ለውጡን ተከትሎ የተጀመረው መነቃቃት በብዙ ተግዳሮቶች እየተፈተነ፤ ሀገርና ሕዝብን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እያሻገረ ስለመሆኑ በየዕለቱ የምንታዘባቸው ተጨባጭ እውነታዎች ማሳያ ናቸው። አይቻልም “አይታሰብም” የሚሉ የትናንት ትርክተቶችን ሳይቀር ወደ ታሪክነት እየቀየረ እየሄደበት ያለው የቁርጠኝነት መንገድ በርግጥም የጀመርነው የለውጥ ጉዞ በብዙ የከሰርንባቸውን ትናንቶች እንደሚክሰን አመላካች እየሆነ ነው።
ሀገርን አበቃላት ከሚል ሟርት ከመታደግ ጀምሮ፤ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እየሄድንበት ያለው በፈተናዎች የተሞላ መንገድ፤ የቱንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍለን ፤ አሁን ላይ እንደ ሀገር እያስመዘገብነው ያለው እመርታ ፤ አዲስ ሀገራዊ ትርክት በመፍጠር መጪው ዘመን የተሻለ እንዲሆን ከሁሉም በላይ የአስተሳሰብ መሠረት የጣለ ነው።
የብዙ ትውልዶችን ብሩህ ተስፋዎች ፤ ያደበዘዙ የትናንት የስህተት መንገዶቻችንን ቆም ብሎ በሰከነ መንፈስ በማየትና በማረም ዘላቂ መፍትሄ በማፈላለግ ላይ የተመሠረተው የለውጡ መንገድ ፤ ችግሮችን በውይይትና በድርድር በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ረጅም ርቀት ተጉዟል። ለዚህም ከፍያለ ዋጋ ለመክፈል የተገደደበት ክስተትም ተፈጥሯል።
ምንም ሳታጣና ብዙ እያላት ላልተገባ ድህነት የተዳረገችውን ኢትዮጵያ፤ ካለችበት ያልተገባ ስፍራ በማውጣት፤ ድህነትን ታሪክ ሊያደርግ የሚችል ብሄራዊ የልማት መነቃቃት በመፍጠርም፤ ዜጎች በነገዎቻቸው ተስፋ እንዲያደርጉ፤ ድህነትን ታሪክ በማድረግ ትግል ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን እያደረገ ነው፤ በዚህም እየተገኘ ያለውም ስኬት ዓለም አቀፍ እውቅና እስከማግኘት የደረሰ ሆኗል።
ፋታ የማይሰጡ የሀገር ውስጥ ችግሮች በሚፈራረቁበት፤ ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሀገርና የሕዝብን ጥቅም አደጋ ውስጥ የሚከቱ ዓለም አቀፍ ጫናዎች በበዙበት ሁኔታ፤ ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ከማስመዝገብ ጀምሮ፤ በችግር ወቅት ሊታሰቡ የማይችሉ የልማት ሥራዎችን በማከናወን የለውጥ አመራሩ ለተነሳበት የለውጥ መንፈስ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል።
ከፍ ባለ ተስፋ እና የሕዝባችን ርብርቦሽ ተጀምሮ አደጋ ውስጥ የነበረውን የዓባይ ግድብ ፤ ከነበሩበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች በማላቀቅ የመጨረሻ ምእራፍ ላይ እንዲደርስ አድርጓል። ብዛት ያላቸው የቱሪስት መዳረሻዎችን በመገንባት በዘርፉ ያለውን ሀገራዊ አቅም ወደ ሀብት መለወጥ ችሏል። በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ተከትሎ በስንዴ ልማት የተገኘውም ስኬት ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት የቻለ ነው።
ከዚህም ባለፈ ላለፉት ሶስት አስርቶች አይነኬ ሆኖ የቆየውን የባህር በር ጉዳይ ፤ለሀገርና ለሕዝብ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ከፍ ባለ ድምጽ በማሰማት ፤ ሕዝባችንን በጉዳዩ ዙሪያ ከተኛበት እንዲነቃ፤ ዓለም አቀፉም ህብረተሰብ እንደ ሀገር በጉዳዩ ዙሪያ ያለንን አቋም እንዲያውቀው እና ከጎናችን እንዲሰለፍ የሚያስችል ፤ የለውጡን ታሪክ የሚያደምቅ ተግባር ፈጽሟል።
ሀገራችን በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች የሚቆጠሩ የባህር በሮች የነበሯት፤ በተለያዩ የታሪክ ስብራቶች እነዚህን ወደቦቿን አጥታ በአሁኑ ወቅት ወደብ አልባ ብትሆንም፤ ይህንን የህልውናችን ጉዳይ የሆነውን የወደብ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ዘመኑን በሚዋጅ የትብብርና የወዳጅነት መንፈስ ዕውን ለማድረግ እየሄደበት ያለውም መንገድ ከተስፋነት ወደሚጨበጥ እውነታነት እየተለወጠ ነው።
እንደ ሀገር ካለን ከፍያለ የሕዝብ ብዛትም ሆነ ከውሃ አካላት ካለን ርቀት አንጻር ነጻና አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት መብታችን በዓለም አቀፍ ሕግ፤ ከታሪክ እና ከሞራል አንጻር የሚደገፍ ቢሆንም ፤ ፍላጎቶች አጅግ በበዙበት በዚህ ዘመን በቀላሉ ሊተገበር የሚችል አይደለም፤ ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ነገን አሻግሮ ማየትና ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት የሚጠይቅም ነው።
ከዚህ አንጻር መንግሥት ከሁሉም በላይ በእጅ ያሉ ሰላማዊ አማራጮችን በአግባቡ አይቶ እና ለይቶ በማሳየት፤ ከዚህ የሚመነጭ መተማመንና ወዳጅነትን በማጠናከር ፤ ነገዎችን ከኛ አልፈው ለሌሎች ብሩህ ሆነው የሚታዩበትን የአእምሮ ውቅር/የአስተሳሰብ መሠረት / በመገንባትና ይህንንም የአደባባይ እውነት አድርጎ በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ መቻሉ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ትልቅ የስኬት መንገድ ሆኗል።
መንገዱ በአንድም ይሁን በሌላ ለሀገራችን አስተማማኝ እና ቀልጣፋ የወደብ አማራጭ ማቅረብ የሚችሉ ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የተሻለ ዕድል የሚፈጥር፤ እጣ ፈንታቸውን የሚያስተሳስር፤ የመጡበትን የወዳጅነትና ወንድማማችነት መንገድ የበለጠ የሚያጎለብትና የቤተሰብነት መንፈሳቸውን በሁለንተናዊ መንገድ የሚያሳድግ ነው።
ከትናንት በስቲያ ከሶማሌ ላንድ ጋር እንደ ሀገር ደህንነቱ የተጠበቀ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ አማራጭ የባህር በር ለማግኘት የደረስንበት የመግባቢያ ስምምነት ፤ ከዚህ እውነት የተቀዳ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገና ለቀጣናዊ ተስስርና ልማት ፈር ቀዳጅ ነው። ከዚህ ባለፈ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች እጣ ፈንታ የሚያስተሳስርና የቀደመውን የወንድማማችነት ታሪካቸውን በጠንካራ መሠረት ላይ ዳግም የሚያንጽ ነው!
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም