ፤ ከድርጅቱ የሚወጣው የፍሳሽ ቆሻሻ የአካበቢውን ማኅበረሰብ ጤና እየጎዳ በመሆኑ ከተገቢው አካል ፈቃድ በመውሰድ በሰባት ቀናት ውስጥ ሴፕቲክ ታንከር በመገንባት የፍሳሽ ቆሻሻውን እንድታስወግዱ የሚል ነው፡፡

የወረዳ 08 ምላሽ

የቅሬታ አቅራቢዋን አቤቱታ በመያዝ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ክፍል የጋዜጠኞች ቡድን፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ 08 ሥራ አስፈፃሚ የሆኑትን አቶ አሰፋ ዩጂ፣ ስለጉዳዩ የሚያውቁትን እንዲያስረዱ፤ መፍትሔ የሚሉትንም እንዲገልጹ ጠይቋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት፤ ወይዘሮ ሙሉ ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ እንደ ወረዳ አመራርም ይህን ጉዳይ ጠንቅቀው ያውቁታል። ግለሰቧ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ በነበረው ቅሬታ መነሻነትም ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ የሚመለከታቸው አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች ጉዳዩን ቦታው ድረስ ወርደው ተመልክተውታል፡፡

እንደ አቶ አሰፋ ገለጻ፣ በ2004 ዓ.ም በወጣው የቤቶች መመሪያ መሠረት እንደ ወረዳ የተወሰደው ርምጃ ትክክለኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ወይዘሮ ሙሉ የያዙት ሁለት የመንግሥት ቤት ነው፡፡ አንደኛው ትልቅ ሆቴል ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ኤሌክትሮኒክስ አክሰሰሪ መሸጫ ነው፡፡ በመሆኑም በመመሪያው መሠረት አንደኛው ቤት ለመንግሥት፣ ሌላኛው ደግሞ ለግለሰቧ የሚቀር ይሆናል፡፡ በዚህ አሰራር ደግሞ በርካቶች ተገዥ ሆነዋል፤ ወይዘሮ ሙሉ ግን ይህን ተግባራዊ ለማድረግ አልፈለጉም፡፡ በመሆኑም ወረዳው የሚጠበቅብንን ማድረግ ነበረበት፤ ያንኑ አድርጓል፡፡

ምክንያቱም፣ ወረዳው ዘንድ ያለው መረጃ ወይዘሮ ሙሉ የፈረሙት ሁለት ውል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አንደኛ ቤት የማይገባቸው በመሆኑ ለመንግሥት እንዲተላለፍ ማድረግ ተገቢነት ያለው ነው፡፡ ሆኖም የግለሰቧ ፍላጎት ከሆቴላቸው ውጭ ያሉትን ዘጠኝ መደቦችን አጠቃለው መያዝ ነው፡፡ ይህን ግን ወረዳው መፍቀድ አይችልም፡፡ ከዚህም ባሻገር ወረዳው በቀሪዎቹ ቤቶች (ክፍሎች) ላይ ከሌሎች ህጋዊ አካላት ጋር ውል ተዋውሏል፡፡

‹‹እኛ እንደ ወረዳ ምንም የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈጠር አልፈልግም›› ያሉት አቶ አሰፋ፤ ዘጠኙን ሱቆች መንግሥት የወረሳቸውም ወይዘሮ ሙሉ ወይንሀረግ ከመንግሥት ጋር ውል ፈፅመው ራሳቸው አሳልፈው ለሌሎች ያከራዩዋቸው በመሆኑ ነው፤ ይህ ደግሞ አግባብነት የጎደለው እና ከሕግ አንጻር የተከራይ አከራይ ሆነው የተገኙ በመሆኑ ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ ተገደናል ብለዋል፡፡ ይህን የፈጸምነውም በመመሪያ እንጂ በራሳችን ፍላጎት ወይንም በጥቂት ግለሰቦች ይሁንታ አይደለም ሲሉ ስለሁኔታው አስረድተዋል፡፡

ቀደም ሲል ወይዘሮ ሙሉ ከመንግሥት ጋር ውል የገቡት የኪራይ ውል 1004 በሚል በተመዘገበው የቤት ቁጥር ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ቤቱን እንዴት ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ተብሎ ለሁለት ተከፈለ? የሚለውን አቶ አሰፋ ሲያስረዱም፤ ቤቱ ቀደም ሲል አንድ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ወይዘሮ ሙሉ ቤቱን ለሁለት ይከፈልልኝ፤ ቁጥርም ይሰጠው ብለው በማመልከታቸው ለቤቱ ሁለት ቁጥር ተሰጥቶታል ነው ያሉት፡፡

አቶ አሰፋ አያይዘውም፣ ወይዘሮ ሙሉ ቤቱ ሁለት ቁጥር እንዲሰጠው የጠየቁበት ማመልከቻ በአቤቱታ አቅራቢዋ እናት ማህደር ውስጥ ስለመገኘቱ የገለጹ ሲሆን፤ ይሄንን የማመልከቻ ሰነድ ግን ማቅረብና ለገለጻቸው አስረጅ አድርገው ለጋዜጠኞች ማሳየት አልቻሉም፡፡

ይሄም ቅሬታ አቅራቢዋ (ወይዘሮ ሙሉ) ያለፍላጎታቸው እና በማያውቁት ሁኔታ ቤቱ ለሁለት መከፈሉን ሲያስረዱ ለነበረውን ጉዳይ ወረዳው በማስረጃ ላይ ተመስርቶ ለዝግጅት ክፍላችን መመለስ ያልቻለ መሆኑን የሚያሳይ ቢሆንም፤ አቶ አሰፋ ግን፣ ወይዘሮ ሙሉ ሁለት ውል እና ሁለት የቤት ቁጥር ይዘው በማግኘታችን አንዱን ቤት ለመቀበል መገደዳቸውን ይገልጻሉ፡፡

አቶ አሰፋ፣ ሕጋዊ የግንባታ ፈቃድ ተሰጥቷቸው የተገነቡ ቤቶችን ከአቤቱታ አቅራቢዋ የተነጠቁበትን ምክንያት ሲያስረዱም፤ ቤቱን የተነጠቁት ለሶስተኛ ወገን አከራይተው በመገኘታቸው መሆኑን ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ ዝግጅት ክፍላችን ቅሬታ አቅራቢዋ ቤቱን ለሶስተኛ ወገን ያከራዩበት የሰነድ ማስረጃ አላችሁ? ሲል አቶ አሰፋን የጠየቀ ሲሆን፤ የአቶ አሰፋ ምላሽ “አዎ! የሰነድ ማስረጃ አለን” የሚል ነበር። ሆኖም እንደ ቀድሞው ሁሉ ለዚህኛው ሃሳባቸው ደጋፊ የሆነ የሰነድ ማረጋገጫ (ግለሰቧ ቤቱን ያከራዩበትን ውል የሚያሳይ ሰነድ) ማቅረብ ሳይችሉ ቀሩ፡፡

ሌላው ከቤቶቹ መተላለፍ ጋር ተያይዞ የተነሳው ጉዳይ የሴግቲ ታንከር ጉዳይ ነው፡፡ ይሄም ወይዘሮ ሙሉ በቅሬታቸው የግንባታ ፈቃድ አውጥተው በአዲስ መልክ ቤቱን ሲገነቡ ለሆቴሉ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ‹‹ሴፍቲ ታንከር›› ከሱቆቹ ሥር መገንባቱን መናገራቸው ነበር፡፡ ዝግጅት ክፍሉም የወይዘሮ ሙሉ የሆቴላቸው ቆሻሻ ማስወገጃ/ማጠራቀሚያ ሴፍቲ ታንከር ላይ ያረፉት ሱቆች ወይም መደቦች ለሌላ ተላልፈው መሰጠታቸው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሴፍቲ ታንከሩን ለአደጋ ማጋለጥ እና ኅብረተሰቡንም አደጋ ላይ መጣል አይሆንምን? የሚለውን ጉዳይ አቅርቦ ነበር፡፡

ምክንያቱም ወይዘሮ ሙሉ ለዝግጅት ክፍሉ ባቀረቡት ቅሬታ ወቅት፣ የሴፍቲ ታንከሩ ጉዳይ ቀደም ሲል በሥራቸው ላይ ችግር የፈጠረ መሆኑን በመጠቆም፤ አሁንም መሰል ችግር ቢፈጠር ማን ሊጠየቅ ነው? ይሄንን በተደጋጋሚ ጠይቄ ሊሰማኝ የቻለ አካል የለም፤ ታዲያ በቀጣይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነቱን የሚችል አካል ማን ነው? የሚሉ ጭምር ነበሩ፡፡

ቀደም ሲልም በዚሁ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ‹‹ሴፍቲ ታንከር›› የጤና እክል በመፍጠሩ የወረዳው የጤና ባለሙያዎች ይህን በማረጋገጣቸው እና ችግር ፈጥሯል በመባሉ የገንዘብ ቅጣት መቀጣታቸውን፤ በሌላ መልኩ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ‹‹ሴፍቲ ታንከር›› ሌላ ቦታ ይገንባ ቢባል እንኳን ቦታ አለመኖሩን በመጠቆም፤ ችግሩ ውስብስብ መሆኑንና ግድየለሽ ውሳኔዎች እየተወሰኑ እንደ ግለሰብም ሆን ተብሎ በደል እየደረሰባቸው መሆኑን ደግሞ ለዚህ ሥጋታቸው እንደ ምክንያት አስረድተው ነበር፡፡

አቶ አሰፋ ግን፣ ወይዘሮ ሙሉ ስለ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ‹‹ሴፍቲ ታንከር›› እስካሁን ቅሬታ አላቀረቡም፤ ይህ አዲስ ስልት ሊሆን ይችላል፡፡ ቤቱ በአዲስ የተገነባው 1987 ዓ.ም ነው፡፡፡ ያም ቢሆን እኔ የሚመለከተኝ ግንባታው እንዴት እና መቼ ተከናወነ የሚለው አይደለም፡፡ ጉዳዩ ዛሬ ለምን በአዲስ ሁኔታ ማንሳት አስፈለገ የሚለውን ማሰብ ይገባል፡፡ ሆኖም ይህ ቅሬታ እውነት ከሆነ እኛ እንደ አስተዳደር የምንመለከተው ጉዳይ ሊኖር ይችላል፤ እንደ አስፈላጊነቱም መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እናደርጋለን ሲሉ ስለ ጉዳዩ አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም፣ “እኔ የምመለከተው ውሉን ነው፡፡ በእጃቸው ላይ ስንት ቤት አለ የሚለውን ማጣራት ነው፡፡ መመለስ የሚጠበቅብኝ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው፡፡ በመሆኑም በሁለት ቤት ውል መዋዋላቸውን በማጣራታችን የተወሰደ ርምጃ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፤” በማለትም የወሰዱት ርምጃ የጋራ መገልገያዎችን ማዕከል በማድረግ ሳይሆን ግለሰቧ ሁለት ቤት የመያዛቸውን እውነት ማዕከል ያደረገ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

ስለቤቱ 1997 ዓ.ም የሲ.አይ.ኤስ መረጃን፣ እንዲሁም የእርሳቸውን ምልከታ አስመልክቶ እንዲያብራሩ በተጠየቁት መሠረትም ሥራ አስፈጻሚው በሰጡት ምላሽ፤ በዚህ ላይ መረጃዎች አሉ፤ በግልጽም ተቀምጧል፡፡ ይሁንና 1997 ዓ.ም የሲ.አይ.ኤስ መረጃዎችን ከወይዘሮ ሙሉ ፋይል ውስጥ ማግኘት አልተቻለም፣ ሲሉ አስረድተዋል። ከመመሪያው ጋር በተያያዘም፣ መመሪያውን ተከትሎ አንድ ቤት ሁለት እና ከዚያ በላይ መሸንሸን እንደሚቻል፤ ወይዘሮ ሙሉም በዚህ አግባብ የሚስተናገዱ፤ ለዚህም መመሪያው እንደሚደግፋቸው ተናግረዋል፡፡

ያለ ምክንያት የምንሰራው ሥራ የለም የሚሉት አቶ አሰፋ፤ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በምንሰራው ሥራም ልንታገዝና ልንበረታታ ይገባል እንጂ ልንወቀስ አይገባም ይላሉ፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት መደቡን/ክፍሎቹን ሕጋዊ አካላት ባሉበት አሽገነዋል፤ በቀጣይ ግን በሕጉ መሠረት ሱቆቹን ወይንም መደቡን ለሌላ አካል አስተላልፈን ውል እንዋዋላለን ብለዋል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ 08 የቤቶች የይዞታ ክትትል ባለሙያ የሆኑት አቶ ንጉሴ ገብረ በበኩላቸው፤ ወይዘሮ ሙሉ ወይንሀረግ አሁን እያቀረቡ ያሉት ቅሬታ ከ12 ዓመታት በፊት መፈታት የነበረበት ጥያቄ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

አሁን ላይ የጉዳዩ መነሳት አግባብ አይመስለኝም የሚሉት አቶ ንጉሴ፤ ግለሰቧ እስከ ዛሬ ዝምታ መርጠው መቆየታቸው በጉዳዩ የተስማሙ እንጂ ተቃውሞ ያላቸው አያስመስልም፡፡ ቅሬታም ካላቸው እስከ ዛሬ መቀመጥ አልነበረባቸውም፡፡ ይህ ውሳኔ የተወሰነው በደመነፍስ ወይንም በግለሰቦች ፍላጎት ሳይሆን በወቅቱ ከገነቡት የተወሰኑትን ሱቆችን ለሌሎች አካላት አከራይተው በመገኘታቸው አከራይ ተከራይ መመሪያ መሠረት ቤቱን ተወርሰዋል፡፡ በ2004 ዓ.ም የወጣው አከራይ ተከራይ መመሪያም መሠረትም ወይዘሮ ሙሉ አሁን የሚጠይቁትን መብት ተነጥቀዋል፤ ሲሉ ጉዳዩን አስረድተዋል፡፡

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You