የሰው ልጆች በተለያየ ምክንያት ለድጋፍ እጆቻቸውን ይዘረጋሉ፤ ሳይፈልጉ የሰው ፊት ለማየት ይገደዳሉ። መንግሥትም እነዚህን ዜጎቹን ከችግሮቻቸው የሚወጡበትን የአጭር ጊዜም ሆነ የረዥም ጊዜ መፍትሔ አበጅቶ ይሠራል። በዚህም በአጭር ጊዜ ለዕለት ችግሮቻቸው እጅ እንዳይሰጡ የሰብዓዊ ድጋፍን ያደርጋል፤ ለዘለቄታውም ከችግራቸው እንዲወጡ ለችግር የዳረጓቸውን ምክንያቶች ቶሎ የመፍትሔ ርምጃ ይወስዳል።
በኢትዮጵያም አንድም በሰው ሰራሽ ችግር፤ ሁለተኛም በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹበት ሁኔታ ተፈጥሯል። መንግሥትም በአንድ በኩል እነዚህ ዜጎች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ የሚያስችል የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎችን እያከናወነ፤ በሌላ በኩል ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮችን መፍትሔ ለመስጠት እየተጋ ይገኛል።
ለምሳሌ ዜጎች ለችግር እንዲጋለጡ ካደረጓቸው ጉዳዮች መካከል ድርቅና ጎርፍን የመሳሰሉ የተፈጥሮ ክስተቶች ተጠቃሽ ናቸው። በመሆኑም ለእነዚህ ዜጎች የዕለት ደራሽ የሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን፤ ችግሮቹን በዘላቂነት መፍታት የድርቅና ጎርፍን ከሳች ጉዳዮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል።
ይሄን መሰል ተግባር ደግሞ ዜጎች የእለት ምግብን ብቻ ሳይሆን፣ በዘላቂነት የምግብ ዋስትናቸውን የሚያረጋግጡበትን አቅም እንዲገነቡ እያደረገ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ በግብርናው ዘርፍ እየተገኙ ያሉ ውጤቶች ዐቢይ ማሳያዎች ናቸው።
በተመሳሳይ መልኩ፣ ዜጎች ለችግር ከሚዳረጉባቸው ምክንያቶች ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲሆኑ፤ ሰላምና ፀጥታ ችግር በተለይም ግጭትና ጦርነት የዚህ ዓይነተኛ ምክንያቶች ናቸው። በኢትዮጵያም በግጭትና ጦርነት ምክንያት በርካታ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍን የሚሹበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በዚህ ረገድም መንግሥት በግጭትና ጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍን ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ለዜጎች መፈናቀልና ችግር ምክንያት የሆነውን የሰላምና ፀጥታ ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ ነው።
ለዚህም መንግሥት ከሰላምና ፀጥታ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥም በሁሉም ክልሎች ነፍጥ ላነገቡ ኃይሎች የሰላም ጥሪ አስተላልፏል። በዚህም በበርካታ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እንዲፈጠርና ሕዝቡም እፎይታ እያገኘ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ዕድል ፈጥሮለታል።
ይሄን ጉዳይ አስመልክቶ ከሰሞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ሰጥቶ ነበር። አገልግሎቱ በመግለጫው እንዳመለከተው፤ መንግሥት ለሰላምም፣ ሰብዓዊ ድጋፍም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። በዚህም አንጻራዊ ሰላም እየመጣ፤ የሰብዓዊ ድጋፍም እየደረሰ ይገኛል። ከዚህ በተቃራኒው ግን የሰላም አማራጭ ያልፈለጉ ኃይሎች አሁንም ሀብት መዝረፍና የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል ለማሳካት አውዳሚና በታኝ አካሄድን እየተከተሉ ያሉ ኃይሎች እኩይ ተግባራቸው ከሕዝብ እየነጠላቸው ይገኛል።
ሰብዓዊ ድጋፍን በተመለከተ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ድጋፍ አደጋዎች በአማራ፣ ትግራይ፣ አፋርና ሌሎች ክልሎች 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች የድርቅ አደጋ እንዲሁም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የጎርፍ አደጋ እንደደረሰባቸው ያመለከተው መግለጫው፤ ለዚህ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን ከመርዳት አኳያም ከሐምሌ ወር ጀምሮ ከዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ጋር በመተባበር 1 ሚሊዮን 725 ሺህ ኩንታል ( ከ15 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን) ሰብዓዊ እርዳታ ቀርቧል።
ይሁን እንጂ ከሰብዓዊ ድጋፍ ጋር በተያያዘ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ያጋጠመውን ድርቅ አስመልክቶ ከሰሞኑ የሰጠው መግለጫ ፈፅሞ የተሳሳተ መሆኑን ነው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መግለጫ ያረጋገጠው። ለዚህም መንግሥት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እያደረገ ስለመሆኑ አገልግሎቱ አብራርቷል።
“ፖለቲካና ሰብዓዊ ድጋፍን ማገናኘት ተገቢነት የለውም” ያለው መግለጫው፤ በትግራይ ክልል በአራት ዞኖች ድርቅ የተከሰተ ቢሆንም በእነዚህ አካባቢዎች መንግሥት ለዜጎች ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን አመልክቷል። በመሆኑም ይሄን እውነት በመግፋት እና በረሃብ ምክንያት የሞተ ሰው አለ የሚል ግምገማ በሌለበት በሕዝብ ሽፋን የሚደረግ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት እንደሌለው ነው መግለጫው በአጽንዖት ያነሳው።
ለዚህም መንግሥት ለዜጎች የሚያደርሰውን ሰብአዊ ድጋፍ በኃላፊነት እየተወጣ ሲሆን፤ ፕሮጀክቶቹን ጭምር አጥፎ አስፈላጊውን በጀት መድቦ የሰብዓዊ ዕርዳታን ለትግራይ ክልል ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ብቻ ሳይሆን በበቂ መጠን እያቀረበ ይገኛል!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም