ኬንያዊው የማራቶን የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ኢሉድ ኪፕቾጌ የ2018 የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ሽልማት አሸናፊ ሆኗል። የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና የማራቶን አሸናፊው ኪፕቾጌ ጋር በሴቶች ኮሎምቢያዊቷ ስሉስ ዘላይ ካትሪን ኢባርገን ሽልማቱን መውሰድ ችላለች። የሽልማት ስነ-ስርዓቱ ከትናንት በስቲያ ምሽት ሞናኮ ከተማ ላይ ሲካሄድ በሌሎች ዘርፎችም በርካታ አትሌቶችና የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።
በወንዶች ዘርፍ ሽልማቱን ማሸነፍ የቻለው ኪፕቾጌ ባለፈው መስከረም በበርሊን ማራቶን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን በሰባ ስምንት ሰከንድ ማሻሻሉ የሚታወስ ሲሆን ያስመዘገበው ሰዓትም 2፡01፡39 ሆኖ ተመዝግቧል። የሴቶች ዘርፍ አሸናፊ መሆን የቻለችው ኢባርገን በበኩሏ የውድድር ዓመቱ የዳይመንድ ሊግ የስሉስና የርዝመት ዝላይ አጠቃላይ አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል። ኪፕቾጌ ይህን ሽልማት በማግኘትም ከዴቪድ ሩዲሻ ቀጥሎ ሁለተኛው ኬንያዊ አትሌት ሲሆን ኢባርገን የመጀመሪያዋ ኮሎምቢያዊት ሆናለች።
ሁለቱ ኮከብ አትሌቶች ይህን ሽልማት ሲያሸንፉ የመጀመሪያቸው ሲሆን በተለይም ኪፕቾጌ በማራቶን የዓለም ክብረወሰን ላይ ላሳየው ትልቅ መሻሻል ሽልማቱን እንዲያገኝ አስችሎታል። የሰላሳ አራት ዓመቱ ኬንያዊ እኤአ ከ1967 አውስትራሊያዊው ዴሬክ ክሌይተን የማራቶን ክብረወሰንን ከሁለት ደቂቃ ከሰላሳ ሰከንድ ባልተናነሰ ሰዓት ካሻሻለ ወዲህ በሰፊ የሰዓት ልዩነት ክብረወሰን መጨበጡ ለሽልማቱ አብቅቶታል። እውቁ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ ከፍተኛ በጀት መድቦ ማራቶን ከሁለት ሰዓት በታች እንዲሮጥ ባደረገው ጥረት ኪፕቾጌ ባለፈው ዓመት ጣሊያን ሞንዛ እቅዱ መሳካት እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ሰዓት አስመዝግቧል። ኪፕቾጌ 2:00:25 በማጠናቀቅ ያስመዘገበው ሰዓት የዓለም ክብረወሰን ሆኖ ለመያዝ እውቅና ባይኖረውም የሰው ልጅ ማራቶንን ጠንክሮ ከሰራ ከ2፡00 በታች ማጠናቀቅ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነበር። የኦሊምፒክ ቻምፒዮኗ ኢባርገን በውድድር ዓመቱ በስሉስ ዝላይ ባደረገቻቸው ስምንት ውድድሮች አንድም ያለመሸነፏ ሽልማቱን ለመጎናፀፍ አስተዋፅኦ አድርጎላታል።
በዚህ ትልቅ ሽልማት በወንዶች በኩል ፈረንሳዊው ሁለገብ አትሌት ኬቪን ሜየር፤ አሜሪካዊው የአጭር ርቀት ሯጭ ክሪስቲያን ኮሊማን፤ ስዊድናዊው ምርኩዝ ዘላይ አርማንድ ሞንዶ እንዲሁም ኳታራዊው የመሰናክል አትሌት አብዲራህማን ሳምባ የመጨረሻ እጩዎች ሆነው ተፎካክረዋል። በሴቶች በኩል ባሃማሳዊቷ የአጭር ርቀት ሯጭ ሻውኔ ሚለር፤ እንግሊዛዊቷ ዲና አሸር ስሚዝ፤ ኬንያዊቷ የመሰናክል አትሌት ቢትሪስ ኪፕኮይች እንዲሁም ቤልጅየማዊቷ ሁለገብ አትሌት ናፊሳቱ ቲያም እጩዎች ነበሩ።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከዚህ ቀደም ሽልማቱን ለማግኘት እጩ ከመሆን ባለፈ ደጋግመው ይህን ክብር መጎናፀፍ ችለዋል። በዘንድሮው ዓመት ግን በሁለቱም ፆታ ከአስሩ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ እንኳን ሳይካተቱ ቀርተዋል። ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ ማህበሩ በሚያዘጋጀው ተመሳሳይ የሽልማት ዘርፍ ወጣትና ወደፊት ትልቅ ተስፋ ባላቸው አትሌቶች ሽልማት ዘርፍ ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከመጨረሻዎቹ ምርጥ አምስት እጩዎች ውስጥ መካተት ችለዋል።
ከሃያ ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶች በሚሸለሙበት ዘርፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች ድንቅ ብቃት እያሳየ የሚገኘው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ከመጨረሻዎቹ አምስት እጩዎች ስም ዝርዝር ውስጥ መካተቱ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ይህን ሽልማት ማሸነፍ የቻለው ስዊድናዊው ምርኩዝ ዘላይ አርማንድ ዱፕሌንቲስ ሆኗል። ይህ አትሌት አውሮፓ ከሃያ ዓመት በታች ቻምፒዮና በራሱ ተይዞ የነበረውን የዓለም ከሃያ ዓመት በታች ክብረወሰን በአንድ ውድድር ላይ ብቻ ሦስት ጊዜ በመሰባበር አስደናቂ ብቃት ማሳየት ችሏል። አርማንድ በዚህ ውድድር 5ነጥብ 95፤6ነጥብ 00፤ 6ነጥብ 05 ሜትር ከፍታ የዘለለ ሲሆን በታሪክ ከሰርጌ ቡካ ቀጥሎ በክብረወሰን ተይዞለታል።
ፊንላንድ ቴምፕሪ ተካሂዶ በነበረው የዓለም ከሃያ ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና የቻምፒዮናውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ያሸነፈ ሲሆን በውድድር ዓመቱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችም በእድሜና በልምድ የሚበልጡትን ምርኩዝ ዘላዮች የሚያስንቅ ብቃት ማሳየት ችሏል። ይህን ሽልማት ያሸንፋል ተብሎ የተጠበቀው የደቡብ ፖሊሱ ክለብ አትሌት የሆነው ሰለሞን ባረጋ ከእድሜው ከፍ ብሎ ከታላላቆቹ ጋር በመወዳደር እያስመዘገበ ላለው ስኬት ከሁለት ወራት በፊት ክለቡ የኢንስፔክተርነት ማዕረግ የሰጠው ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት እያሳየ ያለው አስደናቂ ብቃት ወደ ፊት ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል። ከአትሌት ሰለሞን በተጨማሪ ኩባዊው የስሉስ ዘላይ ጆርዳን ዲያዝ፣ የኖርዌዩ የመካከለኛ ርቀት ሯጭ ጃኮብ ኢንብሪግስተንና ኬንያዊው የረጅም ርቀት ሯጭ ሮኔክስ ኪፕሩቶ የዓመቱ ምርጥ ታዳጊ ፅጩዎች ናቸው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ታላላቅ የውድድር መድረኮች መጥቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የስፖርት ቤተሰቡ አይን ማረፊያ የሆነው ወጣት አትሌት ሰለሞን ባረጋ ውጤቱና አስደናቂ ብቃቱ ኢትዮጵያ በቅርቡ በታላላቅ መድረኮች አረንጓዴውን ጎርፍ ዳግም የማየት ብሩህ ተስፋ እንዳላት ማሳያ ነው።
ድንቅ የሩጫ ተሰጥኦው በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዙፋን ላይ እንደሚወጣ የስፖርቱ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይመሰክሩለታል። ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች የዓለም ወጣቶች ቻምፒዮና አሸናፊ መሆን የቻለው ሰለሞን ባለፈው የለንደን የዓለም ቻምፒዮና በቀጥታ ወደ ትልቅ ደረጃ ተሸጋግሮ የኢትዮጵያውያንን የአምስት ሺ ሜትር ስብስብ ምን ያህል አስፈሪ እንዳደረው ይታወሳል፡፡
በሁለት ኦሊምፒኮችና በሦስት የዓለም ቻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ በሞ ፋራ የተነጠቀችውን የአምስት ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ለንደን ላይ በሙክታር ኢድሪስ አማካኝነት ስታስመልስ የሰለሞን ሚና ቁልፍ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በበርሚንግሃሙ የዓለም ቻምፒዮና ዮሚፍ ወርቅ ባጠለቀበት ውድድር ሰለሞን የብር ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን ያሳየው ድንቅ አቋም በቀጣይ ዓለም አቀፍ መድረኮች ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀቶች ኢትዮጵያውያን የበላይነታቸው ከወዲሁ ጎህ እየቀደደ እንደሚገኝ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው።
በ2018 የውድድር ዓመት የአምስት ሺ ሜትር አጠቃላይ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ መሆን የቻለው ሰለሞን ባረጋ በርቀቱ ከሃያ ዓመት በታች የዓለም ክብረወሰንን 12፡43፡02 በሆነ ሰዓት ከመጨበጡ ባሻገር እኤአ 2005 ላይ ቀነኒሳ በቀለ በርቀቱ ካስመዘገበው ሰዓት ወዲህ ፈጣን ሰዓት መሆኑ ይታወሳል። ሰለሞን በዓለም ከሃያ ዓመት በታች ቻምፒዮናና በአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮናም በርቀቱ አራተኛ ደረጃን ይዞ በመፈፀም በውድድር ዓመቱ በርካታ ስኬቶችን አግኝቷል። ሰለሞን በወጣቶች ዘርፍ ሽልማት ማግኘት ባይችልም ከሽልማት ዘርፎች አንዱ በሆነው የፎቶ ግራፍ ውድድር ምስሉ አሸናፊ መሆን ችሏል። ሰለሞን በውድድር ዓመቱ ስፔን ኢልጎባር ላይ የአገር አቋራጭ ውድድር ሲያሸንፍ የተነሳው ፎቶ ግራፍ አሸናፊ ሲሆን በስፔናዊው የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ፌሊክስ ሳንቼዝ አራዞላ የተነሳ ነበር።
በተመሳሳይ በሴቶች መካከል በተካሄደው ምርጫ አሜሪካዊቷ የአጭር ርቀት ተወዳዳሪ ሲድኒ ማክላፍሊን አሸናፊ መሆን ችላለች። ይህች አትሌት በውድድር ዓመቱ በራሷ ተይዞ የነበረውን የዓለም ከሃያ ዓመት በታች የአራት መቶ ሜትር መሰናክል ክብረወሰን 52፡75 በሆነ ሰዓት ያሻሻለች ሲሆን ይህም ሰዓቷ የዓመቱ ፈጣንና በታሪክ በርቀቱ ፈጣን ከሆኑ አስር ሰዓቶች የአንዱ ባለቤት አድርጓታል። ሲድኒ በውድድር ዓመቱ በአራት መቶና በአራት መቶ ሜትር መሰናክል ውድድሮች አንድም ሽንፈት ያላስተናገደች ሲሆን በውድድር ዓመቱ በተለይም በሦስትና አራት መቶ ሜትር ውድድሮች በታሪክ ከሃያ ዓመት በታች አትሌት ያላስመዘገበውን ሰዓት ማስመዝገብ መቻሏ ሽልማቱን እንድታሸንፍ አስችሏታል።
በዚህ የውድድር ዘርፍ ኢትዮጵያዊቷ ወጣት አትሌት መሰረት በለጠ ከመጨረሻዎቹ አምስት እጩዎች አንዷ መሆን እንደቻለች ይታወሳል። መሰረት በውድድር ዓመቱ በግማሽ ማራቶን ውድድር ከዓለም ከሃያ ዓመት በታች ምርጥ የተባለውን 1፡07፡51 ሰዓት ማስመዝገቧ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪ በስፔን ቫሌንሲያ ተካሂዶ በነበረው የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮና ላይ ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ቢሆንም በቡድን የወርቅ ተሸላሚ ነበረች። በጉተንበርግ ግማሽ ማራቶንም አሸናፊ ሆና ማጠናቀቋ አይዘነጋም።
ሌላኛዋ ወጣት ኢትዮጵያዊት አትሌት መስከረም ማሞ ከእጩዎቹ መካከል የተካተተች ሲሆን በውድድር ዓመቱ በዓለም ከሃያ ዓመት በታች የሦስት ሺ ሜትር ውድድር 8፡33፡63 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ የፈጣን ሰዓት ባለቤት ነች። በተመሳሳይ በአምስት ሺ ሜትርም 15፡05፡21 የሆነ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች። በአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ደግሞ በአምስት ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ለማጥለቅ በቅታለች።
የአፍሪካ አገር አቋራጭ ቻምፒዮኗ ኬንያዊቷ የመሰናክል ውድድር አትሌት ሴሊፒን ካስፖል በውድድር ዓመቱ ካሳየችው ድንቅ አቋም አኳያ በሽልማቱ ተፎካካሪ ነበረች። ጃማይካዊቷ የመቶና የሁለት መቶ ሜትር ተወዳዳሪ ብሪያና ዊሊያምስ በርቀቶቹ የዓለም ከሃያ ዓመት በታች ቻምፒዮን መሆኗ ከመጨረሻዎቹ አምስት እጩዎች አንዷ እንድትሆን አስችሏታል።
በ1998 እኤአ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በ2004እና በ2005 እኤአ ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት ቀነኒሳ በቀለ፤ በ2007 እኤአ መሰረት ደፋር፤ በ2015 እኤአ ገንዘቤ ዲባባና በ2016 አልማዝ አያና የዓለም ኮከብ አትሌት የተባሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው፡፡
ከአትሌቶችም በተጨማሪ በ2006 እኤአ አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ብቸኛውን የአይኤኤኤፍ የህይወት ዘመን ስኬት ሽልማት ያገኙ ሲሆን በ2005ና በ2008 ጥሩነሽ ዲባባ እንዲሁም በ2006 እኤአ መሰረት ደፋር የዓመቱ ምርጥ ብቃት ሽልማትን መጎናፀፍ ችለዋል።
የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ የተጀመረው በ1988 እኤአ ላይ ሲሆን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፋውንዴሽን ምክር ቤት እና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) ቅንጅት በፈረንሳይቷ ከተማ ሞናኮ ውስጥ በየዓመቱ ይካሄዳል፡፡
የአይኤኤኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌት የሽልማት ስነ-ስርዓቶች በወንዶች ምድብ የ11 አገራት አትሌቶች ተሸላሚዎች ሲሆኑ አሜሪካ 8 ጊዜ በማሸነፍ ግንባር ቀደም ናት፡፡ 7 ጊዜ ጃማይካ፤ 3 ጊዜ እንግሊዝ፣ ሞሮኮ እና ኢትዮጵያ እንዲሁም ኬንያ የዘንድሮውን ጨምሮ 2 ጊዜ፤ 1 ጊዜ አልጄሪያ፣ ዴንማርክ፣ ቼክሪፐብሊክ፣ እና ፈረንሳይ በወንዶች ምድብ አሸናፊዎች በማስመዝገብ ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡ በወንዶች ምድብ ለ6 ጊዜያት በ2008፣ በ2009፣ በ2011፣ በ2012፤ በ2013ና 2016 እኤአ ላይ በማሸነፍ ጃማይካዊው ዩሴያን ቦልት ከፍተኛውን ስኬት ያስመዘገበ ሲሆን፤ የሞሮኮው ሂካም አልገሩዥ በ2001፣ በ2002 እና በ2003 እኤአ ለ3 ጊዜያት እንዲሁም ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ በ2004 እና በ2005 እኤአ ለሁለት ተከታታይ ጊዜ በመሸለም ተከታታይ ደረጃ ያገኛሉ፡፡
በሴቶች ምድብ ደግሞ ያለፉትን ሰላሳ የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማቶች ለማሸነፍ የበቁት 12 አገራት ናቸው፡፡ 9 ጊዜ በማሸነፍ አሜሪካ አንደኛ ደረጃ ስትወስድ፤ 4 ጊዜ ራሽያ፤ እያንዳንዳቸው 2 ጊዜ ጀርመን፣ ጃማይካ፣ እንግሊዝና ኢትዮጵያ እንዲሁም እያንዳንዳቸው1 ጊዜ ኒውዝላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ክሮሽያ፣ ሮማንያ እና ኩባ አሸናፊዎች የነበሩ ሲሆን ኮሎምቢያ በዘንድሮው ዓመት እዚህ ዝርዝር ውስጥ መግባት ችላለች።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2011
ቦጋለ አበበ